በዘመኑ ፈረደ
መቼም ሁልጊዜም ቢሆን ጭቆናና ግፍ እስካለ ድረስ ይህንን የሚፃረር የመረረ ትግል መደረጉ አይቀሬ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጭቁን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ታሪክም የሚያስረዳን ይህንኑ ነው፡፡ ህዝቡ በተለይ የፊውዳል ገዢዎች እየተፈራረቁ ያደርሱበት የነበረውን ጭቆናና ግፍ በመቃወም አያሌ ትግሎችን አካሂዷል፡፡ በተለይ የአፄ ኃይለስላሴ ፊውዳላዊ የዘውድ አገዛዝ በህዝባዊ ቁጣ እጅጉን የተናጠ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡
በተለያዩ አመታት
የተነሳው የደቡብ ኢትዮጵያና የኦሮሞ አርሶ አደሮች አመፅ፣ ከ1934-1935 ዓ.ም የተካሄደው የጐጃም አርሶ አደሮች ፀረ ግብር እንቅስቃሴ፣ ከ1935 እስከ 1936 ዓ.ም የነበረው የትግራይ ወያኔ እንቅስቃሴ፣ በ1950ዎቹ አመት ውስጥ የታየው የላብ አደሮች ተቃውሞ፣ በነዚሁ ዓመታት ተጀምሮ ደረጃ በደረጃ እያደገ፣ እየሰፋና ታላቅ ትኩረትን እየሳበ የቀጠለው የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ የ1962ቱ የወሎ አርሶ አደሮች አመፅና ሌሎችም ታሪክ የሚያወሳቸው በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን መንግስት የታዩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ተቃውሞዎች አንዴ ብልጭ ብለው መልሰው እየጠፉ ቆይተው ነበር በመጨረሻ በየካቲት 1966 ዓ.ም አብዮት ያስከተሉት፡፡ የየካቲት 1966ቱ አብዮት በይዘቱ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት የነበረ ሲሆን ከአብዮቱ በፊት የነበሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ድምር ውጤት እንደሆነ በጉዳዩ ላይ ያጠኑ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በአብዮቱ በርካታ ጥያቄዎች ቢቀርቡም የአፄ ኃይለስላሴ መንግስት አንዳቸውንም ሊመልስ ስላልቻለ ተናጋ፡፡
ይህን አብዮት ተከትሎ ሰኔ 21/1966 ዓ.ም ራሱን “የጦር ኃይሎች የፖሊስ ሰራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ደርግ” ብሎ የሰየመው ኃይል “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል መፈክር አንግቦ ወደ ስልጣን መጣ፡፡ የህዝቡን ትግልም ያኮላሽ ጀመር፡፡ ቀስ በቀስም ይህ የወታደር ስብስብ አድራጊ ፈጣሪ ኃይል እየሆነ የህዝቡን ትግል ያመነምን ጀመር፡፡ እራሱንም ከህዝቡ ትግል ፊት ደነቀረ፡፡
ይሁንና ምንም እንኳን ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የአፄ ኃይለስላሴን መንግስት አንቅሮ በተፋው ህዝብ ስም እየማለ ሲገዘት ህዝቡን ቢያደናግርም በሂደት ግን ደርግ ህዝባዊ ባህሪ ያልተላበሰ እንደሆነ ተጋለጠ፡፡ በተለይ ለአብዮቱ ዘላቂ ድል የሚተልሙ ሆኖም ግን ገና በቅጡ ያልተደራጁና ያልተጠናከሩ ተራማጅ ቡድኖች ወደ መድረክ ብቅ በማለትና የተቃውሞ ወረቀቶችንም በመበተን የደርግን ሴራ ያጋልጡ ጀመር፡፡
ከሚበተኑ የተቃውሞ
ወረቀቶች መካከል “አብዮት” “ዴሞክራሲ” እና “የሰፊው ህዝብ ድምፅ” የሚባሉት ይገኙበታል፡፡ “የሰፊው ህዝብ ድምፅ” የሚያሳትሙት ቡድኖች አድር ባይ መስመር ከማራመዳቸውም አልፎ ቀስ በቀስ ከደርግ ጋር ተዋሀዱ፡፡ “ዴሞክራሲያ” ና “አብዮት” ቡድኖች ግን አልፎ አልፎ ብዥታ ያልተላቀቃቸው ቢሆንም ደርግን በህዝባዊ ትግል መምታት እንደሚያስፈልግ መንግስቱም ፀረ ህዝብ እንደሆነ ያጋልጡ ጀመር፡፡ በሂደትም እነዚህ ሁለት ቡድኖች እየተቀራረቡ በመምጣት ነሐሴ 26/1967 ዓ.ም ባደረጉት ኮንፈረንስ ኢህአፓን መሰረቱ፡፡
ለትግሉ መሪ ይፈልግ የነበረው ህዝብም በአጭር ጊዜ ለኢህአፓ ድጋፉን ሰጠ፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች አላማውን ወደውና ፈቅደው ተቀብለውት በዙሪያው በመሰለፍ “ህዝባዊ መንግስት አሁኑኑ!” “ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ!” “ፋሽስቶች ይውደሙ!” የሚሉ መፈክሮችን እያስተጋቡ ደርግን ፋታ ነሱት፡፡ ኢህአፓ ጥያቄዎችንና መፈክሮችን በማንሳት ብቻም ሳይሆን ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጐን ቆሞ ደርግን በተግባር ታግሎታል፡፡ አባላቱና ደጋፊዎቹም እየወደቁም፤ እየሞቱም
“ፍፁም ነው እምነቴ
የትግሉ ነው ህይወቴ
ልጓዝ በድል ጐዳና
በተሰዉት ጀግኖች ፋና…” የሚለውን የንቅናቄ መዝሙራቸውን እየዘመሩ እነርሱም ቃላቸውን ሳያጥፉ ተዋድቀዋል፡፡
የብአዴን 20ኛ
አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በ1993 ዓ.ም ለህትመት የበቃችው “ፅናት” የተሰኘችው መፅሐፍ “የኢህአፓ መግነን ግን በአብዮቱ ጉዞ ላይ ሁለት አበይት ችግሮችን አስከተለ” ትለናለች፡፡ በአንድ በኩል ኢህአፓ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሲያድግና ሲጠናከር የደርግ
ውድቀት በጣም አጥሮ የሚታይበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ይህ አመለካከትም ኢህአፓ በመጀመሪያ በፕሮግራሙ የነደፈውን የተራዘመ የገጠር የትጥቅ ትግል መስመር ክዶ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ እንዲሯሯጥ ገፋው፡፡
“በሌላ
በኩል ኢህአፓ በአለም ላይ ካሉት ኮሚኒስት ፓርቲዎች የላቀና ተአምር ሰሪ፤ እጅግ የመጠቀና የረቀቀ የወቅቱ ብቸኛ ጥቁር ቦልሼቪክ ፓርቲ፤ አቻ የማይገኝለትና ወደር የሌለው የሰርቶ አደሩ አቦካቶ …ወዘተ ብሎ ራሱን ስለቆጠረና በየቦታው ስለተነገረለት እጅግ በርካታ ትግል ፈላጊ የድርጅቱን ምንነት መርምሮ ለማወቅ ሳይጣጣርና ሳይችል የትግል ፍላጐቱን ብቻ ሰንቆ ተቀላቀለው” ስትል “ፅናት” ሁለተኛውን ምክንያት ትተነትናለች፡፡
በዚህ ሳቢያም በንድፈ ሀሳብ ተጠናክሮ የትግሉን ሂደት በውል ተረድቶ ከሚንቀሳቀስ አባል ይልቅ የደርግን ውድቀት ብቻ እያማተረ የሚነጉድ አባል በመበራከቱ በሂደትም ውስጣዊ ሁኔታም የፈጠራቸው ልዩነቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ብቅ አሉ፡፡ አባላቱ ለሚያነሱት ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ፈጥሮ ወደ ውይይት ከመምጣት ይለቅ “ኢህአፓ በውስጡ የሚነሱ ጠላቶቹንም እየታገለ ጥራቱን ይጠብቃል” በማለት በፓርቲው አቋም ላይ ልዩነት የሚያነሱ አባላትን ያፍን፣ ያስርና ይገድል ጀመር፡፡ ፋሽዝምን ተቃውመው ትግል ሲያደርጉ ከነበሩ ኃይሎች ጋርም ከመተባበር ይልቅ “የላብ አደሩን ፓርቲ የኢህአፓን መሪነት መቀበል አለበት“ የሚል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ይጋጭ ጀመር፡፡ እዚህ ላይ በህወሓት አሸናፊነት የተደመደመው ለአንድ ወር የዘለቀው ጦርነት ተጠቃሽ ነው፡፡
ከኢህአፓ ሰራዊት(ኢህአስ) እና ከካድሬው የተወጣጡ የህቡዕ ስብስቦችም በኢህአፓ ላይ ሳይንሳዊ አቋም መያዝና መገምገም ጀመሩ፡፡ እነዚህ ሁለቱ ማዕከሎች ትግሉ በዴሞክራሲያዊ ህብረ ብሔራዊ ድርጅት ደረጃ መቀጠል የሚል አቋም ይዘው በበለሳ ውስጥ ሰፊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ያደርጉ ጀመር፡፡
የኢህአፓ አመራር
ድክመቶች በመጋለጣቸውና ኢህአፓ አብዮቱን የመምራት ብቃት ያለው ፓርቲ አለመሆኑ እየተረጋገጠ በመምጣቱ ከኢህአፓ ጋር የተያያዙ ፖለቲካዊ ውይይቶች በየማዕከሉ ደሩ፡፡ በዚህን ጊዜም ነበር የኢህአፓ ውድቀት የኢትዮጵያ አብዮት ውድቀት ተደርጐ ተወስዶ “ደርግን ማስወገድ ተራራን በገመድ እንደመጐተት ይቆጠራል” የሚል ተንበርካኪ ተረት የተተረተው፣ በ3ኛው አለም አብዮት ማድረግ አይቻልም ሲባል የተደመደመው፡፡ ከዚህ በኋላ በ1967 ዓ.ም የተመሰረተው ኢህአፓ የ5 አመታትን የትግል ቆይታ ብቻ አድርጐ በ1972 ዓ.ም ከትግሉ ሜዳ ውጭ ሆነ፡፡ በትግል ወኔያቸው ላይ ኢህአፓ ውሃ ቸልሷልና ብዙዎች “ከእንግዲህ ትግል!” ሲሉ ተስፋ ቆረጡ፡፡ አንዳንዶች በሱዳን አድርገው ተሰደዱ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ደርግን ተቀላቀሉ፡፡ በለሳ ላይ ትልም ያወጡት የዴሞክራሲያዊ ንቅናቄው 112 አንቀሳቃሾች ግን ትግሉን ሊቀጥሉ ሰኔ 4 1972 ዓ.ም ትግራይ ገቡ፡፡ ትግራይ በገቡ ማግስትም “ትግል ማድረግ እንደሚቻልና እንደማይቻል” እንዲሁም “ትግሉ እንዴት ይቀጥል” በሚለው ላይ ሰፊ ውይይት አደረጉ፡፡
እነዚህ ኃይሎች በኢትዮጵያ ሊያታግል
የሚችል አብዮታዊ ሁኔታ እንዳለ፣ ትግል ሊካሄድም እንደሚቻል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ “ትግሉ እንዴት ይቀጥል” በሚለው አጀንዳም ሁለት በታኝና ገንቢ ሀሳቦች ቢቀርቡም ትግሉ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ወታደራዊ መሆን እንዳለበት አስፈላጊውን ድርጅት የመፍጠር ዝግጅት ሀገር ውስጥ ሆኖ ከተሟላ በኋላ ፖለቲካዊ ወታደራዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መፍጠር እንደሚቻልና በሁለቱም መስኮች ትግሉን ማካሄድ እንደሚቻል ውጭ ካለው ታጋይ ኃይል ጋር በድርጅቱ የውጭ ክንፍ በኩል መገናኘት እንደሚቻል የተነሳው ገንቢ ሀሳብ በብዙሃኑ ድጋፍ አገኘ፡፡
ሰኔ 19/1972 ዓ.ም በትግራይ አካባቢ ትግል ሲያካሂድ ከቆየው የህወሓት ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ጋር ግንኙነት ተደረገ፡፡ ኮሚቴዎችም ተደራጅቶ ሊታገል ለመጣው ታጋይ ስለ ህወሐት ድርጅታዊ ሁኔታ፣ ህወሐት በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ስላለው አቋም፣ ህወሐት በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ድርጅቶች ላይ ስላለው አመለካከት ገለፃ ሰጡ፡፡ “ለመደራጀት እስከፈለጋችሁ ድረስ ህወሐት ባለው አቅም ለመተባበር ዝግጁ ነው” የሚል የድጋፍ መግለጫም ተሰጣቸው፡፡ ከዚህ ስብሰባ ማግስት 36 አባላት ወደ ሱዳን ለስደት ተጓዙ፡፡ ቀሪው ኃይልም ሊደራጅ ወስኖ አዲስ አደረጃጀት አዋቀረ፡፡ በ59 የሰው ኃይል በ4 ጋንታዎች ተዋቅሮ ለመደራጀት የሚያስፈልገውን ሂደት ያሟላ ጀመር፡፡
ይህ ኃይል የመደራጀት ዝግጅቱን በ3 መድረኮች ከፋፍሎ ነደፈ፡፡ የእርምት ንቅናቄ ማካሄድ፣ አደራጅ ኮሚሽን አቋቁሞ የመደራጀቱን ዝግጅት መቀጠል፣ መስራች ጉባኤ ጠርቶ ድርጅት መመስረት የሚሉ ነበር፡፡
የእርማት ንቅናቄው
በመጀመሪያ በጋንታ ቀጥሎም በኃይል ደረጃ ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 20 ቀን 1972 ዓ.ም ድረስ ባሉት 26 ቀናት ሙሉ ተካሄደ፡፡ በዚህ መድረክ የዴሞክራሲያዊ ንቅናቄው አጭር ታሪክ፣ የማዕከላቱ ግምገማ፣ የመርሆዎች አጠቃቀም፣ በዴሞክራሲያዊ ንቅናቄው ውስጥ የነበረው አሰራር፣ የቅራኔዎች አያያዝና በውስጥ ትግል ላይ የነበሩ አመለካከቶች፣ ከህዝቡ ጋር የነበረ ግንኙነትና ሊኖር የሚገባው ግንኙነቶች የሚሉ አጀንዳዎች ቀረቡ፡፡
ሐምሌ 22፣ 1972 ዓ.ም የጠቅላላ አባላት ስብሰባ ተጠርቶ ስለቀጣዩ የዝግጅት መድረክ ከተወያየ በኋላ የነበረውን ስብስብ እንደ አዲስ የሚያደራጅና ለመስራች ጉባኤውና ለሚመሰረተው ድርጅት አስፈላጊውን ዝግጅት የሚመራ 9 አባላት ያሉት አደራጅ ኮሚሽን ተመረጠ፡፡
በዝግጅት ወቅት
ግን ሌላ ዱብ እዳ ተፈጠረ፡፡ “ራሴን ከትግሉ አግልዬ ሁኔታውን ማየት እፈልጋለሁ” ያሉ አንዳንድ አባላት ወደ ሱዳን ለመሄድ ስንብት ጠየቁ፡፡ ይሁንና በቀሪው ኃይል በ52 የስብስብ ቁጥር የመደራጀቱ ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡
በኮሚሽኑ ስር
የተደራጁት ኮማቴዎች የየራሳቸውን ተግባር በልዩ ወኔና ተነሳሽነት ይከውኑ ጀመር፡፡ ድርጅታዊ ኮሚቴ የሚመሰረተውን ድርጅት ህግና ደንብ፣ አሰራርና አወቃቀር ነድፎ በማውጣት ለውይይት አወረደ፡፡ የፖለቲካ ኮሚቴው መስመርና በተለያዩ መሰረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ የሚኖረውን አቋሞች በተመለከተ ዘጠኝ የውይይት ፅሑፎችን አውጥቶ ያወያይ ገባ፡፡ ወታደራዊ ኮሚቴውም የድርጅቱ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምን መምሰል እንዳለበት በተዘጋጀ ማወያያ ፅሁፍ ማወየየት፣ ስብስቡን በወታደራዊ መስክ ማዘጋጀት፣ ልምምድ የማድረግና አካልን በስፖርት የማጠናከር ስራዎችን ይመራ ጀመር፡፡ በዚህን ወቅትም ተጨማሪ 5 ጓዶች “ከዚህ ስብስብ ድርጅት መጠበቅ ከንቱ ነው በማለት የስንብት ጥያቄያቸውን አቅርበው ወደ ሱዳን ተሰደዱ፡፡
በየመሀሉ ይገጥሙ
የነበሩ ፈተናዎችን በመቋቋም ለ5 ወራት በአዲስ መልኩ ለመደራጀት ያላሰለሰ ጥረትና ዝግጅት ተደርጐ ከህዳር 7 እስከ 11 1973 ዓ.ም በተደረገው መስራች ጉባኤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ኢህዴን) ተመሰረተ፡፡ ድርጅት ለመመስረት ከበለሳ ወደ ትግራይ የገባው ኃይል 135 የነበረ ይሁን እንጂ ትግራይ ውስጥ ተክራርዋ መንደር ኢህዴንን የመሰረቱት 37 ታጋዮች ነበሩ፡፡
በተለያዩ ጊዜ
የተረጋገጡ እንቅፋቶችንና የተለያዩ ምርኩዞች እየተደገፉ የተራመዱ ጨለምተኛና በታኝ አመለካከቶችን በተንሰራፋበት ወቅት በፅናት፣ በትግስትና በብሩህ ንፁህ የትግል መንፈስ ለመስራች ጉባኤው መድረሱ በወቅቱ የነበረው ኃይል አኩሪና አስደናቂ ታሪክ እንደሆነ “ፅናት” ትተርካለች፡፡
“ፅናት”
ስለ ኢህዴን ምስረታ አስፈላጊነት ስታብራራ “የጠላት ጐራ ባንፃራዊነት አይሎ፡ የትግሉ ጐን ባንፃራዊነት ተዳክሞ በነበረበት፣ አሉ የሚባሉት ብሔራው ትግሎችም ከሌላው ህዝብ ጋር ሊቆራኙ ባለመቻላቸው የህዝባችን የትግል አንድነት ማረጋገጥ ወቅታዊ በሆነበት፣ በኢህአፓ ምትክ ሀቀኛ የትግል መሪ ድርጅት በሚጠበቅበት ወቅት ነበር፣ ኢህዴን ባነስተኛ የሰው ኃይል ግን በተሻለ መስመር ወደ ትግሉ መስክ የተሰማራው” ትላለች፡፡
ከምስረታ ማግስት
ኢህዴን ተክራርዋ ላይ የማዕከላዊ ኮሚቴ የመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባ ጠርቶ ለ4 ቀናት መከረ፡፡ በስብሰባው ጉባኤው ያወጣቸውን አበይት እቅዶች መሰረት ያደረገ በፖለቲካ፣ በወታደራዊና በድርጅት መስክ የተከፋፈለ እቅድ ወጣ፡፡ ለአባላቱ ቀርቦም ለተግባራዊነቱ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ የትግራይ ነፃ መሬት ዞሮ ተጐበኘ፣ ሶስት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ወደ ሱዳን አቀና፤ ወታደራዊ ስልጠናው ይካሄድ ጀመር 5 አባላት ያሉት ቡድን ደግሞ የትጥቅ ትግል የሚጀምርበትን ቦታ ሊያጠና ወደ ወሎ ተንቀሳቀሰ፡፡ በተለይ ይህ የጥናት ቡድን በዋግና በራያ ተንቀሳቅሶ ጥናቱን ሲያከናውን እግረ መንገዱንም በሰቆጣ፣ በኮረምና አላማጣ ከተሞች የኢህዴን ፕሮግራምና ልሳኑን “ፍልሚያ”ን በመበተን የኢህዴንን መፈጠር ያበስር ነበር፡፡
አስፈላጊውን ዝግጅት
ካጠናቀቀ በኋላ ሚያዚያ 11፣ 1973 ዓ.ም ሰቆጣ አካባቢ ሚስግ ሚካኤል በተባለ ቦታ ላይ የትጥቅ ትግል መጀመሩን አወጀ፡፡ ከደርግ ጋር የመጀመሪያውን ውጊያ በማድረግም ሚያዚያ 13፣ 1973 ዓ.ም ጧት ጀርባ የተባለውን አካባቢ ተቆጣጠረ፡፡ ሁለተኛውን መደበኛ ስብሰባውን ከሚያዚያ 17 እስከ 22 1973 ዓ.ም ያካሄደው ኢህዴን የ6 ወር ሂደቱን ገመገመ፡፡ እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከሩና ወደሌሎች ወረዳዎች ትግሉን የማስፋት እንቅስቃሴ እንዲደረግ ወሰነ፡፡ ይህን ጊዜ ነበር ወትሮም ቢሆን ድርጅቱ እንዳይመሰረት በታኝ አመለካከት ይነዛ የነበረው አያሌው ከበደ ተሰማ (ያሬድ) ከድቶ ወደ ደርግ እንደገባ የተሰማው፡፡
ስብሰባውን ተከትሎም
የመጀመሪያው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ሚያዚያ 30 ተጠራ፡፡ ይህ ጉባኤ ኢህዴን ገና ከጅምሩ ለዴሞክራሲያዊ አሰራር ያለው ታማኝነት የታየበት ኮንፈረንስ ነበር፡፡ ይህንን ጉባኤ ልዩ የሚያደርገው ኢህዴን በረጅሙ ለሚጠብቀው ትግል ሊያሟላቸው የሚገቡ አንገብጋቢ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ፈጣን መልስ የሰጠበት በመሆኑ ነበር፡፡
ሶስተኛው የማዕከላዊ
ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ሲደረግ ደግሞ ሌላ ፈተና ታየ፡፡ በመስራች ጉባኤው ከተመረጡት 9 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ወደ ደርግ ከከዳው ከአያሌው ከበደ ተሰማ በተጨማሪ ወደ ውጭ አገር ተልከው የነበሩት 3 አባላት ተራ በተራ ተሰናብተው መክዳታቸው የታወቀው በዚህ ስብሰባ ነበር፡፡ ከ9 አባላት በ5 ብቻ የቀረው ማዕከላዊ ኮሚቴ በተንበርካኪ ቀኝ አድርባዮች ክህደት ሳይደናገጥ ድርጅቱን መርቶ ለማስጓዝና የአባላቱን ሞራል ጠብቆ ለመራመድ በታላቅ ቁርጠኝነት መነሳቱን አረጋገጠ” ስትል ፅናት የነበረውን የትግል ፈተና፤ ይህን ፈተና ለመወጣት ግን ጥቂቶች ቆራጦች የነበራቸውን የትግል ወኔ ትገልፃለች፡፡
ይህን እውነታ በማጤን ነበር ታጋዮቹ
“ስንቶች
ተኮላሽተው ካረንቋ ዘቀጡ
ስንቶች ተሸንፈው ከጐዳና ወጡ
ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው
ነገ እልፍ እንሆናለን ታሪክ ምስክር ነው” የሚለውን ራዕያዊ ስንኝ የቋጠሩት፡፡
ኢህዴን በመራር መድረኮች በትግስትና በፅናት አልፎ ነበር ለድል የበቃው፡፡ ለዚህም ነው ድርጅቱን “በእሳት የተፈተነ ወርቅ” የምንለው፡፡ ድርጅቱ ከምስረታው ጀምሮ በርካታ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮችን አስተናግዷል፡፡ ከላይ ኢህዴን ያመናቸውና የተማመነባቸው ሳይቀሩ እንደካዱት አይተናል፡፡ ከሶስት አቅጣጫ (ቡግና፣ ሰቆጣና በለሳ) በተዘረጋ የደርግ የስለላ መረብም ኢህዴን ከባባድ ፈተናዎችን አይቷል፡፡
ከቡግና የሚዘረጋው የስለላ መዋቅር የሰራዊቱን እንቅስቃሴ የሚከታተልና ወደ ቡግና የማስፋት እርምጃ እንዳይኖር አስቀድሞ ለማገድ ዜና ይሰበስባል፡፡ ከሰቆጣ የሚዘረጋው ደግሞ በዋነኝነት ሰራዊቱን ሰርጐ በመግባት ድርጅቱን በአጭር ለመቅጨት የሚቻልበትን መንገድ የመፍጠር እቅድ ያለው ሆኖ በመርዝ የማጥፋት ሙከራንም የጨመረ ነበር፡፡ የበለሳው ደግሞ በዋነኝነት ከሰቆጣው ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ድርጅቱን በርከት ባሉ ሰላዮች ሰርጐ በመግባት የድርጅቱ እድሜ ለማሳጠር የሚረባረብ ነበር፡፡
ደርግ ለስለላ ስራ በመንግስት ደረጃ ከሰጠው አብይ ትኩረትና ቀደም ሲል ከነበረው የእስራኤል፡ የምዕራብ ጀርመንና የአሜሪካ የስለላ ተሞክሮ ላይ የኬጂቢን ተመክሮ አክሎ ካሳደገው የላቀ የስለላ ብቃት ጋር የኢህዴን የፀረ ስለላ ተመክሮና የፀጥታ ንቃት ዝቅተኝነት ተዳብሎ ለጠላት ስለላ ክፉኛ የተጋለጠ አድርጐታል፡፡ ይሁንና ለጠላት ፍላፃ የማይንበረከከው ኢህዴን በተናጠልም ይሁን በተደራጀ ሁኔታ የሚልኳቸውን ሰላዮችና ገዳይ ቡድኖች ተቋቁሞ ድርጅታዊ ህልውናውን አስጠብቆ ትግሉን አስቀጥሏል፡፡
ኢህዴን ከተመሰረተ በኋላ ፈተናዎች ቢበዙበትም በርካታ ድርጅታዊ፣ ፖለቲካዊና አኩሪ የውጊያ ተግባራትን ከውኗል፡፡ በተለይ ህዝቡን በፖለቲካ በማንቃት፣ በማደራጀትና በማስታጠቅ ከኋላ ቀር አመለካከቶች ነፃ ሆኖ እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር የሚያስችል ህዝባዊ አስተዳደር ኮሚቴዎችን በህዝቡ ምርጫ ያቆም ነበር፡፡ ኢህዴን ነፃ ባወጣባቸውና በተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎች ያሉ ህዝቦች የኢህዴንን ህዝባዊነት እንዲገነዘቡ አስችሏቸዋል፡፡
አብዮታዊ ሰራዊቱን
በመገንባትና ድርጅታዊ አቋሙን በማጠናከር ነፃ በሚያወጣቸው አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በገበሬ ማህበራት እያደራጀ ለዘመናት በፊውዳልና በፋሽስት ገዢዎች ያላገኘውን የዴሞክራሲ መብት ታግለው እንዲያገኙ አብቅቷቸዋል፡፡ ህዝቡ ከደርግ ብዝበዛና ግፎች እንዲላቀቅ አስችሎታል፡፡ ደርግ መሬት ለማግኘት ግብር መክፈልን ቅድመ ሁኔታ በማድረጉ መሬት አልባ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸው ለቆዩ አርሶ አደሮችም ኢህዴን መሬት አድሏል፡፡ በ1977 ዓ.ም በትግራይና በወሎ ክፍላተ ሀገራት በደረሰው ረሀብ ለተጐዱ ህዝቦችም ኢህዴን ያደረገው አስተዋፅኦ ሁሌም ታሪክ የሚያነሳው ነው፡፡ መሪ ድርጅታቸው ኢህዴን ከደርግ በተሻለ ሁኔታ ባደረገላቸው እርዳታ የተደሰቱት የወሎ አርሶ አደሮች ዜማና ግጥም ደርድረው
“የክፉ
ቀን ስንቄ፣
የፌሽታ እለት ወርቄ
ታማኝ ድርጅቴ በቃልሽ ያደርሽው
ከፍዬ የማልዘልቀው ውለታሽ ከባድ ነው” ሲሉ ተቀኝተው ነበር፡፡
ኢህዴን ትግሉ የዴሞክራሲያዊ ኃይሎችን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑንና ለዚህ ጥያቄ ወቅታዊ ምላሽ አለመስጠት ከነገሮች ወደኋላ መጐተትን የሚያመጣ መሆኑን ተረድቶ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በ1980 ዓ.ም አጋማሽ እንዲመሰረት የበኩሉን ድርሻ አበርክቷል፡፡
ለኢህአዴግ ምስረታና
በኢህዴን መጠናከር የተደናገጠው ፋሽታዊው ደርግ በ1980 ዓ.ም በኢህዴንና ነፃ በወጣው የጐንደርና የወሎ ህዝብ ላይ ተደጋጋሚና ሰፊ ወረራዎችን አካሂዷል፡፡ በዚህ ወቅት ብቻ በወሎና በጐንደር ከ8 ብርጌዶች በላይ ቢያዘምትበትም ኢህዴን ወረራውን በብቃት ሊመክተው ችሏል፡፡ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮም የተዋጊ ሰራዊቱን ኃይል አደረጃጀት ወደ ክፍለ ጦሮች ደረጃ በማሳደግ የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝቦች መከታ ሊሆን የቻለ ደልዳላ ኃይል መገንባት ችሏል፡፡ ከየካቲት 1981 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ ባደረገው ከፍተኛ የመስመር የማጥራትና የመጨበጥ ትግል አማካኝነት ያለፉ ድክመቶችን በመጠነ ሰፊ ሴሚናሮችና ኮንፍረንሶች ከተመለከተ በኋላ 2ኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ከሰኔ 11 እስከ 15 1981 ዓ.ም በማካሄድ ጠንካራ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ሆኖ ሊቆም በቃ፡፡
ህዝቡም የደርግን ስርዓት ሊገረስስ በደጀንነት ተሰልፎ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደርግ ጀመር፡፡ ከ1982 ዓ.ም የመጀመሪያ ወራት ጀምሮ ነፃ በወጡ አካባቢዎች የሚገኘው ህዝብ ህዝባዊ ሸንጐዎችን እየመሰረተ ስልጣኑን በእጁ እንዲያስገባ ተደረገ፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ሰፊ አብዮታዊ የህዝብ መነሳሳት በመፍጠር ትግሉን ወደ ከፍተኛ ጥንካሬ አሸጋገረው፡፡ በደርግ ይሰነዘርበት የነበሩ ጥቃቶችን ህዝቡ በሸንጐዎቹ አስተባባሪነት ይመክት ገባ፡፡ የአካባቢው ችግሮች እየገመገመ መፍትሄ የመስጠት ልምድም ደረጃ በደረጃ አሳደገ፡፡ በተለይ ደርግ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ሽምቅ ተዋጊዎችን ወደ ነፃ የኢህዴን መሬት በማሰማራት ትግሉን ለማዳከም ያደረገውን ጥረት በማክሸፍ በኩል ሸንጐዎች ህዝቡን አስተባብረው ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የመሬት ክፍፍል በማድረግና የምርቱም ነፃ ተጠቃሚ እንዲሆን በማድረግ የህዝቡን ደጀንነት ለማጠናከር ተቻለ፡፡
በተለያዩ ድሎችና
ተግባራቱ ብቃት ያለው ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑን ያስመሰከረው ኢህዴን በአደረጃጀትና በቴክኒካዊ ብቃት ሊጠናከር እንደሚገባ ታምኖበት ከሁለተኛው ጉባኤ ማግስት ጀምሮ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ሰፋፊ ምልመላዎች ተካሄዱ፡፡ የሰራዊቱ ብዛት በሶሶት እጥፍ እንዲያድግ ተደረገ፡፡ በክፍለ ጦር ደረጃ እንዲደራጅ ተደርጐም ቴክኒካዊ ብቃቱን ለማጐልበት ከፍ ያለ ስልጠና ተሰጠው፡፡
በደርግ ውድቀት ወቅት ኢህዴን ላባደር፣ ቴዎድሮስ፣ አዋሽ፣ ሰንገደ፣ ዋለልኝ የሚባሉ ክፍለ ጦሮችና የከባድ መሳሪያ ሬጅመንቶች (ሻለቃዎች) እንደነበሩት የድርጅቱ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪ ለዚህ ግዙፍ ሰራዊት ድጋፍ የሚሰጡ የመገናኛ፣ የስንቅና ትጥቅ፣ የህክምናና የመሳሰሉት የተጠናከሩ ድጋፍ ሰጪ አካላትም ነበሩት፡፡
የኢህዴን ሰራዊት
በሰላም በትግል ዘመቻ ተልዕኮውን ይበልጥ በመወጣት ከህወሓት ሰራዊት ጋር ሆኖ ባካሄደው የተቀናጀ ርብርብ በደርግ ሰራዊት ላይ ጠንካራ በትሩን አሳረፈ፡፡ በየጊዜው የገጠሙትን ፈተናዎች እየተጋፈጠ በትግስትና በፅናት የታገለው ኢህዴን ወዳይቀሬው የደርግ ውድቀትና የህዝቦች ድል የመጣው በዚህ አግባብ ነበር፡፡
በደርግ ውድቀት ዋዜማና ማግስት ሀገራችን የነበረባትን የመበታተን አደጋ በመታደግ ረገድም ኢህዴን የጐላ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር መድረክ እንዲፈጠር ያስቻለ ኃይልም ነው፡፡ ምንም እንኳን ኢህዴን ህዝቡን ባሳተፈ የትጥቅ ትግል ፋሽስታዊውን አገዛዝ ቢገረስስም አላማዎቹን ለህዝብ አቅርቦ ዘላቂ የፖለቲካ ስርዓት ለመመስረት የሚያስችለው ህጋዊ ስልጣን የመጨበጥ አላማ አራምዷል፡፡
ኢህዴን ለመላ የሀገራችን ህዝቦች ለአማራ ጭቁን ህዝቦች ጭምር መብትና ጥቅም የታገለ ድርጅት ነው፡፡ በተናጠል ለአማራ ብሔር መብት የመታገል ተልዕኮ አልነበረውም፡፡ በኢህዴን ትግል ውስጥ ከአማራ ተጋዳዮች በተጨማሪ የኦሮሞና የደቡብ እንዲሁም የሌሎች ኢትዮጵያውያን ታጋዮች ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የድርጅቱ እንቅስቃሴ በወሳኝነት አማራው በሰፈረባቸው አካባቢዎች በመሆኑና በዋነኝነት ያታገለውም ይህንኑ ህዝብ መሆኑ ከዚህ ህዝብ ጋር የነበረው ትስስር ጠንካራ እንዲሆንና በሂደትም ብሔራዊ ተልዕኮውን ለመሸከም የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ የፈጠረለት ነበር፡፡
በመሆኑም ኢህዴን
ለአማራው ብሔር መብትና ጥቅም የመታገል ተልዕኮን ተሸክሞ ይራመድ ዘንድ ራሱን ከህብረ ብሔራዊነት ወደ ብሔራዊ ድርጅትነት ከጥር 12 እስከ 17/1986 ዓ.ም ባካሄደው ሶስተኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ቀየረ፡፡ ስያሜውንም የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ብሎ ጠራ፡፡ የሶሶተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ መግለጫ ኢህዴን ያደረገውን ሽግግር አስፈላጊነት በዚህ መልኩ ገልፆት ነበር፡፡
“ሶስተኛው
ድርጅታዊ ጉባኤ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት ዴሞክራሲያዊ አላማዎችን ለማሳካት በህብረ ብሔራዊ የድርጅት መልክ የታገለው ኢህዴን የብሔሮችን እኩልነት የማስከበር ግዴታውን በተወጣበት ታሪካዊ ሁኔታ የተካሄደ ነው፡፡ ነፍጠኞቹ የአማራ ገዥ መደቦች የአማራው ብሔር ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ብሔር መለያ መሆኑን ክደው በግዴታ ሌሎችንም የሚወክል እንዲሆን ያደረጉበትን ሂደት በመቃወም የተካሄደው ትግል በድል አድራጊነት ተጠናቋል፡፡ ኢህዴን የነፍጠኞቹን ትምክህተኛና ፀረ ጭቁን ብሔሮች መንግስት ለማስወገድ አንግቦ የተነሳውን ህዝባዊ አላማ ከአጋሮቹ ህዝቦች ድርጅቶች ጋር በመሆን ታግሎ ተፈላጊው ግብ ላይ አድርሶታል፡፡ ትግሉ ዳር በመድረሱም ዛሬ ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በየራሳቸው ብሔራዊ መለያዎች የሚወከሉበትና ብሔራዊ ጉዳያቸውን ባሻቸው መንገድ የሚወስኑበት አዲስ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በዚህ አዲስ እውነታ ምክንያት የኢህዴን ተልዕኮ ከህብረ ብሔራዊነት ወደ ብሔራዊነት ተሸጋግሯል፡፡ ሁሉም የሀገራችን ብሔሮችና ብሔረሰቦች በየራሳቸው ብሔራዊ ቋንቋና ባህል ሊጠቀሙ የሚችሉ በመሆናቸው የመላ ህዝቦችን ጥቅምና መብት ለማስከበር በነፃ ተደራጅተው ሊታገሉ የሚችሉበት ሁኔታ በመፈጠሩ ኢህዴንም ወደ ዴሞክራሲያዊ ብሔራዊ ንቅናቄ ተሸጋግሯል፡፡ ለ13 አመታት በትግል እሳት የተፈተነው የጭቁኖች ድርጅት ኢህዴን በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ወሳኝነት ወደ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄነት አድጓል፡፡”
ብአዴን ያነገበው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔረተኝነት በይዘቱ የአማራ ገዥ መደብ ሲያራምደው ከኖረው ትምክህተኛ ብሔርተኝነት የሚለይበት መሰረታዊ ገፅታ በሚገባ ተብራርቶ የድርጅቱ አባላት ብቻ ሳይሆኑ የአማራ ሰፊ ህዝብ እንዲያውቃቸውና እንዲመራባቸው ተደርጓል፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሁሉም ብሔሮች መብት መከበርን መሰረት በማድረግ በህዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነትን እንደሚደግፍ ለዚህም እንደሚታገል፤ የአማራ ህዝብ በክልሉም ሆነ በሌሎች ክልሎች ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ተጐራብቶና ተሰባጥሮ የሚኖር በመሆኑ የህዝቦች መብት መጠበቅ የጋራ ጥቅምን የሚያረጋግጥ መሆኑን የሚያምን እንደሆነ በፅኑ ያምናል፡፡ በመሆኑም በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲፈጠር ብአዴን በፅናት ታግሏል፡፡
አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ
ኃይል ብአዴን ከታገለላቸው አላማዎች አንዱ በነፃ ህዝባዊ ምርጫ የሚቋቋም ህዝባዊ መንግስት መመስረትና ህዝቡ በመረጣቸው እንደራሴዎች አማካኝነት የመንግስታዊ ስልጣን ባለበት እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በየደረጃው በሚዋቀሩት ምክር ቤቶች አማካኝነት ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ማቋቋም የሚል አላማ ነው፡፡ ይህንን አላማ በተግባር ያረጋገጠው ብአዴን በ1987 ዓ.ም የአማራ ክልል ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን መስርቷል፡፡
ከክልላዊ መንግስቱ
ምስረታም በኋላ ብአዴን ድል ከመጐናፀፍ አልተገደበም፡፡ ፅናት፣ ትግስት፣ ህዝባዊነትና ቁርጠኝነት ገንዘቡ የሆነው ብአዴን ልክ እንደ ትጥቅ ትግሉ በሰላሙም ጊዜ በርካታ የልማትና የዴሞክራሲ ድሎችን ደራርቧል፡፡ የክልሉን ህዝብ ከድህነትና ከኋላቀርነት ለማላቀቅ የተጋው ብአዴን ከክልሉ ውጭም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተገኘው የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ እመርታዎች የራሱን አሻራ አሳርፎባቸዋል፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላም ብሔራዊ ተዋፅኦው የተስተካከለና ለሀገርና ለህዝብ ሉአላዊነት፣ ለሰላምና ለልማት የቆመ ሰራዊት ለመፍጠር በተደረገው እንቅስቃሴ እርሾ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ለአሁኑ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ጉልህ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኝ የጦር መሪዎችን ለማፍራት የቻለ ድርጅትም ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ያቀደችውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በላቀ ሁኔታ ለማሳካትም ብአዴን ላልቶ የማያውቅ ወገቡን ይበልጥ አጥብቋል፡፡ በአማራው ስም የሚነግዱ ትምክህተኛ ኃይሎችንም ገና በጨቅላነቱ ጀምሮ በጠነከረው ክንዱ እየተፋለማቸው ነው፡፡ ክልሉንና አጠቃላይ ሀገራችንን ከድህነት አረንቋ በማላቀቅ ወደ መካከለኛ ገቢ የኢኮኖሚ ሰልፍ ለማሰለፍ አሁንም እንደ ድሮ ግንባር ቀደም ሆኖ በመትጋት ላይ ይገኛል፡፡
No comments:
Post a Comment