ከእብናት በለሳ ጉሃላን ከተማዋን ይዞ እንደገናም ምስራቅ በለሳ አርባ
ፀጓር እስከ መና ወንዝ፣ ወንዙንም ተሻግሮ በርሃውን ሰንጥቀው ወደ
ዋግኽምራ በመሻገር ሳህላ ዝቃላ ድረስ ኢህዴኖች ይንቀሳቀሱበት የነበረው ግዛታቸው ነበር፡፡ ወደ ኋላም ቆላ ሃሙሲት፣ ጨውጫዊት፣
ታችና ላይ አርማጭሆ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ ፈላሻ ጭቃ ማርያም፣ ከንፈል ሚካኤል፣ ፈልፈል ማሰሮ…እስከ አንገረብ ወንዝ ድረስ ኋላም
ላይ ጉና፣ ጋይንት፣ እስቴ፣ ፋርጣ፣ ደብረታቦር እንደገናም በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ መራኛ የኢህዴን ታጋዮች እጅግ አስደናቂና አስገራሚ
ለማመንም ለመገመትም በማይቻል ከባድ አስቸጋሪ የመሬት ገፅ ውስጥ በመንቀሳቀስ ዓላማቸውን ዳር ለማድረስ ታግለዋል፡፡ ተዋግተዋል፡፡
ከባድ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ለድልና ለአሸናፊነትም በቅተዋል፡፡ ህዝቡ ባህር እነርሱ ደግሞ ዓሳ ሆነው ዋኝተውበታል፡፡
ከዚህ በታች የተጠቀሱትም ዋና ዋና ታሪካዊ ቦታዎችና ስፍራዎች ባለውለታ ናቸውና በእጅጉ ሊዘመርላቸው የሚገቡ
በመሆናቸው ልናስታውሳቸው ወደድን፡፡
ሚስግ ሚካኤል- በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ ወረዳ የሚገኝ ትንሽ መንደር ሲሆን ኢህዴን ሚያዚያ
11 ቀን 1973 ዓ.ም የትጥቅ ትግል መጀመሩን ያወጀበትና ይህን የሚያበስር የመጀመሪያው ጥይት የተተኮሰበት ቦታ ነው፡፡
ጀርባ ዮሃንስ- በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር
የሚገኝ ሲሆን የኢህዴን ሰራዊት ሚያዚያ 13 ቀን 1973 ዓ.ም የመጀመሪያውን ዘመቻ ያደረገበትና ነፃ ያወጣው ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡
በዚህ ታሪካዊ ቦታ ከህዳር 14 እስከ ህዳር 21 ቀን 1976 ዓ.ም ድረስ ኢህዴን አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን አካሄዶበታል፡፡ ጀርባ
ዮሃንስ ለረጅም ጊዜ የድርጅቱ አመራር ፅ/ቤት ሆኖ ያገለገለ ሲሆን 11ኛው ዙር የኢህዴን ወታደራዊ ስልጠናም ተሰጥቶበታል፡፡
ሰቆጣ ከተማ- የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ርዕሰ ከተማ ስትሆን በትግሉ ወቅት የኢህዴን
ቤዝ ሆና ያገለገለችና የከተማዋ ወጣቶች በብዛት ወደ ትግሉ የተቀላቀሉበት ነው፡፡ በትግሉ ወቅት ሰቆጣ ከ11 ጊዜ በላይ በአውሮፕላን
የተደበደበች ሲሆን ይህን የአየር ጥቃት ህዝቡ የመሬት ውስጥ ቤት በመስራት ይከላከል ነበር፡፡
አምደ ወርቅና አርፋ- በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በዳህና ወረዳ አምደ ወርቅ የአየር ድብደባ የደረሰበት
ሲሆን አርፋ በትግሉ ዘመን የምስራቅ ሪጅን ፅ/ቤት ሆኖ ያገለገለ ለህዝብ ስራ፣ ለሰራዊትና ለውጭ(ሱዳን) የ24 ሰዓት የሬዲዮ ግንኙነት
አገልግሎት መስጫ ጣቢያ የነበረ እና ከ1977 እስከ 1982 ዓ.ም የህዝብ ስራ አመራርና ህክምና ስልጠና ይሰጥበት የነበረ ቦታ
ሲሆን ከመሬት በታች ተቆፍሮ የተሰራም ልዩ ፅ/ቤት ነበረው፡፡
አውሲግ(እነ ለጋ ዋሻ)- በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በዳህና ወረዳ ቀበሌ 03 የሚገኝ ቦታ ሲሆን
በመጋቢት/ ሚያዚያ 1981 ዓ.ም የኢህዴን ኮንፍረንስና ጉባኤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ሃይል(ኢማሌህ) ኮንፍረንስና
ጉባኤ የተካሄደበት እንዲሁም ከህወሓት ጋር ኢህአዴግ በሚል ግንባር መፍጠሩን ያወጀበትና ከሐምሌ ወር 1981 መጨረሻ እስከ መስከረም
ወር 1982 ከኢህአዴግ(ኢህዴንና ህወሓት) የተውጣጡ መሃል ሀገር የሚመደቡ ክፍለ ህዝቦች የሰለጠኑበት ታሪካዊ ዋሻ ነው፡፡
አዲስ ዘመንና እብናት- በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኝ ከተማ ሲሆን በ1983 ኢህዴን 24ኛ ዙር ወታደራዊ
ስልጠና የሰጠበት ቦታ ነው፡፡
ዳዩ ቆቦ- በቀድሞው ራያ ቆቦ አውራጃ በአሁኑ ራያ አላማጣ የሚገኝ ሲሆን የኢህዴን ሰራዊት በ1982 ዓ.ም
22ኛ ዙር ስልጠና የሰጠበት ነው፡፡ በቆቦ/ አራሞ የነበረው የሰልጣኝ ስም (ታሊሞ) ‘‘አንንበረከክም” ነው፡፡ ስልጠናው ለሁለት
ተከፍሎ በላሊበላ ዙሪያ ሲመኖ ወንዝ ተሰጥቷል፡፡
ዙይ ሀሙሲት- በሰሜን ጎንደር ዞን ከጉዋህላ አርባ ፀጉዋር በሚወስደው ዋናው መንገድ ላይ የምትገኝ የምስራቅ
በለሳ ወረዳ ንዑስ ከተማ ናት፡፡ ሰኔ 13 1981 ዓ.ም በደረሰ የደርግ የአውሮፕላን ድብደባ 210 ህዝብ ተጨፍጭፏል፡፡ በወቅቱ
ለገበያ የወጡ በርካታ እንሰሳት ጭምር አልቀዋል፡፡ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አምስት ሰዎች በአንድ ቀን አልቀዋል፡፡ ይህን የሚስታውስ
ሃውልት በከተማዋ እምብርት ላይ ቆሟል፡፡ዙይ ሃሙሲት ሰፊ ገበያ የነበራት ሲሆን የተለያዩ የፋብሪካ ምርቶች ለኢህዴንና ህወሓት በግዢ
የሚገኝባት ቦታ ነበረች፡፡
ማሰሮ ደንብ ከንፈረ ማርያም ቤዝ- በሰሜን ጎንደር ዞን ታች አርማጮህ ወረዳ ከወረዳው ዋና ከተማ ከሳንጃ
39 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ከንፈረ ማርያም የኢህዴን ሰራዊት ወታደራዊ ቤዝ ሆኖ በ1977 ዓ.ም የተመሰረተ በኢህዴን ታሪክ
የኮማንዶ ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጠና የሰጠበት ሲሆን በደርግ በተደጋጋሚ የአውሮፕላን ድብደባ የደረሰበት ቦታ ነው፡፡
ደለሳ - በሰሜን ጎንደር ዞን በታች አርማጮህ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ይህ ቦታ በአንገረብ ቤዝና ፈልፈል መካከል
የሚገኝ የስንቅ ማደራጃ ሲሆን ከአንገረብ ቤዝ ኩታ ገጠም ነው፡፡ በትግሉ ወቅትም ኢህዴን በዘመናዊ መንገድ የእርሻ ስራ ይሰራበት
የነበረ ቦታ ነው፡፡
ዝቃላ- በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን
ዝቃላ ወረዳ በእግሪ በተባለ ቦታ 3ኛ ዙር የኢህዴን ወታደራዊ ስልጠና የተሰጠበት ደርግ በሰልጣኝ መልክ አደራጅቶ በላካቸው
ሰላዮች አማካኝነት ታጋይ ብርሃኑ የተሰዋበት ቦታ ሲሆን በትግሉ ታሪክ የመጀመሪያው መስዋዕትነት የተከፈለበት ልዩ ቦታ ነው፡፡
ቡግና- ሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞን የሚገኝ ወረዳ ሲሆን በዚሁ ወረዳ አያን ሚካኤል በተባለ ቦታ በተደጋጋሚ
ከደርግ ጋር ውጊያ የተካሄደበትና ላይድባ ወይም መቀላ በተባለ የውጊያ አውድ የድርጅቱ ሦስት መስራች አባላት(ዘርጋው፣ ክበበውና
እዮብ) የተሰዉበትና ታጋይ መለስ ጥላሁን የቆሰለበት ቦታ ሲሆን በቦታው ላይም ለታጋዮች መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሀውልት ተሰርቷል፡፡
ሸምሺህ- በሰሜን ወሎ ዞን በላሊበላ ይገኛል፡፡ ኢህዴን እስከ 1976 ዓ.ም ድረስ ሦስት ኃይል ሰራዊት
ብቻ ነበረው፡፡ በ1977 ዓ.ም ሁለት አዳዲስ ኃይል አደራጀ፡፡ በዚህ ወቅት በሰነዘረው ማጥቃት በቡግና ወረዳ አሁን ላሊበላ ከተማ
የሸምሺህ አውሮፕላን ማረፊያን ተቆጣጥሮ አንድ የእርዳታ አውሮፕላን ማረከ፡፡ በወቅቱ አብራሪዎቹ ጀርመናዊያን ስለነበሩ በጀርመን
የአማርኛ ሬዲዮ ዝግጅት ክፍል ስለ ኢህዴን ህልውናና ድል አድራጊነት ካልተገለፀ እናቆያችኋለን ስለተባሉ በማግስቱ የኢህዴን ሰራዊት ላሊበላን ተቆጣጠረ የሚል
ዜና ተነገረ፡፡ እርዳታውም ለታለመለት ዓላማ እንዲውል አደረገ፡፡ እናም የኢህዴን ስም ናኘ፡፡ ከአድማስ አድማስ አስተጋባ፡፡
አልዋቅ- በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች ኮንፍረንስ
የተካሄደበት ተደጋጋሚ የአውሮፕላን ድብደባ የተፈፀመበት ቦታ ነው፡፡ ወታደራዊ ስልጠናም ተሰጥቶበታል፡፡ የምስራቅ ሪጅን ለሁለት
ተከፍሎ አንደኛው ምዕራብ ወሎ ሲሄድ የቀረው ሪጅን ፅ/ቤት ማዕከል ሆኖ አገልግሏል፡፡
ብአዴን ፅናቱንና ህዝባዊነቱን ጠብቆ የህዳሴውን ጉዞ ያፋጥናል!!
No comments:
Post a Comment