የድርጅታችን ኢህአዴግ ሊቀመንበር ጓድ ኃይለማርያም
ደሳለኝ፣ 10ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ መነሻ በማድረግ
በበርካታ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ጉባኤውን ምክንያት በማድረግ ለተዘጋጀችው ልዩ
እትም መጽሄት በተመጠነ መልኩ ከቃለ መጠይቁ
የተወሰኑትን ብቻ እዚህ አቅርበናል። መልካም ንባብ።
ጥያቄ፦ ጓድ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢህአዴግ ሊቀመንበር በመጀመሪያ ለ10ኛው
የድርጅታችን ጉባኤ እንኳን በሰላም አደረሰህ።
ጓድ ኃይለማርያም፦ ሁላችንም እንኳን በሰላም አደረሰን።
ጥያቄ፦ እስከ ዛሬ የተካሄዱት የኢህአዴግ ጉባኤዎች ምን ተጨባጭ ለውጥ
አስገኙ? በተለይም ወሳኝ የሚባሉት ጉባኤዎች በአገራችንም ሆነ በድርጅታችን
ጉዞ ላይ የፈጠሩት ለውጥ ብትገልፅልኝ?
ጓድ ኃይለማርያም፦ የድርጅታችን ጉባኤዎች በድርጅታችንም ሆነ በአገራችን ሁለንተናዊ
እንቅስቃሴ ላይ ያለቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን። ጉባኤዎች
ድርጅቱ ያለበትን ደረጃ በጥልቀት በመገምገም ከአንድ ምዕራፍ ወደሌላኛው
እንዲሸጋገር የሚያደርጉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ታላቅ መድረክ ነው። ስለዚህ
በድርጅታችን ታሪክ ውስጥ ጉባኤዎች የሚጫወቱት ሚና በጣም ትልቅ ነው። ከዚህ አኳያ የመጀመሪያው የኢህአዴግ ጉባኤ
የሽግግሩ ወቅት ምን መምሰል እንዳለበት፣ ምን
ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ
ፖሊሲዎች ሊዘረጉ እንደሚገባ፣ በዚህ የሽግግር
ወቅት ማን መሳተፍ እንዳለበት፣ እንዴት
መሳተፍ እንዳለበት፣ ከአንድ አምባገነንና ሰው
በላ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ
ስርዓት የሚሸጋገርበትን ሁኔታ ያመቻቸ ትልቅ
ጉባኤ ነው። በኢህአዴግ ታሪክ ውስጥ መላውን
የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች
ለማታገል የሚያስችል አጀንዳ በሚገባ ተለይቶ
የተያዘበት ጉባኤ ነው።
ስለዚህ የአንደኛው ድርጅታዊ ጉበኤያችን አሁን
ላለንበት ሁኔታ ሁሉ መሠረት የጣለ ጉባኤ
ነው። በሽግግሩ ወቅት የነበሩ ድሎች በሙሉ
በዚህ ጉባኤ በተወሰኑ መስመሮችና አቅጣጫዎች
ባይሄዱ ኖሮ አገሪቱ ወደ መበታተን፣ ወደ
እልቂት፣ ወደአላስፈላጊ ነገሮች ትገባ ነበር።
ጉባኤው ይህንን ቀልብሶታል። ስለዚህ ትልቅ
ታሪካዊ ጉባኤ ነው ማለት ይቻላል።
ሌላኛው ወሳኝ ጉባኤ የተሃድሶ ጉባኤያችን
ነው።ይህ ጉባኤ በድርጅታችን ውስጥ የተፈጠሩ
ጉድለቶችን በሚገባ አንጥሮ በማስቀመጥና መሠረታዊ የሆነ የድርጅታችንን
መስመር አጥርቶ የነደፈበትና ያፀደቀበት አራተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ነው። ይህ
የህልውና ማዳኛ ጉባኤ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። አራተኛው ድርጅታዊ
ጉባኤያችን በጣም ታሪካዊ ጉባኤ ነው። ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ
የተሃድሶ መስመር ተግባር ላይ ውሎ አሁን ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ትልቅ
ለውጥ እንዲያመጣ መሠረት የጣለው። በእርግጥ ይህ ማለት ከዚያ በፊት
ከአንደኛው ድርጅታዊ ጉባኤ እስከ አራተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በተካሄዱት
ስራዎች ኢህአዴግ ለውጥ አላመጣም ማለት አይደለም። በዴሞክራሲ፣
በህዝብ ተጠቃሚነት፣ በህዝቦች መብት ጉዳይ ላይ፣ በእኩልነት ጉዳይ ላይ
መሠረታዊ የሆኑ በሽግግሩ ጊዜ የተቀመጡ መፍትሔዎች አሁንም ትልቁ መፍትሔ ሆነው ቀጥለዋል። በህገ መንግስቱም ተጽፈው በሚገባ ተግባራዊ
እየሆኑ መጥተዋል። ነገር ግን ፖለቲካል ኢኮኖሚው የሚመራበት አቅጣጫን
በተመለከተ በሚገባ አልተመለሰም ነበር። ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች ናቸው
በአራተኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የተመለሱት።
ሌላኛው ወሳኝ ጉባኤ ብለን የምንወስደው ስምንተኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችንን
ነው። ከአራተኛው እስከ ስምንተኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን ባሉ ዓመታት
ድርጅታችን በፈጣን ሁኔታ ዕድገት አስመዝግቧል። በተለይም ከአምስተኛው
ድርጅታዊ ጉባኤያችን ቀጥሎ ባሉ ጊዜያት ፈጣን የሆነ ዕድገት ተመዝግቧል።
ይህ ፈጣን ዕድገት በመሠረቱ በገጠር በአርሶ አደር ባካሄድነው እንቅስቃሴ፤
በከተሞችም በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ በሰራናቸው ስራዎች በድምር ውጤት
እስከ ስምንተኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን ለሰባት ተከታታይ ዓመታት ፈጣን
እድገት አስመዝግበናል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ስምንተኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን ያስቀመጠው አንድ መሠረታዊ ጉዳይ
ደግሞ ፈጣን ዕድገት አለ፤ ህዝቡ በየደረጃው
ተጠቃሚ መሆን ጀምሯል። ነገር ግን በኢኮኖሚው
በራሱ ውስጥ ግብርናን ወስደን በምናይበት ጊዜ
የመጠን ዕድገቶች ያሉንን ያህል መዋቅራዊ ለውጥ
በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያልመጣ መሆኑን ገምግመናል።
ከዚያም አልፎ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው መዋቅራዊ
ለውጥ እንዲያመጣ ካስፈለገ ግብርና በፍጥነት ማደጉ
እንደቀጠለ ሆኖ በሂደት ኢንዱስትሪ የመሪነት ሚና
የሚጫወትበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆን ነበረበት።
ስለዚህ ዕድገት ብቻ ሳይሆን ትራንስፎርሜሽንም
ማረጋገጥ አለብን። በእርግጥ ዕድገት ለትራንስፎርሜሽን
ወሳኝ ቢሆንም ትራንስፎርሜሽን ራሱን ሊያረጋግጥ
የሚችል ተጨማሪ ጥረት ተጨማሪ ስራ መሠራት
አለበት የሚል ነበር የተወሰ ነው። ስለዚህ
ስምንተኛውን ድርጅታዊ ጉባኤያችንን በምናይበት ጊዜ
የዕድገት ብቻ ሳይሆን የትራንስፎርሜሽን ጉባኤ ሆኖ
ነበር የተከናወነው።
ጥያቄ፦ ዘጠነኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን ከታላቁ
መሪ ከጓድ መለስ ዜናዊ እልፈት በኋላ የተካሄደ
ጉባኤ ነው። ከዚህ አንፃር በወቅቱ ከአገር ውስጥም
ከውጭም ኢህአዴግ አብቅቶለታል፤ ያለ ጠንካራ
መሪ ቀርቷል የሚል አስተያየት ነበረ። ከዚህ አንፃር ጉባኤውንና የወሰናቸውን ውሳኔዎች እንዴት ታስታውሰዋለህ?
ጓድ ኃይለማርያም፦ ዘጠነኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችንን ከመሪያችን ከጓድ
መለስ ዜናዊ መስዋዕትነት በኋላ የተካሄደ በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል።
መሪያችን ሲሰዋ በርካቶቹ ኢህአዴግ አበቃለት ያሉም ነበሩ። ኢህአዴግ
ህይወት አይኖረውም ያሉ፣ በመሪዎቹ መካከል ትርምስ እንደሚነሳ የተነበዩ
ቀላል አልነበሩም። በመጀመሪያ ደረጃ የጓድ መለስ ጥንካሬ ከሚለካባቸው
ጉዳዮች አንዱ ተቋም የመገንባት ችሎታው ነው። ብዙ ሰዎች መረዳት
ያለባቸው ጉዳይ ቢኖር ጓድ እንዲውልም በማድረግ የማይተካ ሚና የተጫወተ ጓድ
ነው። ነገር ግን ደግሞ ሐሳብ ማመንጨትና ተግባራዊ
ማድረግ ብቻ ሳይሆን ተቋም በመገንባት በኩልም
ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። የአንድ ድርጅት ህልውና
የሚለካው በተቋማት ጥንካሬ ነው። እንደሚታወቀው
ድርጅታችን በጓድ መለስ አመራር ዘመን በተለይም
ከተሃድሶ ጊዜ ጀምሮ ግንባር ቀደሞችን በስፋት ያፈራ
ድርጅት ነው። ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች፣ ግንባር
ቀደም የጥቃቅንና አነስተኛ ሠራተኞች፣ ግንባር
ቀደም መምህራን፣ ግንባር ቀደም የዩኒቨርሲቲ
ተማሪዎች፣ ግንባር ቀደም የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ
ተማሪዎች፣ ግንባር ቀደም የመንግስት ሠራተኞች
የድርጅታችን አባል እንዲሆኑ ጥረት ተደርጎ ይህም
የተሳካ እየሆነ የመጣበት ወቅት ነው።
ስለዚህ ጓድ መለስ ከሰራቸው ነገሮችና የእሱ ውርስ
ናቸው ከምንላቸው ጉዳዮች አንዱ የተቋም ግንባታ
ነው። ብዙዎች ይህን ሀሳብ የሚያቀርቡ ያልተረዱት
ነገር፣ የጓድ መለስ ዋናው ስራ የተቋም ግንባታ
እንደሆነ አለማወቃቸው ነው። እሱ ይህን ስራ ሰርቶ
ለእኛ አስረክቦ በተሰዋበት ጊዜ ይሄ ተቋም ስራውን
ቀጥሏል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መሰረታዊ አቅጣጫ፣
ፖሊሲና ስትራቴጂ ያለን በመሆኑ፣ አመለካከቱ፣ መለስ የንድፈ ሐሳብና የተግባር አመራር፣ ድርጅቱ
አሁን የያዘውን አመለካከት መስመር በማመንጨት፣ በመንደፍ፣ ተግባር ላይ መስመሩ፣ ፖሊሲዎችና ሰትራቴጂዎች ካሉ እንዲሁም
የሰው ሃይሉ እየበቃ የመጣ ከሆነ ድርጅታችን
የሚናጋበት ሁኔታ በምንም መልኩ ሊኖር አይችልም
ማለት ነው። ስለዚህም ይህ ተግባር ላይ ውሎ ተፈትኖ
የወጣበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል።
ድርጅታችን የህዝብ ድርጅት ነው፤ የታጋዮች ስብስብ
ነው። ለስልጣን የሚሰጠው ትርጉም ሌሎች ለስልጣን
ከሚሰጡት ጉዳይ የተለየ ነው። ስልጣን የሚፈለገው
ህዝብን ለማገልገል ነው። ስልጣን የሚፈለገው
መስዋዕት ሆነህ፣ አንተ ቀልጠህ ሌላው ሰፊው
ህዝብ የሚጠቀምበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው።
ድርጅታችን ይህን የሚያመቻቹ የታጋዮች ስብስብ
የሚመሩት መሆኑ የተመሰከረለት ነው። እኛ ስልጣንን
የምናየው ለህዝብ አገልጋይነት ካለው ጥቅምና ለውጥ
ለማምጣት ካለው አስተዋፅኦ ጋር አያይዘን ነው።
ስልጣን ለህብረተሰባዊ ለውጥ ካለው ጥቅም አንፃር
እንጂ ለብቻው ምንም ትርጉም የሌለው እንደሆነ ነው
የምናየው። ከዚህ አኳያ ከጓድ መለስ ህልፈት በኋላ
ቀውሶችና ነውጦች ይከሰታሉ ብለው ያስቡ የነበሩ
አካላት አሁን ረጋ ብለው ይሄ ድርጅት ምን አይነት
ተቋማዊ ጥንካሬ እንዳለው እንዲያዩ የተገደዱበት
ሁኔታ መኖሩን መረዳት ይቻላል።
ጥያቄ:- የ5ኛው አገራዊ ምርጫ ሂደቱንና ውጤቱን እንዲሁም የህዝቡን መልዕክት
እንዴት ትገልፀዋለህ? ተቃዋሚዎች የምርጫው ውጤት እንዳልተዋጠላቸው ሲናገሩ
ይደመጣሉ። የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት አበቃለት የሚል አስተያየትም ይሰነዝራሉ።
ይህን አስተያየትስ እንዴት ታየዋለህ?
ጓድ ኃይለማርያም:- ምርጫ አንዱና ትልቁ የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫ ነው።
ነገር ግን የዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫ ምርጫ ብቻ አይደለም። ህዝቡ በቀጥታ
በተለያየ መልኩ የሚሳተፍባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ህገመንግስቱም ያስቀመጠው የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት ስለሆነና ኢህአዴግም
የሚያምነው ይህን ስለሆነ እዚህ ሀገር ውስጥ በአንድ ፓርቲ ወይም በአንድ አስተሳሰብ
አምባገነናዊ የበላይነት የምንመራበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ገና ከሽግግሩ ጊዜ
ጀምሮ የተወሰነ ውሳኔ ነው። ስለዚህም ህገመንግስታችን ይሄ ሆኖ የመድብለ ፓርቲ
ስርዓት በሀገራችን እየተገነባ መጥቷል።
የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚጀምረው በአገራችን ፓርቲዎች በነፃነት ተመዝግበው፣
አባል አፍርተው የራሳቸውን አመለካከትና አስተሳሰብ ለመቅረፅ በሚያደርጉት
እንቅስቃሴም ነው። ከዚህ አኳያ ከ70 የማያንሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን
ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ነው። በ5ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫም 58 ያህል
ፓርቲዎች ተወዳድረው ህዝቡ የሰጣቸውን ብይን የተቀበሉበት ሁኔታ አለ። በብይኑ
መሰረት የሚገዛ ስርዓት ካለ መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት አለ ማለት ነው።
ስለሆነም መድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት በአገራችን ዛሬም አለ፣ ነገም ይኖራል።
በትግሉ ወቅት በርካታ ወጣቶች መስዋዕት ሆነዋል። መስዋዕት የሆኑበት
ጉዳይ አምባገነንነትን በመታገል ነው። አምባገነንነትን የታገለ ድርጅት በአገሪቱ
አምባገነንነት እንዲሰፍን በምንም መልኩ ሊፈቅድ አይችልም። አምባገነንነትን
ታግለህ አምባገነንነትን ማሰብ ስለማይቻል በምንም መልኩ አምባገነንነት በአገሪቱ
ሊኖር አይችልም።
አንዳንዶች ኢህአዴግ አምባገነን ድርጅት ሆኗል ብለው የሚያቀርቡት ሀሳብ ከመሰረቱ
የተሳሳተ ነው። በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት የመገንባት ጉዳይ
እኛ በተደጋጋሚ እንደምንለው የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን ከዚህ በፊትም ሀገራችንን
ወደ መበታተን ጫፍ አድርሷት የነበረው አምባገነንነት እንዳይመለስ የማድረግ ጉዳይ
ነው። ትግሉ የተካሄደውም ለዚህ ነው። ይሄ በመሆኑም አገራችን ተረጋግታ ብዙ
እምነቶችን አስተናግዳ በዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ እየተጓዘች ያለች ጠንካራ አገር
እየሆነች ያለችበት ሁኔታ መጥቷል። በተግባርም ስናይ ይኸው ሁኔታ እየተገለፀባት
ያለች ሀገር በመሆኑ አምባገነናዊ የሆነ የአንድ ፓርቲ ስርዓት ሊኖር እንደማይችል
በሚገባ መታወቅ አለበት።
በመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ አውራ ፓርቲ የተመሰረተባቸው በርካታ
አገሮች አሉ። የበለፀጉ አገሮች የሚባሉት እነ ጃፓን ፣ ሲዊድን፣ ከአፍሪካም እነ
ቦትስዋና የመሳሰሉ ሌሎችም በርካታ አገሮች አንድ ፓርቲ ለበርካታ ዓመታት ስልጣን ላይ
የቆየባቸው የአውራ ፓርቲ ስርዓት የገነቡ አገሮች አሉ። ስለዚህ ይሄ ማለት የመድብለ
ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት ጠፍቷል ማለት አይደለም። የአውራ ፓርቲ መድብለ ፓርቲ
ዴሞክራሲ ስርዓት በሂደት ደግሞ ወደ ተተካኪ ፓርቲዎች የሚሸጋገርበት የራሱ
ምዕራፍ አለው። ስለዚህ እጅግ አብዛኛው ጉዳይ ላይ የአገሪቱ ህዝቦች መግባባት
በሚፈጥሩበት ጊዜ ፓርቲዎች የተወሰነ ልዩነት ይዘው የሚተካኩበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ይሄ የእድገት ደረጃ እንጂ አንድ ፓርቲ የበላይነት የወሰደበት ጉዳይ ተደርጎ ሊታይ
አይገባም። በኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አሁንም
ጎልብቶ አለ፤ ወደፊትም ጎልብቶ የሚቀጥል ነው የሚል አስተያየት አለኝ።
ምርጫውን በተመለከተ በእኛ እምነት በተከታታይም እንደገለፅነው የዚህ
ስርዓት ባለቤቶች የኢትዮጵያ ህዝቦች ናቸው። ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ
ልማታዊ ስርዓታችን ጎልብቶ እየሄደ ያለው አርሶ አደሩ ባደረገው አስተዋፅኦ
ነው። አርሶ አደሩ ባለቤት በመሆኑ ነው። አርብቶ አደሩ ባለቤት በመሆኑ
ነው። ሰፊው የከተማው ህዝብ በየተሰማራበት መስክ ባለቤት በመሆኑ ነው።
ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ባለቤቶቹ ራሳቸው ማለትም መላውና ሰፊው
የአገራችን ህዝቦች ለሚጠቅማቸው ነገር በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብይናቸውን
አሳርፈዋል። ምርጫቸውን አሳውቀዋል፤ ሲመርጡ እኛ የኢትዮጵያ ህዝቦች
ቀጣዩን ጊዜ ኢህአዴግ እንዲመራን እንፈልጋለን ብለው ይሁንታቸውን
ሰጥተዋል።
ይሄ ለእኛ ከባድ ሸክም ነው፣ ከባድ አደራ ነው፣ ትልቅ ኃላፊነት ነው።
ስለዚህ ህዝቡ አምኖን በዚህ ደረጃ ከሰጠን እኛ ደግሞ የህዝቡን አደራና
ኃላፊነት፣ የተሰጠንን ሸክም በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ የሚገባን ወቅት ላይ
ነን። እንቅልፍ ሳይወስደን ሌት ተቀን ተረባርበን የህዝቡን አደራ ለመወጣት
መስራት ይጠይቀናል። ይሄ ከላይ እስከ ታች መሄድ አለበት። ነገር ግን አንድ
ነገር መሰመር ያለበት የልማት አቅሞች በሙሉ መንቀሳቀስ ካልቻሉ ይሄ
አደራ ሊፈፀም አይችልም። ይሄ በድርጅትና ድርጅት በሚመራው መንግስት
ብቻ ሊፈፀም የሚችል አይደለም። የልማቱ ባለቤትና ዋናው አንቀሳቃሽ ህዝቡ
ነው። እኛ እንደ ኢህአዴግም እንደ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትም
በምንሰጠው አመራር ደረጃ ያለውን ጉድለት መቅረፍ አለብን። ስለዚህ እኛ
የበኩላችንን እንሰራለን፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የበኩሉን ከሰራ
ድምር ውጤቱ አሁን ህዝቡ የሚፈልገውን ነገር ለማሳካት ያስችለናል።
ጥያቄ፡- ክቡር ሊቀመንበር በመጨረሻ አስረኛውን የድርጅታችንን ጉባኤ መነሻ
አድርገህ ለድርጅታችን አመራሮች፣ ለአባላት፣ ለደጋፊዎቻችንንና ለህዝቡ
የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ?
ጓድ ኃይለማሪያም፡- በመጀመሪያ ደረጃ እጅግ የሚያበረታታው አገራችን
በትክክልም የህዳሴ ጉዞ ጀምራለች፡፡ በማያቋርጥ የለውጥ ጉዞ ውስጥ
ገብታለች፡፡ ይህ የለውጥ ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ፡፡ በ2017 የዛሬ
10 ዓመት አካባቢ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ጎራ የምትቀላቀል አገር
ልናደርጋት ይገባል፡፡ በሂደትም በዚህ ላይ ተስፈንጥረን ወይም መደላድል
አድርግን የሚቀጥለውን የብልፅግና ጉዞ መጀመር ይገባል፡፡ ይህ ራዕይ ሊሳካ
የሚችለው መላው የአገራችን ህዝቦች የዚህ ራዕይ ተጋሪ ሆነው በዚህ ራዕይ
ዙሪያ ተሰልፈው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልክ ነው፤ ፍጥነቱም እንደዚሁ።
ሂደቱም የሚወሰነው በህዝቡ የነቃ የተደራጀ ተሳትፎ ነው፡፡ መስመራችንና
ጉዟችን የሚወሰነው ህዝቡን በዚህ ንቅናቄ ውስጥ ባስገባነው ልክና መጠን
ነው፡፡ የምንፈልገውን የህዝብ ንቅናቄ በፍጥነት ማምጣት ካልቻልን የዕድገት
ጉዟችንም ማዝገሙና መገታቱ የሚቀር አይሆንም፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል
በየደረጃው የሚገኙ የኢህአዴግ አመራሮች የአመራር ሚናችንን በአግባቡ
መወጣት አለብን፡፡ ይህ የሞት የሽረት ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በምንም መልክ ለአንድ አፍታም ቢሆን ዕድገታችን
መቀዛቀዝ የለበትም፡፡ በጊዜ የለንም መንፈስ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ከእኛ
የሚፈለገው ቁርጠኝነትም በዛው ልክ ማደግ አለበት፡፡ ስለዚህ አመራሮቻችን
ከላይ እስከ ታች ቁርጠኝነታቸው ከእድገታችን ጋር እያደገ መሄድ አለበት፡፡
ሰለዚህ ሙስናን መጠየፍ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችንና ተግባሮችን
ያለምህረት መታገልና ማስተካከል ይገባናል፤ ወደፊት እንዳንገሰግስ የሚገታን ሀይል እሱ ስለሆነ። ይህን ሀይል በመቆጣጠር እኛን ወደ ፍጥነት ጎዳና እንዳንሄድ
በማይከለክል ደረጃ ተደፍቆ እንዲኖር ማድረግ ይገባል፡፡ ይህን ያለምህረት
ከመታገል ውጭ ሊመጣ የሚችል አይደለም፡፡
ይህን ስርዓት ለማየት ብዙ ወጣቶች ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ዛሬ
እንደቀደምት ወጣቶች ራሳችንን አሳልፈን የምንሰጥበት የሚታይ ተጨባጭ
እሳት እንኳን ባይኖር ነገር ግን እንደ እሳት የሚያንገበግበንና መሟላት
ያለበት የህዝብ ፍላጎት ግን አለ፡፡ ስለዚህ ዋነኛ ጠላታችን የሆነው
ድህነትን በተደጋጋሚም እንደምንለው ለማፍረስ መንቀሳቀስ ይገባናል፡፡ አሁን
ደግሞ የእድገት ደረጃችን የደረሰበት ደረጃ ዕድገት ብቻ ሳይሆን መዋቅራዊ
ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግርን የሚጠይቅ የትራንስፎርሜሽ ወቅት
ሆኗል፡፡ ስለዚህ በየተሰማራንበት ሙያ ይህ ትራንስፎርሜሽን እንዲረጋገጥ
መስራት ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አኳያ የሚጠበቅብን ነገር በጣም ትልቅ እንደሆነ
ማየትና ራሳችንንም ማዘጋጀት ይገባናል፡፡ አንዱ መልዕክቴ ይህ ነው፡፡
አባሎቻችንም በየተሰማሩበት ዘርፍ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እየሆኑ ለውጡን
በመምራትና ከለውጡም ተጠቃሚ በመሆን የአገራችን የህዳሴ ግስጋሴ ማስቀጠል
ፋታ የማይሰጥ ተልእኳቸው መሆኑን ተገንዝበው መንቀሳቀስ አለባቸው።
መላው የሀገራችን ህዝቦችም በየተሰማሩበት የልማትና የዕድገት መስክ እንደዚሁ
በቁርጠኝነት ሊሰለፉ ይገባል፡፡ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የሚያደርገው
እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ ወጣቶችና አገራዊ ባለሀብቶች በልማታዊ መንገድ
ትራንስፎርሜሽኑን ለማረጋገጥ ተልዕኳቸው የተለየ የሚሆንበት ወቅት ላይ
እንገኛለን፡፡ አገራዊ ባለሀብቶቻችን የመንግስትን ድጋፍ ተጠቅመው የበለጠ
ወደ ማኑፋክቸሪንግና እሴት ፈጣሪ ዘርፎች ወይም አምራች ዘርፎች ራሳቸውን የሚቃኙበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ይህ ወቅት የአገራችን ዕድገት
ደረጃ ያመጣው ወቅት መሆኑን ተገንዝበው ሚናቸውን መጫወት አለባቸው፡፡
ደካማ ሀገራዊ ባለሀብት በሚኖርበት ሁኔታ ትራንስፎርሜሽን ማረጋጥ
አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሀገራዊ ባለሀብቶቻችንም በከፍተኛ ደረጃ መዘጋጀት
አለባቸው፡፡ መንግስት እንቅፋቶችን ለማሰወገድ በሚያደርገው ጥረት አብረው
ሊታገሉ ይገባል፡፡ በቀይ ምንጣፍ ላይ ተራምዶ የሚመጣ ልማት የለም፡፡
ከሚኖሩ እንቅፋቶች ጋር እየታገልን ነው ልማት ሊመጣ የሚችለው፡፡ እነዚህን
እንቅፋቶች ለመታገል መንግስት ዝግጁ ነው፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግም በዚህ
ደረጃ አመራር ለመስጠትና ለማስፈፀም ከፍተኛ ዝግጁነት አለው፡፡ ጉባዔያችንም
ይህን ንቅናቄ በሚፈጥር ሁኔታ ትግል ይለኩሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ
በዚህ መንፈስ ወደ ፊት ለመሄድ ሀገራዊ ባለሀብቶቻችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ
ለማበርከት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
ወጣቶች በተለይ ደግሞ የነገ ሀገር ተረካቢዎች የአሁኑ አልሚዎች እነሱ
ናቸው፡፡ ስለዚህ በፖለቲካውም በማህበራዊውም በልማቱም የሚፈለግባቸውን
አስተዋፅኦ ለማበርከት መነሳት የሚገባቸው ይሆናል፡፡
ጉባዔያችን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችል ውሳኔ እንደሚወስን
ይጠበቃል፡፡ በዚህ ላይ ተመስርተን ሁላችንም ወደፊት እንድንገሰግስ ለመላው
የአገራችን ህዝቦች መልዕክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡
የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጓድ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ለሰኸጠን ምላሽ
እናመሰግናለን
ጓድ ኃይለማሪያም፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment