በገነት ደረጃ
መስከረም 19 ቀን
2008 ዓ.ም 11፡30 ሰዓት ላይ ነጯ ኮስተር የቀጠሮው ቦታ ከነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ለመድረስ ማንም
አልቀደማትም፡፡ አንጋፋ የጥበብ ሰዎችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች
ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎችና ከ የአዲስ አበባ ተሰብስበዋል፡፡
የንጋቱ ብርድ ሳይበግረው፤ የጠዋት እንቅልፍ ሳይደልለው፤ በተገኘው የትራንስፖርት አማራጭ ተጠቅሞ ሁሉም በተባለው የቀጠሮ ሰዓት
መገኘቱ የሚዲያ ባለሙያዎቹና የጥበብ ሰዎች ከስራቸው እኩል ሰዓት አክባሪነታቸውንም አረጋገጡ፡፡
ቀድማ በቦታው
ከተገኘቸው ኮስተር በተጨማሪ 11፡45 አካባቢ በቦታው በደረሱ በሽንጠ ረጃጅሞቹ ሁለት የሰላም ባሶች ሁሉም ተጓዥ ለስራውና
ለቆይታው የሚያስፈልገውን ትጥቅ ሸከፉ፡፡ ባሶቹ ፊትለፊታቸው ላይ
‹‹የጥበብ ጉዞ›› የሚል ፖስተር እንደተለጠፈባቸው ወዲያው ተጠባቂው እንግዳ ከተፍ አሉ፡፡ አንጋፋው ታጋይና
የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ጓድ ካሳ ተክለብርሃን፡፡ ስለጉዞው በቁም ነገር የተሞላና አጠር ያለ ንግግር አደረጉ፡፡ ‹‹እንግዲህ ወደምትሄዱበት ቤተ መጽሓፍት የሉንም፤
ቤተ-መጽሓፍታችን ህዝቡ ነው›› በማለት ፍንጭ ሰጪ ንግግር አደረጉ፡፡ የአማራ ህዝብና የመሪ ድርጅቱ ትግል ታሪክ በአግባቡ
ባለመገለጹ ‹‹እናንተው አይታችው፤ ከህዝቡ ሰምታችሁ፤ ለሌላው አድርሱ›› በሚል ንግግራቸውን ቋጩ፡፡
የብአዴን/ኢህአዴግን
35ኛ የምስረታ በዓልን አስመልክቶ ያልተነገሩ/ያልተሰሙ የትግል ታሪኮችን ፍለጋ ከጠዋቱ 12፡30 የጉብኝት ቡድኑ ‹‹ለጥበብ
ጉዞ›› አዲስ አበባን ተሰናብቶ ወጣ፡፡ በጎጀም መስመር የነሱሉልታ፤ ጫንጮ፤ ደብረጽጌ፤ ፍቼ፤ ገብረጉራቻ የመሳሰሉትን የኦሮሚያ
ከተሞችን አቋርጦ እኩለ ቀን ላይ የህዳሴን ድልድይ በእግር በመሻገር የጋዜጠኞች፤ የካሜራ ባለሙያዎችና የጥበብ ሰዎች ቡድን
አማራ ክልል ገባ፡፡ በድልድዩ አቅራቢያ በሚትገኘው አነስተኛ ሻይ ቤት በተደረገለት አቀባበል ቆይታ በማድረግ የደረሱ የሰብል
ምርቶችን፤ ለምለም አካባቢን እያጋመሰ ደብረ ማርቆስ ሲደር የምሳ ግብዣና ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ቡድኑ ጉዞውን
በመቀጠል ከምሽቱ 3፡00 ባህርዳር ከተማ ሲደርስም የተለያዩ
የወጣት ማህበራት አቀባበል ተደርጎለት ወደ የቡድኑ አባላት ወደየሚያርፉበት
ቦታ አመሩ፡፡
በነጋታው መስከረም
20 ቀን 2008 ዓ.ም የጉብኝቱን በይፋ መጀመር አስመልክቶ
በብአዴን/ኢህአዴግ ጽ/ቤት በተዘጋጀው ስነ ስርዓት ላይ የጉዞው ተሳታፊዎች መካከል የሀገራችን ስመጥርና አንጋፋ
አርቲስቶች እንደነ ዳዊት ይፍሩ፤ ሰለሞን አለሙ፤ ተፈሪ አለሙ፤ ሰራዊት ፍቅሬ፤ ሸዋፈራው ዳሳለኝ፤ ሳምሶን ማሞ፤ አለለኝ
መኳንንት ጽጌ፤ ሰርጸ ፍሬስብሃት፤ ስናፍቅሽ ዘለቀ፤ ህይወት አራጌ፤ አኒሳ ሽኩር፤ ሜሪ ጃፈር፤ ካሳሁን ታዬ(ሶራ)፤ እመቤት
መኮንን(ሸደይ)ና ሌሎች፤ አንጋፋና ወጣት የሚዲያ ሰዎች ባጠቃላይ 180 ‹‹የጥበብ ጉዞ›› ተሳታፊዎች በተገኙበት ስነ ስርዓት
የጽ/ቤቱ ሀላፊና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጓድ አለምነው መኮንን ለጎብኝዎች ‹‹ስለ ብአዴን/ኢህዴግና ስለህዝቡ የትግል
ጉዞ እኛ አንነግራችሁም፤ የምትሄዱባቸው ተራሮች፤ ገደሎችና ሸለቆዎች ጎብኝታችሁ ትረዳላችሁ፣ ህዝቡም ይነግራችኋል›› በማለት የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በእጃቸው ዳሰው፤
በአይናቸው አይተው፤ ከህዝቡ ሰምተው ታሪኩንና የትግሉን ሂደት በሚገባ ተገንዝበው የብአዴን/ኢህአዴግና የአማራ ህዝብ ያደረገው
ተጋድሎ በየሥራ መስኮቻቸው ለሌላው እንደሚያሳውቁ ያላቸው እምነት ገልጸው ነበር፡፡ ጓድ አለምነው ይህንን ሲገልጹ የጉዞውን
አድካሚነትና የመልከዓ ምድሩን ፈታኝነት ያሠበ አልነበረም፡፡
በመቀጠልም የያኔው
ታጋዮች ሲጠቀሙበት የነበረው መለዮ ስታደል ግን ሁሉም ስለሚጠብቀው ነገር በትንሹም ቢሆን እንዲያስብ አድርጎታል፡፡
በብአዴን/ኢህአዴግ ጽ/ቤት ውስጥ የነበረው 180 የጥበብ ሰዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች የጎብኝ ቡድን ከዥንጉርጉር አለባበስ
በአንዴ ወደ ወጥ አለባበስ ተቀየረ፡፡ አመድማ መልክ ያላቸው ካኪ ኮፊያ(የድርጅቱ አርማ ያለበት)፤ ሱሪና ኮት በተጨማሪ
ዥንጉርጉር ቡናማ እንዲሁም አረንጓዴ ቀለም ያላቸውና አንገት ላይ ጣል የሚደረጉ ሽርጦች፤ የታጋይ መለዮ የነበሩት ‹‹በጥበብ
ጉዞ›› የጎብኝዎች መለያም ሆነ፡፡ ጓድ አለምነው በሰው ቁመት ልክ ለመተኛነት የሚያገለግለው፤ በጥቁርና ቡኒ ከለር የተሰራና
ከላይ እስከ ታች በዚፕ የሚቆለፈውን በመጥቀስ ‹‹እንግዲህ የመኝታ ችግር ቢያጋጥማችሁ እንኳን በ‹ስሊፒንግ ባጉ› መጠቀም
ትችላላችሁ›› እንደ ቀልድ ወስደው ፈገግ ያሉ ቢኖሩም የጉብኝቱን ፈታኝነት ያመላከተ ነበር፡፡
በባህርዳር የምሳ
ቆይታ በኋላ ዋግኽምራና አርማጭሆ የሚል የመስመር ስምና ቁጥር የተጻፈባቸው 70 የሚሆኑ ሃርድ ቶፕ መኪኖች፤ ከ3 እስከ5 ጎብኝ
በመጫን ባህርዳርን ለቀው ወጡ፡፡
ፎገራ፤ ወረታ፤ ታጋዮችን
በማፍራትና በማር ጠጅ የምትታወቋ እብነትን በማለፍ የኢህዴን/ብአዴን የተጠነሰሰበት ጨውጫዊትን፤ ቆላ ሀሙሲትና በለሳ ለዓይን በሚማርኩ በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው እየተደመሙ ጎብኝዎቹ በጠበቃቸው አቀባበል
ከህዝቡ ጋር አፍታ ቆይታ አደረጉ፡፡ በጨውጫዊት አካባቢ የሚገኙ እንደነ ዋልዋ ተራራና ሌሎችም ህዝቡና ታጋዮች ደርግን ለመፋለም
ለመደበቂያነትና የስብሰባ ቦታ በማድረግ ሲገለገሉባቸው እንደነበር አንጋፋ ታጋዮችና የአከባቢው ህብረተሰብ ለጎብኝዎቹ
ገልጸዋል፡፡ የጨውጫዊት አርሶ አደሮች ደርግን በእጅጉ ይፈትን እንደነበረም ተናግረዋል፡፡ በለሳም በትግሉ ታሪክ የገነነ ስም የነበረውና በደርግ አስከፊውን
መስዋእትነት የከፈለ አካባቢ እንደነበረ የአካባቢው ነዋሪዎችና ታጋይ አርሶአደሮች ሲያስረዱ በመገረም ስሜት እጁን በአፉ ላይ
ያልጫና ጎብኝ አልነበረም፡፡
የበለሳ ህዝብ
ለጎብኝው ደማቅና ቤተሰባዊ አቀባበል ካደረጉ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነበር፡፡ እንደ ታጋዮቹ ሁሉ በተሰጣቸው ትጥቅ ተጠቅልሎ ኮከቦችን እየቆጠሩ ማደርን
በበለሳ የጀመሩት ጎብኝዎች በትንሹም ቢሆን የትግልን ምንነት ደጋግመው እንዲያስቡትና ይበልጥ እንዲረዱት ያስቻለ ክስተትም
ነበር፡፡ በ‹‹የአንድ ሰው ተሞክሮም ቢሆን፤ ትውልድን ይቀይራል፤ አይተህ ስትነግረው ደግሞ ይታመናል፤ ጠንካራ ነገሮችና ችግሮች
ታልፈው ትልቅ ደረጃ ሲደረስ ትምህርት ነው፤ ባለሙያዎቹ የተሻለ
መረዳት ኖሯቸው ይሰራሉ›› በማለት የጉዞውን አላማ ከጅምሩ ጎብኝው መረዳቱን ከገለጹት መካከል አርቲስት ህይወት አራጌ ናት፡፡
በበለሳ በነበረው አጋጣሚ በሀገራችን ስመጥርና አንጋፋ አርቲስቶችና የሚዲያ ባለሙያዎቹ ህዝብ ጋር በጥቂቱም ቢሆን
ተጨዋውተዋል፡፡ ስለበሰላ ገናናነት በጹሑፍ እንደሚያውቀውና ‹‹እንደው ሳስበው ስለበለሳ ብዙ የማውቅ ይመስለኛል›› የሚለውና
ቦታውን ለማየት ዋግኽምራ የጎዞ መስመር እንደመረጠ የሚናገረው አንጋፋው ጋዜጠኛ ደረጀ ሀይሌ በለሳ በብአዴን/ኢህአዴግ ትግል
ውስጥ የነበረውን ድርሻና ስለከፈለው መስዋዕትነት፤ ስለጎዞው ባቀረበው ጽሑፍ በውብ ቃላት ገልጾ ነበር፡፡
መስከረም 21 ቀን
ከበለሳ ጠዋት 11፡30 ሰዓት ቀጣይ ጉዞ የጀመረው ቡድኑ በመጀመሪያው በጨውጫዊትና በበለሳ የሰሙት የትግል ታሪክ የድርጅቱንና
የህዝቡን ተጋድሎ ይበልጡን ለመስማት እንዲዘጋጁ ያደረገ ነበር፡፡ ከባህርዳር 229 ኪ.ሜ ጉዞ በኋላ ሌላ የጨለማ ዘመን ገፈት
ቀማሽ ከነበረችዋ አርባ ጸጓር (ጸባሪያ) ሲደረስ እንደነ ታደሰ ካሳ በትግል ስሙ(ጥንቅሹ)፤ ተሾመ እሸቴ በትግል ስሙ (ሃባር)
እንዲሁም ታጋይ አማረች ጣሰው በትግል ስሟ (አሰፋሽ) ለጎብኝው ከሚነግሩት በተጨማሪ ታጋይ አርሶ አደሮች ስለ ትግሉ ጽናትና
መራራነት ሲናገሩ ጎብኝውን ይበልጥ ያስደመመ ነበር፡፡ የአርባ ጸጓር ህዝብ ጽናት አሁንም አለ፡፡ ነዋሪዎች በራሳቸው ገንዘብ አዋጥተው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል የሚያስተናግድ ት/ቤት ገንብተዋል፡፡
ልጆቻቸውን ወደ ገነቡት ት/ቤት መላክ ብቻም ሳይሆን እድሜያቸውን በትግል ሣያለፉ አርሶ አደሮችም ከልጆቻቸው ጋር እንደሚማሩ ተነግሮናል፡፡
አርባ ጸጓር ላይ የጎብኝት
ቡድኑ ቀድሞ በተደለደለው መሰረት በሁለት መስመር ተከፈለ፡፡ የኢህዴን/ብአዴን የትግል ቦታዎችን በከፊልም ቢሆን ለማዳረስ
በተያዘው እቅድ መሰረት በአርማጭሆና በዋግኽምራ መስመር ጉዞ ቀጠለ፡፡ ከቀኑ 8፡00 ገዳማ ቡድኑ በሰሃላ የምሳ ቆይታ በማድረግ
በትጥቅ ትግሉ ለታጋዮች አስፈላጊውን ትጥቆችና ቁሳቁሶች በማጓጓዝ ድርሻ የነበራቸው ሁለት አህዮችም ለማየት ችሏል፡፡ ከሰሃላ
ቀጥሎ በዝቋላ ለተደረገለት አቀባበል ምስጋና በማቅረብ ሰቆጣ
ገብቶ ያደረው ቡድኑ መስከረም 22 ቀን 2008ዓ.ም በአበርገሌ አድርጎ ወደ ትግራይ ክልል ዘለቀ፡፡
የዋግኽምራው መስመር
ቡድን የኢህአፓ መፈራረስን ተከትሎ ጥቂት ቆራጥ ታጋዮች በትግራይ ክልል ቆላ ተምቤን ወረዳ፤ ሽልም አምኒ ቀበሌ በያኔው
የህወሓት ነጻ መሬት ተጠልለው ተክራርዋ በተባለው ቦታ
ኢህዴን/ብአዴንን የመሰረቱበት ቦታም አይተዋል፡፡ በቦታው ትንሽዬ ቤት እንደነበረ የሚያሣይ የድንጋይ ካብ ይታያል፡፡ ከህዳር
7-11 ቀን 1973 ዓ.ም መስራች ጉባኤ በማካሂድ ድርጅቱ የተመሰረተበት ቦታ በደረሰ የስንዴ ሰብል የተከበበ ነው፡፡ ያኔ
ድርጅቱን ከመሰረቱት 37 ታጋዮች መካከል ሁለቱ ሴቶች አማረች ጣሰውና ገነት ታደሰ ሲሆኑ፤ አማረች ጣሰው(አሰፋሽ) በቦታው ላይ
ካቡ ስር ያለውን ግራር ተደግፋ ከ35 ዓመት በፊት ስለነበረው
ሁኔታ በትዝታ ትተርካለች ፤ የአካባቢው ህዝብ ለድርጅቱ ያደርግ የነበረው ድጋፍ ለጎብኝው አስረድታለች፡፡ ድርጅቱ አሁንም
ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ያለው ቁርኝት ጠንካራ መሆኑንና መቀጠሉን የሚያሣይ ‹‹ቤት ትምህርቲ ኢሕዴን›› የሚባል ት/ቤት
ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
በት/ቤቱ ውስጥ
የኢህዴን/ብአዴን ታጋዮች የፎቶ ኤግዝቢሽንም ለጎብኝዎች ቀርቦ ነበር፡፡ ከ37ቱ የኢህዴን/ብአዴን መስራቾች አለበል በግዱ፤
ሀይሉ ስማዳው፤ አስማረ ኮበሌው፤ አስጨናቂ፤ ሻረው፤ ክበበው፤ ኢዮብ፤ ዘርጋው፤አስራደ፤ ኦስማን አሽኔ፤ ዘለቀ፤ ከልካይ ጉበና፤
አብዲና ሙሉአለም አበበ በህይወት የሉም፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎችና
የጥበብ ሰዎች ቡድን በትግሉ ወቅት ለተሰው ሰማዕታት በጧፍ ማብራትና በህሊና ጸለት አስቧቸዋል፡፡ በቆላ ተምቤን ቡድኑ የነበረው ቆይታ በህዝቡ አቀባበል የደመቀና ማራኪ
ነበር፡፡
ቡድኑ በአቢይ ዓዲ አድሮ በነጋታው ወደ አማራ ክልል ተመልሶ ሞቃታማውን የአየር ሁኔታና
እልህ አስጨራሽ የመልከዓ ምድር አቀማመጦችን በመጋፈጥ የኢህዴን/ብአዴን የዘመቻ ማዕከል የነበረውን ግፋላን ተመልክቷል፡፡ በቦታው ለመድረስ ቁጥቋጦና እሾሃማ፤
አሸዋማና ቁልቁለት የበዛበትን 1ሰዓት ገዳማ የሚፈጅ የእግር ጉዞ ማድረግ ግድ ይል ስለነበር እጅጉን ፈታኝ ነበር፡፡ በግፋላ የድርጅቱ
መድሃኒት ቤት እንዲሁም የታጋዮች ቢሮ የነበሩትን በእድሜ ብዛት ክዳናቸው
የወላለቀውን ቤቶች ይታ፡፡ ግፋላ በተራሮች ተከበበችና ተራሮቹ ታጋዮችን ለማሰልጠን ሲውሉ እንደነበር ታጋይ አርሶ አደሮች
ይናገራሉ፡፡ በግፋላ የሚገኙ የድርቱ ቅርሶችም በእድሜ ብዛትና በጊዜ ዑደት እየፈራረሱ መሆናቸው ደግሞ የጎብኚዎቹን ልብ እጅጉን
የነካ ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የተከዜ ወንዝ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙና የክፉ ቀን ባለውለታ የነበሩ ወሻዎችም በደለል ተሞልተዋል
በመባሉ ጎብኝዎቹ ወንዙንና ሸለቆውን ብቻ አይተው ለመመለስ ተገደው ነበር፡፡
በቀጣይ ድርጅቱ
በሚሲግ ሚካኤል ጦርነትን በይፋ በማወጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ደርግን የተፋለመትና ድል ያደረገበት እንዲሁም የመጀመሪያ ድርጅታዊ
ጉባኤውን ያካሂደበት ጀርባ ዮሓንስን አይቷል፡፡ ከጅርባ ዮሃንስ መልስ በአምደ ወርቅ ድጋሚ በቡድኑ አጠራር ‹‹በባለሚየን ኮከብ
ሆቴል›› (በሰማይ ላይ የተበተኑ ኮከቦችን ለማለግለፅ) በተንጣለለ ሜዳ ላይ ለሊቱን በማሳለፍ የትግል ቦታዎችን ለማዳረስ ቡድኑ
ድጋሚ ለሁለት ተከፍሎ ጉዞ ቀጠለ፡፡ በነገራችን ላይ አምደ ወርቅ በደርግ የሄሊኮፕተር ጥቃት በተደጋጋሚ ያስተናገደች ከተማ
ናት፡፡ አንደኛው ቡድን እዚያው አምደ ወርቅ አካባቢ የሚገኘውን ዋሻ፤ ሌላኛው ቡድን ደግሞ በአውሲግ አካባቢ የሚገኘውን እነለጋ
ዋሻ ጎበኘ፡፡
ወደ እነለጋ ዋሻ የተደረገው
ጉዞ እጅጉን አስፈሪና በፈታኝነቱ ቀዳሚ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሶስት ሰዓታትን የፈጀ ጉዞ ነበር፡፡ ጉዞው ጥቂቶች ከመጀመሪያው
ያልሞከሩ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ አቋርጠው ለመመለስ ተገደው ነበር፡፡ ቦታው ድረስ ደርሰው መመለስ ያቃተቸውና በሌሎች እርዳታ
የተመለሱም ነበሩ፡፡ እነለጋ ዋሻ የድርጅቱ 2ኛ ጉባኤ የተስተናገደበትና የውጭ ድርጅቶም የተጋበዙበት እንደነበረም ነው
የተገለጸው፡፡ የዋሻው መቀመጫዎች በእርከን መልክ የተሰሩና የሜጋ አንፊ ትያትር ቅርጽ ያላቸው ሲሆን ‹‹እንዲህም አለ አንዴ››
ያሠኘ ነበር፡፡ እነለጋ ኢህአዴግ ግንባር መፍጠሩንም ያወጀበት ዋሻ ነው፡፡
ከእነለጋ መልስ ቡድኑ
የትግል ቦታዎችን ጎብኝቶ ባያዳርስም የተያዘው ቀን በማለቁ እግረመንገዱን የላሊበላ ውቅር አብያተክርስትያናትንን አይቶ ነበር፡፡
ሌላው የትግሉ ፈርጥ የነበረውን የጉና ተራራ በሩቁ እያየ መስከረም 26 ቀን 2008 ዓ.ም የጉዞ መነሻ ወደነበረች ባህርዳር የገባ ሲሆን፤ በጎብኝቱ ሂደት ጎብኝዎቹ
በተንቃሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ የትግሉን ሂደት ከነውጣ ውረዱ ትላንት የተደረገ ያህል እያንዳንዷን ክስተት የሚተርኩ በርካታ
ታጋይ አርሶ አደሮችን ሲያናግሩ ደግሞ ብዙ ያልተነበቡ ባለብዙ ገጽ መጽኃፍቶች መኖራቸውን ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ታጋይ አርሶ አደሮቹ
አብዛኛዎቹ በ1960ዎቹ ዓለምን ስለ አጥለቀለቀው ማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡ እንዲያውም በቅጽል ስማቸው
ሌኒን የሚባሉም አሉ፡፡ በመሆኑም ከአርሶደር ታጋዮች ገለጻ በመነሳት የድርጅቱና የህዝቡ የትግል ታሪክ ትኩረት አልተሰጠውም
ለማለት ያስደፍራል፡፡
የድርጅቱና የህዝቡ
የትግል ታሪክ በአግባቡ መሰነድ ሳያንሰው የትግል ቦታዎችና ቅርሶች ተጎሳቁለው በማየታቸው የጎብኝዎች ስሜት እጅጉን ተነክቶ
ነበር፡፡ አንዳንዶቹ በቦታው የሉም፡፡ የተገኙትም ቢሆንም በታጋይ አርሶ አደሩና በአካባቢው ህብረተሰብ ጥበቃ ለዛሬ የበቁ ናቸው፡፡ ስለታሪኩም ቢሆን ‹‹ድርጅቱ ታሪክ መስራትን እንጅ ታሪክ ማውራትን
የማይፈልግ በመሆኑ ሊሆን ይችላል›› የሚሉ አስተያየቶች በርክተው ነበር፡፡ ለተለያዩ ዌብሳይቶች፤ ጋዜጦችና መጽኄቶች ፎቶ
በማንሳት የሚታወቀው ፎቶ ግራፈር ሲሳይ ጉዛይ ይህንኑ ይጋራል፡፡ በአርማጭሆ መስመር የተጓዘው ሲሳይ በአንገረብ አካባቢ ባየው
የትግል ስፍራ እንደተመመ ገልጾ ‹‹ለድል የበቁት ታጋዮች፤ ለኛ አሳዩን እንጅ አይናገሩም፤ እኛ ያየነውና እነሱ ያለፉበት
ተመጣጣኝ አይደለም›› ይላል፡፡ ሲሳይ በጉብኝቱ ወቅት ከ1ሺ
በላይ ፎቶዎችን ማንሳቱንና ይህንን እድል ላላገኙት በፎቶ ኤግዝብሽን መልክ እንደሚያቀርብ ተናግሯል፡፡ ከኢትዮጵያ ደራሲያን
ማህበር የመጣው አባይ አዳሙም ይህንኑ ሀሳብ ይጋራል ‹‹ብአዴን
ወርቃማ ታሪክ ነው ያለው፤ ግን አልተጻፈም፤ ከካህናቱ፤ ከወንዱ፤ ከሴቱ፤ ከምሽጉ ተሰባስቦ ካልተጻፈ ለቀጣዩ ትውልድ የሚቀመጥ
ካልሆነ ተረት ነው የሚሆነው፤ ታሪክ መሆኑ ቀርቶ›› ይላል፡፡
ጎብኝዎቹ የትውልዱንም
ጽናትና ቁርጠኝነት ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ የፖሊስ ፕሮግራም
ም/ዋና አዘጋጅ ሳጅን ሉልሻ ንጉሴ ከእልህ አስጨራሹ ጉዞ መልስ ስለታጋዮቹ ሲናገር ‹‹በአንድ በኩል ከተፈጥሮ ጋር በዚህ በኩል
ደግሞ ከአምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጋር፤ ቁርጠኝነታቸው የሚገርም ነው፤ ተፈጥሮ ይፈትነሃል፤ ርቀቱ ይፈትነሃል›› በማለት
የታጋዮችን ጥንካሬ ገልጾአል፡፡ በጉብኝቱም ‹‹ለስራችንም የሚሆነውን በቂ ግብዓት አግኝተናል›› ይላል፡፡
ባጠቃላይ በጎብኝቱ
ሶስት ማህበረሰቦች(አማራ፤ ዋግኽምራ፤ ትግራይ) ባህሎችንም ለማየት ተችሏል፡፡ ከ1974ዓ.ም ጀምሮ ነጻ በወጣው በዋግኽምራ
ያሉት አብዛኞቹ ቦታዎችና ሰፈሮች በደርግ የሂኮፕተር ድብደባ በተደጋጋሚ ተፈጽሞቧቸዋል፡፡ አብዛኞቹ የትግል ስፍራዎች የነበሩት
ከዋናው መንገድ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ያላቸው ቢሆኑም በአሁኑ ጊዜ ለአካባቢው ማህበረሰብ የትምህርትና የጤና ኤክስቴንሽን
አገልግሎት ማዳረስ የተቻለበት ሁኔታም እናዳለ ተመልክተናል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉት
የሚዲያ ባለሙያዎችና የጥበብ ሰዎች የብአዴን/ኢህአዴግና የክልሉ ህዝብ የትግል ሂደት በአስተማሪነቱ ለትውልድ ሊተላለፍ የሚገባና
የሀገራችን ታሪክ አካል ቢሆንም በአግባቡ እልዳልተዘከረ፤ የትግል ቦታዎችና ቅርሶች አያያዝ ትኩረት የሚሻ መሆኑንና ድርጅቱ
ከታላቅ ህዝብ የወጣ ራሱን የቻለ የትግል ታሪክ ያለው እንደሆነም እንደተገነዘቡ በጋራ የተስማሙበት ነበር፡፡ ሁሉም እንደየስራ መስካቸው
ካዩትና ካሰባሰቡት መረጃዎችን አቀናብረው ለህዝቡ በተለያዩ መንገዶች ስለታሪኩ እንደሚያደርሱ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ መንግስትና
ድርጅቱም ስራዎችን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አብስሯል፡፡
ከሁሉም በላይ የክልሉ
በተለያዩ ቦታዎች ህዝቡ ቀን ከሌተ ሳይል ለቡድኑ ላደረገው ደማቅ አቀባበል እንዲሁም የፖሊሶች ትህትና፤ ከ70 በላይ የሚሆኑትና
ጎብኝዎችን በጥንቃቄ ሲያጓጉዙ የነበሩት ሾፌሮች ያሳዩት ስነምግባር በጎብኝዎቹ ዘንድ የማይረሳ ነበር፡፡
በሀገራችን የተፈጸሙ
ህዝባዊ የትግል ታሪኮችን ለተተኪው ትውልድ በሚገባ ማሳወቅ ታሪካዊ ግዴታ በመሆኑ ባለሙያዎች ከቦታው ድረስ በመዝለቅ የታሪኩ
ባለቤቶችንና ግንባር ቀደም ታዋናዮችን እንዲሁም ታሪኩ የተፈጸመባቸውን ቦታዎች በማየት ለሰፊው ህዝብ እንዲያሳውቁ የማድረጉ
ጉዳይ ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ክብርና ሞገስ ለትግሉ
ሰምዕታት! ድልና ድምቀት ለብአዴን/ኢህአዴግ 35ኛ የምስረታ በዓል!
No comments:
Post a Comment