EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 11 September 2015

የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትኩረት የሚሻ አንገብጋቢ አጀንዳ!




በአሜሳይ ከነዓን
በተለያየ ጊዜ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ሁሉም በየፊናው መክሮበታል አቅጣጫም አስቀምጦበታል፡፡ ከዚህ በኋላ አይደገምም ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል መነሳት አለብን ሲል ፈፃሚው አካልም ድምፁን አሰምቷል ጮክ ብሎም ዘምሯል፡፡ የኋላ ኋላ ወደ ተግባር ሲገባ መልኩን ይቀይርና በአገልግሎት አሰጣጥ የሚታየው የመልካም አስተዳደር መጓደል ረቆና ጠቦ አገልግሎት ተቀባዩን ምሬት ውስጥ ሲከት ይታያል፤ ይኽው ህዝብን ለማገልግል ቆርጬ ተንስቻለሁ ሲል የነበረ ፈፃሚ የህዝብ ምሬት መነሻ ይሆናል፡፡

የመልካም አስተዳደር ያለመረጋገጥ ጉዳይ ወደ አንድ አካል የሚወረወር አይደለም፡፡ ይልቁንም ሁላችንም ኃላፊነታችንን በሚገባ ባለመወጣታችን የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን በአገራችንን ያለውን ልማት በማፋጠን በፍላጎት መስፋት የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ላለፉት ዓመታት ደረጃ በደረጃ እየፈታ መምጣቱ እሙን ነው፡፡ አሁንም ህዝባችን ከፍላጎቱ መስፋት ጋር እያነሳቸው ያሉ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እቅድ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል አሁንም በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡  

ህዝባችን ይህን በቅጡ የሚገነዘበው በመሆኑ ልማቱን ኢህአዴግ ከሚመራው መንግስት ጎን በመቆምና የልማት ኃይል በመሆን በርካታ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል፡፡ ዛሬ በአገራችን የተመዘገበው ሁለንተናዊ እድገትና ለውጥም መሰረቱ ህዝባችን ነው፡፡ ህዝብ ያልተሳተፈበት ልማት ስኬታማ መሆን እንደማይችል የሚገነዘበው ድርጅታችን ኢህአዴግ ከህዝብ ጋር በመሆን በርካታ ግዙፍና በእኛ አቅም አይታሰቡም የተባሉ ስራዎችንም እየሰራ መሆኑ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንዳንድ የስነምግባር ችግር ባለባቸው አመራሮችና ፈፃሚዎች የሚፈፀሙ የመልካም አስተዳደር ጉድለት ሆነው ህዝባችንን ለከፋ ምሬትና ጉስቁልና እየጋበዙ ያሉ ተግባራት ግን በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም፡፡ ህዝባችን በአገራችን በሚካሄዱ ፈጣንና ተከታታይነት ያላቸው ልማቶች የሚፈቱ ጉድለቶች በጊዜ ሂደት እንደሚፈቱ በማሰብ በኃላፊነት መንፈስ እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡ ሆኖም በእኛ አቅም መፈታት የሚችልና በቅንነትና በአገልጋይነት ስሜት እጦት የህዝባችን የእለተ ተእለት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ እየተነሳ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር  ጊዜ የማይሰጠው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል፡፡    

በአገልግሎት አሰጣጥ መዛባት የሚፈጠሩ የህዝብ ቅሬታዎችን ደግሞ አመራሩ በየእለቱ በመገምገምና ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጋልጡ አሰራሮችን በመፈተሽ፣ የተጠያቂነት ስርዓቱንም በጥብቅ ዲስፕሊን በመምራት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት ቆርጦ መነሳት ይገባዋል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት የስርዓታችን አደጋ ነው ብለን በተደጋጋሚ በሰነዶቻችን ላይ አስፍረናል፤ ተደጋጋሚ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችም ተሰጥተዋል፡፡ መንግስታዊ አገልግሎትን  በመስጠት የዜጎችን እርካት መፍጠር ሲገባው አገልግሎትን በአድሎና በገንዘብ በመሸጥ እንዲሁም ህዝብን ሆን ብሎ ለማማረር የሚሰራ አካል የሚኖር ከሆነ በስርዓታችን ላይ የተደቀነ አደጋ በመሆኑ አመራሩ በኃላፊነትና በቁርጠኝነት ሊታገል ይገባል፡፡ ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር ራሱን አለአግባብ ከመጥቀምና ከኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር በማፅዳት በጥብቅ ዲስፕሊን ሊታገለውና የቆመለትን ህዝባዊ ዓላማ ያለመሸራረፍ ሊፈፅመው ይገባል፡፡

ነሐሴ ወር የተካሄደው የኢህአዴግ 10ኛ ድርጅታዊ ጉባኤም የመልካም አስተዳደር ጉዳይን አንገብጋቢና በአፋጣኝ ምላሽ የሚያስፈልገው አጀንዳ መሆኑን በማመን በጥልቀት ተወያይቶበታል፤ አቅጣጫም አስቀምጧል፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የመልካም አስተዳደር መገለጫዎቹ በርካታ ቢሆንም ህዝባችን አፋጣኝ ምላሽ የሚፈልግባቸው በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የስነ ምግባር መጓድሎች ግን በአፋጣኝ እልባት ሊያገኙ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ልማታችንን በማፋጠን ከህዝባችን የማደግ ፍላጎት ጋር ተያይዘው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ኢህአዴግ አሁንም ቀጣይነት ያለው እድገት በማስመዝገብና ልማታችንን በህዝባችን ፍላጎት ልክ በማፋጠን መፍታት እንደሚገባ ያምናል፣ በዛም ልክ ይንቀሳቀሳል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በሌላ የመልካም አስተዳደር ገፅታ የሚነሱ እንቅፋቶችን ግን በአፋጣኝ መፍታት ጊዜ የሚሰጠው ተግባር አለመሆኑን ጉባኤው ገምግሟል፤ ውሳኔም አሳልፏል፡፡

በቀጣይ ዓመታት ኢህአዴግ ከመላው ህዝባችን ጋር በመሆን ኪራይ ሰብሳቢነትን በማስወገድ ያልተገባ ጥቅም በማግበስበስ በአቋራጭ ለመክበር የሚደረገውን ሩጫ በሩን በመዝጋትና በመግታት የህዝባችንን አንገብጋቢ ጥያቄ ለመመለስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተለይ የመላ አገራችን ህዝቦች ርብርብና እገዛን ይፈልጋል፡፡ መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳይ ለአንድ አካል የሚተው ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነውና አዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ የምንነሳበትና ህዝባዊነትን በተሻለ ተላብሰን ለህዝብ ዘብ የምንቆምበት ሊሆን ይገባል፡፡ የድርጅታችንን ውሳኔ በተሟላ መልኩ ተፈፃሚ ለማድረግም አመራራችን፣ አባላችንና መላው የአገራችን ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ቁርጠኝነት መነሳት ይገባናል፡፡ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!!

No comments:

Post a Comment