ኢህአዴግ10መደበኛጉባኤውን ከነሀሴ 22 እስከ 25 ቀን 2007ዓ.ም በመቀሌ ከተማ ማካሄዱ ይታወሳል። ከጉባኤው አስቀድሞ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢተኮርባቸው ያሏቸውን አስተያየቶች ሲሰጡ ነበር። ፓርቲውም እነዚህን አስተያየቶች በመቀመር፤ አሉብኝ ያላቸውን የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲን ጨምሮ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማንሳትና የመፍትሔ አቅጣጫን በማስቀመጥ ጉባኤውን አጠናቅቋል።
እኛም ጉባኤው በቆይታው ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች እንዲሁም ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ በኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብና የውጭ ግንኙነት ሀላፊ ከሆኑት ከአቶ ደስታ ተስፋው ጋር አጠር ያለ ቆይታን አድርገናል።
አዲስ ዘመን፤ ጉባኤው ምን ያህል የተሳካ ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል?
አቶ ደስታ፤ ጉባኤው በአንድ በኩል አምስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በስኬት በተጠናቀቀበትና ህዝቡም በከፍተኛ ደረጃ ለኢህአዴግ ይሁንታውን በገለጸበት ማግስት የተካሄደ መሆኑ፤ እንዲሁም የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተጠናቅቆ ሁለተኛውን እቅድ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ባለንበት ሁኔታ የተዘጋጀ መሆኑ በራሱ ወሳኝ ያደርገዋል።
ይህንን በመያዝም ጉባኤው ያለፉት አመታት አፈጻጸም ምን ይመስላል የሚለውን ከእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ አፈጻጸሙ ጋር እንዲሁም ዘጠነኛው ጉባኤ ካስቀመጣቸው ውሳኔዎች ጋር አስተሳስሮ አፈጻጸሙን ምን ይመስላል የሚለውን አይቷል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉ በራሱ የጉባኤውን ስኬታማነት ያመለክታል።
አዲስ ዘመን፤ የጉባኤው አበይት ጭብጦች ምን ምን ነበሩ?
አቶ ደስታ፤ ጉባኤው በዋናነት የውስጥ ድርጅት ዴሞክራሲን፣ የፖለቲካና የድርጅት ስራዎችን፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን፣ የልማት፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ለመመልከት ችሏል። የድርጅቱ የቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርትም ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።
ከእነዚህና መሰል ወይይቶች በኋላ የተከናወነው አብይ ተግባር የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀ መንበርና የቁጥጥር ኮሚሽኑን የሚመሩ ሊቀ መንበርና ምክትል ሊቀ መንበር መምረጥ ነበር። ሌላው በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይም ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ በመወያየት ለህዝብና ለአገር የሚጠቅም ውሳኔና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ነው የተጠናቀቀው።
አዲስ ዘመን፤ ከጉባኤው በፊት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ሲያነሱ ነበርና ለእነዚህ አጀንዳዎች ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቷል?
አቶ ደስታ፤ ጉባኤው በዋናነት የህዝብ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ነው ውይይቱን ሲያደርግ የነበረው። አንደኛው ልማቱን የማስቀጠል ጉዳይ ነው። አገሪቱ ባለፉት 12 ዓመታት ባለ ሁለት አሀዝ ፈጣን እድገት አስመዝግባለች። ይህም ትልቅ ውጤት ነው። ምንም እንኳን በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ቢቻልም አሁንም በቤተሰብ ደረጃ የማረጋገጡ ሂደት ገና ብዙ ስራ የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም ይህንን ከግብ ለማድረስ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ከወዲሁ መጀመር እንዳለባቸው በጽኑ ተመክሮበታል።
ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጠናከር፣ የህዝብ ምክር ቤቶች የህዝብ ድምጽ የሚሰማባቸው እንዲሆኑ፤ የህዝብ አደረጃጀቶች፣ የብዙሀንና የሙያ ማህበራት ተጠናክረው የሚቀጥሉበት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑ የታየበት ጉባኤም ነው።
አዲስ ዘመን፤ በተለይ የአገሪቷ ቁልፍ ችግር የሆኑት የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግሮችን በተመለከተ የተቀመጠው አቅጣጫ ምን ይመስላል?
አቶ ደስታ፤ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ጉባኤው ከፍተኛ አጽንኦት ሰጥቶ ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። በጉባኤው ላይ ህዝቡ የሚያነሳቸው ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ቀርበው ተመክሮባቸዋል። በተለይም በመልካም አስተዳደር ችግር ላይ የሞት ሽረት ለውጥን ማምጣት አለብን የሚል አቋም በጉባኤው ተይዟል።
እንደ አቅጣጫ የተቀመጠውም በተለይም በአስፈጻሚ አካላት አቅም ማነስ ምክንያት ለሚፈጠሩት የመልካም አስተዳደር ችግር ህዝቡን ድጋፍ በማድረግ በቅደም ተከተል እያዩ ተጠያቂ ማድረግና ችግሮቹን መፍታት የሚል ነው። አድሏዊ አሰራርን፣ ሙስናንና ከአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና ጋር የተያያዙትን ችግሮች ከህዝቡ ጋር በመሆን የግልጽነትና የተጠያቂነትን አሰራር በመዘርጋት የሚፈቱበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት በሚለው ላይም ምክክር ተደርጎባቸዋል።
በሌላ በኩልም ጉባኤው የአገሪቱን የልማት ሁኔታ በአስተማማኝ መልኩ ያስቀጥላል ያለውን የአምራች ኢንደስትሪ አጠናክሮ የማስቀጠል፣ የወጪ ንግድ ላይ የሚታየውን ክፍተት የመሙላት፣ የአገር ውስጥ የቁጠባ አቅምን አጠናክሮ የማስቀጠል እንዲሁም በማህበራዊና በመሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ የሚታየውን የተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። ጉባኤው በአጠቃላይ ሲታይም ከስኬቶቹ በላይ ድክመቶቹንና ጉድለቶቹ ላይ የመከር ነበር ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፤ ጉባኤው የመተካካት ሂደቱን እንዴት ተመለከተው ?
አቶ ደስታ፤ መተካካት በድርጅታችን የተቀመጠ አቅጣጫ ነው። ይህ አቅጣጫም በ8ተኛው ጉባኤ ላይ ነው የተቀመጠው፤ መተካካቱም ከኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ ጋር የተያያዘ ነው፤ ጉዞው በአንድ ትውልድ ብቻ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ የትውልድ ቅብብሎሽ ያስፈልገዋል።
የአመራር መተካካቱ ታሳቢ የሚያደርገው የኢትዮጵያን ህዳሴ ነው፤ ሰው እድሜው ሲደርስ፣ ሲታመም አልያም በአፈጻጸሙ ደካማ ሲሆን አይደለም ሊሰናበት የሚገባው፤ መስራት እየቻለ የእድሜም ሆነ የጤና ችግር ሳይከሰትበት ከፊት ረድፍ ወደ ኋላ እየመጣ አዲሱን ትውልድ እያስቀደመና ክፍተት ሳይፈጠር እየተደጋገፈ መቀጠል አለበት። የኢህአዴግ የመተካካት አቅጣጫም ይኸው ነው።
በመተካካቱ አቅጣጫ በተለይም በትጥቅ ትግሉ ከፍተኛ አመራር ቦታ ላይ ቁልፍ ሚና የነበራቸው አባላት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በሶሰት ምዕራፍ ለመተካት ጥረት ተደርጓል። በእዚህም በስምንተኛው ጉባኤ ማግስት በዘጠነኛው ጉባኤና አሁን በ10ኛው ጉባኤ ላይ ተፈጻሚ ሆኗል።
ይህ የመተካካት ሂደት ደግሞ በከፍተኛ አመራሮች ላይ ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን እስከ ታች ድረስ በመውረድ የሚካሄድ ነው። ተፈጻሚነቱንም በቀጣይ ዝርዝር የአሰራር ሂደት ወጥቶለት መፈጸም አለበት የሚል አቅጣጫ ተቀምጧል።
አዲስ ዘመን፤ በጉባኤው መቋጫ ቀን የኢህአዴግ ሊመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለተቃዋሚ ፓርቲዊች «የአብረን እንሰራለን» ጥሪ አስተላልፈው ነበርና ይህንን ጥሪ ተፈጻሚ ለማድረግ ፓርቲው ምን ያህል ተዘጋጅቷል? የፖለቲካ ፓርቲዎቹም የተለመደ ጥሪ ነው አዲስ ነገር የለውም እያሉ ነውና ምን ያህል አዲስ ነገር ይዟል?
አቶ ደስታ፤ ኢህአዴግ አገሪቱ ውስጥ መገንባት ያለበት ስርዓት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት መሆኑን ያምናል። የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ደግሞ በርካታ አመለካከቶችና አስተያየቶች የሚንጸባረቁበት፣ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የሚገኙበት ስርዓት ነው። በመሆኑም ኢህአዴግ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሬ እሰራለሁ የሚለው አቋሙ ዛሬ የወጣ ሳይሆን ቀደም ብሎ ያለ ነው።
ከእዚህ አንጻር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስርዓቱ በፈቀደላቸው፣ ህገ መንግስቱ ባጎናጸፋቸው መብት የመጡ በመሆናቸው ኢህአዴግ ከ2002ዓ.ም ምርጫ ማግስት ጀምሮ የጋራ ምክር ቤትን በማቋቋም በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱት ጋር አብሮ እየሰራ ነው። አሁን ይህንን ሁኔታ አጠናክሮ ይቀጥላል።
በተለይም በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ለስርዓታችን ይጠቅማሉ፣ ፓርላማም ባይገቡ አመለካከታቸው የሚሰማበት ሁኔታ ይፈጠራል። መንግስት በሚያዘጋጃቸው ፓሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይም የሚመክሩበት ግብዓት የሚሰጡበትና የሚወያዩበት የሚዲያ መድረኮች እየተመቻቹ ነው። በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች የሚደረጉበት ሁኔታም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ጽንፍን በመምረጥ አልያም ህገ ወጥ በሆነ ሁኔታ የመንቀሳቀስ ፍላጎት ያላቸው ፓርቲዎች አቋማቸውን አስተካክለው ወደ ሰላም የሚመጡ ከሆነም በእድሉ መጠቀም ይችላሉ።
«የተለመደ ነው» ላሉትም አዎን የተለመደ ነው። ምክንያቱም የኢህአዴግ አቋም ስለሆነ ይህ ሁኔታ ደግሞ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም ይደገማል። ነገር ግን የተለመደ ነው ለውጥ አይመጣም ብለው ቁጭ ካሉ ማየት ያለባቸው ራሳቸውን ነው።
በሌላ በኩልም በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በሌላ በኩልም በምከር ቤቱ በኩል የኢህአዴግን ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው ጠይቀዋል ይህንን መድረክም ለማመቻቸት በዝግጅት ላይ ነን። ራሳቸው ባነሷቸው የወይይት አጀንዳዎች መሰረትም የሚካሄድ ነው የሚሆነው።
በመሆኑም በቀጣይ ለህዝቡ ይበጃል የሚሏቸውን የራሳቸውን ፓሊሲና ስትራቴጂዎች እያቀረቡ በባላንጣነት ስሜት ሳይሆን በጋራ አገርን የመቀየር ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ይፈለጋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለሁላችንም በመሆኑ ነው። በቀጣይ አምስት ዓመት ተሳትፏቸውን በተለያዩ መንገዶች ያረጋግጣሉ ተብሎ ይታሰባል።
በመሆኑም «የአብረን እንሰራለን» ጥሪው ለይስሙላ የሆነ ሳይሆን ከልብ በመነጨ ፍላጎት የመጣና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው አካሄድ የወለደው ነው። በመሆኑም የማይዋዥቅ የኢህአዴግ አቋም ስለሆነ ይሄ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፤ በመጨረሻም ጉባኤውን ተንተርሰው ለህዝቡ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
አቶ ደስታ፤ በአጠቃላይ ጉባኤው የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ነው። የህዝብ ጥያቄዎች የተንጸባረቁበት፣ ፓርቲውም ህዝቡ በምርጫ የሰጠውን አደራ አጠናክሮ ለመቀጠል ቃል የገባበት ጉባኤ ነው። ህዝቡ ከመሪው ኢህአዴግ ጋር ሆኖ በጉባኤው የተወሰኑ ውሳኔዎችን በመከተልና በልማት፣ በሰላምና በሌሎች ተግባራት ላይም ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል። ይህንን ማድረግ ከቻልን ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር ሆኖ የማይፈታቸው ችግሮች አይኖሩም።
አዲስ ዘመን፤ ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ
አቶ ደስታ፤ እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
No comments:
Post a Comment