EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 5 August 2015

ሰሚ ያጣው የፅንፈኛ ዲያስፖራ ጩኸት

(በዮሃንስ ከበደ)
ለአንድ ሃገር የገፅታ ግንባታ የዲያስፖራ ሚና ከፍተኛ ቦታ ሊይዝ እንደሚችል የማያጠራጥር ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዘርፎች ቅድሚያ በመስጠት በተለይም በኢንቨስትመንት ዙሪያ ራሳቸውን ጠቅመው ህዝባቸውንና ሃገራቸውን እንዲጠቅሙ የተለያዩ ማበረታቻዎች እያደረገ የሚገኘው። ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ጀምሮ በብሄራዊ ደረጃ የሚጠቃለለው የዲያስፖራ ፌስቲቫልም የዲያስፖራው ልማታዊ ሚና ጎልቶ የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዲያስፖራው በሀገሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለው ተሳትፎ ሲታይ የተዥጎረጎረ ገፅታ ያለው ነው። በተጨባጭ እንደሚታየው ብዙ ቁጥር ያላቸው ዲያስፖራዎች በተለያዩ የልማት ስራዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ። እውቀታቸውንና ገንዘባቸውን አስተባብረው በሀገራቸው በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉ አሉ። በቀጣይም ይህን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ በመሆናቸው ከራሳቸው የኪራይ ሰብሰቢነት ፍላጎት ይልቅ የአገራቸው ጥቅም የሚያስቀድሙ በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ አገራቸው ገብተው አገራቸውን እንደሚያለሙ ጥርጥር የለውም።
በአንፃሩ ጥቂት የማይባሉ ርካሽ የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት በየአደባባዩ የሀገራቸውን ስም ሲያጠፉና በአስነዋሪ ሁኔታ እውነቱን በማይገለፅ መልኩ ሲያነሱ የሚታዩ ዲያስፖራዎች አሉ። የዓለማችን ልዕለ ሃያል ሃገር አሜሪካ ፕረዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ተብሎ ከተነገረ ጀምሮ እነዚህ የሃገር ፍቅር ምን እንደሆነ የማያውቁ በአሜሪካ የሚኖሩ የፅንፈኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተላላኪ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያን እንዳይገበኙ ሲጎተጉቱ ሰንብተዋል። ሌላው ቀርቶ በደብዳቤ ተፈራርመው ኦባማ ኢትዮጵያ መሄድ እንደሌለባቸውና ይህን ካደረጉ ለሃገሪቱ እውቅና መስጠት እንደሆነ አበክረው ተናግረዋል። ኢሳትን ጨምሮ በተለያዩ ሚድያዎችም ሃሳባቸው ሲያቀርቡ ተደምጠዋል። ሆኖም ግን ከላይ ታች ቢንከራተቱም ጩኸታቸው ተራ የቁራ ጩኸት ሆኖ ቀርቷል። ፕሬዝዳንቱ ባቀዱት መሰረት ጉብኝታቸውን ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ኦባማ ለምን ኢትዮጵያን ጎበኙ?
ይህ ጥያቄ ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ ከመምጣቸው በፊትና ከመጡ በኋላም የተለያዩ የዓለማችን ሚድያዎች የተለያዩ ትንታኔ ሲሰጡት ነበርና ፅንፈኛ ዲያስፖራዎች ባይጥማቸውም ሊቀበሉት የሚገባ እውነታን የሚያመለክት ነው።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ መጥቷል። ይህ እውን መሆን የቻለው በሀገሪቱ እየታየ ያለው ፈጣን ባለ ሁለት አሃዝ የምጣኔ ሃብት ዕድገት፣ በሃገሪቱ ያለው የተረጋጋ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም በጎረቤት ሃገሮችና በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በሰላም ማስከበር ዙርያ አምባሳደር በመሆን ለተረጋጋች አፍሪካ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ያለች በመሆኗ ነው። የእነዚህ ጥረቶቿ ድምር ሀገራችን በአፍሪካ ብሎም በዓለም ያላት ተቀባይነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ አስችሏል።
ሌላውና ዋናው ጉዳዩ ደሞ በዚህ ወቅት ዓለማችንን እያመሳት የሚገኘው ሽብርተኝነት ነው። አገራችን ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና ብሎም ለማጥፋት ተኪ የሌለው ሚና እየተጫወተች ያለች ሃገር መሆኗ ግልፅ ነው። ስለዚህ ይሄን ሁሉ ስኬት በተግባር ያሳየችና ብሩህ ራዕይ ያላት ሃገር በመሆንዋ ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት መሪዎች ለመጎብኘት ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል። በነዚህም ምክንያቶች ነው የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን አባማ በፍጥነት እያደገችና ለአፍሪካም ለዓለምም ተምሳሌት እየሆነች ያለችውን ኢትዮጵያ ለመጎብኘት የወሰኑት።
የጉብኝቱ ፋይዳ?
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ከሁሉም በላይ የሁለቱን ሃገራት የኢኮኖሚ ትስስር ወደ ተሻለ ደረጃ ያሳድገዋል። መሪዎቹ በተለያዩ ስራዎች አብረው ለመስራትም ተስማምተዋል። በተለይም በሃይል ማመንጨት ዙሪያ፣ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ሁለቱም ሀገሮች በአጋርነት እንደሚሰሩ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል። እንዲሁም ኢትዮጵያ ምን ያክል ወሳኝ እና ቁልፍ ሃገር መሆንዋ በተግባር የተረጋገጥበት ጉብኝት ነበር።

ሌላውና በጣም ቁልፍ ጉዳይ ደግሞ የዓለማችን ታላላቅ ሚዲያዎች ትልቁ ትኩረታቸው ኢትዮጵያ ሆና መክረሟ ነው። ይህም ዓለም ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን እውነታ እንዲያውቅ ይረዳል። ታላላቅ ኩባንያዎችና ኢንቨስተሮችም በኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያቸው እንዲያፈሱ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል የሚል ሃሳብ አለኝ። ስለዚህ ባራክ ሁሴን ኦባም በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የፅንፈኛውን የጥፋት አጀንዳ ያመከነ ብቻ ሳይሆን ለአገራችን ዘላቂ እድገት ምቹ ሁኔታዎችንም የፈጠረ ነው።

(ይህ ፅሁፍ በፌስቡክ ገፃችን EPRDF official በውስጥ መልዕክት የደረሰን ነው። ተሳታፊያችንን እያመሰገንን ሌሎቻችሁም በፅሁፍ ስራዎች እንድትሳተፉ እናበረታታለን።)

No comments:

Post a Comment