(በአሜሳይ ከነዓን)
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሰዎች በራሳቸው መልካም ፍቃድና ተነሳሽነት የልፋታቸውን ዋጋ ሳይጠይቁ ወይም ከድርጊታቸው በስተጀርባ ሌላ አጀንዳ ሳይጠነስሱ በአብዛኛው ጊዜ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት ሰብአዊ ተግባር ነው፡፡ በአለማችን በተለያዩ አገራት የበጎ ፍቃድ ተግባር የሚያከናውኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በርካታ ናቸው። በኢትዮጵያም ዜጎች በመልካም ተግባር በመሳተፍ ማሕበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የሚያስችላቸው አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን ከሆነ ወዲህ ዜጎች በበርካታ ዘርፎች ላይ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በግልና በቡድን የተደራጁ ግለሰቦችም አረጋውያንን፣ በህመም የሚሰቃዩ ወገኖችን፣ ልዩ ከለላ የሚያስፈልጋቸው የተጎዱ ሴቶችንና ህፃናትን ያለምንም የልፋት ዋጋ (በገንዘብ የሚተመን ክፍያ ሳይደረግላቸው እና እነሱም ይከፈለን ብለው ሳይጠይቁ) ሙሉ አልያም ትርፍ ጊዜያቸውን በመጠቀም ሲያግዙና ሲረዱ ይስተዋላል፡፡ ውድ አንባብያን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መገለጫው ብዙ ቢሆንም ዛሬ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተመለከተ ትንሽ ነገር ማለት ወደድኩ፡፡
የክረምት ወቅት ለአብዛኛው የአገራችን ተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ነው፡፡ ገሚሱ ዘመድ በመጠየቅ፣ ገሚሱ ደግሞ በትምህርት ተጨናንቆ የነበረው አዕምሮውን ዘና ለማድረግ በጉጉት የሚጠብቀው ወቅት ነው፡፡ ለአንዳንዶቹ የአገራችን ወጣቶች ደግሞ የክረምት ወቅት ለማህበረሰቡ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ተግባር ለመፈፀም በበጎ ስራ ላይ በመሰማራት ሲታትሩ የሚስተዋልበት ነው፡፡
በርካታ ወጣቶች የክረምት ጊዜያቸውን የበጎ ፍቃድ አገልገሎት በሚሰጡ ተቋማትና አደረጃጀቶች አማካኝነት ጊዜያቸውን ለሌሎች ሲሰጡና ወገኖቻቸውን በሚጠቅም ተግባር ላይ ሲያውሉ በዚያው ልክ ደግሞ በሀገራቸው ዕድገት ላይ ገንቢ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ማየት አሁን አሁን እየተለመደ መጥቷል፡፡ በዘንድሮ የክረምት ጊዜያትም በተለያዩ የአገራችን ክልሎች የሚገኙ ወጣቶች በበጎ ስራ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ የችግኝ ተከላ በማካሄድ፣ የደም ልገሳ ንቅናቄ በማዘጋጀትና ራሳቸውም ደም በመለገስና ሌሎችም ደም በመለገስ የወገናቸውን ህይወት ማትረፍ እንዳለባቸው በመቀስቀስ አኩሪ ተግባር በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡ በመዲናችን አዲስ አበባም በትራፊክ ደንብ ማስከበር አገልግሎት፣ በችግኝ ተከላና፣ በማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት እንዲሁም ህሙማንን በመንከባከብ በበጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በርካታ ናቸው፡፡
አሁን አሁን ደግሞ ሀገራችን የቀየሰችውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተከትሎ ክረምት ሲመጣ አብዛኛው ወጣትና በርካታ የህብረተሰባችን ክፍል ተረባርቦ የሚፈፅመው የችግኝ ተከላ ተግባር የማይረሳ ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ ሁሉም አቅራቢያው ከሚገኝና በመንግስት ከተከለሉ ቦታዎች ላይ በንቅናቄ መልኩ ችግኝ በመትከል የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ ሲያለመልም ይስተዋላል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ዛሬም መነጋገሪያ ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ያደጉ ሀገራት አሁን ለደረሱበት ብልፅግና ያበቃቸው የእድገት ሂደት በከባቢ አየር ላይ ያደረሰው ጥፋት ያመጣው ጣጣ በርካቶቻችንን በተለይ ደግሞ በዕድገት ወደኋላ የቀረንውን ሀገራት ሰለባ አድርጎናል። ይህን በሰው ልጆች ላይ የተደቀነ አስከፊ አደጋ ለመታገል የተለያዩ ሀገራትና ህዝቦች ይበጀናል ያሉትን የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። ሀገራችንም የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመቀየስ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም በአርአያነት የሚጠቀስ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነች። ክረምት በገባ ቁጥር ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ያለ የሌለ አቅሞቻቸውን በማስተባበር በችግኝ ተከላ ላይ እየተረባረቡ ያሉትም ይህንን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት ነው።
ሀገራችን እ.አ.አ በ2011 የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችላት ስትራቴጂ ቀይሳ ለተግባራዊነቱ በንቃት መረባረብ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል። ታላቁ መሪ ጓድ መለስ ዜናዊ አፍሪካውያንን በመወከል በጥልቅ እውቀት ላይ የተመሰረተ ድምፃቸውን በአለም መድረኮች ላይ ከፍ አድርገው ያሰሙና በተለይ የበለፀጉ አገራት በፈፀሙት የካርበን ልቀት ያላጠፉት ታዳጊ አገራት ሊገጡ አይገባም፤ እንደውም ካሳ ነው የሚገባቸው በማለት ተከራክረዋል፡፡
በአገራችንም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመተግበር የራሳችንን የቤት ስራ መስራት ይገባናል በሚል በተደረገው እንቅስቃሴ ባለፉት ዓመታት ከጫፍ እስከ ጫፍ ህዝባችንን በማነቃነቅ ተጨባጭ ስኬቶች ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የተመናመኑ ደኖች ወደቦታቸው ተመልሰዋል፡፡ የደን ሽፋናችንም እየተሻሻለ መምጣት ችሏል፡፡ የሃይል አማራጮቻችን ከብክለት ነፃ ከሆኑ እንደ ውሃ፣ ንፋስ፣ የፀሃይ ብርሃንና እንፋሎት ከመሳሰሉት ምንጮች መሆኑ ሲታይ ደግሞ ሀገራችን በአጀንዳው ላይ ያላት ቁርጠኝነት የሰው ልጆችን በመታደግ በኩል ምን ያህል ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተወጣች እንዳለች ለመረዳት አያዳግትም።
ኢትዮጵያ በአለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህንን ቀጣይነት ባለው መንገድ ለማስቀጠል ደግሞ ተግዳሮቶቿን ከስር ከስር መፍታት ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ወቅቱ የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና ነውና ይህም እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስም ይህ እውነታ እንዳለ መቀጠሉ ስለማይቀር የአየር ንብረት ለውጥና መዘዙ ደግሞ አንዱና ዋነኛው የእድገታችን ማነቆና ስጋት ነው፡፡ የግብርና ልማት ስራችን ባሰብነው ልክ የእድገታችን ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል ካስፈለገ የመሬት መሸርሸርን በመከላከልና የደን ልማታችንን በማፋጠን የአየር ንብረት ለውጡ ግንባር ተጠቂ እንዳንሆን መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ከእድገታችን ጋር በቀጥታ ስለሚያያዝ በቁርጠኝነት መረባረብ አለብን የምንለው፡፡
የክረምት ወቅት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችንን በተሟላ መልኩ ለማስቀጠል አይነተኛ ሚና አለው፡፡ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የታላቁን መሪ ዘመን ተሻጋሪ አስተሳሰብ ለማስቀጠልና በእርሳቸው ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተቀረፀውን ለአረንጓዴ ልማት የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት ግብ ለማሳካት እየታተሩ ይገኛሉ፡፡
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስጠት በሀገራዊ የፀረ ድህነት ትግሉ ላይ የማይፋቅ የራስን አሻራ ማኖር ነውና በዋጋ የማይተመን የመንፈስ እርካታንም ያጎናፅፋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከዚህ በተሻለ መልኩ መጎልበትና ባህል ሊሆን የሚገባ መልካም ተግባር ለማድረግ ደግሞ ወጣቱ አሁን የተጀማመሩ መልካም ተግባራትን ይዞ ለበለጠ ውጤትና ተጠቃሚነት ይኖርበታል።
No comments:
Post a Comment