
ብዙ አቅደው ብዙ አስበው ቀሪ እድሜያቸውን አገርና ህዝብ በሚጠቅሙ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አሻራቸውን አስቀምጠው ለመሄድ ሌት ተቀን የሰሩ፣ ህልማቸውን ወደ ተግባር በመቀየር ዘመን የማይሽረው ታሪክ በመስራት በህዝብ ተወደውና ተከብረውየህዝብ ፍቅር እንደተጎናፀፉ ያለፉ ጥቂት የአለማችን መሪዎች ገና ተአምር ይሰራሉ እየተባሉ እነሱም ገና ነን እንጥፍጣፊ ሰዓታችንን ለህዝባችን አውለን ነው የምናልፈው ሲሉ ድንገት ሞት የሚባል ክፉ ምቀኛ ንጥቅ ያደርጋቸዋል፡፡
ጓድ መለስ ዜናዊ አገራችን ለአለም ያበረከተችው ውድ
ስጦታችንንም እንዲህ ሳናስበው ነበር ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት ሞት ከጉያችን የነጠቀን፡፡ በወቅቱ ሞቱን መቀበል ተቸግረን
የነበርን ህዝቦች ትቶልን ስለሄደው ትውልድ ተሻጋሪ ነገር እያሰብን ለመፅናናት ብንሞክርም ዛሬም ሳይጨርሰው የሄደው አድማስ
ተሻጋሪ ራዕዩ ሰፊ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ለዛም ነው ዝክራችንን ሃሳቡንና ህልሙን ቀጣይ በማድረግ፤ ከግብ በማድረስ ሊሆን
ይገባል የምንለው፡፡ ዛሬ ውዱ መሪያችን ከጎናችን ከተለየን ሶስት አመታት ተቆጥረዋል፤ ስራዎቹ ግን ዛሬም ለህዝባችን ብርሃን
ለአገራችን ብልፅግና መሰረት ሆነው ቀጥለዋል፡፡ በቀጣይም ትውልድ የሚቀባበላቸው የማይነጥፉ አስተሳሰቦቹ በትውልድ ህሊና ውስጥ
እየተዘከሩና እየተተገበሩ ይቀጥላሉ፡፡ ጓድ መለስን እኛ ብቻ ሳንሆን አፍሪካዊያንና መላው አለም ጭምር በስራውና በበሳልነቱ
ሲያስቡት ይኖራሉ፡፡ «ምርጡና አስተዋዩ፤ ብልሁና በሳሉ፤ ንግግር አዋቂው የኢትዮጵያ መሪ» በማለት በድፍረት የሚናገሩለት መሪም
ነው ጓድ መለስ፡፡
አገራችንን በርካታ መሪዎች በየጊዜው ተፈራርቀው መርተዋታል፡፡ አምባገነኑን
የደርግ ስርዓት ጨምሮ እስከ 1983 ዓም የነበሩ የሀገራችን ገዥዎች ገሚሱ ወደ ኋላ ገሚሱ ደግሞ ወደ ፊት አንዳንዱም ባለህበት
ሂድ እያለ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ሲያስተዳድሩ የህዝብን ፍላጎት ማሟላት ብሎ ነገር በመዝገበ ቃላታቸውም በአግባቡ አልሰፈረም
ነበር። ከ1983 በኋላ በኢህአዴግ የአመራር ዘመን ነው የኢዲሲቱ ኢትዮጵያን አዲስ ዴሞክራሲያዊ ጉዞ በማስጀመር በሰለጠነና
አለም የሚጠይቀውን የመምራት ክህሎት በመላበስ በህዝብ ሙሉ አቅም የሚተማመንና ለጥቂቶች ሳይሆን ለብዙሃኑ የአገራችን ጭቁን ህዝቦች
ዘብ መቆም የተጀመረው። ለዚህም ከፍተኛ የሆነ መስዋእትነት እስከ መክፈል ተደረሰ። በዚህ ሂደት የጓድ መለስ አስተዋፅኦ
ከፍተኛና አንፀባራቂ ነው፡፡ በርሃብና በተመፅዋችነት የምንታወቅ፤ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ በኩራት አንገታችን ቀና አድርገን
ስለራሳችን እንዳንናገር አንገታችንን ያስደፋን ጠላታችን ድህነት ነውና ይሄን ብቸኛ ጠላታችንን አሽቀንጥረን ማስወገድ አለብን
በሚል ከድህነት የማምለጫ ስልቶችን በመንደፍ ጭምር ህዝባችን ፊቱን የድህነትን ተራራ ወደ መናድ እንዲያዞር ያደረገ ታላቁ መሪያችን
ነው፡፡ ዛሬ አገራችን በምግብ እህል ራሷን በመቻል አለም የመሰከረላት የፈጣንና ፍትሐዊ ዕድገት ምሳሌ መሆን ችላለች፡፡
ኢህአዴግም ሀገርን በትክክል ሊቀይሩ የሚችሉ ሀገር በቀል የፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ባለቤት እና ለተግባራዊነታቸውም በከፍተኛ
ቁርጠኝነትና ዲሲፕሊን የሚረባረብ ጠንካራ ህዝባዊ ድርጅት
መሆኑንም በተግባር ማስመስከር ችሏል፡፡
ህዝብና ድርጅቱ ኢህአዴግ የሰጠውን የመምራት ኃላፊነት ደከመኝ
ሰለቸኝ ሳይል ያለእረፍት በብቃት የተወጣው ጓድ መለስ ለህዝብ ጥቅም መስዋዕት የሆነና መቼም የማይፋቅ የህዝብ ፍቅር ባለቤት
መሆኑን ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ አጋጣሚ በሙሉ ልቡ ሲናገር ማዳመጥ ዛሬ ስድስት ዓመቱ ላይ ቆመን ስናስበው ለሁላችንም
ኩራትና ክብር እንዲሰማን ሆኗል፡፡
ወድ አንባብያን ስለጓድ መለስና ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች እንዲሁ በአጭሩ
ዘርዝሮ ለመጨረስ መሞከር ውቅያኖስን በጭልፋ እንዲሉ ይሆናል፡፡ ለሁላችንም የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ለመላው
የአገራችን ህዝቦች በተለይ ደግሞ ለወጣቱ የእምነትና የአቋም ፅናትን ሆኖ በተግባር ያሳየን የምርጥ እና ምጡቅ ስብዕና ባለቤት
መሆኑ ነው፡፡ ሁላችንም ላመነው ነገር እንዲህ በንፁህ ማንነት መስዋዕት እስከመሆን የደረሰ ስብዕናን መላበስ ምንኛ መታደል
እንደሆነ ከታላቁ መሪያችን መማር እንችላለን፡፡ ጓድ መለስ ኢህአዴግ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የህዝብ ነው፣ መለስም ለህዝብ የታገለ
ህዝብን በማገልገለ መስዋዕት የሆነ፤ የማያወላውል፣ በጥቅም የማይደለል የአላማ ፅናት መገለጫው የሆነ ህዝባዊ ታጋይ ነው፡፡ ዛሬ
ይህንን ማንነት ሁሉም ሲላበስ ራዕዩን ማስቀጥል የሚችል ጫንቃ ይኖረዋል፡፡ የመለስ ስብዕና የእኛ እና የመላው ጭቁን ህዝቦች ጉልበት
እና ፅናት ነው፡፡ በኢህአዴግ ታሪክ በርካቶች ስለ አገርና ህዝብ መስዋዕት ሆነዋል፡፡ ይህ ክቡር መስዋዕትነት ዛሬም የህዝብ
አገልጋይነት ስሜትን በመያዝ መከፈል አለበት፡፡
ነሃሴ 14 ቀን 2009 ይህች ቀን በሁላችንም ዘንድ የማትረሳ
ቀን ሆና ትቀጥላለች፡፡ ሁላችንም መሪሩ ሃዘናችንን ሳንፈልገው እንድንቀበል ሆነናል፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ሙግት አይገጠምምና ሰርቶ
ያለፈ ሰው በስራው ህያው ነውና መሪያችን ሁላችንም ጓዳ ሁላችንም አዕምሮ ውስጥ የማይፋቅ አሻራ ትቶ አልፏልና ስራውን እያሰብን
ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ዛሬም ቃላችንን ማደስ ይገባናል፡፡ ሳይጨርሳቸው ያለፋቸውን፤ አገራችንንና ህዝባችንን ከድህነት ለማላቀቅ
የጀመረውን ሩጫ ጓድ መለስ በራሱ አንደበት እንዳለው ትግል እንደ ማራቶን አንዴ ሩጠው የሚያጠናቅቁት ሳይሆን የዱላ ቅብብል
ነውና እኛም ራዕዩን ተቀብለን ከዳር ለማድረስ ሌተ ተቀን በየተሰማራንበት የስራ መስክ ስኬታማ በመሆን ቃላችንን ማደስ
ይገባናል፡፡ የመለስ ስብዕና ጉልበታችን ነውና እንላበሰው፡፡ ሰላም፡፡
ዘላለማዊ
ክብር ለትግሉ ሰማዕታት
No comments:
Post a Comment