ሠይፈ ደርቤ /ኢዜአ/
“በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የህዝባችንን ፍላጎት ያረካሉ ብለን የቀየስናቸው አቅጣጫዎችና እቅዶች
ያሉን ቢሆንም ያገኘነውን እጅግ ሰፊ የህዝብ አደራ ታሳቢ በማድረግ እነዚህን እቅዶች ለመተግባር ከመረባረብ ጎን ለጎን የሰጣችሁንን
ከፍተኛ ኃላፊነት በይበልጥ ለመወጣት ከነገው ዕለት ጀምሮ እቅዶቻችንን በዝርዝር ፈትሸን መከለስ እንደምንጀምር ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።
በዚህ አጋጣሚ ያገኘነው ከግምታችን በእጅጉ የላቀ ውጤት፣ ተጨማሪ ከባድ ሸክም ያሸክመን እንደሆነ እንጂ እንደማያኩራራን እንደገና
ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ።…”
በ2002 ዓ.ም የተካሄደውን አራተኛ አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ
በህዝብ ድምፅ መንግስት የመመስረት ስልጣን ያገኘው ኢህአዴግ በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አማካኝነት መንግስት ላይ አደራ የሚጥል፣
የህዝቡን ፍላጎትና ተጠቃሚነት ደግሞ የሚያረጋግጥ ስራ እንደሚሰራ የፓርቲውን አቋም ለመላው የአገራችን ህዝቦች ገልጾ ነበር፡፡ ይህን የአደራ ቃል ወደ ተግባር ለመቀየር እቅዱን ወደመከለስ
ያመራው ተመራጩ መንግስትም የተለጠጠና ወገብ ያጎብጣል የተባለውን አዲስ አቅጣጫ ይዞ የመጪውን አምስት ዓመት አገራዊ ጉዞ የሚያሳይ
አዲስ ፍኖት አመላካች እቅድ አዘጋጀ፡፡ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት በተሰጠው የአምስት ዓመት ኮንትራት ብዙ ለመስራትና
ለመፈፀም መዘጋጀቱንም አረጋገጠ፡፡
የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ፀድቆ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ
በነበረበት ወቅት አንዳንድ የአገራችን ተቃዋሚዎች ሰነዱ ለፖለቲካዊ ፍጆታ የተዘጋጀና ሊፈፀም የማይችል ነው በሚል በፅኑ ተችተዋል።
እቅዱ የውጭ የልማት አጋሮችንና ህዝቡን ለማማለል የተዘጋጀ በመሆኑ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ሊፈፅመው ቀርቶ ማሰቡም ሊታመን
የማይችል ነው በማለትም አጣጥለዋል።
የእቅዱ የከፍታ መገለጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በታላቁ
መሪ መለስ ዜናዊ ሲጣል በተምታታ ገለፃ ፋይዳውንና የግንባታውን ወቅታዊነት በመተቸት የእቅዱን አገራዊ ተልዕኮና ግብ ከጅምሩ ለማሳነስም
ሞክረዋል። በተለይ የግድቡ የመሰረት ድንጋይ በተጣለ ሰሞን በአንድ የተቃውሞ ጎራ ውስጥ የተሰለፉ ሁለት
ጎምቱ የተቃዋሚ አመራሮች በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተሰይመው የተናገሩት የማይረሳ ነው፡፡ …
“…ቅድሚያ
ሊሰጠው የሚገባ ስንት የልማት ስራ እያለና ለግድቡ የሚወጣው ወጪ በርካታ ሌሎች ግድቦች ሊገነቡበት እየተቻለ የህዳሴውን ግድብ መገንባት
ተገቢ አይደለም” በሚል፡፡
እኒህ ተቃዋሚዎች የአገራችን ህዝቦች ሆ ብለው በጋራ የተነሱበትንና የረጅም
ዘመናት ቁጭታቸውን የተወጡበትን የመቻል አሻራ ኢህአዴግ ከህዝቦች ዘላቂ ጥቅም መከበር አኳያ ትኩረት ስለሰጠው ብቻ በተለመደ ጭፍን
አመለካከት ሊያጣጥሉ መሞከራቸው የኋላ ኋላ ምን ያህል እንዳሳፈራቸው አይተናል፡፡ ይልቁንም መንግስትና ህዝብ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባሻገር የእቅዱን ዝርዝር ጉዳዮች ታሳቢ ያደረጉ
በርካታ ስራዎችን በማከናወን ከናዳ ለማምለጥ እንደሚሮጥ ሰው ባለ ፍጥነትም በሁሉም ዘርፎች ርብርብ በማድረግ በታላላቅ የሜጋ ፕሮጀክቶች
ግንባታ ጭምር ስራቸውን ቀጠሉ። በውጤቱም ወትሮ በተለያዩ ፈልሞች ስንመለከታቸው የነበሩ መንገዶች፣ ዘመናዊ ባቡሮች፣ መኖሪያ ቤቶች፣
የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች፣ ትላልቅ ህንፃዎች፣ ፋብሪካዎችና ግንባታዎች
በእኛም አገር እውን ሆኑ።
የሁላችንም የጋራ ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአይቻልምን አስተሳሰብ
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብሯል፡፡ በርካታ የሃይል ማመንጫ ግድቦችን
መገንባትም ጀምረናል። አንዳንዶቹም ኃይል በማመንጨት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ምንጮቻችን እንዲሆኑ አድርገናል። በእነዚህና መሰል ፕሮጀክቶች
በጥቂት ዓመታት በፈጠርናቸው የስራ እድሎች ከ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎቻችን የስራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል።
ይህ ወደ ሁለንተናዊ ድል እየተሸጋገረ ያለ አገራዊና ህዝባዊ
ልማት፣ ዓለም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የልማት አውራዎች ተርታ፣
ከዓለማችንም ፈጣን አዳጊ አገሮች ጎራ ቀላቅሎ እንዲመለከታት አስችሏል። እግሮች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመሩም አድርጓል፡፡
ከዓለማችን ቱጃሮች እስከ ልዕለ ኃያላን አገራት መሪዎች የኢትዮጵያን
በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ተገንዝበዋል፤ መንግስታት አገራችንን ሁነኛ የሰላምና ደህንነት እንዲሁም የልማት አጋር እስከ ማድረስ የዘለቀ
ግንኙነትም መስርተዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ከድህነት በመውጣት በፈጣን አዳጊና ተስፋ ያላቸው አገሮች ጎራ ለመሰለፍ ተግተን ስለሰራን
ነው።
የከፍታውን መሰረት ያረጋገጠ ፅናት
በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የአምስት ዓመት
ጊዜ ውስጥ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን መሰረት ያፀኑ ናቸው። በተለይ በመሰረተ ልማት፣ በግብርናና
ኢንደስትሪ ዘርፎች ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅና ማንም ሊክደው የማይቻለው አገራዊ ውጤት እንዲመዘገብ አድርገዋል።
የተለጠጡ ሰፋፊ ግቦችን የሰነቀው የመጀመሪያው የዕድገትና
ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በውጤታማ ስራዎች ታጅቦ በስኬት ተጠናቋል። በአገራችን ታሪክ ይፈፀማሉ፣ ይሰራሉ ተብለው ያልታሰቡ እንደ ህዳሴው
ግድብ ያሉ የማይደፈሩ የሚመስሉ ስራዎች፣ ትላልቅ የባቡር መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችና የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ረጅም ርቀት ተጉዘዋል፤የአገራዊ
ልማቱ አዲስ ምዕራፍ አመላካች ሆነውም ተስተውለዋል። የእቅድ ዘመኑ መጠነ ሰፊ የስኳር፣ የማዳበሪያና ሌሎች ፕሮጀክቶች
የተጀመሩበት ነው፤ ፕሮጀክቶቹ አገራችን ውስጥ በተፈጠረ አቅም መገንባት መጀመራቸው በቀጣይ ለሚፈጠረው ዘላቂ አገራዊ ልማትም ተደማሪ
ጉልበት መሆን ያስችላቸዋል።
ለረጅም ዘመናት በተረጂነት ስሙ ሲነሳ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ በእቅዱ ልክ ፈጥኖ በመጓዙ
ትርፍ አምራች በመሆን ጭምር የተሻለ ገቢ ማግኘት ችሏል። በምርቱ ስፋት ራሱን ጠቅሞ አገሩንና ህዝቡን ተጠቃሚ አድርጓል። በፖሊሲና
በሙያተኞች የጠነከረ ድጋፍና ክትትል በማድረጉ እንዲሁም የመሰረተ ልማት አቅርቦትን በማሻሻሉ የአነስተኛ አርሶ አደር የመኸር ሰብል
ምርት በ2002 ከነበረበት 180 ሚልዮን ኩንታል በ2006 ወደ 270 ሚሊዮን ኩንታል አድጓል።
በእቅድ ዘመኑ መንግስት የአገራችንን ህዝቦች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የ11 በመቶ
አማካይ ዓመታዊ እድገትን ለማስጠበቅ፣ የእድገት ልህቀት ግባችንን ወደ 14 ነጥብ 9 በመቶ በመለጠጥ ተንቀሳቅሷል። ከ1996 እስከ
2006 ባሉት 11 ዓመታትም ኢኮኖሚያችን በየዓመቱ በአማካይ በ10 ነጥብ 9 በመቶ እንዲያድግ አስችሏል፡፡
እድገቱ ከሀገራችን ጋር በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ የሚገኙ ከሰሃራ-በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት
ከሚያስመዘግቡት አምስት በመቶ እድገት ጋር ሲነፃፀር እጥፍ ከመሆኑም በላይ በአገራችን ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገበው ውጤት
ከፍተኛ የህዝብ የመለወጥ ተስፋና መነሳሳት ከመፍጠር ባለፈ አገራት
ከኢትዮጵያን ፈጣን ልማትና ስኬት ተሞክሮ እንዲማሩ አነሳስቷል፡፡
የቀጣይ ዘመን ተልዕኮ
የፈጣኑ ዕእድገታችን ቀጣይነት በመጎልበቱ ወደ ህዳሴ ለመድረስ የሚያስችለን አስተማማኝ መሰረት
በመጣል ላይ ይገኛል፡፡ነገር ግን አሁንም የበለጠ በመስራትና ጉድለቶችን አሻሽሎ ወደ ስኬት በመቀየር በኩል ብዙ ስራ ይቀረናል፡፡
በተለይ የአመራሩን ቁርጠኝነት፣የህዝቡን የነቃና የተደራጀ ተሳትፎ፣ የተቋማት ተናብቦና ተቀናጅቶ መስራት ግድ ይላል፡፡
በአምስተኛው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ህዝቡ ለመረጠው መንግስት ተጨማሪ ኃላፊነትና ታላቅ
አደራን ሰጥቷል፤ ተመራጩ መንግስትም ለ2ኛ ጊዜ የቀየሰውን የእድገትና
ትራንስፎርሜሽን እቅድ በላቀ ህዝባዊ ወገንተኝነት ለማሳካት የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን አወያይቷል፤ የተመረጠው መንግስት
በቅርቡም እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ባደረገው የግምባሩ 10ኛ ጉባኤ የህዝቡን አደራ ለማሳካትና የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞ እውን ለማድረግ
ከመቼውም ጊዜ በላቀ አፈፃፀም ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የድርጅቱን 10ኛ ጉባኤ መጠናቀቅ ተከትሎ በጉባኤው
ባደረጉትንግግር ፓርቲያቸው የህዝቡን ፍላጎት ለማሳካትና የአገሪቱን ከፍታ ለማረጋገጥ ድርጅቱ የተሃድሶ ጉባኤ ብሎ በሚጠራው አራተኛው
የኢህአዴግ ጉባኤ አይነት አቅጣጫ ከናዳ ለማምለጥ እንደሚሮጥ ሰው ባለ ፍጥነት እቅዱን ለማሳካት ይተጋል ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ የተሃድሶ ጉባኤ ብሎ የሚጠራው አራተኛው ጉባኤ በ1993 ዓ.ም የተካሄደ ነው፡፡ በወቅቱ
ሻዕቢያ አገራችንን የወረረበት፣ በኢህአዴግም ውስጥ ጥገኛ ዝቅጠት የሰፈነበት ነበር፡፡ ይህንኑ ጨምሮ ከ1993 በፊት በነበሩ ዓመታት
በአገራችን እድገት ቢመዘገብም እድገቱ በቂ አለመሆኑ የተገመገመበትና የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ቅኝት ጉድለት የነበረበት መሆኑ ታይቷል፡፡
በዚህም ምክንያት ድርጅቱ በውስጡ ያለውን የጥገኛ ዝቅጠት አደጋ በወሳኝ መልኩ ለመቅረፍ ትኩረት
በመስጠት የአመራሩንና የአገሪቱን አጠቃላይ ችግሮች ለማስወገድ የማያወላውል አቋም ይዞ ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም ግምባሩ ውስጡን አፅድቷል፤
በመንግስት ደረጃ አዳዲስ ፖሊሲዎች እንዲቀረፁ አድርጓል፤ በአምባገነኑ የኤርትራ መንግስትም ላይ ጠንካራ ምት እንዲያርፍ በማድረግ
የአገራችን ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ አስችሏል፡፡
የኢህአዴግ 10ኛ ጉባኤ ይህንኑ መነሻ በማድረግ መጪውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በተሃድሶ
ጊዜ እንደነበረው ድህነትን ለማሸነፍ የልማቱ ዋነኛ ሳንካ የሆነውን
የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለማስወገድ በእልህ እንደሚሰራ አረጋግጧል፡፡ ቀጣዩ ጉዞ ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ
የሞት ሽረት ትግል የሚደረግበት መሆኑንም አመላክቷል፡፡
ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት በህዝቡ የነቃ ተሳትፎና የጋራ አገራዊ ልማት የሚጓዝ ከሆነ፣ ሁለተኛው
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አገራችን አፍሪካን ወክላ በመደራደርና የዘላቂ ልማት ግቦችን ከፖሊሲና ስትራቴጂዋ ጋር በማጣጣም
የጀመረችውን ፈጣን፣ ቀጣይና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ለማስቀጠል ያስችለናል። የተጀመረውን የትራንስፎርሜሽንና የህዳሴ ጉዞ
በማፋጠን ኢትዮጵያን በ2017 ዓ.ም የመጀመሪያው ረድፍ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የሚያስችል ወሳኝ ስራም በዚሁ
የሁለተኛው የእቅድ ምእራፍ ይሰራል። የዜጐችን እኩል የልማት ተሳታፊነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትም ይረጋግጣል።
በሁለተኛው የእቅድ ዘመን መንግስት የአገሪቱን የግብርና ልማት ለማዘመን፣ በኢንዱስትሪያላዜሽን፣
ትራንስፎርሜሽንንና የኤክስፖርት ልማትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ለዚሁ የሚመጥን እቅድ አዘጋጅቷል። በሚቀጥሉት 10 ዓመታትም
ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ለመገንባት በሰፊውና በተጠናከረ መልኩ ይንቀሳቀሳል፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የእስካሁኑ ዕድገታችን ዋነኛ መሰረት የሆነው ግብርና
ዘመናዊነቱ ይበልጥ ይደረጃል፤ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ያለው ሚና ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ ኢንዱስትሪው በፍጥነትና በስፋት እንዲያድግ የላቀ
አስተዋፅኦ ያበረክታል። የዕቅድ ዘመኑም የፈጣን የኢንዱስትሪያላይዜሽንና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ መሠረት የሚጣልበት ይሆናል፡፡
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ የማረጋገጡ ቀዳሚ አጀንዳ ድህነትን በማሸነፍ ወደ መካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ
መሸጋገር ነው፤ መዋቅራዊ ሽግግሩ ያለ ፈጣንና ዘመናዊ ኢንዱስትሪ ልማት የሚሳካ ባለመሆኑ ለዚሁ ግብዓት የሚሆነው የግብርና ክምችት
በአርሶአደሩ የተጠናከረ የግብርና ልማት ተሳትፎ አስተማማኝ መሰረት እንዲይዝ ይደረጋል። በእቅድ ዘመኑ የታሰበውን ያህል እድገት
ያልታየበትን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የማስፋፋቱን ስራ በቁርጠኝነት በመፈፀም የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ
ቀዳሚ ጉዳይ ይሆናል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በኢንዱስትሪ ልማቱ መስፋፋት ድህነትና ስራ አጥነት ይቀንሳል፤ ከጥቃቅንና
አነስተኛ ዘርፍ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማት የሚሸጋገሩ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች በቁጥርና በአቅም ይበልጥ ይጨምራሉ። በጥቃቅንና
አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ይበልጥ ተወዳዳሪ ሆነው ቀጣይነት ያለው ፈጣን ልማት የሚያስመዘግቡ ስራ ፈጣሪዎች ለኢንዱስትሪው ልማት
አስተማማኝ መሠረት ይጥላሉ። እነሱም በፈንታቸው ወደ ልማታዊ ባለሃብትነት በመሸጋገር የመዋቅራዊ ለውጡን ሽግግር ያፋጥናሉ። በዚህም
ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ሴቶችና ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የከፍታ ዘመን ጥሪ
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዝግጅት አገራችን የሚሌንየም የልማት ግቦች ማሳካትን
እንደ አንድ መነሻ ወስዳ ሰፋፊ ሥራዎች ሰርታለች። ባለፉት አምስት
ዓመታት በተደረገ ሰፊ ርብርብ የሚሊኒየም የልማት ግቦች ተብለው ከተለዩ ስምንት ግቦች አብዛኛዎቹን አሳክታለች። አለም አቀፉ የገንዘብ
ድርጅት በያዝነው የፈረንጆቹ የ2015 አመት በአፍሪካ ከፍተኛ እድገት እንደሚያስመዘግቡ ከሚጠበቁ ጥቂት አገራት ኢትዮጵያን በቀዳሚዎቹ
ተርታ አሰልፏል። የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የዘንድሮ ዓመት እድገት ከ10 በመቶ
እንደሚልቅ ተንብዮአል፤ እድገቱ በዓለማችን ከሚመዘገቡ የኢኮኖሚ አፈፃፀሞች የላቀ እንደሚሆን ገልፆ፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለ
ፈጣን ልማትና እድገት በተለይ ከ2013 ወዲህ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከድህነት መውጣታቸውን አመልክቷል። ኢትዮጵያ ይህንኑ
እድገት በዘላቂነት በማስቀጠልና ድህነትን በማሸነፍ በጥቂት ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እንደምትሰለፍም አመላክቷል።
ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ኢትዮጵያን በመጎብኘት የመጀመሪያ የሆኑት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም በቅርቡ
በአገራችን ለ3 ቀናት በነበራቸው ቆይታ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም ፈጣን እድገት እያሳዩ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ መሆኑን መስክረዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገበው ፈጣን እድገት ሚሊዮኖች ከድህነት እንዲወጡ ማስቻሉንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ከዴሞክራሲ እድገቱ ጋር አያይዘው ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የሀገራችን
ልማትና እድገት እንዳይደናቀፍ አሜሪካ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለተመረጠው የኢትዮጵያ መንግስት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
የፕሬዚዳንቱ ንግግርና የአሜሪካ መንግስት ትኩረት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት
ከዴሞክራሲ ነጥለው በመመልከት በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ መሰረት የለሽ ወቀሳና ትችት ለሚሰነዝሩ ወገኖችም ተገቢ ምላሽ
ሰጥቷል። በኢትዮጵያ በግብርና በተለይም በሰብል ምርት፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በጤናና በትምህርት ዘርፎች እየተመዘገበ ያለው
እድገት የዜጎች መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ለማድረጉ ማረጋገጫም ይሆናል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮንቬንሽን መሰረት፣ የዜጎች የመልማት መብት
የሰብዓዊ መብት አካል ሆኗል። በዚህም ምክንያት አባል አገራቱ ሰዎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞቻቸው በእኩል እንዲጠበቅ
የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት በፈረንጆቹ 1986 በ41ኛ መደበኛ ስብሰባው የሰዎች የመልማት መብት በማንም
ሊጣስ እንደማይችል በመደንገግ፣ ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ተሳትፎ በማድረግ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጥቅሞቻቸውን የማስጠበቅ
መብት እንዳላቸው ደንግጓል። ኢትዮጵያ ይህን ዓለም አቀፍ ድንጋጌ የህልውናዋ መሰረት አድርጋ መተግበር በመቻሏ ውጤታማ እየሆነች
መጥታለች።
በኢትዮጵያም ዓለም እየመሰከረለት ያለውና ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች በማሳካት
ተጠቃሽ አገር እየሆነች ያለው በትምህርት፣ በጤናና በግብርና ልማት እድገትና በመሳሰሉት ነው፡፡ የዜጎች ለአርሶ አደሩ ቅርብ የሆኑና ምርቱን በቀላሉ ወደ ገበያ በማድረስ
ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ መንገዶች ኢኮኖሚው ባመነጨው አገራዊ ሀብት ዜጎች ፍትሃዊ ድርሻ እንዲኖራቸው አስችሏል።
በየአካባቢው የተቋቋሙ ጤና ጣቢያዎችና የቅድመ በሽታ መከላከል ስራዎች፣ የዘመናዊ መንገድ አቅርቦት፣
የሃይልና የቴሌኮሙኒኬሽን አቅርቦቶች የሰዎችን አኗኗር ቀላል በማድረግ ለመልማት ብቻ ሳይሆን በህይወት የመኖር መብትን በማረጋገጥ
ረጅም እድሜ የሌለውን የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ እያጎለበቱ ነው። አገራችን ፈጣን አዳጊነቷን እያስመሰከረችበት ባለው የዕድገትና
ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ክንውንም ይኸው ጎልቶ ለመውጣቱ በርካታ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ምሁራን ጭምር የርዕዩተ-ዓለም ልዩነት ሳይገድባቸው
ሲመሰክሩት የምንሰማው ነው።
አሁን በእነዚህ ድምር ጥረቶች ውጤትና በመጀመሪያው አገራዊ እቅድ የጠነከረ ህዝባዊ ተሳትፎ
ጎልቶ የወጣው አገራዊ ስኬት ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ህዝቡ በ5ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሰጠውን ታላቅ
አደራ በመያዝ ወደ ፊት ለመራመድ፣ መሪ ድርጅቱም በ10ኛው ጉባኤ
የወሰናቸውን አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ውሳኔዎች ለመተግበር በሚያስችለን የከፍታ ዘመን ላይም ተገኝተናል፡፡
እንደ አገር በመጀመሪያው እቅድ
እንዳሰብነው ባልሄድንባቸው መስኮች በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ክንውን በመረባረብ የማይቋረጥ ጉዞና በከፍታ ላይ
የተመሰረተ የእድገት ልህቀት ማስመዝገብም ይጠበቅብናል።
በሁለተኛው ዘመን ጉዞ ለአገራችን ሰፊ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን ለመፍጠር፣
የራሳችንን ምርት በማሳደግ የውጭ ምንዛሪያችንን ለመቆጠብና ገቢያችንን ለማሳደግ፣ የተወዳዳሪነት አቅም እንዲሁም የቀጠና የኢኮኖሚ
ትስስርን ለማጠናከር በሚያስችል አግባብ ልንንቀሳቀስ ይገባል፡፡ የመንገድ፣ የባቡር፣ የደረቅ ወደብ፣ የአየር ትራንስፖርት፣ የኢነርጂ፣ የቴሌኮም፣
የውሃና የመስኖ ሥራ በልዩ ትኩረት የሚስፋፉበት በመሆኑ የአገራችን መፃኢ ዕድል ብሩህነት የሚረጋገጥበት፣ የጋራ ተጠቃሚነታችንም
ይበልጥ የሚጎለብትበት መሆኑ አያጠራጥርም።
ሁለተኛው ዘመን ከተሞቻችን ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጠርባቸው፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት የሚቃለልበት፣
ከገጠሩ ልማት ጋር በአግባቡ የተሳሰሩና ለግብርና ዘርፍ ምርታማነት ዕድገት አስፈላጊውን አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ ኢንደስትሪዎች የሚጎለብቱበት
ዘመን በመሆኑም የህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚረጋገጥበት እንደሚሆን ይጠበቃል።
"ህዝባዊ አደራን በላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን" በሚል መሪ ቃል የተካሄደው 10ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ
ዋነኛው ማጠንጠኛው ህዝባዊነት ነበር፡፡ ጉባኤው የመከረባቸውና ያስተላለፋቸው
ጉዳዮችና መልእክቶች የህዝብ ፍላጎቶችን ማእከል ያደረጉ ናቸው፡፡
አራተኛው አገራዊ ምርጫ ወደ መጀመሪያው የእቅድ ዘመን ይዞን እንደተጓዘው ሁሉ፣ ምርጫ
2007 ወደ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አዲስ የከፍታ ዘመን ይዞን ሊጓዝ የበረራው መጀመር በኢህአዴግ 10ኛው ድርጅታዊ
ጉባኤ ተበስሯል።
በእቅዱ የመጀመሪያ ዘመን ታላቅነታችንን ለማስመለስ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ስናኖር
ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ “ግንበኞቹም እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮቹም
እኛው…” በሚል ለሁልጊዜም ኮርኳሪና አንቂ መልዕክት ብቻ ሳይሆን የመፍትሄውም አካል እኛው መሆናችንን እንድንረዳ ያመላከቱንን በማስታወስ በአዲሱ የከፍታ ዘመን ላለመረጋጋት መንስኤ የሚሆነውን አክራሪነት፣ የልማት
ሰንኮፍ የሆነውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመዋጋት ይበልጥ መስራት ይኖርብናል፡፡ ህዝቡ በ2007ቱ ምርጫ በድምፁ የሰጠው ውሳኔ
ተከብሮ አጀንዳችን ቁርጠኝነት የተሞላበት ልማት፣ እድገትና ህዳሴ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግም የጋራ ስራችን ይሆናል።
No comments:
Post a Comment