(በፈድሉ ጀማል)
ሀገራችን በከፍተኛ እድገትና በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗ በበርካቶች ዘንድ መነገር ከጀመረ ሰንብቷል፡፡ አለም በከፍተኛ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ሀገራችን ግብርናን መሰረት ባደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ አማካኝነት በተከታታይ እያስመዘገበች ያለችው ፈጣን እድገትና በዚሁ እድገት የዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጧ በየመድረኮቹ ተምሳሌት እንድትሆን አስችሏታል፡፡
የሀገራችን ፈጣን እድገትና በዲፕሎማሲውም ረገድ እየመጣ ያለው ለውጥ ቀደም ሲል ሀገራችን ከበለፀጉ ሀገራት ጋር የነበራትን ግንኙነት ከተመፅዋችነት ወደ በጋራ የመልማትና የንግድ ሽርክና እንዲሸጋገር በማድረግ የሀገራችንን ገፅታ በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረው ይገኛል፡፡ በርካታ ያደጉ ሀገራት ከሀገራችን ጋር በመፍጠር ላይ ካሉት የንግድና የገበያ ትስስር እስከ ግዙፍ የአለማችን ኩባንያዎች በሀገራችን መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ የጀመሩበትን ሁኔታ ለዚህ በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ አገራችንን የጎበኙትን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ ባለፉት ተከታታይ ሶስት አመታት የታላላቅ ሀገራት መሪዎች ቀድሞ ባልነበረ ሁኔታ ወደ ሀገራችን መምጣታቸውም የዚሁ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
የየአገራቱ መሪዎች ጉብኝት አላማ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር የጋራ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ነው፡፡ ይህን አይነቱን ግንኙነት ደግሞ አገራቱ እንደሚፈልጉት ሁሉ እኛም እንዲሁ የምንፈልገው ነው፡፡ የበለፀጉት አገራት ግንኙነቱን ለዘላቂ እድገታቸው እንደሚሹት ሁሉ እኛም ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ ያግዘናልና አጥብቀን እንሻዋለን፡፡ የሰሞኑ የፕሬዚዳንት ባራክ ይፋዊ ጉብኝትም በዚሁ ማዕቀፍ የሚታይ ነው፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ እአአ በ1903
የመጀመሪያውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩ ሲሆን አሜሪካ በ1906 ኢምባሲዋን በአዲስ አበባ ከፍታለች፡፡ ሀገራችንም በ1943 በዋሽንግተን ኢምባሲ በመክፈቷ የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሯል፡፡ በወቅቱ በሀገራችን በነበረው ፊውዳላዊ ስርዓት የተነሳ ግንኙነታችን ጠንካራና ወጥነት ያለው መሆን ባይችልም በርካታ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮችን መፍጠር የተቻለበት ነበር፡፡ በደርግ ስርዓት ሀገራችን የሶሻሊዝም ስርዓትን መከተል ስትጀምር በሀገራቱ መካከል የነበረው ግንኙነት ርዕዮተ አለማዊ ጠላትነትን በመላበሱ አሜሪካ ጀርባዋን እንድትሰጠን ያደረገ ሆኖ እስከ ስርዓቱ ፍፃሜ ዘልቋል፡፡
አምባገነኑ የደርግ ስርዓት መወገዱን ተከትሎ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በአዲስ ምዕራፍ እአአ በ1992
እንደገና ጀምሮ በኤምባሲዎቻቸው አማካኝነት ቀጣይነት ያለው ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ፈጥረዋል፡፡ ከታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አንስቶ በርካታ የሀገራችን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አሜሪካንን በተለያዩ ወቅቶች በመጎብኘት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ትርጉም እንዲኖረው ያስቻሉ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡ በሀገር ውስጥ የምናካሂደውን የፀረ ድህነት ትግልና በአለም አቀፍ ደረጃ ንቁ ተሳትፎ የምናደርግበትን የፀረ ሽብርተኝነት ትግል ጨምሮ በሌሎች ክልላዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ ጠንካራ ግንኝነቶችን መፍጠር ችለናል፡፡
አሁን በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ እድገት እና እድገቱን ተከትሎ የተፈጠረው የዜጎች የመግዛት አቅም ምርቶችና አገልግሎቶችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱና ለሚያቀርቡ እንዲሁም ከውጭ ለሚያስገቡ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማበብ ትልቅ እድል የሚከፍት ነው፡፡ በተግባርም በርካታ የቻይና፣ የህንድ፣ የቱርክና ሌሎች ሀገራት ኩባንያዎችና ባለሃብቶች በሀገራችን በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት በማድረግ በሀገር ውስጥ ገበያና ኤክስፖርት በማድረግ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛል፡፡
ከአሜሪካ ጋር ያለን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ጠንካራ ቢሆንም በንግድና ኢንቨስትመንት ያለን ትስስር ግን በሚጠበቅበት ልክ ያደገ አይደለም፡፡ በርግጥ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት በሰጠችው ምርትን ከቀረጥ ነፃ ወደ አሜሪካ በማስገባት የመሸጥ እድል አገራችንም ተጠቃሚ መሆኗ ይታወቃል፡፡ አሜሪካም በአለም አቀፍ ደረጃ የእድገታችን አንዱ ማሳያ ተደርጎ ለሚወሰደው አየር መንገዳችን በርካታ የቦይንግ አውሮፕላኖችን በመሸጥ ለበርካታ አሜሪካውያን የስራ እድልን ታገኛለች፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ካላት የካፒታልና የቴክኖሎጂ አቅም እንዲሁም የመግዛት አቅም አንፃር የአሜሪካን ባለሃብቶች በሀገራችን በስፋት ኢንቨስት ቢያደርጉ ሁለቱም ሀገራት ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ይህን ነባራዊ ሁኔታ በመቀየር ሁለቱ አገራት እንደ ዲፕሎማሲው ሁሉ የጠነከረ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር እንዲፈጥሩ ያግዛል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ በተለያዩ የቢዝነስ አይነቶች በተሰማሩና ከልዩ ልዩ ዘርፎች በተውጣጡ ልዑካን ታጅበው በሀገራችን ጉብኝት ያደረጉት ባራክ አባማ በነበራቸው የጥቂት ቀናት ቆይታ ካከናወኗቸው በርካታ ተግባራት አንዱም ይሄኑ የተመለከተ ነው፡፡
ከጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት ሁለቱ ሀገራት ተደጋግፈው በሚሰሩባቸው ሁኔታዎች ላይ መግባባት መድረሳቸውን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል፡፡ በተለይ በሀገራችን ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ አሜሪካ በምታደርገው ድጋፍና አሜሪካዊ ባለሃብቶች በሀገራችን ኢንቨስት በማድረግ ተጠቃሚ ሊሆኑ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው ተወያይተዋል፡፡
ቀድሞም ቢሆን ለሀገራችን እድገት እውቅናን የሰጡት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለችና በአፍሪካ በትልቅነት ከሚጠቀሱት ኢኮኖሚዎች የአንዱ ባለቤት መሆኗን በመግለፅ አሜሪካ በንግድና በኢንቨስትመንት በመተሳሰር ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርግና ለሀገራቸው ዜጎችም ተጨማሪ የስራ እድል የሚፈጥር እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያም ለዚህ አይነት ግንኙነት መዳበር ያላትን ፍላጎትና ቁርጠኝነት አረጋግጣለች፡፡ እናም በመሪዎቹ እና በሁለቱ አገራት የንግድ ማህበረሰቦች መካከል የተደረሰውን ስምምነት እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ የቀጣይ ጊዜ ትኩረት ሊሆን ይገባዋል፡፡
No comments:
Post a Comment