(በየማነ ገብረስላሴ)
የዘር ሃረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዘው ባራክ ሁሴን ኦባማ እኤአ በ2008 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ በተለይ ለአፍሪካውያንና ለሌሎች ጥቁር ህዝቦች ተስፋና ኩራት ሆነዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ኦባማ በሁለት ዙር የስልጣን ዘመናቸው ሰባት የአፍሪካ አገራትን በመጎብኘት በስልጣን ላይ እያሉ ብዙ የአፍሪካ አገራትን የጎበኙ የአሜሪካ መሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቀደሙት የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች የጎበኟቸው የአፍሪካ አገራት ቢደመሩ ኦባማ ብቻቸውን ከጎበኟቸው ያነሱ ናቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ውክልና ባለው የአፍሪካ ህብረት በመገኘት ንግግር ያደረጉ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዝዳንትም ናቸው፡፡ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ተምሳሌት፣ የጥቁር ህዝቦች መመኪያ፤ የአፍሪካውያን የፖለቲካ ማዕከል፤ የሰው ዘር መገኛ በሆነችው አዲስ አበባ ያደረጉት ጉብኝት ደግሞ ባራክ ኦባማ ከአፍሪካ ህዝቦች ጋር ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ያጠበቀ ነው፡፡
የፕሬዝዳንት ኦባማ ጉብኝት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ለተሻገረው የኢትዮ - አሜሪካ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ እየተገለፀ ይገኛል፡፡ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ሲል 112 ዓመታትን ያስቆጠረው የአገራቱ ግንኙነት ኢህአዴግ አገሪቱን ባስተዳደረባቸው ባለፉት ሁለት አስርት አመታት እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ሁለቱም አገራት በተለይ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ መስኮች በትብብር ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ሽብርተኝነትንም በጋራ እየተጋሉ ይገኛሉ፡፡ የሰሞኑ የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት ደግሞ ይህን የሁለትዮሽ ግንኝነቱን ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያና አሜሪካ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ጠንካራ ግንኙነት የመሰረቱ ቢሆኑም በንግድና ኢንቨስትመንት ረገድ ግን ውስንነቶች እንዳሉባቸው ሲገለፅ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ የአጎዋ ውል (አሜሪካ ለተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች የሰጠችው ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ውጭ እንዲያስገቡ የሚፈቅድ ውል) ተጠቃሚ ብትሆንም በራሷ የአቅም ውስንነት ምክንያት ዕድሉን በአግባቡ አልተጠቀመችበትም፡፡ በዓለም ግዙፍ የሆኑት የአሜሪካ ኩባንያዎችም ቢሆኑ በኢትዮጵያና በአጠቃላይ በአፍሪካ የሚጠበቀውን ያህል በኢንቨስትመንቱ መስክ እየተሳተፉ አይደለም፡፡ ከቻይና፣ ህንድና ቱርክ ኩባንዎች ጋር ሲነፃፀር የአሜሪካ ኩባንያዎች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እናም የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በዚህ ረገድ ያለውን ሁኔታ እንደሚቀይረው ይታመናል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋር በሁለትዮሽ፣ አካባቢያዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ከወይይታቸው በኃላ
ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ውይይቱን ‹‹ፍሬያማ›› ብለውታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጉብኝቱን ኢትዮጵያ በልማት፣ በሰላምና በፀጥታ እንዲሁም በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እመርታ እያስመዘገበችበት ባለችበት ወቅት የተደረገ ወቅታዊ ጉብኝት ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ከፕሬዝዳንት ኦባማ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውንና አሜሪካ በኢትዮጵያ ንግድንና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ድጋፍ በምታደርግበት ዙሪያ መምከራቸውን ገልፀዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረውም ነው የተናገሩት፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ በበኩላቸው “ህዝቦቻችን ለ100 ዓመታት ያህል በጋራ ኖረዋል፤ ተገበያይተዋል፤ እንዲሁም አንዳቸው ለአንዳቸው ተረዳድተዋል” በማለት ነበር ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የገለፁት፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአሜሪካ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሲሆኑ መቆየታቸውንና ኢትዮጵያም በርካታ የአሜሪካ የሰላም መልዕክተኞችን መቀበሏንም አንስተዋል፡፡ በዋሺንግተን ዲሲ ከየትኛውም ሌላ የውጭ ከተማ የበለጠ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን መኖራቸውንም የዚሁ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሳያ አድርገው ጠቅሰውታል፡፡
“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዓለም ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ ነው፣ ይህንን ማስቀጠል እንፈልጋለን፣ አብረንም እንሰራለን” ያሉት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ይህ እድገት ለኢትዮጵያውን ብዙ መልካም ዕድሎችን ከመስጠቱ በተጨማሪ የአሜሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲጠናከር በማድረግ የስራ ዕድል እንዲስፋፉ አግዟል በማለት ነው የገለፁት፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያ በድርቅና ረሃብ ትታወቅ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ይህ ሁኔታ መቀየሩን አመልክተዋል፡፡ በተለይ ባለፉት 15 ዓመታት የተመዘገበው ፈጣን እድገት ሚልዮኖች ከድህነት እንዲወጡ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአለም ሰላም መስፈን እየተጫወተች ያለውን ትልቅ ሚና አድንቀው በቀጣይም አሸባሪነትን ለመታገል በሚደረገው ጥረት አብረው እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ ስላለው የዴሞክራሲ ስርዓት ሁኔታ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ አጭር ዕድሜ ያለው መሆኑንና ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ “ሕገ መንግስቱ ከፀደቀ በተነፃፃሪ አጭር ጊዜ ነው፣ በተካሄዱ ምርጫዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ መንግስት ተመርጧል” ሲሉም ነው የገለፁት፡፡
እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ በፈጣን የእድገት ምህዋር ከገባች ቆይታለች፡፡ ለ12 ተከታታይ ዓመታት ያስመዘገበችው ፈጣን ዕድገት ዜጎችን በየደረጃው ተጠቃሚ ከማድረጉ በላይ ከድርቅና ረሃብ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ገፅታችን እንዲቀየር ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ አገራችን ከመበታተን አደጋ ወጥታ አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ለመሆን በቅታለች፡፡ ከራሷ አልፋም ሰላም ላጡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ፈጥና የምትደርስ መሆኗ ከፍተኛ ክብርና አድናቆት እንዲቸራት አስችሏታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ስሟ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ 90 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብም ሰፊ የገበያ አቅም ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከተረጂነት ተላቃ ለጋራ ብልፅግና ብዙዎች አብረው ለመስራት የሚመኟት አገር ለመሆን በቅታለች፡፡
ኢትዮጵያ በኢህአዴግ መሪነት ከፍፁም አምባገነናዊ ስርዓት በመላቀቅ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመሸጋገር ረገድ እያስመዘገበችው ያለው አንጸባራቂ ጉዞም የሚደነቅ ነው፡፡ እስከ አሁን አምስት ስኬታማ አገር አቀፍና አካባቢያዊ ምርጫዎችን በማድረግ የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ተግባራዊ ሆኖባታል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዞው ከተጀመረ ገና አጭር ዕድሜ ያለው ቢሆንም በስኬቶች ታጅቦ በግንባታ ሂደት ላይ ያለ ነው፡፡ እናም
አገራትና መሪዎቻቸው ከዚህች በትክክለኛ የእድገት መስመር ካለች አገር ጋር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ቢወስዱ ተገቢ ነው፡፡ የፕሬዝዳንት ኦባማ ጉብኝትም የዚሁ ነባራዊ እውነታ ማሳያና አሜሪካ በሁሉም መስኮች በአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆነች ከመጣችው ኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
በዓለም ከፍተኛ ተደማጭነትና ተነባቢነት ያላቸው እንደ እነ ቢቢሲ፣ ኤቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ ሲሲቲቪ ያሉ የመገናኛ ብዙኃንም ይህንኑ የጉብኝቱን ተገቢነትና ወቅታዊነት አፅንዖት ሰጥተውታል፡፡ በዘገባዎቻቸውም በኢትዮጵያ እየታየ ስላለው አስደናቂ ለውጥ አንስተዋል፡፡ ጉብኝቱ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያሳድገውም አትተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment