ለተሻለ
ኑሮ ፍለጋ አልያም በተለያዩ ምክንያቶች ከራስ አገር ወጥቶ በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች መኖር ያለና የተለመደ ነው፡፡ ወደ 3 ሚሊዮን
የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ፣ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በሌሎች የአለማችን ክፍሎች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ እነዚህ
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በአገራቸው ልማት ላይ የሚያደርጉት አስተዋፆ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና አየተሻሻለ
ቢሆንም በቂ ነው ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ይልቅ የውጭ ባለሃብቶች በአገራችን ውስጥ እያፈሰሱ
ያሉት መዋዕለ ንዋይ የተሻለ ነው፡፡
የኢትዮጵያ
መንግስት የዲያስፖራውን ተሳትፎ ሊያጠናክር የሚችል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስር የዲያስፖራ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ያቋቋመ ሲሆን
በየክልሉም በቀጥታ ዲያስፖራውን የሚደግፍ ቢሮ የማደራጀት ስራ ተሰርቷል፡፡ በቢሮዎቹ አማካኝነት ዲያስፖራውን የመደገፍና በርካታ
ማበረታቻዎችን የመስጠት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡
የኢንቨስትመንት
ማበረታቻዎችን በመመቻቸቱ ቁጥራቸው አነስተኛም ቢሆን ኢትዮጵያውያን በግብርና፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በማሽነሪ
ኪራይና በአገልግሎት ዘርፍ በመሰማራት የውጭ ምንዛሬም እያስገኙ ይገኛሉ፡፡ ዲያስፖራዎች ለራሳቸውም ለህዝባቸውም በሚሆን የኢንቨስትመንት
መስክ ላይ ተሰማርተው በአገራቸው እድገት ላይ አስተዋፆ ማበርከታቸው ከራሳቸው አልፈው አገርና ወገንን መጥቀም ነውና እርካታው ከገንዘብ
ትርፍም በላይ ነው፡፡
የዲያስፖራ
ኢንቨስትመንትን ከማበረታታት ባሻገር የዲያስፖራ ቀን በመሰየም ዲያስፖራው ወደ አገሩ ገብቶ እየተካሄደ ያለውን ሁሉን አቀፍ ዕድገትና
ልማት በማየት ቀጥታ ተሳታፊ የሚሆንበት ሁኔታ ለመፍጠር በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ
ያለውን የዲያስፖራ ፌስቲቫል ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ወደ አገራችን እየገቡ ያሉ ዲያስፖራዎች የዚህ ጥረት
ውጤት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ‘ጆሮህን ታምናለህ አይንህ? ቢሉት አይኔን እንጂ ጆሮዬማ ክፉንም ደጉንም ሳይነጥል ይሰማል’ እንዲሉ በአገራችን
የሚካሄደውን ተጨባጭ ልማት ከመስማት ባሻገር በአይናቸው ማየት የሚያስችላቸውን እድል በማመቻቸት ረገድም የዲያስፖራ ፌስቲቫል መከበሩ
ፋይዳው የላቀ ነው።
ዲያስፖራዎች
በቀጥታ አገራቸውን ከማልማት ባሻገር በያሉበትም ለአገራቸው አምባሳደሮች ሆነው ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዛሬ በአገራችን ማንም
ሊክደው የማይችል እና በራሱም ገለጫ ከመሆኑ የተነሳ በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ዕውቅና የተቸረው የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ
ይገኛል፡፡ አገራችን የተለጠጠ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አዘጋጅታ ላለፉት 5 ዓመታት ተግባራዊ በማድረጓ በአገራችን በሁለንተናዊ
መልኩ መላ ህዝባችንን አነቃንቀን ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ችለናል፡፡ ከደርግ መንግስት ውድቀት በኋላ ወትሮ በትርምስና በርሃብ
የምትታወቀው አገራችን ስሟ ፍፁም ተለውጧል፡፡ ህዝቦቿ እለት እለት ህይወታቸው እየተለወጠ ነገን በተስፋ ማየት የሚችሉ እና ከአንድ
ቀላል ድል ወደ ቀጣዩ ከፍተኛ ድል እየተሸጋገሩ ህዳሴአቸውን እውን ለማድረግ ሌት ተቀን የሚረባረቡ ህዝቦች መሆን ችለዋል፡፡ በዛሬ
ጥረታቸው ያላሰኩት ነገር እንኳን ቢኖር በቀጣይ ርብርባቸው ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ከተጨባጭ ተግባሮቻቸው እየተማመኑ የተሻለች
ሀገር የመገንባት ግባቸውን እውን ለማድረግ በአንድ ልብ እየገሰገሱ ይገኛሉ።
ህዝባችን፣
ኢህአዴግና በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት በሚያካሂዱት እልህ አስጨራሽ የፀረ-ድህነት ትግል የህዳሴ
ጉዟችን እንደሚሳካ በእርግጠኝነት መተንበይ የሚያስችሉ ድንቅ ስኬቶች ማስመዝገብ ተችሏል። አገራችን ላለፉት 12 ተከታታይ ዓመታት
ባለ ሁለት አሃዝ እድገት በማስመዝገብ አሁንም እድገቷ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ማረጋገጥ ችላለች፡፡
ዕድገቱ
ፈጣንና ቀጣይነት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁሉንም የሀገራችን ህዝቦች በማሳተፍና ከዕድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ በማድረግ በኩልም
በዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ዘንድ ዕውቅና የተቸረውና በምሳሌነት እየቀረበ የሚገኝ ነው። ለዚህም ነው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ
ኦባማ “ስለ
ልማት ለመናገር ከኢትዮጵያ የተሻለ ምሳሌ ማቅረብ አይቻልም” በማለት ምስክርነታቸውን የገለፁት።
የህዝባችንንና
የአገራችንን ለውጥ አንዳንዶች በተዛባ መልኩ በማሰራጨት ዲያስፖራው ሌላ ስዕል እንዲይዝ ጥረት ቢያደርጉም እውነትን ሸፍኖ ማኖር
አይቻልምና ዛሬ ለውጣችንን ማንም ሊያድበሰብሰውና ሊሸፋፍነው በማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ዲያስፖራውም እውነቱን የማየት እድሉን
ማግኘት ችሏል፡፡ ለዚህም ነው የሰማሁትና አሁን በዓይኔ ያየሁት ነገር ፍፁም የተለየ ነው እያለ ዲያስፖራው ሲመሰክር የሚደመጠው፡፡ ለነገሩ ይህንን እውነታ የሚመሰክረው ዲያስፖራው ብቻ ሳይሆን ከየትኛውም የዓለማችን
ጫፍ በሆነ ጉዳይ ወደ ሀገራችን የሚገባ ማንኛውም ሰው ጭምር ነው። ምክንያቱ ደግሞ የሀገራችን ዕድገት በራሱ መናገር የሚችል ተጨባጭ
እውነታ በመሆኑ ነው። ይህንን አንፀባራቂ ድል ዲያስፖራዎች ለቀሪው አለም በማስተዋወቅ ተጨማሪ የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለዘመናት
ተበላሽቶ የነበረውን የአገራችንን ገፅታ ለማስተዋወቅ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ከ70
በመቶ በላይ የሚሆነውን አገራዊ በጀት በድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ላይ በማዋል ድህነትን የማስወገድ ጉዳይ ለነገ የማይባል ተግባር
አድርጎ በቁርጠኝነት እየሰራ ያለው በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገሩ ልማት ላይ በስፋት እንዲሳተፍና
በተሳትፎው ልክም የልማቱ ተቋዳሽ እንዲሆን በማድረግ አገራችንን በተባበረ ክንድ ወደ ፊት ለማራመድ እንድንችል ያለመታከት እየሰራ
ይገኛል፡፡ በክልሎችና በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ያለው የዲያስፖራ ቀን ዓላማም በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ሚና ለማሳደግ
ያለመ ነው፡፡
በአንድ
ወቅት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከዲያስፖራዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ከኢትዮጰያ ውጭ
ሌላ አገር እንደሌላቸው፣ አገራቸውን የማልማት የሞራል ግዴታ እንዳለባቸውና ከኢትዮጵያውያን ውጭ የኢትዮጵያን ችግርም ቀድሞ መሸከም
የሚገባው ሌላ ማንም አካል እንደሌለ ገልፀው ነበር፡፡ በእርግጥም እኛ ኢትዮጵያውያን ሌላ አገር የለንም፣ አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡
ሳይማር ያስተማረን ወገናችንን ማገዝና መርዳት፤ አገራችንን ወደ አደጉ አገራት ተርታ በማሰለፍ በዓለም አቀፍ መድረኮች አንገታችንን
ቀና አድርገን በኩራት የምንናገርላት አገር መፍጠር የምንችለው ሁላችንም እንደየአቅማችንና እንደየችሎታችን በምናደርገው አስተዋፆ
ልክ በመሆኑ አሁንም ወደ ራሳችን ቤት መመልከቱ ለነገም የምንለው ወይም ለሌላ የምንሰጠው ተልዕኮ አይደለም።
No comments:
Post a Comment