(በገነት ደረጄ)
የሰው ልጅ በተለያዩ ምክንያቶች የተወለደበትን ወይም ያደገበትን አካባቢና ሀገር ለቆ ይሰደዳል፡፡ የአንድ ሀገር ዜጎች የተሻለ
የስራ እድል፣ ትምህርትና
ኑሮ ፍለጋ ሀገር ለቅቀው ይሄዳሉ። የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት እንዲሁም
ልዩነቶችን የሚያቻችል የፖለቲካ ስርዓት አለመኖርም ለስደት
ምክንያት ናቸው።
በሀገራችን በቀደሙት ስርዓቶች በነበረው
የፖለቲካ አለመረጋጋትና እሱን
ተከትሎ በተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት የተነሳ ከኢትዮጵያ ወጥተው
ኑሯቸውን በውጭ ሀገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ሀገራችንን ያጋጠሟት ድርቅና ረሃብም እንዲሁ ዜጎቻችንን ለስደት ዳርገዋል።
አሁንም ዜጎች ህይወታቸውን የተሻለ ለማድረግና የእውቀትና የሙያ ባለቤት ለመሆን ወደበለፀጉት አገራት ይጓዛሉ።
የአብዛኛዎቹ መዳረሻ ደግሞ አሜሪካ፣ አውሮፓና የአረብ ሀገራት ናቸው።
አንዳንድ መረጃዎች የሚያመለክቱት ከሀገራቸው ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ሶስት ሚሊዮን እንደሚጠጋ ነው።
በውጪ የሚኖሩ የሀገራችን ዜጎች በተለያዩ መንገዶች የሀገራቸውን የልማት እንቅስቃሴ ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ ይህም
ገንዘብ በመላክ፤ በእውቀት (በጥናትና ምርምር)፤ በገጽታ ግንባታና መሰል ስልቶች የሚገለፅ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለመደገፍ ዳያስፖራው ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዢና
በስጦታ በማበርከት አሻራውን አኑሯል። የዲያስፖራው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ
መጠንም 4.7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በሀገር እድገት ላይ የዳያስፖራው ተሳትፎ እየጨመረ ቢሆንም ሀገራችን በምታደርገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በሚፈለገው ደረጃ አስተዋጾ አድርጓል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሀገሩን እየናፈቀ ሳይሞላለት ቀርቶ ከዛሬ ነገ ወደ ሀገሬ ተመልሼ የድርሻዬን እወጣለሁ
እያለ ዓመታትን ከሚያስቆጥረው ውጪ በሚሰማው የተወናበደ መረጃ ግራ ተጋብቶ እጁን
አጣጥፎ ባለበት
መቆየትን ምርጫው ያደረገ በርካታ ቁጥር ያለው ዳያስፖራ ይገኛል፡፡ ሀገሩን ከማልማት ይልቅ ከጥፋት ሃይሎች ጋር ለማበር የመረጠም
አይታጣም።
መንግስት ዲያስፖራው ያለበትን የመረጃ ክፍተት
በመሙላትና የተዛቡ መረጃዎችን በማስተካከል
በሀገሩ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ለማስቻል እየሰራ ይገኛል። በዚሁ ወር የተካሄደው የኦሮሚያ የዲያስፖራ ፌስቲቫልና ከነሃሴ 6/2007 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው
ሀገር አቀፍ የዲያስፖራ ሳምንት
የዚህ
ተግባራዊ እንቅስቃሴ አንድ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በተጠናቀቀው የኦሮሚያ ዲያስፖራ ፌስቲቫልና በሀገር አቀፉ የዲያስፖራ ሳምንት ላይ በአውስትራሊያ፣ አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ መካከለኛ ምስራቅና በሌሎች በርካታ ሀገራት የሚኖሩ
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው የሚሰሙትን
የተሳሳተ መረጃና
አሉታዊ አስተሳሰብ በማሸነፍ ራሳቸው በቦታው ተገኝተው ግንዛቤ ለማግኘትና ምስክር ለመሆን መጥተዋል፡፡
ዶ/ር ተረፈ ገ/መስቀል ከአሜሪካ ዳላስ የ18 ዓመታት ቆይታ በኋላ በሀገራቸው በኢንቨስትመንት ለመሰማራት እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ በምዕራብ ወለጋ ከአዲስ አበባ 328 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙትን የገጠር ቀበሌዎች የጎበኙት ዶክተር ተረፈ “ያኔ እጅግ ጥቂት የነበሩ መሰረተ ልማቶች አሁን ተስፋፍተዋል፤ በጤናም ረገድ አገልግሎቱን በየገጠሩ ተደራሽ ለማድረግ እየተደረጉ ያሉት እንቅስቃሴዎች አበረታች በመሆናቸው፤ በወሊሶ ላይ በጤና ዘርፍ ለመሰማራት በሂደት ላይ ነኝ፤ ያለውን ለውጥ ለመገንዘብ አዳጋች አይደለም” ይላሉ፡፡ ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያና ከአዲስ አበባ ትዝብቱን ከጀመረው ዳያስፖራ መካከል ሲሰማ የነበረውና ያዩት ነገር በመለያየቱ ስሜታቸውን በለቅሶ የገለጹም ነበሩ፡፡
ከ40 ዓመታት በፊት ደርግን ለመፋለም ወደ በረሃ አቅንተው በሱዳን ወደ አሜሪካ የተሻገሩት አቶ ቢራቱ መገርሳ በምዕራብ ኦሮሚያ ለጉብኝት ከተጓዘው የዳያሥፖራ ቡድን ጋር በአንድ የገጠር ቀበሌ በአርሶ አደር ቤት ተገኝው ያሥደመማቸውን ለውጥ በማየታቸው ፊታቸው በፈገግታ እያበራ የተሰማቸውን አጫወቱኝ፡፡ “ያኔ እኔ ደርግን ለመፋለም የወጣሁት ገበሬውና ልጆቹ አሁን ያየሁትን ኑሮ እንዲኖሩ በማሰብ ነበር፤ አሁን ገበሬው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆኗል፤ በገጠር ሶላርና ባዮጋስ እየተጠቀመ ነው፤ በሕይወት ኖሬ ይህንን በማየቴ ደስተኛም እድለኛም ነኝ” በማለት ነበር ልዩነቱን የገለጹት፡፡
የመንገድ፣ መብራትና ቴሌኮሚኒኬሽን መሰረተ ልማቶች መሟላት ለዜጎች ከሚሰጡት
አገልግሎት በተጨማሪ የኢኮኖሚ
እድገቱን ለማስቀጠል የሚያስችሉ
ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲዘረጉና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። በሀገራችን እነዚህ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት እየተስፋፉ መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ በላስቬጋስ 16 ዓመት የኖሩት አቶ አብርሃም አብዲሳም ይህንን እውነታ ይጋራሉ፡፡ “ሀገራችን በከፍተኛ የለውጥ ማዕበል ላይ ያለች ሀገር ነች፤ በከተሞች መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ ት/ቤቶችም በመስፋፋታቸው ከእንግዲህ የሃሰት ፖለቲከኞች
ሰለባ የሚሆን ወጣት አይኖርም” ይላሉ።
በአለም ውስጥ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት መካከል በመሆናችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሻለ ደረጃ እንደምንሸጋገርም አቶ አብርሃም እርግጠኛ ሆነዋል፡፡ “አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ካለፉትና አሁን በአለም ላይ ካሉት ጋር ሳስተያየው በፖሊሲ ደረጃም የተሻለ ነገር እንዳለው ይሰማኛል” በማለት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩ ለእድገታችን ትክክለኛ አቅጣጫ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ የሀገራችን ገጽታ በአብዛኛው ዳያስፖራ ዘንድ የሚታወቅ መሆኑንና ጥቂቶች ግን እያወቁ ለተሳሳተ ፖለቲካና ለሚዲያ ፍጆታ እንደሚያውሉትም አልሸሸጉም፡፡ “የፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች አሉ፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ነጠላ የፖለቲካ ሩጫ የትም አያደርስም፤ የኢትዮጵያን እድገት አንድ ግለሰብ ሳይሆን ዓለም የመሰከረለት ለውጥ ነው” ሲሉ ምክራቸውንም ለግሰዋል አቶ አብርሃም።
አንዲት ዲያስፖራም በአንድም በሌላ መልኩ ኑሮውን በሌላ ሀገር ቢያደርግም የዳያስፖራው ልብ ለሀገሩ የሸፈተ መሆኑን ‘የተውሶ በሬ ሲመሽ ወደ ቤቱ’ በሚለው ሀገረኛ ተረት አዋዝተው ነግረውኛል። “ጠቅልለን {እዚህ ለመኖር} አሊያም ደግሞ ተጠቅልለን {ህይወታችን ሲያልፍ}
እንመጣለን፤ ካለፍን በኋላም በሰላም የምናርፍባት ቦታ ኢትዮጵያ ናት” በማለት ለሀገራቸው ያላቸውን
አተያይ ስሜት በሚነካ አነጋገር ገልፀውታል ዲያስፖራዎቹ።
በሜኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ በድህረ ምረቃ ፕሮግራም የገጠር ልማት የሚያጠኑት ወ/ሮ ነገደፀሃይ አካለወልድ በሚኖሩበት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መስራትና መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ያላቸው በርካታ ዳያስፖራዎች መኖራቸውንና የመረጃ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው ወደፊት ሁለቱን ፍላጎቶች ማጣጣም እንደሚገባ በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡ “የምንሰማው ነገር ትንሽ ከበድ ይላል፤ መንገድ እንኳን እንደሌለ ነበር የሚወራው፤ አሁን ከአዲስ አበባ 320 ኪሎ ሜትር ርቀን ተጉዘናል፤ በፍጥነትና ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ነው የመጣነው፤ ከሀገር ርቆ ለሚኖረው ዳያስፖራ ያለውን እውነታ እንዲገነዘብ ለማድረግ የተጀመረው ስራ ወደዚያ የሚያደርስ ነው” ይላሉ ወይዘሮ ነገደፀሃይ።
ዳያስፖራዎቹ ባዩት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፤ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፤ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች፤ የአርሶ አደሮች መንደር መሻሻል፤ የፋብሪካዎች እንቅስቃሴ ተደንቀው ብቻ አላበቁም፡፡ የሌሎች ሀገራትን ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ስራዎች ባዩበት ጊዜም “እኛስ የት ነበርን?” ያሉም አልጠፉም፡፡ ማየት ማመን በመሆኑ የልማቱ አካልና የእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡም ይገኙበታል፡፡ በርካታ ቁጥር ያለው ዳያስፖራ ከሚኖርባት የጀርመኗ በርሊን የመጡት አቶ ሱራፌል ኢያሱ ከነዚህ አንዱ
ናቸው፡፡ አቶ ሱራፌል ጊዜ ማጥፋትም አልፈጉም። “የኖርኩበት ሀገር የጊዜን ምንነት አስተምሮኛል፤ በርግጥ ዘግይቻለሁ፤ ከአሁን በኋላ ግን ጊዜየን ማባከን አልፈልግም፤ ብዙ የጀርመን ካምፓኒዎችም ወደዚህ መጥተው መስራት ይፈልጋሉ” በማለት በአስቸኳይ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ጥያቄ አቅርበው ለቡና ልማት የሚሆን መሬት እንደሚሰጣቸው ቃል ከተገባላቸው መካከል ናቸው።
በአንድ ወቅት አንገታችንን እንድንደፋ ያደረጉን ክስተቶች በልማትና በአስተማማኝ ሰላም በመለወጣቸውና ልማቱንም አይተው በማረጋገጣቸው ከሃብትና እውቀታቸው ባሻገር በየሄዱበት በገጽታ ግንባታ ለሀገሪቱ አምባሳደር ለመሆን፤ ለከተሞችና ለዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ሀገራት እህት ድርጅቶችን በማፈላለግ እንደሚሳተፉ ዳያስፖራዎቹ ቃል ገብተዋል።
በርግጥ መንግስት ለዳያስፖራው የተለያዩ እድሎችንና ውይይቶችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል። እውነታው የሚያሳየው
ግን ከተሰራውም በላይ ሊሰራ የሚገባው እንደሚልቅ ነው። በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችንን ከሀገራቸው ጋር የሚያገኙ ድልድዮችን በመፍጠር መሰል ተግባራት ቀጣይነት አንዲኖራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ማድረግ ይገባቸዋል። የተጎናጸፍነው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የተዘረጋው የፌዴራሊዝም ስርዓት የልማቱ ምሰሶዎች በመሆናቸው እነዚህን እሴቶቻችንን መንከባከብን ሳንዘነጋ በተጀመረው የኢትዮጵያ ህዳሴ የድሉ አካል ለመሆን ሁላችንም ልንረባረብ ይገባል።
No comments:
Post a Comment