(በሰይፈ
ደርቤ)
የኢትዮጵያ
ህዝቦች ከጭቆናና አፈና በትግላቸው ነፃ በወጡበት 24ኛው ዓመት የግንቦት 20 ድል በዓል ዋዜማ አገራችን ነፃ፣ ፍትሃዊና
ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለ5ኛ ጊዜ በስኬት አካሂዳለች። ምርጫው ካለፉት አራት አጠቃላይ ምርጫዎች ጋር ሲነፃፀር በተሳትፎ፣ በሰላማዊነቱና
በፍትሃዊነቱ የተሻለ ሆኖ መገኘቱም የአገራችን ዴሞክራሲ ከጊዜ ወደጊዜ እየጎለበተ ለመምጣቱ አመላካች ሆኖ አልፏል።
ዘንድሮ
የተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ተዓማኒ መሆኑንም የምርጫው ባለቤት የሆኑት የአገራችን ህዝቦች እንዲሁም ምርጫውን የታዘቡት
የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ጥምረትና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን አረጋግጠዋል። ምዕራባውያን አገራትና የመገናኛ
ብዙሃኖቻቸውም የምርጫውን ተዓማኒነት ሊያጣጥል የሚችል አንዳች ምክንያት ባለማግኘታቸው ፅንፍ የወጡ ተቃዋሚዎች የሚያሰሙትን
መሰረተ ቢስ ወሬ ከመጥቀስ በስተቀር የኢትዮጵያ ህዝቦች በንቃትና በብዛት የተሳተፉበት ሰላማዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ
ማካሄዳቸውን ለመካድ አልደፈሩም።
መላ
ህዝባችን በአገሩ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ሙሉ እምነት ጥሎ ይህም በራሱ የነቃ ተሳትፎ እንደሚሆን ተረድቶ የመራጭነት
ካርዱን በጊዜው ወስዷል። እድሜው ለመራጭነት የደረሰው ህዝብ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመትመሙ 36ነጥብ8
ሚሊየን ህዝብ የመራጭነት ካርድ አውጥቷል።
በአንፃሩ
ፅንፈኛ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝቡ ካርድ እንዳያወጣ በምርጯው ሂደትም እንዳይሳተፍ ሲከለክሉት ከርመዋል። የተቃዋሚ ፖለቲካ
ፓርቲ አመራሮች በዘንድሮው ምርጫ ኢህአዴግን ለመጣል ቆርጠው እንደተነሱ ሲምሉና ሲገዘቱ እየዋሉ ነገር ግን የመራጭነት ካርድ
እንኳን ሳያወጡ ቀርተዋል። በዚህም ዴሞክራሲን የሚያወሩለት እንጂ የሚኖሩበት እንዳልሆነ ዳግም አሳይተውናል።
በምረጡኝ
ቅስቀሳ ሂደትም ተቃዋሚዎች የራሳቸው ፕሮግራምና ፖሊሲ ሳይኖራቸው ከኢህአዴግ ሁለንተናዊ ስኬቶች ውስጥ ጉድለቶችን ብቻ
በመምዘዝና አጋንኖ በማቅረብ የህዝቡን እምነት ለመሸርሸር፣ ድምፅም ለማስጣል ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። ኢህአዴግን ሊገዳደር
የሚችል የፖሊሲ ሃሳብ የሌላቸው መሆኑን ራሳቸው በተጨባጭ ባረጋገጡበት የምርጫ ክርክር “ኢህአዴግን መቃወም በራሱ አማራጭ ነው”
በሚል በፖለቲካ እውቀት ላይ ባልተመሰረተ ድፍረት መቅረባቸው አጀንዳቸው የብጥብጥ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ያጋለጠም ነበር።
ኢህአዴግ
ግን ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አባላቱና ደጋፊዎቹን እንዲሁም መላውን ህዝብ በሰላምና በዴሞክራሲ ዙሪያ ለማሰለፍ ሌት
ተቀን በመስራቱ የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነትና ፍትሃዊነት ማረጋገጥ ችሏል። ለዴሞክራሲ መጎልበት ሲል በምርጫው የተመደበለትን
የአየር ጊዜ ጭምር ለተቃዋሚዎች በመደጎም በስራውና በውጤቱ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ በፅናት የቆማ መሆኑን ማሳየት ችሏል።
ህዝቡም
የረባ አማራጭ ሳያቀርቡለት ምረጠን የሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ጊዜ አርበኞች እንጂ የህዝብ ወገንተኞች የሌላቸው መሆናቸውን
በመረዳቱ የኢህአዴግን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ አማራጮች አክብሮ ለኢህአዴግ ተደማሪ እውቅና ሰጥቷል። እስካሁን ባለው
የምርጫ ቦርድ ይፋዊ ወጤት መሰረትም ኢህአዴግና አጋሮቹ በተወዳደሩባቸው ምርጫ ክልሎች ሁሉ ማሸነፋቸው ተረጋግጧል።
በነፃ፣
ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ መለኪያ 36 ነጥብ8 ሚሊየን ህዝብ የመራጭነት ካርድ የወሰደበትን፣ 58 የፖለቲካ
ፓርቲዎች በሚወዳደሩበት አካባቢና በመገናኛ ብዙሃን በነፃና ዴሞክራሲያዊ አግባብ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ያደረጉበትን፣ የአገሪቱ
ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች አፈፃፀምና ሂደት እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫ ምን መሆን አለበት በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ለ9
ጊዜያት የቴሌቪዥንና ሬዲዮ መድረኮች ክርክር የተካሄደበትን፣ ህዝቡም በበቂ መጠን ስለ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
የተገነዘበበትን፣ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ያለምንም ችግር ቅስቀሳቸውን ማጠናቀቃቸውን የገለፁበት ሁኔታ እያለ በውጤቱ
ለወንበር ያልበቁ አንዳንድ ተቃዋሚዎች የህዝቡን ድምፅ ክደው የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት ለማጣጣል ሞክረዋል።
በምርጫውም
ለእነሱ የተቆጠረ ትንሽም ቢሆን የህዝብ ድምፅ እንዳለና በመበለጥ እንደተሸነፉ ተረድተው ለመረጣቸውና ላልመረጣቸው ህዝብ ምስጋና
ለማቅረብ አልደፈሩም። ሚዛን ባልደፋውና የህዝብ ተቀባይነት
በሌለው ፅንፈኛ አስተያያቸው ትዝብትም ላይ ወድቀዋል።
ኢህአዴግ
ግን ትላንት ለአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ ለእኩል ተጠቃሚነትና ለሉዓላዊ የስልጣን
ባለቤትነት የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል እንደታገለው ሁሉ ዛሬም ከመላው ህዝብ ጋር ይህ የዴሞክራሲና የህዝቦች የመወሰን
መብት እንዲከበር በፅናት እየሰራ ይገኛል።
ኢህአዴግ
የመንግስትነት ስልጣን ከመያዙ አስቀድሞ ከአምባገነኖች እጅ ነፃ ባወጣቸው አካባቢዎች ሳይቀር ዴሞክራሲያዊነትን በተግባር
የተለማመደና ያለ ህዝብ ተሳትፎና እምነት ምንም ነገር ከመተግበር የተቆጠበ ድርጅት ነበር። ይህንኑ ባህሪውን አጠናክሮ
በመቀጠሉም በተደራራቢ ድሎች ታጅቦ ጉዞውን ቀጥሏል። እነሆ ዛሬም ምርጫ የዜጎች የመወሰን ስልጣን ማረጋገጫ መሆኑን አምኖ የመንቀሳቀስ
ባህሉን ገፍቶበታል።
ኢህአዴግ
በምርጫ 97 በአዲስ አበባ ህዝቡ ተቃዋሚዎችን መርጦ በዝረራ ሲሸነፍ የህዝቡን ትክክለኛነት በማመንና ለዚሁ እንደታገለ በመግለፅ
ህዝቡን እንዳከበረ ሁሉ አሁንም ተቃዋሚዎችን በመዘረር ሙሉ ድምፁን የሰጠውን ህዝብና ድምፁን ያልሰጠውን ህዝብ ፍላጎት ጭምር
ለማሳካት ሌት ተቀን እንደሚሰራ ለህዝቡ ቃል ገብቷል። ህዝቡ በመራጭነት ካርዱ ስልጣን ሲያስረክበው ተደማሪና ብዙ ተጨማሪ
የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን እንዲሰራለት፣ የተጀመረውን ዴሞክራሲም እንዲያጎለብት በማሳሰብ መሆኑን እንደሚረዳም
አስታውቋል።
ከእስካሁን
ታሪኩ ተነስተን ስንገመግመውም ኢህአዴግ አሁንም ከፊቱ እንደ ተራራ የገዘፉ ታላላቅ አገራዊ ስራዎች እንዳሉበት በመረዳት ያለ
እረፍትና ድካም ከህዝቡ ጋር እንደሚሰራ፣ ህግና ስርዓትን አክብረው ከሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ጋር ተባብሮ ለውጤት
እንደሚንቀሳቀስ ለማረጋገጥ አይከብድም።
No comments:
Post a Comment