EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday, 9 June 2015

ድሉ ከቁጥሩም በላይ ነው!

(በከበደ ካሳ)
ግንቦት 16/2007 የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካኝነት ይፋ ሆኗል። ውጤቱ እንደሚያመለክተው ኢሕአዴግ በተወዳደረባቸው ሁሉም የምርጫ ክልሎች አሸንፏል። ይህ ብቻ ሳይሆን አጋር ድርጅቶቹም በተመሳሳይ አሸንፈዋል። ቀሪ የምርጫ ክልሎች ውጤት ተጠናቆ እስካሁን በቦርዱ ባይገለፅም ከዚህ የተለየ ውጤት እንደማይኖር መገመት አይከብድም። የምርጫው አጠቃላይ ውጤት ሰኔ 15/2007 የሚገለፅ ሲሆን ኢሕአዴግ ግን እስካሁን ባገኘው ድምፅ ብቻ መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምፅ እንዳገኘ አረጋግጧል። በመሆኑም ለቀጣይ አምስት አመታት መንግስትን የመምራት ሃላፊነት በእርሱ ትከሻ ላይ ያረፈ ነው።
ኢሕአዴግ ወደ ምርጫ ሲገባ ካስቀመጣቸው ሶስት ግቦች አንዱ በምርጫው መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን ድምፅ ማግኘት ነበር። መንግስት ለመመስረት ደግሞ 50+1 /majority vote/ መያዝ በቂ ነው። እናም አሁን ላይ ሆነን ስናየው ግቡ ተሳክቷል፣ ተሳክቷል ብቻም ሳይሆን በእቅዱ ከተቀመጠውም በላይ የሆነ አንፀባራቂ ድል አስመዝግቧል። ለመሆኑ ይህ ድል ከቁጥር ባለፈ ምን የሚነግረን ነገር አለ? ኢሕአዴግ ከ57 ፓርቲዎች ጋር ተወዳድሮ እንዴት በሁሉም ምርጫ ክልሎች ማሸነፍ ቻለ? ተፎካካሪዎቹ ለምን በዚህ ደረጃ ተሸነፉ? የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት የግል አስተያየቴን ማስፈር እፈልጋለሁ።

ኢሕአዴግ የድህነት ዘበኛ የነበረውን የደርግ ስርዓት ከገረሰሰ በኋላ ቀዳሚ ተግባሩ ያደረገው የውድቀታችንና የኋላቀርነታችን ምንጭ የሆነውን ድህነት መዋጋትና ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ነው። ሂደቱ የፈረሰ ቤትን ዳግም የመገንባት ያክል ነበርና ከዋናው የፀረ ድህነት ትግል ጎን ለጎን ብዙ ጥገናና ለውጥ የሚሻቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ሙሉ ሃይሉ በዋናው ግብ ላይ ነበር ለማለት ይከብዳል። ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች የበረቱበት በአንፃሩ የመፈፀም ብቃት ደካማ የሆነበት ወቅት ነበር። በመጀመሪያዎቹ አመታት በተለይም እስከ ተሃድሶው ወቅት ድረስ ያካሄደው ትግል አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ወሳኘ የሆኑትን መሰረቶች የጣለበት ቢሆንም ድህነትና ኋላቀርነትን በሚገባው ልክ የቀረፈበት አልነበረም። እድገታችንም ብልጭ ድርግም የሚል ነበር።
ኢሕአዴግ ውስጡን አጥርቶ በመስመር ጥራትም ይበልጥ ጎልብቶ ከሄደበት ተሃድሶው በኋላ ግን ሙሉ ትኩረቱንና ሃይሉን ድህነትን ወደ መዋጋት አሸጋገረ። ዋነኛው ጠላታችን ድህነት እንደሆነ በመፈረጅ መላ ሕዝቡ በፀረ ድህነት ትግሉ ከጎኑ ተሰልፎ እንዲረባረብ ማድረግ ችሏል። እነሆ በዚህ ድርጅት መሪነት፣ በሕዝቦች ተዋናይነት፣ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር እየተጓዝን ለ12 ተከታታይ አመታት ፈጣን እድገት ማስመዝገብ ቻልን። ያስመዘገብነው የኢኮኖሚ እድገት የዜጎቻችን ህይወት በመቀየርና የተበላሸውን አለም አቀፍ ገጽታችንን በማስተካከል የጎላ ሚና ተጫውቷል። በዚህ የልማት ጉዞ ውስጥ ተሳታፊና በየደረጃው ተጠቃሚ የሆነው ሕዝብ የተቀየሰው ስትራቴጂ ሀገራችንን ከድህነት የሚያወጣ እንደሆነና ተጠቃሚ እንደሚያደርገው እርግጠኛ ሆነ። እናም ሙሉ ድጋፉን የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ በሆነው ድምፁ ገለፀ። ስለሆነም በምርጫ 2007 ተቃዋሚዎች በድጋሜ በዝረራ የተሸነፉበት አንዱ ምክንያት ከምርጫው አመት በፊት የተመዘገበው ልማታዊ ድል ነው።
ኢሕአዴግ የመንግስትን ስልጣን ከመያዙ በፊት ሀገራችን ለማያበራ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ተዳርጋ ነበር። የ1980ዎቹ የመጀመሪያ አመታት በብሄር ቅራኔ ምክንያት ለመበታተን ጫፍ የደረሰችባቸው እንደነበሩ እንኳን እኛ ውስጧን የምናውቀው በውጭ ያሉትም የመሰከሩት ነው። በዛ አለማችን የሶቪየትን የመበታተንና የሱማሊያን የመፈራረስ ዜና በሚሰማበትና ኢትዮጵያም ከዛሬ ነገ የእነሱ እጣ ፋንታ ይደርሳታል እያለ በስጋት በሚጠብቅበት ወቅት ሀገር የመምራት ሃላፊነት የተረከበው ኢሕአዴግ የወሰዳቸው ቁልፍ እርምጃዎች ኢትዮጵያን ወደ ሰላምና መረጋጋት መልሰዋታል።
የብሔር ቅራኔ ምንጭ የሆኑትን እኩል ያለመታየትና የአንድ ወገን የበላይነት ችግሮች በመቅረፍ፣ ሁሉም ቅራኔ ያላቸው ሃይሎች ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር፣ ኦነግን ጨምሮ የመገንጠል አጀንዳ ያነሱ ቡድኖች ሁሉ በሽግግር መንግስት ምስረታው እንዲሳተፉ በሩን ክፍት በማድረግና ለአመታት የቆየው የኤርትራ ችግር ሰላማዊና ዘላቂ እልባት እንዲያገኝ የበኩሉን በመወጣት ኢሕአዴግ ወቅቱ ግድ የሚላቸውን ምላሾች በመስጠት በቋፍ ለነበረችው ሀገር የሰላም መሰረት ጥሏል።
በመጀመሪያዎቹ አመታት ለተጣለው የሰላም መሰረት ሕዝቡ ዘብ ሆኖ በመቆሙ ይህ ነው የሚባል ግጭት በውስጣችን ሳይነሳ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሲነሱም ዘላቂ መፍትሄ ጭምር እየተበጀላቸው በስጋት ሳይሆን በእፎይታ የምንኖርባት ሀገር ገንብተናል። እኛ ብቻ ሳንሆን የውጪ ዜጎችም ቀን ከለሊት በሰላም የሚንቀሳቀሱባት፣ መሃሉ ብቻ ሳይሆን ዳሩም የሰላም አየር የሚነፍስበት ሁኔታ የተፈጠረው ኢሕአዴግ ለሰላም መከበር ካለው ቁርጠኝነት በመነሳት በወሰዳቸው እርምጃዎች ነው። የሻዕቢያ መንግስት የከፈተብንን ግልፅ ወረራ ለመመከት ከተሰለፍንበት አስገዳጅ ጦርነትና ራሱን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት ብሎ ከሚጠራው አሸባሪ ቡድን የተጋረጠብንን ስጋት ለማስወገድ ካደረግነው ዘመቻ ውጭ ሀገራችን ላለፉት 24 አመታት የውጭ ጥቃትም ሳይሰነዘርባት ሉዓላዊነቷን አስከብራ ቆይታለች።
ያቺ ወልደው ለማሳደግ የሚሰጉባት ሀገራቸው ዛሬ በየቀኑ ስለመለወጣቸው እንጂ በሰላም ውለው ስለመግባታቸው የማይጨነቁባት መሆኗን የተረዱ ሕዝቦች፣ ያቺ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር እየተባለ የተፎከረባት ሀገራቸው ዛሬ ሁሉም ነገር ወደልማት ሲባልላት የታዘቡ ሕዝቦች፣ ያቺ በየእለቱ የጦርነት ነጋሪት የሚጎሰምባት ሀገራቸው ዛሬ ስሟ በአለም አደባባይ በሰላም አስከባሪነት በክብር ሲነሳ ያዩ ሕዝቦች ታዲያ በዘንድሮው ምርጫ ኢሕአዴግን ቀዳሚ ምርጫቸው ለማድረግ አልተቸገሩም። እናም በምርጫ 2007 ተቃዋሚዎች በባዶ የወጡበት ሌላው ምክንያት ከምርጫው በፊት ደህንነታችንን በማስከበር የተመዘገበው ስኬት ነው።
የድርጅቱ መስራች ወጣቶች ወደ በረሃ ሲያቀኑ የነበረው ሁኔታ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የማይቻልበት ብቻ ሳይሆን እንደሚቻልም በቅርብ ርቀት የተስፋ ጭላንጭል የማይታይበት ነበር። ሃሳብን በነፃነት ማራመድ ብቻ ሳይሆን ማሰብም የሚያስወነጅልበት ወቅት ነበር። በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በመደብ፣ ወዘተ… ልዩነቶች ያሏትን ሀገር በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ካልሆነ በስተቀር በሃይል አንድ ለማድረግ የሚደረግ መፍጨርጨር ለብተና እንደሚዳርግ የተረዱ ታጋዮች የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉበት ትግል በግንቦት 1983 በድል ተጠናቋል። ከድሉ በኋላ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ የሃይማኖት፣ የብሔርና የፆታ እኩልነት፣ የህግ የበላይነት፣ የመንግስት ስልጣን ገደብና ተጠያቂነት የተረጋገጠበት ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሰፍኗል።
ኢሕአዴግ ሀገር የመምራት ስልጣን በያዘ በአንድ ወር ውስጥ ስልጣኑን በማጋራት፣ በቀጣይም ሁሉም ወገኖች የተወከሉበት የሽግግር መንግስት በመመስረት የዴሞክራሲ ግንባታ ሀሁን አስጀምሯል። በመፃፍ ብቻ ሳይሆን በአደባባዮች ተሰልፎ ተቃውሞን መግለፅ የሚቻልበት፣ በአንድ አላማ ዙሪያ ተደራጅቶ በመቃወም የመንግስትን ስልጣን መያዝ የሚቻልበት ስርዓት የተጀመረው ኢሕአዴግ ሀገር መምራት ከጀመረ በኋላ ነው።
የመንግስት ስልጣን የሚያዘው በጠመንጃ አፈሙዝ መሆኑ ቀርቶ ከምርጫ ኮሮጆ በሚገኝ የህዝብ ድምፅ እንዲሆን ያደረገው ኢሕአዴግ ነው። የዘንድሮውን ምርጫ ጨምሮ በተካሄዱት አምስት ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫዎች የመንግስትን ስልጣን ለመያዝ የሚችሉበትን ውድድር አድርገዋል። ሕዝቡ ከቀረቡለት ውስጥ የኢሕአዴግ አማራጭ የተሻለ መሆኑን በማመንና በተግባር መሬት ላይ የመጣውን ለውጥ በማየት ይሁንታውን ለኢሕአዴግ ሰጥቶታል። ዘንድሮ በተካሄደው ምርጫም ሕዝቡ በዚህ ደረጃ ሙሉ መተማመኑን በኢሕአዴግ ላይ ሲያሳርፍ ድርጅቱ ከምስረታው እስከ አሁን ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን ቁርጠኝነት በማየት ነው። እናም በአምስተኛው ዙር ምርጫ ተቃዋሚዎች አይወድቁ አወዳደቅ የወደቁበት ሌላው ምክንያት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ፍሬ በማፍራቱ ነው።
ኢሕአዴግ ከ57 ተቃዋሚዎች ጋር ተወዳድሮ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ለማሸነፍ ያስቻለውን ድምፅ ሲያገኝ በራሱ የደከመበት የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ግንባታ ስኬት የአንበሳውን ድርሻ ቢይዝም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ነባራዊ ሁኔታ አስተዋፆም የማይካድ ነው። የኢሕአዴግ የንድፈ ሃሳብ መፅሄት በሆነችው አዲስ ራዕይ (ቅፅ 3 ቁጥር 3) ላይ እንደሰፈረው የኢሕአዴግ መስመር አንፀባርቆ እንዲወጣ ተቃዋሚዎች ተጨማሪ ምክንያት ሆነዋል።
“ተቃዋሚዎች ኢሕአዴግ ያስገኘውን መልካም ውጤት ተቀብለውና አድንቀው ከዚህ የተሻለ ውጤት እንዴት እንደሚያስገኙ ከማስረዳት ይልቅ የትኩረታቸው ዋነኛ ነጥብ አድርገው የወሰዱት ሕዝቡ በአይኑ ያየውንና ተጠቃሚ የሆነበትን ልማት መካድና ማብጠልጠል ነበር። ልማቱን ከመካድና ከማብጠልጥል ባሻገር እርስ በእርሱ የሚምታታ ባዶ ተስፋ ሊመግቡትም ሞክረዋል። ‘ኒዮ ሊበራል መስመር እናራምዳለን ስለሆነም የመንግስትን ጣልቃ ገብነት እንቃወማለን’ ብለው ከመጨረሳቸው በፊት ‘ይህን ችግር መንግስት በድጎማ ይፍታ፣ ያንን ችግር ደግሞ በደሞዝ ጭማሪ ይፍታ’ እያሉ በሆነ ባልሆነው የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ሲሰብኩ ህዝቡ ታዘባቸው። በአንድ በኩል ‘ግብር እንቀንሳለን’ ብለው ይሰብኩና ይህንኑ ተናግረው ሳይጨርሱ ‘የሰራተኛ ደሞዝ እንጨምራለን’ ይላሉ። የመንግስትን ገቢ ቀንሰው ወጪውን በማናር ምን አይነት ኢኮኖሚ እንደሚፈጥሩ ግራ ገብቶት ሕዝቡ ታዘባቸው። ኢሕአዴግን በጭፍን የመጥላትና የመቃወም አላማ ካልሆነ በስተቀር ይህ ነው የሚባል የልማት አላማ እንደሌላቸው፣ የኢህአዴግን ስኬታማ ስትራቴጂ ከመካድና ከማብጥለጠል፣ ህዝቡን በባዶ ተስፋ ለመሸንገል ከመሞከር በስተቀር ዳገት የሚወጣ የልማት ስትራቴጂ እንደሌላቸው ህዝቡ ታዘበ። እናም ልማታዊ መስመራችን የኪራይ ሰብሳቢነትን መስመር በተግባር የሚያሸንፍበት ሁኔታ ተፈጠረ።”
ስለሆነም እንዴት ተቃዋሚዎች በዚህ ደረጃ ሊሸነፉ ቻሉ የሚለውን ጥያቄ በአጭሩ በኢሕአዴግ ጥንካሬና በራሳቸው ድክመት ብሎ መመለስ ይቻላል።
ያም ሆኖ በአምስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ኢሕአዴግ ያስመዘገበው ድል ከጀርባው የሚያሳየው ሌላ እውነታ አለ። በተገኘው ለውጥ ገና ያልረካ፣ ስለሆነም ሌሎች አማራጮችን /የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮች ቢሆኑም እንኳን/ እያየ ያለ የህብረተሰብ ክፍል መኖሩን ውጤቱ ይናገራል። ተቃዋሚዎች በድምሩ ኢሕአዴግ ካገኘው ድምፅ ተቀራራቢ ውጤት ያገኙባቸው አንዳንድ የምርጫ ክልሎች አሉ። በብዙ አጋጣሚዎች ለሽብር ሃይሎች ቀኝ እጅ መሆናቸውን ያመለከቱን ፓርቲዎች፣ አማራጭ ሳይኖራቸው በኢሕአዴግ ድክመቶች ላይ የተንጠለጠሉ ፓርቲዎች፣ የምርጫውን ውጤት አስቀድመው እንደማይቀበሉ የተናገሩ ፓርቲዎች ቀላል የማይባል ድምፅ አግኝተዋል። በአዲስ አበባ ሰማያዊ ፓርቲና መድረክ ያገኙትን ድምፅ በአብነት ማንሳት ይቻላል። ስለሆነም የዚህን ድል ፋይዳ በአግባቡ ማጣጣም የሚቻለው ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን ኢሕአዴግን ያልመረጠውን ሕዝብ ስሜት በመረዳትም ነው።
በምርጫ 97 ማግስት ኢሕአዴግ ሕዝቡ ቅር የተሰኘባቸው ነገሮች ለማወቅ የመረጠውንም ሆነ ያልመረጠውን በሰፊው አነጋግሯል። ቅሬታዎቹን ለቅሞ በመያዝ በአጭር ጊዜ የሚስተካከሉትን ወዲያዉኑ ሲያስተካክል በሂደት የሚፈቱትን መቼና እንዴት እንደሚፈቱ ከሕዝቡ ጋር በመምከር አቅጣጫ አስቀምጧል። ሕዝቡ የተሳሳተ ግንዛቤ የያዘባቸውንም በከንቱ ቃላት ሳይሸነግል አቋሙን አስረድቷል። በዛን ወቅት ያጋጠመውን ፈተና ወደ ምቹ አጋጣሚነት መቀየር የቻለው ድርጅት ፍሬውን በአራተኛውና አምስተኛው ዙር ምርጫዎች ማጣጣሙን ቀጥሏል። አሁንም ይህንኑ ልምድ አጠናክሮ በማስቀጠል የዘንድሮው ድል ለቀጣይ ምርጫዎችም እርሾ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፣ ይገባልም።
በርግጥ ሕዝቡን ማወያየትና ችግሮቹን መፍታት የሚያስፈልገው ለምርጫ ስኬት ብቻ አይደለም። ድህነታችን ስር ሰድዶ የኖረ ስለነበር ከዚህ በላይ እድገት ያስፈልገናል። መልካም አስተዳደር የማስፈን ጥረቱ የሕዝብን ርካታ ገና አላረጋገጠም። ዴሞክራሲያችን ገና በጅምር ግንባታ ላይ ያለ ነው። መላ ሕዝቡ ከእስካሁኑ ለውጥ ተጠቃሚ ቢሆንም በየዘርፉ ያልተቀረፉለት ችግሮች አሉበት። ከሕዝቡ ተምሮ ለላቀ ውጤት ለመነሳት በሂደቱም ራሱን ሕዝቡን በምልዓት ተሳታፊ ተሳታፊ ለማድረግ የመወያየት አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።

No comments:

Post a Comment