EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 10 June 2015

አሻራችንን እናሳርፍ!

(በቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ)
የዜጎች ሕይወት እየተለወጠ ነው ሲባል እንደመስማት የሚያስደስት ነገር የለም። አገራችን በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን የሚክድ አይኖርም። ካለም ካለመገንዘብ ይሆናል። በእርግጥ ለውጡን የምንገነዘብበት መንገድና መጠን ሊለያይ ይችላል፣ መካድ ግን ያስተዛዝባል።
ከተነሳንበት አኳያ ረዥም ርቀት መሄዳችን እሙን ቢሆንም ገና መረባረብና ልማቱን ማቀጣጠል ያለብን መሆኑ ደግሞ የማይካድ ሀቅ ነው።

የዜጎቻችንን ሕይወት ለመቀየር የሚደረጉ ጥረቶች ግለታቸውን ጠብቀውና ተጠናክረው በቀጠሉ ቁጥር የበለጡ ለውጦችን እናያለን። በመሆኑም አገር ወዳድ ኢትዮጰያዊ ሁሉ ከልማቱ ጎን በመቆም ዜጎቻችን ከድህነት ሙሉ በሙሉ እስኪላቀቁና አገራችን ወዳደጉት አገራት ጎራ እስክትቀላቀል ድረስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅብናል።
አገራችን የሰራችው ሥራ እውቅና አግኝቶ ለሽልማት መብቃቷ ለድህነት ቅነሳ ባበረከተችው አስተዋጽኦ መሆኑ አሁንም ያለመታከት ሰርተን በአጭር ጊዜ የበለጸገች አገር የሚል ሽልማት የምናገኝበት ደረጃ ላይ እንድንደርስ ጉልበት ሰጪ ነው።
በወላይታ አንድ ተረት አለ። "ጮራይ ጩችድ ወንግሪያ ኩንቴስ" ይባላል። "ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" የሚለው የአማርኛ አባባል ሊገልጸው ይችላል። መንግሥትም ሆነ ፓርቲ ብቻውን ያስመዘገበውም ሆነ የሚያስመዘግበው ውጤት የለም፣ አይኖርም። ውጤቱ የእያንዳንዳችን ነውና። መንግሥት ሁኔታዎችን ሊያመቻች ይችላል። የልማቱ ባለቤት ግን ሕዝብ ነው።
ፓርቲንም ሆነ መንግሥትን ያለመደገፍ ብሎም መቃወም መብት ነው። ልማቱ የህዝብ ስለሆነ ልማቱን የመደገፍና የበኩላችን አስተዋጽኦ የማበርከት ኃላፊነት ግን አለብን።
እንደ ድህነት አስቀያሚ የለም። አገር ደሃ ስትሆን አትደመጥም፣ አትከበርም፣ ቦታ አይሰጣትም። ቢያንስ ከድህነት ለመውጣት የምትፍጨረጨር ከሆነ ምናልባት ነገ አጋር ልትሆን ትችላለች በሚል ትንሽ ቦታ ሊሰጣት ይችላል። ኢትዮጵያን እንደ ማሳያ መዉሰድ እንችላለን።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝባችን ጠላት ድህነት ነው ማለቱ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ደሃ ከሆንክ በማንም ትደፈራለህ፣ የሰውን መብት ሳትነካ ብቻ ሳይሆን መብትህን ተጋፍቶም መልሶ ሊያጠቃህ ይፈልጋል። ስለዚህ ትልቁ ጠላት ድህነት ነው የሚለው መርህ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሰብዓዊ ትርጉም አለው።
ስለሆነም ውድድሮቹ፣ ክርክሮቹ፣ ጥረቶቹ ወዘተ. ድህነትን ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ ለማዉረድ ሲሆን በእያንዳንዱ ቤት ትርጉም አለው። ምክንያቱም የእያንዳንዱን ጓዳ ይዳሰሳልና።
በመሆኑም አገራችን ድህነትን ለማጥፋት በምታደርገው ዘመቻ ልዩነቶቻችን ወደ ጎን በመተው መተባበር አለብን። ልማቱን ስንደግፍ ቤተሰባችን፣ ልጆቻችን፣ እህቶቻችን፣ አባቶቻችንና እናቶቻችንን ነው የምንደግፈው።
በአንዳንድ ቤቶች ዉጭ አገር የሚኖር የቤተሰብ አባል ይኖራል። በብዙ ልፋት ካገኛት ገቢ የተወሰነውን ወርዉሮ የቤተሰብ ሕይወት የሚለወጥ የሚመስላቸው ሊኖሩ ይችላሉ። ላባችን ጠብ አርገን ካገኘነው የምንልከው ገንዘብ የሚዉለው ለልማት ይሁን ለጥፋት የምንከታተል ስንቶቻችን ነን? ስንቶቹን ሱሰኛና ቁማርተኛ እያደረግናቸው እንደሆነስ የምንከታተል ስንቶቻችን ነን? ቁጭ በሎ መብላትን የለመደን ሥራ መባል ያመዋል። በአገሪቱ የተመቻቹ ሀብት ለማፍራት የሚያበረታቱ ዕድሎችን በመጠቀም በልማቱ ተሳታፊ በመሆን ራሳቸውእንዲችሉ የምናደርግ ስንቶቻችን ነን? ብቻ ሁሉንም በልማት መነጽር ማየቱ ጠቃሚ ይሆናል እንጂ አይጎዳም።
አንዳንድ የሚሰሙ ነገሮች የሚያሳፍሩ ናቸው። በብዙ ልፋት ከሚያገኙት ገቢ ልማትን ለሚያደናቅፉ ተግባሮች ለማዋል፣ ለብጥብጥና ሁከት ለመጠቀም ለሚጠይቁ ግለሰቦች የሚመጸዉቱ አሉ ሲባል አንድም አለማወቅ፣ ሁለትም በኢትዮጰያ ዉስጥ ያለዉን ተጨባጭ ሁኔታን አለመገንዘብ ይሆናል። ተግባሩ ግን ቆም ብሎ ማሰበን የሚጠይቅ ነው።
ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይም ትዉልድ ትርጉም ላለው የህዳሴ ግድባችን ቢዉል ኩራት ነው የሚሆነን የነበረው። ኢትዮጵያ ከድህነት ለመዉጣት በምታደርገው ጥረት ሁላችንም አሻራች እናሳርፍ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሁሉንም ልጆቿን ባሉበት ሁሉ ይባርክ!

No comments:

Post a Comment