EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 29 June 2015

ስንዴውን ከእንክርዳዱ የለየ የህዝብ ድምፅ

(በየማነ ገብረስላሴ)
ግንቦት 16 የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነበር፡፡ በቅድመ ምርጫ ሂደቱ ፓርቲዎች አማራጮቻቸው ለህዝብ የሚያቀርቡበት ሰፊ ዕድል አግኝተው የምረጡኝ ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የተደረጉ ዘጠኝ የፓርቲዎች የክርክር መድረኮችን ጨምሮ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮና በጋዜጣ እንዲሁም በመንገድ ላይ ሰልፍናና ሌሎች ስልቶች ቀስቅሰዋል፡፡ ይህ የቅስቀሳ ሂደት ሁሉም ፓርቲዎች አማራጮቻቸው እንዲያቀርቡ ሰፊና እኩል ዕድል የሰጠ ነበር፡፡ የምርጫው እለትና የድህረ ምርጫው ሂደትም በተመሳሳይ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ መሆኑን ማየት ይቻላል። ምርጫውን በታዛቢነት የተሳተፉት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ጥምረትና የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድኖች ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የዚህን ምርጫ ውጤት ይፋ ሲያደርግ እንደታወቀው ኢህአዴግ ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት አሸንፏል። ኢህአዴግ በ5 ክልሎች በ500 ወንበሮች ተወዳድሮ ዋጋ ካለው 33 ሚሊዮን 201ሺ969 ድምጽ ውስጥ 27 ሚሊዮን 347ሺ 332 (82.4 በመቶ) በማግኘት ሙሉ በሙሉ አሸንፏል፡፡ በቀሪዎች 46 ወንበሮች ደግሞ የኢህአዴግ አጋሮች ያሸነፉ ሲሆን በደቡብ ክልል የጊምቦ ገዋታ ምርጫ ክልል ውጤት ተጠናቆ ለቦርዱ ቀርቦ ባለመጽደቁ ቦርዱ ውጤቱን ይፋ ባደረገበት ሪፖርት ላይ አልተካተተም፡፡
በምርጫው ላይ የተገኘው ውጤት ዘርፈ ብዙ መልዕክቶች አሉት፡፡ በዋናነት ህዝቡ በኢትዮጵያ የሰፈነው አስተማማኝ ሰላም፣ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለአፍታም ቢሆን እንዲደናቀፍ እንደማይፈልግ ጠንካራ አቋም መያዙን ያሳየ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ እጦትና ስር ለሰደደ ድህነት ዳርጎን የነበረው ስርዓት በትጥቅ ትግል ተፋልሞ በማስወገድ የመጀመርያው የትግል ምዕራፍ በድል አጠናቋል፡፡ ከድሉ በኋላ እየተከናወነ ባለው ሁለተኛው የትግል ምዕራፍም አስደናቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ የድህነት መጠን ከግማሽ በላይ ቀንሷል፣ እንደ ትምህርትና ጤና ባሉ የማህበራዊ ልማት መስኮች አንጸባራቂ ስኬቶች ተመዝግበዋል። አገራችን በአሁኑ ወቅት ግዙፍ የመሰረተ ልማት አውታሮች ግንባታ የሚከናወኑባት ለመሆን የበቃችው ኢህአዴግ በቀየሰው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ረገድም ረጅም ርቀት ተጉዘናል፡፡ ለአንዲት የዴሞክራሲ ጀማሪ አገር የሚያስፈልጉ የዴሞክራሲ ተቋማት ተመስርተዋል። መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚደረገው ትግል ውስብስብና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም መልካም ውጤቶች እየተመዘገቡበት ነው፡፡
በአገራችን የነበረውን ስር የሰደደ ድህነት በመቀነስ ረገድ አንፀባራቂ ድል የተመዘገበ ቢሆንም አሁንም ግን ቁጥሩ የማይናቅ ህዝብ በድህነት ውስጥ ይኖራል፡፡ ነገር ግን የተቀየሰው መስመር ህይወታቸውን በበጎ ሊቀይር የሚችል መሆኑን ዜጎች አምነዋል። በተጀመረው የእድገት ፍጥነት ከቀጠልን እንደ አገር ከድህነት ለመላቀቅና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ እንደምንችል ተስፋ በማድረጋቸው ነው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መራጮች ድምፃቸውን ለኢሕአዴግና ለአጋሮቹ የሰጡት። ህዝቡ ኢህአዴግን ሲመርጥ መልካም ነገሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ እስካሁን መፍትሄ ያላገኙ ችግሮችን ደግሞ በአፋጣኝ ሊፈታ እንደሚገባው ማሳሰቢያ በመስጠት ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት እንደታየው አብዛኛዎቹ ተቀዋሚ ፓርቲዎች የኢህአዴግን መልካም ስራዎች ከማጠልሸትና በስራ ሂደት የሚፈጸሙ አንዳንድ ችግሮችን ከማራገብ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ ይዘው አልቀረቡም ብቻ ሳይሆን ህጋዊና ህገ ወጥ መንገድ እያጣቀሱ የተጀመረው ብሩህ ጉዞ ለማደናቀፍ ላይ ታች ሲሉ ከርመዋል፡፡  የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ የተገነዘቡት የኢትዮጵያ ህዝቦች ግን የእነዚህ ኃይሎች መሳርያ መሆን እንደማይችሉ ዳግም በማረጋገጥ በድምፃቸው ስንዴውን ከእንክርዳዱ ለይተዋል፡፡  
ገና ከጅምሩ የመራጩን ህዝብ ቀልብ ሊስብ የሚችል አጀንዳ ይዘው እንዳልቀረቡ የሚያውቁ አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች ገና ምርጫው ሳይካሄድ ነበር ሂደቱን ማጥላላት የጀመሩት፡፡  ማንኛውንም ሂደት ማብጠልጠልና በተለይ ለውጭ ኃይሎች ክስ ማቅረብ የተለመደ ባህርያቸው ነውና አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህ አይነት የከሸፈ ስልት ያዋጣናል ብለው ቢመርጡትም ግን እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ በዝረራ ለመሸነፍ አብቅቷቸዋል፡፡
ምንም እንኳን የሚበዙት ፓርቲዎች የምርጫውን ውጤት አክብረው በቀጣይ ውስጣቸውን በመፈተሽ ጠንክረው እንደሚሰሩ የገለጹ ያሉ ቢሆኑም አንዳንድ ፓርቲዎች ከስህተታቸው ከመማር ይልቅ የምርጫው ውጤት ከተገለጸ በኃላም በሰላማዊነቱና ዴሞክራሲያዊነቱ የተመሰከረለትን የምርጫ ሂደት ከማጠልሸት አልተቆጠቡም፡፡ ለዚህም መነሻ የሚያደርጉት ደግሞ አንድ ፓርቲ ሙሉ የህዝብ ድምፅን ማግኘት አይችልም፣ ስለሆነም የተጭበረበረ ውጤት ነው የሚል ነው። ይህ ድምዳሜ ግን መነሻውም ጭምር ስህተት ነው።
አንድ ፓርቲ ሌሎች ፓርቲዎችን በዝረራ ማሸነፍ እንደሚችል ሌላ ቦታ ሳንሄድ የቅርብ ጊዜ የአገራችንን የምርጫ ታሪክ መፈተሽ በቂ ነው። በ1997 ዓም በተደረገው ሶስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ቅንጅት ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ኢህአዴግን ሙሉ በሙሉ አሸንፎ እንደነበር ይታወቃል፡፡  በወቅቱ ኢህአዴግ ውጤቱን አሜን ብሎ በመቀበል ወደ ወስጡ ማየትን ነበር የመረጠው፡፡ ከህዝቡ ጋር ተወያየቶ፣ ራሱን በሚገባ ፈትሾ ድክመቶቹን በማሻሻሉ በቀጣዩ ምርጫ ከሁለት ምርጫ ክልል በስተቀር፣ በዘንድሮው ምርጫ ደግሞ በሁሉም የተወዳደረባቸው ምርጫ ክልሎች ማሸነፍ ችሏል፡፡ እናም እነሱ ሲያሸነፉ ‹‹ምርጫው ዴሞክራሲዊ ነው›› ሲሸነፉ ደግሞ ‹‹ዴሞክራሲዊ አይደለም›› የሚሉት ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡

ኢህአዴግ ይሄን ያህል ወንበር ቢያሸንፍም ኢህአዴግን ያልመረጡ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ዜጎች እንዳሉ አይካድም፡፡ እነዚህ ዜጎች ተቀዋሚ ፓርቲዎችን የመረጡት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕቅድና ፖሊሲ አማልሏቸው እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም ቀድሞውንም የረባ አማራጭ አልቀረበላቸውምና። እነዚህ ዜጎች ኢህአዴግን ያልመረጡት ባልፈታቸው እንደ መልካም አስተዳደር ያሉ ችግሮች ተማረው እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም አሁንም ኢህአዴግ ወደ ውስጡ በማየት ችግሮቹን ፈትሾ ለማስተካከል በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ልክ እንደከዚህ ቀደሙ የመረጠውንም ሆነ ያልመረጠውም ህዝብ የበለጠ ትጋት ለማገልገልም ህዝባዊ አደራውን እስከተቀበለ ድረስ የሚመራበት የልማታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ከዚህ የበለጠ ልዕልና ኖሮት የህዝቦች ምርጫ መሆኑ አይቀርም፡፡

No comments:

Post a Comment