EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday, 5 May 2015

የትምህርት ፖሊሲያችን ለህዳሴያችን!!

ኢህአዴግ የተከተለው ትክክለኛ የትምህርት ፖሊሲ ለህዳሴ ጉዟችን አስፈላጊውን የሰው ኃይል በማሟላት ላይ ይገኛል!!
የአንድን ሀገር መፃኢ እድል ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱ ትምህርት ነው፡፡ ትምህርት ለአንድ አገር እድገትና ብልፅግና እጅግ አስፈላጊ ብቻም ሳይሆን ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ዘመናዊ ትምህርት በሀገራችን ከተጀመረ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም ያለፉት መንግስታት በሰጡት ዝቅተኛ ትኩረትና የተሳሳተ ፖሊሲ ምክኒያት እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡
በሀገራችን በኢህአዴግ አመራር የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ህዝቡን ያሳተፈ ፖሊሲ ተቀርፆለት ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በልማትና በእድገት ጉዟችን ትልቅ አሻራን ያሳረፉ በርካታ ስኬቶች መመዝገብ ችለዋል። ባለፈው የቅስቀሳ ፕሮግራማችን በአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ማለትም በቅድመ መደበኛ፣ በመጀመሪያ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ የተመዘገቡ ስኬቶችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዛሬው የምርጫ ቅስቀሳ ፕሮግራማችን  በቴክኒክና ሙያ ስልጠና እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ትኩረት በማድረግ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
ሀገራችን የሚያስፈልጋትን መለስተኛና መካከለኛ ባለሙያ በማፍራት የህዳሴ ጉዟችንን ለማፋጠን ይቻል ዘንድ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ኢህአዴግ የቴክኒክና የሙያ ስልጠና ተቋማቱ መደበኛና አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት፤ አስፈላጊ የሰው ኃይል በማሟላት ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ለተቀመጠው ግብ ያላቸው ድርሻ የላቀ እንደሆነ በመገንዘብ  በትኩረት በመስራቱ ሀገራዊ ልማታችን የሚጠይቀውን በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል በማፍራት አበረታች ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ናቸው፡፡ 
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ስራ ፈጣሪ ዜጋ በማፍራትም ሆነ ለልማቱ የሚያስፈልገውን መካከለኛ የሰለጠነ ባለሙያ በማቅረብ ውጤታማ ስራዎች እንዲከናወኑ ያስቻሉ ናቸው፡፡ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ለማስፋፋት በተካሄደው ጥረት አስከ አለፈው አመት ድረስ 1ሺህ 312 ተቋማትን ተቋቁመው ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡
የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ተቋማቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የሚመረቱባቸው፤ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ምርምሮች የሚካሄዱባቸውና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግባቸው ማዕከላት ወደ መሆን እየተሸጋገሩ ይገኛሉ። ወደ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የተሸጋገሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ብቻ ብንመለከት በ2003ዓም 252 የማይበልጡ የነበሩ ሲሆን 2006ዓም 2ሺህ 627 የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማሸጋገር ተችሏል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ፕሮግራምን ተግባራዊ ካደረግንበት ዓመት ጀምሮ በርካታ የስራ ፈጠራ ባለሙያዎችን የጥቃቅንና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ችግር ፈቺ የቴክኖሊጂ ውጤት ማቅረብ የሚችሉ ወጣቶችን በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡ ይህም የሀገራችንን ህዳሴ ለማሳካት የሚያስችለን እርሾ በመፍጠር በኩል ተቋማቱ ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን የሚያሳይና ኢህአዴግ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ትክክለኛነት የሚያሳይ ነው።
በተቋማቱ የክህሎት ባለቤት እየሆኑ ያሉ ባለሙያዎችም ቁጥር እየጨመረ መምጣት ችሏል፡፡ በ2003ዓ.ም በጥቅሉ 371ሺህ 347 የነበረው የሰልጣኝ ቁጥር 2006 በመደበኛ 222ሺህ 113 በአጫጫር ስልጠናዎች ደግሞ 1ሚሊዮን 975 በማደግ በተቋማቱ ብቁ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ለፍሬ ማብቃት ተችሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር በየዓመቱ በሚካሄደው የሳይንስ፣ የሒሳብና የፈጠራ ውድድርም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ያሉ ተቋማት በሚያቀርቧቸው አዳዲስ ፈጠራዎች ዕውቅና በማግኘት ላይ መሆናቸው እንዲሁም በዘርፉ ሙያ ቀስመው የሚወጡ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀት ስራ ፈጥረው ሀብት ማፍራታቸው የፕሮግራሙን ስኬታማነት ያረጋግጣል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አሁን ለተመዘገቡ ስኬቶች የበቃው ተቋማቱ መማር ያልቻሉና በፈተና ውጤታቸው የወደቁ ተማሪዎች የሚሰባሰቡባቸው ማዕከላት ናቸው የሚለውን የተሳሳተ ግንዛቤዎና አመለካከት በመታገል ጭምር ነው። ዘርፉ በፕሮግራሙ እንደተመላከተውም ሆነ በተግባር እንደታየው አማራጭ ያጡ ሰዎች የሚሰባሰቡበት ሳይሆን ዜጎች ህይወታቸውን ለመምራት የሚያስችላቸውን ሙያዊ ዕውቀት ለማግኘት የሚገቡበት፣ በአመለካከት፣ በክህሎትና በአሰራር ዳብረው የሚወጡበት አቅም መገንቢያ ዘርፍ ነው። በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ሰልጥነው የሚወጡ ወጣቶች በሁለንተናዊ መልኩ የክህሎት ባለቤት በመሆን በአንድ በኩል በተለያዩ የልማት ዘርፎች ተቀጥረው በመስራት በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸው ስራ ፈጣሪ በመሆን ወደ ስራ በመሰማራት ስኬታማ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
የከፍተኛ ትምህርት ዋነኛ ተልዕኮ መሰረታዊና ወቅታዊ በሆኑ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ በእውቀት፣ በሙያና በምርምር የታነፁና ችግሮችን ለመፍታት የሚችሉ ዜጎችን ማፍራት መሆን እንደሚገባው አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት መንግስታት ስር የሰደዱትንና ሲንከባለሉ ለዘመናት የኖሩትን የትምህርት ስርዓት ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበና ሩቅ ያለመ የከፍተኛ ትምህርት ስርዓት በመዘርጋትና መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ስልቶችና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገብ ችለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የማስፋፋትና በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በመገንባት ተደራሽ እንዲሆኑ የተከናወነው ስራ እመርታዊ የሚባል ውጤት አስገኝቷል። በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ታጥሮ የቆየው የትምህርት ስርዓት ከ1983 ወዲህ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የስርጭቱን ፍትሃዊነት በመጠበቅ በአሁኑ ወቅት 33 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተገንብተው ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ 

የከፍተኛ ትምህርት የቅበላ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ በ1983ዓም ከ5ሺህ የማይበልጥ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት የቅበላ አቅም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎም በቅድም ምረቃ ፕሮግራም በ2006ዓም ወደ 31 በመቶ አድጓል፡፡ ይህ ሰፊ ቁጥር የሚይዘው የተማረ የሰው ኃይል በየዓመቱ በተለያዩ የስራ መስኮች በመሰማራት ተቋማቱ አገራችን ያሉባትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍና አገራዊ ራዕያችንን ለማሳካት በሚደረገው ትግልና ልማትን ለማፋጠን በምናደርገው ርብርብ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተሰጡ ያሉት የትምህርት ፕሮግራሞች ከሀገሪቱ የሰው ኃይል ፍላጎት ጋር ተጣጥመው እንዲሄዱ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አዳዲስ የትምህርት መስኮችን የመክፈትና የማጠናከር ስራ ተሰርቷል። ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚገቡ ተማሪዎች መካከል 70 በመቶዎቹ በምህንድስና በሌሎች የተፈጥሮ ሳይንስ መስኮች እና  30 በመቶዎች ደግሞ በተለያዩ የማህበራዊ ሳይንስ መስኮች እንዲማሩ አቅጣጫ በማስቀመጥ ለህዳሴ ጉዟችንን ስኬታማነት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቤተ ሙከራ ማዕከላት እንዲጠናከሩ በማድረግ እንዲሁም ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ትምህርትና ስልጠናውን በተግባር ለማስደገፍ የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ በመሆን ላይ ይገኛል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስርጭትን ፍትሐዊና ወደ ህብረተሰቡም ተደራሽ ለማድረግ ከተከናወኑ ስራዎች ባሻገር የጥራት ጉድለቶችን በሂደት እያረሙና እያሟሉ የሚሄዱ አቅጣጫዎች ተቀምጠው ተግባራዊ እየሆኑ ናቸው፡፡ መምህራንን በተለያዩ መንገዶች በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በማሰልጠን የመምህራንን አቅም በማጎልበት የትምህርት ጥራቱን የማስጠበቅ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሊኖሩ የሚገቡና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቁ የተግባር ማሰልጠኛ መሳሪያዎችን እጥረት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፤
ኢህአዴግ በተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲ እንደ አጠቃላይ የትምህርት ዘርፉ ሁሉ በቴክኒክና ሙያ እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፎችም ህዝባችን የሚያውቃቸው ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ሆኖም ሁሌም የኢህአዴግን ስኬቶች ማጠልሸትን እንደ ፖሊሲ አማራጭ የሚቆጥሩት የሀገራችን ተቃዋሚዎች በትምህርት ዘርፎች ያገኘናቸውን ድሎች ሲያጣጥሉ ይታያሉ፡፡  የበርካታ ዜጎቻችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተጨባጭ ስኬቶችን ያስመዘገበውን የትምህርት ፖሊሲ ዛሬም ትውልድ ገዳይ ነው ከሚለው የጥላቻ ዜማቸው አልተላቀቁም፡፡ በአፈፃፀም ላይ ያሉ ጥቃቅን ችግሮችን በመልቀም ከፖሊሲ ጋር ለጥፈው ሲያብጠለጥሉ ይታያሉ፡፡
ምንጊዜም ለህዝብ ተሳትፎ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ኢህአደግ የትምህርት ልማቱንም በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ እየፈፀመው ነው፡፡ በትምህርት መስክ የተመዘገበው ውጤት የሀገራችን ህዝቦች በተለይም መምህራን፤ ወላጆችና ተማሪዎች ባደረጉት ያልተቆጠብ ትግል እንደሆነ ኢህአዴግ ያምናል፡፡ ዛሬ ለዘመናት ትምህርት እንደሰማይ ርቋቸው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የትምህርት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ የአርሶ አደርና አርብቶ አደር ልጆች በእውቀት የዳበረ ኃይል ይዘው ወገናቸውን በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡ በሀገራችን ትምህርት የልማትና የብልፅግና መሰረት መሆኑ በተጨባጭ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች ራሳቸውን ለስራ ዝግጁ በማድረግና የስራ ፈጠራ ፍላጎትን በማዳበር ከጠባቂነት ተላቀው በራሳቸው መንቀሳቀስ የሚችሉበትን አቅም መያዝ ችለዋል፡፡ ኢህአዴግ አሁንም ይህንን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጥ ይወዳል፡፡
ኢህአዴግን መምረጥ ህዳሴን መምረጥ ነው!!
ኢህአዴግን ይምረጡ!!
ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተው ታታሪዋ ንብ ነች!!

No comments:

Post a Comment