EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 4 May 2015

የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ የትምህርት ፖሊሲ !!

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
ዜጎች ሊሟሉላቸው ከሚገቡ መሰረታዊ መብቶች ውስጥ የመማር መብት አንዱ ነው፡፡ የአንድን አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ልማት ለማረጋገጥ ትምህርት ቁልፍ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል። ወደ ኋላ መለስ ብለን ከ1983.ም በፊት የነበረውን የአገራችንን የትምህርት አቅርቦት ስንቃኝ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነበር፡፡ የትምህርት አቅርቦቱ በተደራሽነትም ሆነ በፍትሃዊነት እጅግ ከፍተኛ ችግር ነበረበት፡፡ በ1983ዓ.ም ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ህፃናት መካከል 19 በመቶው ብቻ ነበሩ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል የመማር ዕድል ያገኙት፡፡
የአገራችን የትምህርት ስርዓት ችግር ግን አገልግሎቱ በሚገባ ያልተስፋፋ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በፍትሃዊነትም ከፍተኛ ችግር ነበረበት። በከተማና በገጠር፣ በወንዶችና በሴቶች እንዲሁም በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የነበረው ስርጭትና ተሳትፎ በእጅጉ የተዛባ ነበር። ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር እድላቸውን የተነፈጉባቸውን ስርዓቶች ነው ያሳለፍንው።
ኢህአዴግ በድርጅታዊ ፕሮግራሙ ደረጃውን የጠበቀና ከአገሪቱ የልማት አቅጣጫዎች ጋር የተቆራኘ ትምህርትና ስልጠና ማስፋፋት እንደሚገባ በማስቀመጥ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ የትምህርት ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ማዳረስ እንደሚገባ፣ ከኢኮኖሚ እድገቱ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የሁለተኛና ከፍተኛ ትምህርት ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ግልፅ የፖሊሲ አቅጣጫ ተቀምጦ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡
ኢህአዴግና የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለትምህርት ትኩረት ሰጥተው በመረባረባቸው በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የትምህርት እርከኖች ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በትምህርት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም አብዛኛው የአገራችን ዜጎች የመማር መብታቸውን ተነፍገው የነበረበትን ሁኔታ በእጅጉ የቀየር በኢህአዴግና በአገራችን ህዝቦች ርብርብ የተገኘ ትልቅ ድል ነው፡፡ ባለፉት ስርአቶች ታፍኖ የነበረው የዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር መብት ህገ መንግስታዊ ጥበቃ ተደርጎለት በአሁኑ ጊዜ 24 በሚሆኑ የብሄር ብሄረሰብ ቋንቋዎች ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡
በቅድመ መደበኛ ወይም አፀደ ህፃናት ትምህርት በ1983ዓ.ም በመላ አገሪቱ 98ሺ 412 ህፃናት ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበረበት ሁኔታ ዛሬ በእጅጉ ተቀይሮ በ2006ዓ.ም ወደ 2.3ሚሊዮን አድጓል። በቅድመ መደበኛ ትምህርት የተገኘውን ስኬት በማጠናከር አገልግሎቱን ይበልጥ ማስፋት እንደሚገባን ተገንዝበን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡

ኢሕአዴግ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም ዜጎች በነፃ መዳረስ አለበት ብሎ በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል፡፡ ከፍተኛ በጀት በመመደብና የህዝብን ተሳትፎ በማረጋገጥ ለህዝቡ ተደራሽ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በ1983ዓ.ም 8ሺ 434 የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ብቻ የነበሩ ሲሆን በ2006ዓ.ም 30ሺ 800 ደርሷል፡፡ ይህም የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶችን ለማግኘት የሚወስደው አማካኝ ርቀት ወደ 2.5 ኪ.ሜትር ዝቅ እንዲል ያደረገ ሲሆን ለበርካታ ዜጎች የትምህርት እድል እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ በ1983ዓ.ም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እድል ያገኙ ዜጎች ቁጥር 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብቻ የነበረው ባለፈው አመት 19.2 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ እድሚያቸው ለትምህርት የደረሰ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ንጥር ተሳትፎ በ1983 ከነበረበት 19 በመቶ በአሁኑ ጊዜ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ንጥር ተሳትፎ 99 በመቶ የደረሰ ሲሆን ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያለው ተሳትፎም 94 በመቶ ደርሷል።  
ባለፉት 23 አመታት በተደረገው ርብርብ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርትም ከፍተኛ ስኬት አስመዝግበናል፡፡ በ1983.416 ሺ ያህል ተማሪዎች ብቻ ያስተናግዱ የነበሩት 284 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ 2ሺ333 አድጎ በ2006ዓ.ም ከ2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉባቸው ማድረግ ችሏል። የትምህርት ስራችን ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ ነው፡፡ በከተማና በገጠር የነበረውን ፍታሃዊ ያልሆነ ስርጭት በእጂጉ ተሻሽሏል፡፡ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅጣጫም በመከተል ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ቀደም ሲል ከትምህርት አኳያ ከፍተኛ ኢፍትሃዊነት የሚታይበት ጉዳይ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ነበር፡፡ ሴቶች በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች የተነሳ በትምህርት የነበራቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ለዚህም ነው የትምህርትና ስልጠና ፖለሲ ሲቀረጽ በዋነኛነት የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን በማካተት ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው። በሂደትም የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ እያደገና ከወንዶች ጋር እየተመጣጠነ ይገኛል።
የልዩ ፍላጎት የትምህርት ፕሮግራም ተግባራዊ በማድረግም የዜጎችን የትምህርት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ እንገኛለን፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በመደበኛ ትምህርት የመማር ዕድል ያላገኙ ዜጎች ከሀገሪቱ የትምህርት ስርዓት ፍትሓዊ ተጠቃሚ በመሆን የህይወት ክህሎታቸውን መገንባትና የተሻለ አምራች ዜጋ መሆን ስላለባቸው የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ተቀርፆ በመተግበር ላይ ነው። እስካሁን 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጎልማሶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን 6 ነጥበብ 6 ሚሊዮን ጎልማሶች ደግሞ በመማር ላይ ናቸው፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
ኢህአዴግ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ፓኬጅ አዘጋጅቶ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ በቂ ማሻሻያና የማበልፀጊያ ግብአት በማሰባሰብ ወደ ትግበራ ተሸጋግሯል፡፡ ከፍተኛ ውጤት እያስገኘም ነው፡፡ የመማሪያ መፅሃፍትንና የመርጃ መሳሪያዎችን አቅርቦት ለማሻሻል እንዲሁም የመምህራንን መጠንና አይነት ለማሻሻል ባለፉት አመታት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችም ተመዝግበዋል።
በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተማሪ መምህር ጥምርታ አንድ ለ54፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አንድ ለ28 ደርሷል፡፡ በተመሳሳይ የተማሪ ክፍል ጥምርታም ለውጦች የተመዘገቡበት ነው፡፡ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያና የማስተማሪያ መጻሕፍት በማሳተምና በማሰራጨት ተደራሽነቱ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ በጥምርታዎቹ የተመዘገበው ለውጥ የተሻለ ትምህርት ለመስጠትና ተማሪዎችን የበለጠ ለማገዝ አስችላል፡፡ ይሁንና ለውጡ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ወጥነት የሌለው በመሆኑ ትኩረት እንደሚሻ ኢሕአዴግ ይረዳል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ረገድ ዋናው ትኩረታችን ጥራት ማስጠበቅ ላይ በማድረግ ስርዓተ ትምህርቱን ለማሻሻልና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ለማሟላት ጥረት ተደርጓል፡፡ የተገኙ ውጤቶችም ስፋት ያላቸው ናቸው፡፡ የሁለት ተቀራራቢ ዓመታትን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ የፈተና ውጤትን ማሳያ አድርገን ብናይ እንኳ የትምህርት ጥራት እየተሻሻለ ለመምጣቱ  ዋቢ  ይሆናል፡፡ በ2002 .ም ማጠናቀቂያ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 2ነጥብ እና በላይ ውጤት ያስመዘገቡ 62.25% የነበረ ሲሆን ይህን ምጣኔ 2005 .ም ወደ 73.34% ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይሁንና ችግሮቹ አሁንም ስላልተወገዱ ስርጭቱን ከኢኮኖሚያዊ እድገታችን ጋር በተቀናጀ አኳኋን የማስፋፋቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ዋናው ስራችን ጥራቱን ማሻሻል መሆን እንዳለበት ኢሕአዴግ ይገነዘባል፡፡

የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፤
ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ለትምሀርት ዘርፍ ትኩረት በመስጠት በመረባረባቸው በትምህርት ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ህዝቡ በትምህርት ቤት ግንባታዎችም ሆነ በሌሎች ተግባራት የነበረው ተሳትፎ ክፍተኛ ነበር፡፡ በትምህርት ዘርፍ ለተመዘገቡ ስኬቶች መምህራን የተጫዎቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ኢህአዴግ ያምናል፡፡ የአገራችን መምህራን የሚያጋጥሟቸውን ችግሮችን በመጋፈጥ አገራቸውና ህዝባቸው የጣሉባቸውን ኃላፊነቶች በመወጣት ያበረከቱትን አስቷዋጽኦ ኢህአዴግ ከፍተኛ እውቅና ይሰጠዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሂደት ትውልድን ለመቅረፅ ከባድ ሃላፊነት የሚጠይቅና የመጪዋን ኢትዮጵያ ዕድል የሚወስን ትውልድ በብቃት የመገንባት ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ኢህአዴግ ለመምህራን ልማት ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል፡፡
ባለፉት አመታት የመምህራን ልማት ፕሮግራም በማዘጋጀት ሰፋፊ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ መምህራን የስራ ላይ ስልጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ አቅማቸውን ለመገንባት ጥረት ተደርጓል፤ በመደረግም ላይ ነው፡፡ ለመምህራንን የሚሰጠው ስልጠና በአንድ በኩል የደረጃ ማሻሻያ በሌላ በኩልም በሙያ ማሻሻያ መርሃ ግብሮች ተከፍሎ የሚፈፀም ነው። የደረጃ ማሻሻያው ስልጠና ከሰርቲፊኬት ወደ ዲፕሎማ፣ ከዲፕሎማ ወደ መጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም ወደ ሁለተኛ ዲግሪ እያለ በመደበኛና በርቀት ሲሰጥ ቆይቷል። ከፍተኛ ወጪ በማውጣትም በርካታ መምህራን የትምህርት ደረጃቸውን በማሻሻል ብቁ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል። ስራው በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
የመምህራንን የኑሮ ሁኔታ ከአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚው ጋር ተያያዞ መለወጡ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት የመምህራንን ኑሮ ለማሻሻል የአገሪቱ አቅም የፈቀደውን ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ይገነዘባል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፤
በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች አልጋ በአልጋ የተገኙ ሳይሆን በርካታ ችግሮችን በማለፍ ነው፡፡ አሁንም ትኩረት ሰጥተን መፍታት ያሉብን ችግሮች እንዳሉም ኢህአዴግ ይገነዘባል፡፡ የቅድመ መደበኛ፣ የጎልማሶች ትምህርት እና የልዩ ፍላጎት የትምህርት ተደራሽነትን ማሻሻል ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች ይጠቀሳል፡፡ የትምህርት የጥራት ፓኬጆችን አጠናክሮ በማስቀጠል በጥራት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ እየፈቱ መሄድም እንደዚሁ ትኩረት የሚሻው ጉዳይ እንደሆነ ኢህአዴግ ተገንዝቦ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
በአንጻሩ የአገራችን ተቃዋሚዎች ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ የሚገኘውን የትምህርት ፖሊሲ በጭፍኑ በመቃወም ሲያጥላሉት ይታያል፡፡ ውግንናቸው ለአብዛኛው ህዝብ ባለመሆኑ የትምህርት ማስፋፋት ስራወቻችንን ሊያጣጥሉ ይፈልጋሉ፡፡ ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች ዜጎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር መብታቸውን ጭምር ይቃወማሉ፡፡ የኢህአዴግ ፖሊሲና ስኬቶችን ከማብጠልጠል የዘለለ ግልጽ የፖሊሲ አማራጭም አያቀርቡም፡፡

በኢህአዴግ አመራር የአገራችን ህዝቦች በትምህርት ዘርፍ የተጎናጸፉት ስኬት ተቃዋሚዎች እንደሚያጣጥሉት ሳይሆን በሁሉም መስፈርቶች ሲታይ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ኢህአዴግ  ትምህርት ለአገራችን ህዳሴ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በቀጣም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኢሕአዴግ ከአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ በተጨማሪ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትም በስርጭት፣ በተሳትፎና ጥራት ማስጠበቅ አመርቂ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ በእነዚህ የትምህርት መስኮች የተመዘገበውን ስኬት በሚቀጥለው የምርጫ ቅስቀሳ ዝግጅታችን የምንመለስበት ይሆናል።

የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ ኢህአዴግን እንምረጥ!

ኢህአዴግን መምረጥ ብቁና በሚገባ የታነፀ ፍሬያማ ትውልድ መቅረፅ ነው፡፡

ኢህአዴግን ይምረጡ!! ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተው ታታሪዋ ንብ ነች

No comments:

Post a Comment