EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 10 May 2015

ለትዝብት ያጋለጠ ተቃውሞ

/በየማነ ገብረስላሴ/
ኢህአዴግ እንደ ሌሎቹ መስኮች ሁሉ በትምህርት መስክም አንፀባራቂ ድሎች የተጎናጸፈ ድርጅት ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ በማቀድ የትምህርት ተደራሽነትን በአጭር ጊዜ ያስፋፋ ድርጅት ነው፡፡ ኢህአዴግ የተከተለው የትምህርት ፖሊሲ ትምህርት ቤቶች እንደ ሰማይ ርቋቸው የነበሩ የገጠር ቀበሌዎች ቢያንስ አንድ ቢበዛ እስከ አራት ትምህርት ቤቶች ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ ትምህርት ለልማትም ሆነ ለዴሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ ያለውን የማይተካ ሚና በመገንዘብ በዘርፉ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን በጥልቀት ገምግሞ ወደ ስራ የገባው ኢህአዴግ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም የጥራት ፓኬጅ ቀርጾ በመረባረብ ላይም ይገኛል፡፡
ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የትምህርት ፖሊሲው ትውልድ ገዳይ ነው፣ የጥራት ችግር አለ፣ ለመምህራን ተገቢ ክፍያ ባለመክፈልና የትምህርት ዕድገት እንዳያገኙ በማድረግ ጉዳት እያደረሰባቸው ነው በማለት ፖሊሲውን ያጣጥሉታል፡፡ የትምህርት ስርዓቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ባለመሆኑ የተቀዋሚ ፓርቲ አባልና ደጋፊ የሆኑ መምህራንን ያገልላል ሲሉ የሚከሱም አሉ፡፡
ሁሉንም ነገር ጥላሸት መቀባት የሚቀናቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን ይበሉ እንጂ ኢህአዴግ የተከተለው የትምህርት ፖሊሲ ያስመዘገበው እምርታ ተጨባጭ ነው፡፡ የትምህርት ፖሊሲው መልካም ስነ ምግባር ያለውና በሀገሪቱ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ትልቅ ሚና የሚጫወት ዜጋ በማፍራት ረገድ ስኬታማ ነው፡፡ ወጣቶች በተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ በሳይንስና ሌሎች መስኮች በቀሰሙት ሙያ አገራቸውን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ጓድ ሽፈራው ሽጉጤ ‹‹በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ በሁሉም የልማት ስራዎች እየተሳተፉ ትልቅ ውጤት በማስመዝገብ ላይ የሚገኙት ኢህአዴግ የተከተለው የትምህርት ፖሊሲ ያፈራቸው ባለሙያዎች ናቸው›› ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
ተቀዋሚ ፓርቲዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በ10ኛ ክፍል እንዲቋጭ መደረጉን ‹‹ፖሊሲው ትውልድ ገዳይ ነው›› ለሚለው ውንጀላቸው በማጠናከሪያነት ያቀርቡታል፡፡ ህዝብ በግላጭ የሚያውቀውን ስኬታችንን በጭፍኑ መቃወም በራሱ ስራ የሚመስላቸው እነዚህ ተቃዋሚዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ 10ኛ ክፍል ላይ መደረጉ ለስራ አጥነትም ምክንያት ነው ይላሉ፡፡
ኢሕአዴግ ይህን ስልት ሲቀይስ በትምህርት የበለፀጉ አገራትን አለም አቀፍ ልምድ በመቀመር ነው፡፡ የትምህርት ፕሮግራሙ ከሚጠይቀው በላይ ተማሪውን ለሁለት ዓመታት ማቆየት በምንም መልኩ የጥራት ችግር አይሆንም፡፡ የስራ አጥነት ችግርንም ሊፈታ አይቻለውም። ተማሪዎችን እስከ 12ኛ ክፍል በማስተማር የስራ አጥነት ችግር የሚፈታ ቢሆን ኖሮ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ በነበረው የትምህርት ስርዓት 12ኛ ክፍልን አጠናቀው ስራ አጥ የሆኑ ወጣቶች ባልተፈጠሩ ነበር።
ተቃዋሚዎች ቀደም ባሉት ስርዓቶች ውስን ተማሪዎች በነበሩበት ጊዜ ሲተገበር የነበረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በ12ኛ ክፍል እንዲቋጭ የማድረግ አሰራር መቀጠል አለበት ሲሉ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ ስለመቀጠሉ እንኳን አያገናዝቡም፡፡ ሃሳባቸው በአሁኑ በወቅት ካለው የተማሪዎች ብዛትና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቅበላ አቅም ጋር ፈፅሞ አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ በ24 ዓመታት ከ30 በላይ አዳዲስ ዩንቨርስቲዎችን በመገንባት አንፀባራቂ ድሎችን ተጎናፅፈናል፡፡ እነዚህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአሁኑ ወቅት ከ500ሺ በላይ ተማሪዎች በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቅበላ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ቢያድግም በአሁኑ ወቅት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥርም በብዙ ዕጥፍ አድጎ ሚሊዮኖች ደርሷል፡፡ ይህን ሁሉ ተማሪ እንቀበል ቢባል እንኳን የዩንቨርስቲዎቻችንን ቁጥር በብዙ እጥፍ ማሳደግን ይጠይቃል፡፡
እናም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በ10ኛ ክፍል እንዲቋጭ በማድረግ ወደ ዩኒቨርስቲው የሚገባው የቅድመ ዝግጅት ትምህርት ወይም 11ኛና 12 እንዲቀጥል ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማይገቡ ደግሞ በተለያዩ ሙያዎች እንዲሰለጥኑ ማድረግ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ አዋጭ ስልት ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያላገኙ ወጣቶች በሙያና ቴክኒክ በተለያዩ ሙያዎች እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በአገራችን ለተመዘገበው ፈጣንና ዘርፈ ብዙ እድገት በሙያቸው ያበረከቱት አስተዋፆ በማንም የማይተካ ነው፡፡ የቀደመው የትምህርት ስርዓት ቢቀጥል ኖሮ አገሪቱ ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጣት የሚችላትን ሃይል ለተጨማሪ ሁለት አመታት በማዘግየት በጊዜ፣ በሰው ሃይል አቅምና በገንዘብ ትከስር ነበር፡፡ ከዚህ አልፎም የትምህርት ስርዓቱ ትኩረቱን የቀለም ትምህርቱ ላይ በማጠር የክህሎት እጥረት ማጋጠሙ አይቀርም ነበር፡፡
አንዳንድ ፓርቲዎች ‹‹መምህራን በቂ ደመወዝ እየተከፈላቸው አይደለም›› በማለት  ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮችን በማሰማት ተቆርቋሪ መስለው ለመታየት ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውም በቴሌቪዥን ክርክር ላይ ታይቷል፡፡ በመምህራንም ብቻ ሳይሆን በጤና ባለሙያዎችም ላይ እንዲሁ አንስተዋል፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት መምህራንን ጨምሮ የሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ያለው የኑሮ ጫና ለመቀነስ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የአገሪቱን አቅም ባገናዘበ መልኩ የደመወዝ ጭማሪም አድርጓል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን የትራንስፖርትና የቤት ችግር ለመቅረፍም የተቀየሱ ስልቶች አሉ፡፡ ይህም ሆኖ አሁንም ሰራተኞች በቂ ክፍያ እያገኙ ነው የሚል እምነት የለውም፡፡ ጓድ ሽፈራው እንዳሉትም “ለመምህራን ይሁን ለሌላቸው የመንግስት ሰራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ በቂ ነው ብለን አናምንም፣ አገር ነው እየገነባን ያለነው፣ ይህ ትውልድ መስዋዕትንነት ካልከፈለ ደግሞ የተሻለች አገር መፍጠር አንችልም፡፡” ዘለቄታዊ መፍትሄው የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ በማስቀጠል አገራችን ያለባትን የካፒታል እጥረት በሚቀረፍበት ደረጃ ላይ ማድረስ ነው፡፡ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞችም ለዚሁ ነው በመትጋት ላይ ያሉት፡፡
ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት መምህራንን በማግለል የሚታማ አይደለም፡፡ ጓድ ሽፈራው እንደሚገልጹት ይልቁንም የትምህርት ፖሊሲው ለመምህራን ልዩ ትኩረት የሰጠ ነው፡፡ መምህራን ብቃትና ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችሉ የትምህርት ዕድሎች በስፋት እንዲያገኙ እያደረገ ያለው በኢሕአዴግ የሚመራው መንግስት ነው፡፡

ትምህርት ቤቶች ከፖለቲካ ገለልተኝነት የፀዱ አይደሉም የሚለውን የፓርተዊዎቹ አባባልም ተቀባይነት የለውም፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሳይቀር የተቀዋሚ ፓርቲ አመራሮች በነፃነት እየሰሩና የመሰላቸውን የፖለቲካ አቋም እያንጸባረቁ ባሉበት ሁኔታ የሚቀርበው ይህን መሰል ውንጀላ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ጓድ ሽፈራው የትምህርት ስርዓቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የጸዳ አይደለም የሚለውን የተቀዋሚዎች አስተያየት የተቀዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሳይቀር በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማስተማር ላይ መሆናቸውንና የመድረክ ፓርቲ አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በስራቸው ምርጥ ተመራማሪ ተብለው በትምህርት ቤቶች ስማቸው መጠቀሱን በመግለፅ ሃሳቡን ውድቅ አድርገውታል፡፡

No comments:

Post a Comment