ኢትዮጵያውያን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም በነቂስ ወጥተው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ”ይመሩኛል” የሚሏቸውን ተወካዮች ሲመርጡ ውለዋል፡፡ የምርጫው ሂደትም ፍፁም ሰላማዊ፣ የተረጋጋና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡ የምርጫ ሂደቱን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ጥምረት ከአገር ውስጥ፣ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ደግሞ ከውጭ አገራት ተወካዮች እንዲታዘቡት ተደርጓል፡፡ ሁሉቱም ቡድኖች ምርጫው የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር በሰጧቸው መግለጫዎች አረጋግገጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ጥምረት በመላ አገሪቱ 42 ሺ ያክል አባላቶቹን በማሰማራት ነው ምርጫውን የታዘበው። ጥምረቱ የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ምልከታ ሪፖርቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት ምርጫው ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆነ እንደተጠናቀቀ ገልጸዋል፡፡
የጥምረቱ ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር "በመላ አገሪቱ የተካሄደው አምስተኛው ምርጫ በሁሉም መለኪያዎች ሲመዘን ደረጃውን የጠበቀ፣ ፍትሃዊ፣ አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ሰላማዊ መሆኑን ታዝበናል" ብለዋል።
በቀድሞ የናሚቢያ ፕሬዚዳንት ሂፊኪፑንያ ፑሃምባ የሚመራው የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በበኩሉ የቅድመ ምርጫና የምርጫ ዕለት የነበረውን ሂደት የሚዳስስ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
የቡድኑ ሰብሳቢ ሚስተር ሂፊኪፑንያ ፑሃምባ “በአጠቃላይ ምርጫው የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ተዓማኒ ነበር” ሲሉ ነው የገለፁት፡፡ የኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱንም አስምረውበታል፡፡ ቡድኑ አዲስ አበባ ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ እስከ ምርጫ ዕለት የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ሰላማዊና የተረጋጋ መሆኑን እንደታዘበም አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማስፈፀም ራሱን በሚገባ አዘጋጅቶ 45ሺ 795 የምርጫ ጣቢያዎች እና 226ሺ የምርጫ ባለሙያዎችን ማዘጋጀቱን ጥሩ አፈጻጸም ሲል ነው የገለጸው፡፡ ለመራጮች የስነ ምግባር ትምህርት በመስጠት ረገድ ያስመዘገበውን ስኬትም አድንቋል፡፡
ቡዱኑ በመግለጫው የምረጡኝ ዘመቻዎቹ በአጠቃላይ ሰላማዊ እንደነበሩ ነው ያመለከተው፡፡ ቅስቀሳዎቹ በአብዛኛው በመገናኛ ብዙኃን የተደረጉ ሲሆን የምርጫ ዕለት እየተቃረበ ሲመጣ በተለያዩ መንገዶች የምርጫ ቅስቀሳዎች እየተጠናከሩ መጥተዋል ብሏል፡፡
የቡድኑ መሪ የምርጫ ካርድ መውሰድ ከሚገባቸው 99 ነጥብ 5 በመቶ እንዲወስዱ መደረጉንም አድንቀዋል፡፡ ሴቶች 48 በመቶ በመራጭነት 27 ነጥብ 9 በመቶ ደግሞ በተመራጭነት መመዝገባቸው የሚበረታታ ነው ብሎታል፡፡ የሴቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ገልጾ ከዚህ በላይ እንዲጠናከር መስራት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ሚስተር ሂፊኪፑንያ ፑሃምባ እንደሚናገሩት 29 የታዛቢ ቡድኖቹ በመላው አገሪቱ በሚገኙ 356 የምርጫ ጣብያዎች ታዝበዋል፡፡ ከነዚህ መካከልም 64 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ጣቢያዎች በገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ በከተማ ያሉ ጣቢያዎች ናቸው።
ከተጎበኙት የምርጫ ጣቢያዎች መካከል 98ነጥብ 7 የሚሆኑት በእቅዱ መሰረት በሰዓታቸው ከጠዋቱ 12 ሰዓት መከፈታቸውን የገለፀው ቡድኑ ምልክታ ከተካሄደባቸው ውስጥ ጥቂት የምርጫ ጣቢያዎች 30 ደቂቃ የሚያክል ዘግይተው መከፈታቸውን አመልክቷል፡፡
የምርጫ ሂደቱ ቦርዱ ባስቀመጣቸው መመርያዎች መሰረት መፈፀሙም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የህዝብና የአገር ውስጥ፣ እንዲሁም የፓርቲና የዕጩዎች ታዛቢዎችም ምርጫውን መታዘባቸውንም ቡድኑ ጠቅሷል፡፡ የምርጫ ውጤቶቹ በየምርጫው ጣቢያዎች መለጠፋቸውንና ውጤቶቹን የመደመሩ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን እንዳየ ቡድኑ ጠቅሷል።
ድህረ ምርጫው እንደ ቅድመ ምርጫውና የምርጫው ዕለት ሰላማዊ እንዲሆን ሁሉም ወገን ቁርጠኛ መሆን እንዳለበትም ነው የቡድን መሪው የተናገሩት፡፡ ቅሬታ ያለው አካል ቅሬታውን ለማቅረብ ህጋዊ መንገዶችን እንዲከተል ታዛቢ ቡድኑ ጥሪ አቅርቧል።
የቡድኑን ገለልተኝነት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበለት ቡድኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ሆነ ከማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ስራውን ማከናወኑን የቡድኑ መሪ ተናግረዋል፡፡
ቡድኑ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም መላው ህዝቦች በህገ መንግስቱ መሰረት የተሳካ ምርጫ በማካሄዳቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብሏል፡፡
I think this election holds water
ReplyDelete