አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ
በአገራችን እየተገነባ ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት በህዝቦች ተሳትፎ እየጎለበተ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው!!
ኢህአዴግ
መላው ህዝቦችን አስተባብሮ ባደረገው ተጋድሎና በህዝቡ ንቁ ተሳትፎ በአገራችን ስልጣን በአፈ ሙዝ የሚያዝበት ሁኔታ ተዘግቶ በምትኩ
በህዝቦች ይሁንታ ብቻ የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከተዘረጋ እነሆ 24 ዓመታትን አስቆጠርን፡፡ በእነዚህ የትግልና የስኬት
ዓመታት ውስጥም የህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠባቸው አራት ስኬታማ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን አካሂደናል፡፡ ምንም እንኳን ሂደቱ ባይጠናቀቅም አምስተኛውን
አገራዊ ምርጫም የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ባረጋገጠ መልኩ አከናውኗል፡፡
ያካሄድናቸው ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ከፍተኛ የሆነ የህዝብ
ተሳትፎ የታየባቸውና አማራጭ አለን የሚሉ ፓርቲዎችም በንቃት የተሳተፉባቸው ናቸው። በየምርጫው የሚሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥርም
በቀጣይነት እያደገ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የሚከበርበት፣ የዴሞክራሲ
ባህልና ተቋማት የሚያብቡበት፣ ህዝቡ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ የነቃ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን
የሚያረጋግጥበትን ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ተነድፎ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመገባቱና በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነትን በማጎልበት የዳበረ
ዴሞክራሲያዊ የመድብለ- ፓርቲ ስርአት ለመፍጠር ጥረት በመደረጉ የተመዘገበ
ውጤት ነው፡፡
የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ እንዲጠናከር ለማድረግ በተከናወኑ
በርካታ ስራዎች በርካታ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የህገመንግስቱ በርካታ አንቀፆችና ድንጋጌዎች የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጠናከር
ዋስትና የሚሆኑ ናቸው፡፡ የመደራጀት መብት፣ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ የራስን ዕድል በራስ
የመወሰን መብት፣ የህግ የበላይነትና ህዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸውና ሌሎች በህገመንግስታችን የሰፈሩ ድንጋጌዎች በአገራችን
የፖለቲካ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ እንዲታይ ዋስትና የሰጡ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲበረታቱ የሚያደርጉ አመቺ የሕግ ማዕቀፎች
መኖራቸው፤ ህጎቹን ተፈፃሚ የሚያደርጉ የዴሞክራሲ ተቋማት መዋቀራቸውና መንግስት በተለይ በምርጫ ወቅት የፋይናንስ ድጎማ እና ነፃ
የአየር ስዓትና የጋዜጣ ዓምድ ድልድል ማድረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስፋት እንዲሳተፉና ምቹ ሁኔታውን ተጠቅመው እንዲጠናከሩ አስችሏል፡፡
ዘንድሮ ያካሄድነው ጠቅላላ ምርጫ ለዚህ ቁልፍ ማሳያ ተደርጎ
ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ምርጫው በመራጮችም ሆነ በተወዳዳሪዎች ዘንድ በተሳትፎ የደመቀ ነበር፡፡ በዚህ ምርጫ ከ36.8 ሚሊዮን በላይ
ህዝቦች በመራጭነት የተሳተፉበት ሲሆን 58 የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመራጭነት ቀርበው ለፓርላማና ለክልል ምክር ቤቶች ተወዳድረዋል፡፡
በዘንድሮም ምርጫም እንደተስተዋለው በምርጫው አጠቃላይ ሂደት
የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመንግስት በኩል በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእያንዳንዱ
የምርጫ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ የሆኑበት ሁኔታ ከመፈጠሩም በላይ የሚያቀርቡት ሀሳብ ተግባራዊ የሆነበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የምርጫ
ጊዜ ሰሌዳ በታቀደለትና ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ በማድረግና የበጀት ድልድሉም ፓርቲዎች የሰጡትን አስተያየት ባካተተ መልኩ የተወሰነ
ነበር፡፡ የአየር ጊዜና የጋዜጣ አምድ ድልድልም ቢሆን በተመሳሳይ ሂደት የተፈፀመ ነበር፡፡ ፓርቲዎቹ በተመቻቹት የክርክር መድረኮችም
በስፋት ተሳትፈው አማራጮቻቸውን ለህዝብ ለማድረስ የሚያስችል ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በምርጫው አጋማሽ ላይ ፓርቲዎች የምርጫ ሂደቱን ገምግመው ሂደቱ መልካም እንደሆነ
ተቀብለዋል፡፡ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በመቋቋሙ ችግሮች ሲፈጠሩ የሚፈቱበት አግባብ ተዘርግቷል፡፡ እንወዳደርበታለን ባሉት የምርጫ
ክልል ልክም እጩዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1 ሺህ 828 እጩዎችን
አቅርበዋል፡፡ በምርጫው ዕለትም አጠቃላይ ሂደቱን ለመከታተል ተወካዮቻቸውን በታዛቢነት ማስቀመጥ እንዲችሉ አሰራሩ ተዘርግቶ ተግባራዊ
ሆኗል፡፡
በአጠቃላይ አምስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ልክ እንደ ሌሎች ምርጫዎች
ሁሉ በቂ ዝግጅት የተደረገበትና ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የመወዳሪያ አማራጭ የተዘረጋበት ምርጫ ነው፡፡ ይህንንም እውነታ በምርጫው ተሳታፊ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ ምርጫውን የታዘቡት
የህዝብ፣ የሲቪክ ማህበራትና የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢዎች አረጋግጠዋል፡፡ መራጩ ህዝብም ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ
እንደነበር መስክሯል፡፡ የፀጥታ አካላትም እንዳስታወቁት ምርጫው ያለምንም የፀጥታ እንከን ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቋል፡፡
ኢህአዴግም ምርጫው ከሂደቱ እስከ ፍፃሜው ድረስ ነጻ፣ ፍትሐዊ፣
ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና በህዝባችን ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል። የምርጫ ስትራቴጂ
በማዘጋጀት፣ ለአመራሮቹ፣ ለአባላቱና ደጋፊዎቹ በስትራቴጂውና በፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ላይ በቂ ስልጠና በመስጠትና
አመራሮቹ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ የምርጫ ስነ ምግባር ደንቡን በተሟላ ሁኔታ ተገንዝበው በኃላፊነት መንፈስና በከፍተኛ ዲሲፕልን እንዲንቀሳቀሱ
አድርጓል። የዕጩዎች መመዘኛ መስፈርት በማዘጋጀትም ህዝቡን በተገቢው
ሁኔታ ለማገልገልና ኢህአዴግ የተያያዘው የህዳሴ ጉዞ ለማስፈፀም ብቃትና
ቁርጠኝነት ያላቸው እጩዎችን አዘጋጅቶ በማቅረብ በህዝብ እንዲተቹ አድርጓል፡፡
የዘንድሮው አጠቃላይ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅና የአገራችን
የዴሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብት የበኩላቸውን ጥረት ላደረጉና በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች
ዕውቅና መስጠቱ በቀጣይ ለምናደርገው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አጋዥ መሆኑ አያጠራጥርም። የምንገነባው ዴሞክራሲ በቀጣይም አስተማማኝ
ደረጃ ላይ ማድረስ ይቻል ዘንድም ኢህአዴግ ሕጋዊና ሰላማዊውን መንገድ ተከትለው ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት
የጀመረው እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የዘንድሮውን ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ
እንደሆነ መስክረዋል፡፡ አንዳንድ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ግን በአገራችን በተካሄዱ ሁሉም ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ ነው የሚሉትን የምርጫ
ሂደት ውጤቱ ሲገለፅና የህዝቡ ይሁንታ አለማግኘታቸውን ሲነገራቸው የህዝቡን ይሁንታ ተቀብለው ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ የምርጫ ክንውኑን
ሲያጠለሹ መስማት አዲስ አይደለም። ይህን መሰሉ በውጤት ማጣት ላይ የተመሰረተ ማጥላላት ሀገራችን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመራት
ከጀመረች ወዲህ በተካሄዱ አራት አጠቃላይ ምርጫዎች የሽንፈት ማጀቢያና ማድመቂያ ሆኖ ተስተውሏል። ህዝብ ይሁንታውን ሲሰጥም ሆነ
ሲነፍግ ትክክል እንደሆነ የሚያምነው ድርጅታችን ኢህአዴግ ግን በዘንድሮው ህዝቡ የሰጠውን ድምፅም እንደተለመደው አክብሮ ይቀበላል፡፡
ሁሉም የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከተለመደው የተሳሳተ አስተሳሰብ በመውጣት ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱና ለህዝቦች ሉዓላዊነትና
ተጠቃሚነት መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል።ከዚህ በተቃራኒው መንገድ መሄድ ግን ከህዝቡ ፍላጎትና ጥቅም በተፃራሪ
ጎን መሰለፍ ስለመሆኑ ለመረዳት ተጨማሪ ምርምር አያስፈልገውም።
ህዝባችን ልማትና ዴሞክራሲን በማስቀጠል በዕለት ተዕለት ህይወቱ
ላይ የተሻለ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መንግስት ለማቋቋም የምርጫን አስፈላጊነት በሚገባ የተረዳ ህዝብ ነው፡፡ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ
ቀጣይነት እንዲረጋገጥለትም ይፈልጋል፡፡ በመሆኑም ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ የተካሄደው አጠቃላይ ምርጫም የህዝባችን ህገመንግስታዊ የስልጣን
ባለቤትነት መብት የሚረጋገጥበት፤ በልማትና እድገት እየገሰገሰች ያለችው ሀገራችን የህዝቦቿ የዕድገትና የብልፅግና ራዕይ የሚሳካበት ይሆን ዘንድ በምርጫው የተገኘውን
ስኬት ወደ ላቀ ምዕራፍ የማሸጋገር ኃላፊነት የሁሉም ሊሆን ይገባል፡፡ አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ እየገነባነው ያለው የዴሞክራሲ ስርዓት
እያበበ እንደሚገኝ ከማረጋገጡም በላይ የሀገራችን ቀጣይ ጉዞ እንዴት መሆን እንዳለበትም ግልፅ መልእክት አስተላልፏል። ዴሞክራሲያችን
የጎለበተ፣ ሰላማችን የተረጋገጠና ልማታችን ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ያገኘነውን ትሩፋቶች እናስጠብቅ፡፡
True True
ReplyDelete