EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 22 May 2015

ሴቶች ለምን ኢህአዴግን ምርጫቸው ያደርጉታል?

በአሜሳይ ከነዓን
እኔ ወጣት ሴት ነኝ። እድሜዬ ፈቅዶልኝ በአገራችን ያለፉ ስርዓቶችን አፈፃፀም በተግባር ባላይም ህያው ምስክር ከሆኑ ወላጆቼ ጨምሮ ከታላላቅ ሰዎች የምሰማው ሴቶች በአገራችን ያለፉበት ውጣ ውረድ ከወንዶችም የከፋ መሆኑን ነው። በርግጥ የአገራችን ብቻ ሳይሆኑ የሌሎች አገራት ሴቶችም ነፃነታቸውን ያገኙበት ዘመን ቢለያይም በርካታ ዓመታትን በጭቆና ቀንበር ውስጥ ተጠምደው ይማቅቁ እንደነበር ነው ከተለያዩ መዛግብት መረዳት የቻልኩት።
አገራችንን ጨምሮ በተለያዩ የአለማችን ክፍል የሚገኙ ሴቶች በፆታቸው ምክንያት ብቻ በርካታ ፈተናዎችን እንዲጋፈጡ ተደርገዋል፡፡ ሴቶች በኢኮኖሚ በወንዶች ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ፣ በፖለቲካም የፈለጉትን አስተዳደር እንዳይመርጡ እንዲሁም በማህበራዊ መስክ ከወንድ አቻዎቻቸው ጋር እኩል የትምህርትና የጤና አገልግሎት እንዳያገኙ ታቅበው ነበር። ይህ አለም አቀፋዊ ይዘት ያለው የሴቶች ጭቆና በአገራችንም የባሰ መልክ ይዞ ዘመናት ተሻግሯል፡፡ በዚህ የተወሳሰበ የጭቆና ጊዜም ቢሆን ሁሌም የሚታወስ ታሪክ ሰርተው ያለፉ ሴቶች እንዳሉ ሁላችንም የማንዘነጋው ሆኖ አብዛኛዎቹ ሴቶች በተደራራቢ የጭቆና ማዕበል ውስጥ አልፈዋል፡፡   
የአገራችን መንግስታት ለሴቶች የተመቸ የፖሊሲ ማዕቀፍ ከማዘጋጀት ይልቅ የሴት ልጅን እንቅስቃሴ የሚገድብ፣ ነፃነቷን የሚገፋና ወደ ኋላ የሚጎትት አካሄድ በመከተልና በጎታች አባባሎች የተደገፈ ባህላዊ ጫና ጭምር እንዲደርስባቸው በማድረግ ሴት ልጅ ህይወቷን ማጀት ውስጥ እንድትገፋና የወንድ ልጅ ግዞተኛ ሆና እንድትኖር አድርገዋል። የኋላ ኋላ ግን የአገራችን ሴቶች በፆታ እኩልነት ከሚያምኑ ወንዶች ጋር ተሰልፈው ባደረጉት ትግልና በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ይህን አስከፊ ኢ-ፍትሃዊ ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ህጋዊ መሰረት እንዳይኖረው አድርገዋል።
ዛሬ በርካታ እናቶችን ሳይ የሚታወሰኝ ያ የአብዛኞቻችን እናቶች ቀና ብለው ስለራሳቸው መናገር አልያም ከወንድ እኩል መሆን ባህልን እንደመዳፈር፣ አደባባይ መውጣትም ከወግ የማፈንገጥ ያህል ተደርጎ እንዳይወሰድባቸው በመፍራት የጭቆና ቀንበር ተሸክመው የኖሩበት ዘመን ነው። የዛሬ ዘመን ወጣት ሴቶች ያን ዘመን ስናስበው መቆጨታችን አይቀሬ ነው። ያ ዘመን ተብትቦ በጓዳ ያስቀራቸው እናቶቻችን ምናልባትም ዛሬ በምሁርነታቸው፣ በአገር መሪነታቸው፣ በተመራማሪነታቸው፣ ወዘተ… በፈፀሙት ገድል ልንዘክራቸው በቻልን ነበር።
ዛሬ ግን በአገራችን የሴቶች ሁለንተናዊ መብት ማክበር ህገ መንግስታዊ እውቅናና ዋስትና አግኝቷል፡፡ ህጎች በሙሉ የሴቶችን መብት በሚያከብር መልኩ ተቀርፀዋል፡፡ ሴቶችን የማበረታታት ጉዳይ የተቋማት ቀዳሚና አንገብጋቢ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል፡፡ ዛሬ ሴቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ መለስ ተሳታፊም ተጠቃሚም መሆን ችለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ታዲያ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት በአገራችን የመንግስትን ስልጣን እየመራ ባለው ኢህአዴግ ቁርጠኛ አቋም የመጣ ለውጥ ነው፡፡
ሴቶች ኢህአዴግን ምርጫቸው ያደረጉት ከምንም ተነስተው አይደለም። እኔን ጨምሮ ለበርካታ ሴቶች ኢህአዴግ ምርጫችን የሆነው የፆታ እኩልነት ሰብዓዊ መብታችንን ለማስከበር ያደረግነውን ትግል መርቶ ለፍሬ ስላበቃልን ነው። የሴቶች እኩልነት ህገ መንግስታዊ ምላሽ ከተሰጠ ወዲህ ባሉት አመታት እንደ ወንዶች ሁሉ በልማቱ፣ በሰላሙና በዴሞክራሲው ውስጥ እኩል የምንሳተፍበትና እኩል የምንጠቀምበትን መብታችንን ያረጋገጠልን ስርዓት ስለሆነ ነው። በዚህ ስርዓት አሁንም የሚገባንን ያህል ተጠቃሚ ሆነን ከድህነትና ኋላ ቀርነት ባንላቀቅም እንደ አገር በሚደረገው የፀረ ድህነት ትግል እኩል ተሳትፈን ከምንጠብቀው አገራዊ ህዳሴ ተጠቃሚ እንደምንሆን ስለምናምንም ነው ኢሕአዴግን ምርጫችን ያደረግንው።
ወጣት ሴቶችና በእድሜ የገፉ እናቶች ዛሬ አደባባይ ወጥተው "ኢህአዴግ ማለት ጓዳችን ነው" ሲሉ የሚደመጡት ወንድሞቻቸውንና ልጆቻቸውን ከጉያቸው እየነጠቀ ለሞት ሲዳርግ የነበረውን ስርዓት በማስወገድ ሰላማቸውን ያረጋገጠላቸው ኢሕአዴግ ስለሆነ ነው፡፡ እናት “የዛሬን ማርልን ሁለተኛ አልወልድም” ያለችበትን ያን ግፈኛ ስርዓት አስወግዶ ሁለንተናዊ መብቷን ያከበረላት ኢሕአዴግ እንደሆነ ስለምታውቅ ነው በነቂስ ወጥታ “ምርጫዬ ኢሕአዴግ ነው ስትል ሰልፉን ያደመቀችው። ወገብ በሚያጎብጡ ስራዎች ተጠምዳ ትምህርት የተነፈገችውን ሴት ወጣት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረባትን በደል የሚያካክስ የድጋፍ እርምጃ የቸራት ስርዓት ኢሕአዴግ በመሆኑ ነው ዛሬ አደባባይ ወጥታ የምትመሰክርለት። በመሆኑም ሴቷ በአመራርነት ዘመኑ በወሰዳቸው ቁርጠኛ አቋሞች ኢህአዴግን ምርጫዋ ማድረጓ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሴቶች የአገራችንን ህዝቦች እኩሌታ የያዙ ናቸው። ሴት ደግሞ የቤተሰብ መሰረት ነች። የቤተሰብ መሰረት የሆነችውን ሴት መብቷን አስከብሮ በተገቢው መንገድ ደግፎ ለአገር ልማት የበኩሏን አስተዋፅኦ እንድታደርግ ማስቻል ለእርሷ የእኩልነት ጥያቄ ፍትሃዊ ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይሆን ለአገር እድገትም አስተማማኝ ሃይል ከፊት ማሰለፍ ነው። ኢህአዴግ የዛሬንና የነገ የሴቶችን ራዕይ ማሳካት የሚችል በበርካታ መመዘኛ ሴቶች ምርጫቸው ያደረጉት ብቸኛ ፓርቲ ነው።

No comments:

Post a Comment