EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 18 May 2015

ለሴቶችና ለወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚተጋ ድርጀት- ኢህአዴግ




የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
የሀገራችን ሴቶችና ወጣቶች ማህበራዊ መብታቸው ተጥሶ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ተገፍፎ እንዲሁም ፖለቲካዊ መብታቸውን ተነፍገው ለዘመናት ኖረዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሴቶችም ሆኑ ወጣቶች ለሀገራቸው ማበርከት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሳያበረክቱ ኖረዋል፡፡ እንደሚታወቀው ሴቶች ባለፉት ስርዓቶች በነበረው የተዛባ የስነ ፆታ አመለካከት ሳቢያ ድርብ ጭቆና ይደርስባቸው ነበር፡፡ ከወንዶች እኩል ተደርገው ስለማይታዩ የሃብት ባለቤትነት መብት አልነበራቸውም፡፡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸው ነባራዊ ሁኔታም አልነበረም፡፡ ወጣቶችም ቢሆኑ በወጣትነት ዘመናቸው ማግኘት ያለባቸውን ሁሉ ተነፍገው ቆይተዋል፡፡ የትምህርት አቅርቦት ያለመስፋፋቱና ባሉት ጥቂት ትምህርት ቤቶችም የአብዛኛው ህዝብ ልጆች የትምህርት ተቋዳሽ እንዳልነበሩ ይታወቃል፡፡ ይልቁንም የወጣቶች የወቅቱ ተልዕኮ ወደ ጦርነት መማገድ ስለነበር በሀገር ግንባታ ሊውል ይችል የነበረ ኃይል እንዲመክን ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ሴቶችና ወጣቶች ከ1983 ዓ.ም በፊት በጨለማ ውስጥ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡

የሀገራችን ሴቶችና ወጣቶች ለእነዚህ ስርዓቶች ሳይንበረከኩ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ አሁን መላው የሀገራችን ህዝቦች ለተጎናፀፉት የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ስርዓት በቅተዋል፡፡ ኢህአዴግ  ሴቶችና ወጣቶች ለልማት ለዴሞክራሲና ለሰላም መስፈን የሚኖራቸው አስተዋፅኦ ቁልፍ አንደሆነ ያምናል፡፡ የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ከሆኑት ሴቶችና ከነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶች ውጭ ልማትም ሆነ ዴሞክራሲ ሊረጋገጥ እንደማይችልም በፅናት ይረዳል፡፡ በመሆኑም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሴቶችና የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የተረጋገጠበት ስርዓት እንዲዘረጋ የመሪነት ሚናውን ተወጥቷል፡፡


በአዲስቷ ኢትዮጵያ የሴቶችና የወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቷል፡፡ ህገ መንግስታችን የወጣቶች ደህንነት መጠበቅ እንዳለበት እንዲሁም የሴቶችን እኩልነት፣ የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚነትና የንብረት ባለቤትነት መብት መከበር እንደሚገባው ደንግጓል፡፡ ሴቶችና ወጣቶች ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ተደራጅተው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡ በመሆኑም ህገ መንግስታችን ሴቶችን የሚጨቁኑ ህጎችና ልማዳዊ አሰራሮችን በሙሉ ውድቅ  በማድረግ የኢ- ፍትሃዊ አሰራር ምንጮችን ያደረቀ ነው። ባለፉት 24 ዓመታት የተከናወኑ የልማት ተግባራትም ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎቹ በተጨባጭ የተተገበሩበት ነው፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ብቻ ሳይወሰን የልማትና የለውጥ ፓኬጆችን ቀርፆ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎቹ መሬት እንዲነኩ ተንቀሳቅሷል፡፡
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የሚገኝ ድርጅት - ኢህአዴግ

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
ኢህአዴግ ባለፉት 24 ዓመታት ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ በሕብረተሰቡ ዘንድ ለዘመናት ፀንቶ የቆየውን የተዛባ የስነ-ፆታ አመለካከትና ከዚህ የመነጨውን ኢ-ፍትሃዊ የሃብት፣ የስልጣንና የስራ ክፍፍል በማስወገድ የሴቶችን እኩልነት በማስፈን ላይ ይገኛል፡፡ ሴቶች በተደራጀ መልኩ የሚታገሉበትን አግባብ ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 6.3 ሚሊዮን ሴቶች በመደበኛ አደረጃጀቶች እንዲሁም ከ12 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በልማት ቡድኖች ተደራጅተዋል፡፡ የሴቶቹ አደረጃጀቶች ነፃነት ያላቸው፣ የዴሞክራሲያዊና ልማታዊ የአስተሳሰብ ልእልና ባለቤት የሆኑ የበሳል አመራር መፍለቂያ በመሆን በሀገራችን የልማት ሠራዊት ግንባታ ውስጥ የህዝብ ክንፉ ቀዳሚ ኃይል ሆነዋል፡፡
የሴቶች የመሪነትና ውሳኔ ሰጪነት አቅማቸው በቀጣይነት መጠናከር እንደሚገባው በማመን ኢህአዴግ ለተፈፃሚነቱ ጠንክሮ በመስራቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እየታየበት ይገኛል። የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ በያዝነው አመት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለውድድር ካቀረባቸው እጩዎች ውስጥ ለፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 በመቶ፣ ለክልል ምክር ቤቶች ደግሞ 48 በመቶ የሚሆኑት ሴት እጩዎች እንዲሆኑ አድርጓል።
የሴቶችን የልማትና የለውጥ ፓኬጅ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ የቻለው ኢህአዴግ በሴቶች ላይ ተጭነው የነበሩትን አድሏዊ ሕጎችና አሰራሮችን በማስወገድ ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸውን አረጋግጧል፡፡ የገጠር ሴቶች የመሬት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ በማድረግ በግብርና ዘርፍ ያላቸው የሀብት ባለቤት ያለመሆንና በወንዶች ላይ የኢኮኖሚ ጥገኝነት ችግር በዘላቂነት የሚፈታበትን ስልት ቀይሶ በመተግበር ላይ ነው፡፡ የገጠር ሴቶች በግብርና ብቻ ሳይሆን ከግብርና ውጭ ባሉ ተያያዥ የስራ መስኮች ተደራጅተው ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው፡፡
የከተማ ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ በጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ዘርፍ ከተፈጠረው የስራ ዕድል የሴቶች ድርሻ 41.47 በመቶ ያክል ነው፡፡ በመንግስት ከተመቻቸው የብድር አገልግሎት ውስጥም የ40.8 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ በተመሳሳይ ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከተሰጠው ስልጠናና ከገበያ ትስስር አንፃር የሴቶች ድርሻ በቅደም ተከተሉ 39.7 በመቶና 36.1 በመቶ ደርሷል፡፡
ያለፉት ስርዓቶች ሴቶች ላይ ያደርሱ በነበሩት አድሎና ጭቆና ሳቢያ እኩልነት ተነፍጓቸው የቆዩ ሴቶች እኩል ተወዳዳሪና ተጠቃሚ ለማድረግ የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው በፅናት የሚገነዘበው ኢህአዴግ በስራ ቅጥርና ደረጃ ዕድገት፣ በቤቶች ልማት፤ በጥቃቅንና አነስተኛ በመሳሰሉት ዘርፎች የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ችሏል፡፡ በቤቶች ልማት ፕሮግራምም የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የ30 በመቶ ቅድሚያ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በትምህርት ዘርፉም የሴቶች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የተደረገው ጥረት ውጤት ታይቶበታል፡፡ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ በአንደኛ ደረጃ ከሞላ ጎደል ከወንዶች ጋር አንድ ለአንድ የደረሰ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ መጀመሪያ ሳይክል 47.3 በመቶና በመሰናዶ 44 በመቶ ደርሷል፡፡ በቴክኒክና ሙያና በቅድመ ምረቃ እንደየቅደም ተከተሉ የ51.25 በመቶና የ32 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡ በዚህ አኩሪ ተግባር በትምህርት ዘርፍ የጾታ ልዩነት እየጠበበ የመጣ ሲሆን በተለይ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ የታየው ውጤት የምዕተ አመቱን የልማት ግብ ለማሳካት ያስቻለ ነው፡፡ በከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤትና በትምህር ቤቶቹ ቆይታቸው ወቅት ሴቶች የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ለዘመናት ተጭኖባቸው ከኖረው ማህበራዊና ባህላዊ ጫና የሚላቀቁበትን ስልት ነድፎ እየተንቀሳቀሰም ነው፡፡
ሴቶች ተልዕኳቸውን በመወጣት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲያበለፅጉ ጤናቸው መጠበቅ እንደሚገባው በፅናት የሚረዳው ኢህአዴግ የጤናው ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ በተደረገው ርብርብ 69 በመቶ ለመቀነስ ተችሏል፡፡ የቅድመ ወሊድ አገልግሎት ተጠቃሚ እናቶች ምጣኔ 98 በመቶ የደረሰ ሲሆን በሰለጠነ ባለሙያ የወለዱ ሴቶች ምጣኔን 41 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ መከላከልን መሰረት ያደረገው የጤና ፖሊሲያችን ከምንም በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን የጤና ኤክስቴንሽን መርኃ ግብር ዋና ማዕከልም ሴቶች ናቸው፡፡
በሁሉም የልማት ዘርፎች የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመንግስት አስፈፃሚ መ/ቤቶች የሴቶችን ጉዳይ በየእቅዶቻቸው እንዲያካትቱ ብሎም ተቋማዊ በማድረግ በባለቤትነት ይዘው እንዲፈጽሙት እየተደረገ ነው፡፡ 

የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የሚገኝ ድርጅት - ኢህአዴግ
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
ወጣቶች በሀገራቸው ጉዳይ ባይተዋር ከሆኑበትና በግዳጅ ጦርነት ከሚማገዱበት ስርዓት ተላቀው ቁልፍ የልማት ኃይል ወደሆኑበት መድረክ የተሸጋገሩት በኢህአዴግ መሪነት በተገነባው ስርዓት ነው፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ወጣቶች ወደ ጦርነት ሳይሆን ወደ እውቀትና ክህሎት ገበያ የሚዘምቱባት ሆናለች፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙባት፣ በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት ሀገራችውንና ራሳቸውን የሚጠቅሙባት ሀገር ነች - አዲሲቷ ኢትዮጵያ፡፡ ኢህአዴግ ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች እንዲደራጁ በማድረግና የብድር፤ የመስሪያ ቦታ፣ የገበያ ትስስርና የስልጠና ሁለገብ ድጋፍ በመስጠት ከልማቱ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነታቸውን እንዲቀርፉ ለማድረግ ሰርቷል፡፡ በውጤቱም 4.89 ሚሊዮን ወጣቶች በጥቃቅንና አነስተኛ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ተደራጅተው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ኢህአዴግ የወጣቶችን ማህበራዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥም ረጅም ርቀት ተጉዟል፡፡ ከ500 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ወደ ሦስት ሺህ የሚጠጉ የወጣቶች የስብእና ልማት ማእከላትን በመገንባት ወጣቶች የቤተ-መጻህፍት፣ የመረጃ ቴክኖሎጅ፣ የመዝናኛ፣ የስነ ተዋልዶ ጤና፣ የኤች ኣይ ቪ የምክር የስልጠናና የመሳሰሉ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በመደረግ ላይ ነው፡፡ ወጣቶች በሀገሪቱ ውስጥ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የልማት እንቅስቃሴ፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ እምቅ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን ለማህበረሰቡ ጠቃሚ በሆኑ መስኮች በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በመስጠት የራሳቸውንና የሌላውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት እንዲደግፉ ተደርጓል፡፡ በዚህም ሥራ የወጣቶችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ በ2002 ዓ.ም ከነበረበት 3 ሚሊዮን ባለፈው አመት ወደ 12.2 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል፡፡
ወጣቶች በሀገሪቱ የልማት፣ የዴሞክራሲ ስርዓትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሂደት ውስጥ የመሪነት ሚና ለመጫዎት ተደራጅተው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሁሉም መስክ የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ወጣቶች ሀገር ገንቢዎችና የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢዎች እንደመሆናቸው መጠን ፖለቲካዊ ብቃታቸውና ተሳትፏቸው ከዚህም በላይ ማደግ እንደሚገባው ኢህአዴግ ያምናል፡፡ ለዚህም ስኬታማነት ከመላ የሀገራችን ወጣቶች ጋር በመሆን ይረባረባል።

የሴቶችንና የወጣቶችን ተጠቃሚነት በዘላቂነት የሚያረጋግጥ ዋስትና ያለው ብቸኛ ድርጅት - ኢህአዴግ

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፤
ሴቶችና ወጣቶች ከላይ የዘረዘርናቸውን ትሩፋቶች እንዲጎናፀፉ ያደረጋቸው በተሳትፏቸው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ትክክለኛ ፖሊሲና የልማት ፓኬጆች መቀረፃቸውና ቁርጠኛ አመራር መሰጠቱ ነው፡፡ ሆኖም የሴቶችንና የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ አሁንም ሰፋፊ ትግሎችና ስራዎች ከፊቱ እንዳሉበት ኢህአዴግ ይረዳል፡፡ የወጣቶችን ስራ አጥነት ከመቅረፍ አኳያ በጥቃቅንና አነስተኛ የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ የማስፋትና ተጨማሪ የስራ እድሎችን የመፍጠር ስራዎች እንደሚጠበቁበት ኢህአዴግ ይገነዘባል። ሴቶች ካሉባቸው ስር የሰደዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ከማላቀቅ አንፃርም ከፊታችን ሰፊ ስራዎች ይጠብቁናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢህአዴግ እስካሁን ካደረገው ትግልና ካስመዘገባቸው ድሎች ባልተናነሰ ወደፊትም ሴቶችንና ወጣቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡
ልክ እንደ ትናንቱ ነገም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ኢህአዴግ ቁርጠኛ ድርጅት ሲሆን በተግባርም ችግሮቹን ለመፍታት እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ በቀጣይም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይም ከሴቶችና ከወጣቶች ጋር በመሆን መጪውን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ይበልጥ ይተጋል፡፡ በዚህ የትግልና የስኬት ጉዞ ውስጥ የሀገራችን ወጣቶችና ሴቶች ልክ እንደ ሁልጊዜው ከኢህአዴግ ጎን እንደሚሰለፉ ሙሉ እምነት አለው፡፡

በአንፃሩ አንዳንድ ተቃዋሚዎች አሁን ያለውን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ወደኋላ ለመመለስ ወጣቶችን ለእኩይ ተግባራቸው መፈፀሚያ ለማድረግ መሞከራቸው ለወጣቱ ክብር የሌላቸው መሆኑን ያሳያል፡፡ የሀገራችን ሴቶች ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ እውን መሆን የከፈሉትን መስዋዕትነት በሚገባ የማያከብሩት የድሮ ስርዓት ናፋቂ ተቃዋሚዎች ሴቶች የተጎናፀፏቸውን መብቶች ለማሳጣት ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላሉ፡፡ ሴቶችና ወጣቶች የእነዚህን ወገኖች ድብቅ አላማ በመገንዘብና የተጎናፀፉትን ጥቅም ላለማጣት ፀረ ልማት እንቅስቃሴዎችን እየታገሏቸውና እያወገዟቸው መሆኑን ኢህአዴግ ይገነዘባል። በቀጣይም የሀገራችን ሴቶችና ወጣቶች የጀመሩትን የሀገር ግንባታ ትግል አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ያለውን እምነት ይገልፃል፡፡

በኢህአዴግ አማራጭ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል የሴቶችና ወጣቶችን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዋስትና ያለው ብቸኛ ድርጅት ኢህአዴግ በመሆኑ ኢህአዴግን ይምረጡ፡፡

ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተው ታታሪዋ ንብ ነች፡፡

No comments:

Post a Comment