EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 17 May 2015

የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲያችን ለፈጣን ልማትና አስተማማኝ ሰላማችን

ኢህአዴግ የተከተለው ትክክለኛ የውጭ ጉዳይና አገራዊ የደህንነት ፖሊሲ በአገራችን ለተመዘገበው ፈጣን ልማትና አስተማማኝ ሰላም ጉልህ ድርሻ ተወጥቷል!!
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን ከመሆኑ በፊት የነበሩት ስርዓቶች ሲከተሉት የነበረው ፖሊሲ የአገራችን ችግሮች ምንጫቸው ውጫዊ እንደሆነ አድርጎ የሚመለከት ነበር፡፡  በአገራችንና በጎረቤት ህዝቦችና መንግስታት መካከል የነበረው ግንኙነት የሌሎች አገራትን ሉአላዊነት ያላከበረ ስለነበር ለረጅም ዓመታት በመተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሳንመሰርት ቆይተናል። የተመሰረተውም ቢሆን ለብሄራዊ ጥቅማችን ቅድሚያ የማይሰጥና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የማይመራ ነበር፡፡
ኢሕአዴግ ያለፉት ስርዓቶች ይከተሉት የነበረውን የጦረኝነት ፖሊሲና አገራችን ለሌሎች ስጋት ሆና እንድትኖር ያደረገውን የተሳሳተ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ ቀይሮ ትክክለኛ የውጭ ግንኙነትና አገራዊ የደህንነት ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ በማድረጉ ስኬቶች ተመዝግበውበታል፡፡ የተከተልነው ፖሊሲ የአገራችን ዋነኛው የተጋላጭነት ችግር ድህነት፣ ኋላቀርነትና የዴሞክራሲ እጦት እንጅ የውጭ ችግር አለመሆኑን በግልፅ በማስቀመጥ መፍትሄውም እነዚህን ችግሮች መፍታትን ማእከል ያደረገ እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነትም በጋራ ተጠቃሚነት፤ የሀገራቱን መንግስታት ሉአላዊነትና እኩልነት በማክበርና በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ባለመግባት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ይህንኑ መነሻ በማድረግ ባለፉት 24 አመታት ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ለማስፈን ባደረግነው ጥረትና ባስመዘገብነው አንፀባራቂ ድል የአገራችን ተጋላጭነታችን እየቀነሰ መጥቷል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
በአለም ደረጃ አንገታችን አስደፍቶን የቆየው ድህነትና ኋላቀርነት ላይ እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረጋችን ድህነትን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ እንደምንችል ያመላከቱ ስኬቶችን ያስመዘገበን ሲሆን በፈጣንና ተከታታይ እድገቷ፣ በሰላም ደሴትነቷ፣ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻነቷ የምትታወቅ አገር ገንብተናል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ተጥሎለት በማደግ ላይ ነው፡፡ ከአካባቢው አገሮች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ለማደግ የሚያስችል እቅጣጫ በመከተላችን የአገራችንን ልማት ጎረቤቶቻችን በበጎ እንዲመለከቱት ያስቻለ ነው፡፡
ጎረቤት አገራት በአገራችን ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ትተው በሰላምና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፍጠር የጀመሩት በሀገራችን የተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ እድገት እነሱንም ተጠቃሚ በማድረጉ ነው፡፡ በመሰረተ ልማት ለመተሳሰር የወሰኑት ኢሕአዴግ ለቀጣናው አገሮችና ህዝቦች የጋራ እድገትና ብልፅግና ያለውን የማይናወጥ ህዝባዊ አቋም ስለተረዱ ነው። ይህ ትብብራችንና አብሮ የማደግ አቅጣጫችን ከጎረቤት አገራት ጋር በሚያዋስኑን አካባቢዎች ሰላም እንዲኖር አስችሎናል፡፡
የውጭ ግንኙነትና የደህንነት ፖሊሲያችን ስኬት ሌላው መገለጫ በጠንካራ ህዝባዊነት፣ ዲሲፕሊንና የውጊያ ብቃት የተገነባው ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊታችን ነው። ሰራዊታችን የአገራችንን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከየትኛውም አደጋ በመጠበቅ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት ህዝባችንንና አገራችንን ከጥቃት የታደገ ነው፡፡ ዛሬ አገራችን ዜጎቿ በሰላም ወጥተው በሰላም ስለመግባታቸው የማይጨነቁባት ይልቁንም በየእለቱ በእድገት ስለመለወጣቸው የሚያስቡባት የሆነችው ሰራዊታችን ከመላ ህዝባችን ጋር በመቀናጀት አስተማማኝ ሰላም በማረጋገጡ ነው። ሰራዊታችን የአገራችን ሉአላዊነት ከማስከበር አልፎ በአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር አስተዋፆ በማድረግ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆኗል፡፡ አገራችን የሰላም ደሴት ተብላ የመጠራቷም ምስጢር አገራዊ ስኬታችን ብቻ ሳይሆን አካባቢያዊ ሰላም እንዲፈጠር ግምባር ቀደም ሆነን በመንቀሳቀሳችን የተገኘ ነው፡፡
ሰራዊታችን በህዝባዊና በዴሞክራሲያዊ አመለካከቱ የተቃኘ፣ ቆራጥና ተዋጊ በመሆኑ ሀገራዊ ደህንነታችንን ከማስጠበቅ አልፎ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የአገራችን ሚና እንዲጎላና የዲፕሎማሲ ድል እንድንጎናፀፍም አስችሎናል። ከሩዋንዳ ጀምሮ በላይቤሪያና ሴራሊዮን እንዲሁም አሁን በሱዳንና በሶማሊያየተሳተፍንባቸው ያሉ የሰላም ማስከበርና ማረጋጋት ስራዎች በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲያችን ስኬታማ የሆንባቸው ናቸው፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
ኢሕአዴግ አክራሪነትና አሸባሪነት የልማታችንና የሰላማችን ጠንቅ መሆናቸውን በመገንዘብ ከመላ ህዝባችን ጋር በመሆን በጽናት እየታገለ ይገኛል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት ትግሉን ለማጠናከር የፀረ ሽብር ህግ በማውጣት፣ የዜጎቻችን ደህንነት በማስጠበቅና ለሽብር ሀይሎች ፈፅሞ የማይመች ሁኔታ በመፍጠር የዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር ትግላችንን አጠናክረን ቀጥለናል። ህዝባዊ የጸጥታና የአገር ደህንነት ሃይላችን ከመላ ህዝባችን ጋር በመሆን በአገራችን የተቃጡ የሽብር ጥቃቶችን አክሽፈዋል፡፡
ኢሕአዴግ እንደሌሎቹ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቶች ሁሉ በውጭ ግንኙነትና የደህንነት ማረጋገጥ መስክም ገና ያልተሻገርናቸው ችግሮች እንዳሉ ይረዳል፡፡ ያልተፈቱ ችግሮችን ከመላ ህዝባችን ጋር በመሆን ለመፍታት እየተረባረበም ይገኛል፡፡
አሁንም የአገራችን ተጋላጭነት ምንጭ የሆነው ድህነትን ሙሉ በሙሉ ያልተወገደ በመሆኑ ልማታችንን ለማፋጠን አትኩረን እየሰራን ሲሆን ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አበክረን እንገነዘባለን፡፡ ከዲፕሎማሲ ስራችን ጋር ተያይዞ የሚታዩ የማስፈጸም አቅም ችግሮችን ለመፍታት ለአቅም ግንባታ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው፡፡ አሁንም የአገራችን ስጋት ሆነው ያሉትን አክራሪነትንና አሸባሪነትን ለመታገል የህዝብ ተሳትፎን በማጠናከር ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ሲሆን የፀረ አክራሪነትና የፀረ ሽብርተኝነት ትግላችን ይበልጥ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
ሁሉንም ነገር በዜሮ ማጣፋት ስራቸው የሆነው የአገራችን ተቃዋሚዎች ግን ይህን ከኢትዮጵያ ህዝብ አልፎ የውጭ አገራትም በአደባባይ የመሰከሩለትን ስኬታችንን በማጥላላት ተጠምደዋል፡፡ በአንፃሩ እነሱ እንከተለዋለን የሚሉት ፖሊሲ የአገራችን ስጋት ውጫዊ አድርጎ የሚመለከት ባለፉት ስርአቶች ተሞክሮ ውጤት ያላስገኘው አቅጣጫ ነው፡፡ አክራሪነትና በአሸባሪነት ትግል ላይ ቁርጠኛ አቋም መያዝ ሲሳናቸው ይታያሉ፡፡ ይብሱኑም አንዳንዶቹ አክራሪነትን በመምራትና በማስተባበር ሲሳተፉ ተስተውለዋል።
ኢህአዴግ ምንጊዜም የሚከተላቸው ፖሊሲዎች የአገርንና የህዝቦችን ጥቅም የሚያስከብሩመሆናቸውና የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲያችንም ይህንኑ አላማ የያዘ በመሆኑ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው፡፡ ለልማታችንና ለሰላማችን ሁነኛ አስተዋፆ እያበረከተ ያለውን ከአገራት ጋር ያለንን መልካም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ደፊትም በማጠናከር ለእመርታዊ ለውጥ እንደምንተጋ ኢሕአዴግ ዳግሞ ያረጋግጣል፡፡
ኢህአዴግን መምረጥ ፈጣኑንና ቀጣይነት ያለው ልማት፣ አስተማማኝ ሰላምና ዋስትና ያለውን ዴሞክራሲ ማስቀጠል ነው፡፡
ለአገራዊና የህዝቦች ጥቅም ቅድሚያ ሰጥቶ የሚተጋውን ኢህአዴግ ይምረጡ!!

ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተው ታታሪዋ ንብ ነች!!

No comments:

Post a Comment