EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 29 April 2015

የሃይል ልማታችን ለዘላቂ ዕድገትና ለተሻለ ህይወት!


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ የሚዘልቅ ኢኮኖሚ  ለመገንባት፣ የዜጎችን ህይወት ለመቀየርና የአኗኗር ዘይቤአቸውን ለማዘመን፣ በዓለ ገበያ ተዳዳሪ ምርት ለማቅረብና ዘላቂ የኢንዱስሪ ዕገት ለማረጋጥ ያለው ድርሻ የላቀ ነው።  ሃይል በየትኛውም ደረጃና ሁኔታ ለሚገኙ ሀገሮችና ህዝቦች ሁሉ አስፈላጊ እንደሆነ ባይካድም እንደኛ ባሉ በተለይም ለረጅም ዘመናት ስር በሰደደ የድህነትና ኋላ ቀርነት አረንቋ ስንማቅቅ ለኖርን ህዝቦች ከድህነት ለመላቀቅ እጅግ ከፍተኛና ወሳኝ አስተዋፅኦ ያለው በመሆኑ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠት የግድ  ይላል።
በሀገራችን የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ከተጀመረ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ቢቆጠርም እስከ 1983 ዓ.ም በሀገራችን የነበረው የኃይል አቅም  ከ370 ሜጋ ዋት ያልበለጠ ነበር። በዚህ ምክንያትም ትንንሽ ከተሞችና ገጠሮች ቀርቶ ለዋና ዋና ከተሞችም ቢሆን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በተሟላ መልኩ ማቅረብ የማይታሰብ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ኢህአዴግ የኃይል አቅርቦት ስራ የልማት ጥያቄዎች በመመለስ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በጥብቅ ያምናል፡፡ በዚህም ምክንያት የኃይል አቅርቦት ጥያቄን ለመመለስ የሚያስችል ግልፅ የፖሊሲ አቅጣጫ ቀርፆ በከፍተኛ ትኩረት ተንቀሳቅሷል። የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ስትራቴጅያችን የህዝባችንን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚችል፣ ከአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም ብሎም የታዳሽ ኢነርጂን ማዕከል ባደረገ አቅጣጫ እንዲፈፀምም አድርጓል።
በዚህ ረገድ የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ግንባታዎችን በማከናወን፣ ኃይል ማመንጫዎችን እንዲሁም  የማስተላለፊያ መስመሮችንና ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በመገንባት ኤሌክትሪክን ለሁሉም ማዳረስ የፖሊሲያችን የማዕዘን ድንጋይ ሆኗል። ኃይል  ከማምረት ጎን ለጎንም ኤክስፖርት በማድረግ በውጭ ምንዛሬ ገቢ ሀገራችን የተሻለ ልማትና የህዝብ ተጠቃሚነት እንድታስፋፋ ማድረግ የኃይል ልማት አንዱ አቅጣጫችን  ነው።
ባለፉት 24 ዓመታት ባከናወናቸው መጠነ ሰፊ ስራዎች ለዕድገታችን ዋስትና የሚሆን የኃይል አቅም ፈጥረናል!
የተከበራቸሁ የሀገራችን ህዝቦች!
የኃይል አቅርቦት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ የዕድገት እንቅስቃሴ ካለው የላቀ ጠቀሜታ አኳያ ዘርፉን ማልማትና ማበልፀግ ለአፍታም ቢሆን ችላ የማይባል ነው። ለዚህም ነው ኢህአዴግ በሀገራችን ቀጣይነት ባለው መልኩ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማርካት ቀጣይነት ያለው ርብርብ በማድረግ ላይ የሚገኘው። ከግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለምናደርገው የኢኮኖሚ ሽግግር የኃይል አቅርቦት መሰረታዊ በመሆኑ ኢህአዴግ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚሁ መሰረት የሀገራችንን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማርካትና  ሀገራችን ያላትን እምቅ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት  ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው።
የሀገራችንን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ባለፉት 24 ዓመታት ባከናወናቸው መጠነ ሰፊ ተግባራት በ1983 ዓ.ም 370 ሜጋ ዋት የነበረውን የኃይል ማመንጨት አቅም ከስድስት እጥፍ በላይ በማሳደግ ዛሬ 2313 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ችለናል።  አሁን እየተገነቡ ያሉ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦቻችንና ፕሮጀክቶቻችን ሲጠናቀቁ ደግሞ ሀገራችን ከ8ሺ እስከ 10ሺ ሜጋ ዋት ታመነጫለች። ይህም የኃይል አቅርቦት ስራችን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ቀጣዩን የሀገራችን ብሩህ የሕዳሴ ጉዞ ታሳቢ አድርጎ እየተካሄደ መሆኑን ያመላክታል።
በአሁኑ ወቅት 6000 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችለንን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጨምሮ የአምስት ፕሮጀክቶች ግንባታ በመፋጠንና በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። የብሄራዊ ኩራታችን ምንጭ የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድባችን ግንባታ በከፍተኛ የህዝብ ድጋፍና ተሳትፎ  እየተካሄደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ42 በመቶ በላይ ደርሷል። ሌላኛው ግንባታው ከ90 በላይ የተጠናቀቀው የጊቤ  ሶስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ሲሆን 1870 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ሲኖረው በያዝነው አመት ማጠናቀቂያ ሀይል ማመንጨት እንደሚጀምርም ይጠበቃል።  በተመሳሳይ 254 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የገናሌ ዳዋ 3 የውሃ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ፣ 153 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የአዳማ 2 የነፋስ ኃይል ለማመንጨት እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች  የኃይል ፍላጎታችንን ለማርካት እየተካሄዱ ያሉ ዋና ዋና ህዝባዊና ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ናቸው።
ኃይል ማመንጨት በራሱ አንድ ትልቅ ስራ ቢሆንም የመነጨውን ኃይል ጥቅም ላይ ለማዋል እጅግ ግዙፍ በጀት በመመደብ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና የከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ተካሂዷል። እስከ 1983 ዓ.ም 3578 ኪሎ ሜትር የነበረው የከፍተኛ ኃይል መስመሮች ግንባታ ባለፉት 24 ዓመታት በተደረገ ርብርብ  ዛሬ ከ13 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ደርሷል። በተመሳሳይ ከ82 የከፍተኛ የኃይል ማከፋፋያ ጣቢያዎች ተነስተን 162 የማከፋፋያ ጣቢያዎች ገንብተናል።
የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለልማትና እድገት ያለው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የሚገነዘበው ኢህአዴግ የኃይል ተደራሽነትን በሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋፋት  ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። ለዚህም ከመቶ በላይ አመታት ከአስር ሽህ በታች የነበረውን የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች ዝርጋታ በሀያ አራት አመታት ብቻ ከ18 እጥፍ በላይ በማሳደግ ዛሬ 180ሺ227 ኪሎ ሜትር  ማድረስ ችሏል።

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ኢህአዴግ የሀገራችንን ህዝቦች የልማት ጥያቄ በመመለስ ከምንም በላይ የሁሉንም ዜጎች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ጥረት ከፍተኛ ነው። ባለፉት ስርዓቶች ከ320 ባልበለጡ ከተሞች ብቻ ተወስኖ የቆየውና እጅግ ኢፍትሃአዊነት ይታይበት የነበረው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ባለፉት 24 አመታት በተከናወኑ  እልህ አስጨራሽ ተግባራት ከ5 ሽህ 100 በላይ የከተማና የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ከ24 ዓመታት በፊት ከ8 በመቶ በታች የነበረው የተጠቃሚዎች ሽፋን ድርጅታችን የመንግስት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ከህዝባችን ጋር ባደረገው እልህ አስጨራሽ ርብርብ ከ54 በመቶ በላይ ደርሷል። ይህ የሚያሳየው በሀገራችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተጀመረ በመቶ የሚቆጠር ዓመታት ዕድሜን ያስቆጠረ ቢሆንም እስከ 1983 ዓ.ም የነበረው ተደራሽነት ሲታይ ግን ከይስሙላ ያለፈ እንዳልነበረ ነው።
የሀገራችንን ህዝቦች የኃይል ፍላጎት ለማርካትና ኢኮኖሚያችን የሚፈልገውን ኃይል ለማምረት ዛሬም ርብርባችንን አጠናክረን ቀጥለናል!


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
በሀገራችን የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሰፊ ልምድ ለመቅሰም ከማስቻላቸውም በላይ ትላልቅ የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታዎችን ጐን ለጐን የመገንባት ሀገራዊ አቅም ላይ አድርሶናል። በኃይል ልማት ዘርፍ የተቀናጀናቸው ሰኬቶች የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም አስችለውናል። የኃይል አቅርቦት ልማታችን የኢንዱስትሪ ልማት ለማፋጠንም ከፍተኛ አቅም ሆኖል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማታችን የዜጎቻችንን የዕለት የኃይል ፍጆታ በማሟላት ህዝባችን የተሻለ ህይወት እንዲመራ የጎላ ሚና እየተጫወተ ነው። ከአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂያችን አንፃርም የአካባቢ መራቆትን በመታደግ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በመጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በተለይ ሴቶች ለማገዶ ፍለጋም ሆነ በእንጨት ለማብሰል የሚያጠፉትን ጊዜና ጉልበት እንዲሁም የጤና መታወክ በመቀነስ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገው ይገኛል።
የምንገነባው የኢኮኖሚ ስርዓትና የኢንዱስትሪ ዕድገታችን በየጊዜው ከሚዋዥቀው የዓለም የነዳጅ ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ የተላቀቀ እና በራሳችን አስተማማኝ አቅም ላይ የተገነባ እንዲሆን እያደረገም ነው። ከዚህ አኳያ በመገንባት ላይ ባሉ ፕሮጀክቶችም ከ50 ሽህ በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ባለቤት ሆነዋል። የኃይል ልማት አቅጣጫችን በኃይል ሽያጭ ከምናገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በላይ የቀጠናውን ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊና የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሚሆንም ይታመናል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
እንደ ሌሎች የልማት ስራዎች ሁሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ስራችን የተካሄደው አልጋ በአልጋ አይደለም። እንደሚታወቀው የኤሌክትሪ ኃይል ልማት ከፍተኛ ካፒታልና ቴክኖሎጂ ይጠይቃል፡፡ ከሀገራችን ኢኮኖሚ አቅም አኳያም ከሌሎች ልማቶች ጋር አጣጥሞ በእራስ አቅም መገንባት ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን ማንም ይገነዘበዋል፡፡ የውጭ የኒዮ ሊበራል ኃይሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቻችን ብድር እንዳያገኙ አድርጓል፡፡  ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ደንታቢስ የሆኑ አንዳንድ የሀገራችን ተቃዋሚዎች የኒዮ ሊበራል ኃይሎችን ደግፈው ኃይል ለማመንጨት የያዝናቸውን እቅዶች ሁሉ በመቃወም የውጭ የፋይናንስ ምንጮችን  ለማድረቅ ተንቀሳቅሰዋል። ይህ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገትና ለህዝብ የላቀ ጥቅም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ዘርፍ ወደ ግል እንዲዛወር በመወትወትና የለጋሽ ድርጅቶችን በር በማንኳኳት ልማቱን ለማሰናከል ዘወትር ሲተጉ ይታያሉ። ይሁን እንጅ የህዝብን ጥቅም በማስቀደምና ለህዝብ የላቀ ጥቅም የትኛውንም አይነት መስዋትነት በመክፈል የሚታወቀው ኢህአዴግ ከውጭም ሆነ ከውስጥ የሚቃጡ ፈተናዎችን ከልማት ወዳዱ ህዝባችን ጋር በመሆን በጽናት በመመከቱ በስኬት ጎዳና መጓዝ ችለናል። ለልማት የቆረጠ መንግስትና ታታሪ ህዝብ ካለ የማይቻል ነገር መኖሩን ያረጋገጡ የአይቻልም መንፈስን የሰበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችንም ገንብተናል፤ በመገንባትም ላይ እንገኛለን፡፡ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ግን ይህንን ተጨባጭ ስኬት ማየት ተስኗቸው ጥላሸት ሊቀቡ ይሞክራሉ፡፡  
ኢህአዴግ በኤሌክትሪክ ኃይል ልማታችን ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ ባለበት ሁኔታ ላይም ሆነን በኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ሳቢያ ህዝባችን ቅሬታ እንዳለው ይገነዘባል፡፡ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ችግሮች ተለይተውና እቅድ ተዘጋጅቶ መፍታት የጀመርናቸው ጉዳዮች ያሉ  ሲሆን በቀጣይም ችግሮቹን በአስተማማኝ መልኩ እንደሚፈታ ኢህአዴግ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡
ስለሆነም በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል እንዲሁም የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ለላቀ ስኬት የሚተጋውን ኢህአዴግ በመምረጥ የህዳሴ ጉዟችን አጠናክረን እናስቀጥል፡፡
ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተው ታታሪዋ ንብ ነች፡፡

ኢህአዴግ የሚያስተላልፋቸውን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶች ከቴሌቪዥን፣ ሬዲዮና ጋዜጣ በተጨማሪ www.eprdf.org.et በድረ ገፃችን እንዲሁም በፌስቡክ ገፃችን EPRDF official ማግኘት ይችላሉ።

No comments:

Post a Comment