EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Saturday, 30 May 2015

ግንቦት 20 የህዳሴያችን ጮራ!



ትንናትን በመልካምነቷም ይሁን ባስቀመጠችው ጠባሳ መዘከር አንዳንዶች ስህተት ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ በእኔ እይታ ትናንት ከስህተት ለመማርም አልያም መልካም ነገር ለመቅሰምም ለዛሬና ለነገ መሰረትነቷ አያጠያይቅም የሚል እይታ ነው ያለኝ፡፡ እናም እስኪ ወደ ትናንቷ 1983 ግንቦት 20 ቀን ልመልሳችሁ፡፡ ምናልባት ለአንዳንዶቻችን የተወለድንባት ቀን ብቸኛዋ ምርጥ ቀን ትሆናለች፤ ለአንዳንዶቻችን ደግሞ ልጅ ያፈራንበት አልያም ጉልቻ የቀየስንበት አልያም በሆነ አጋጣሚ ከአስቸጋሪና አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ የወጣንበት ቀን ለእኛ ምርጡና የማይዘነጋው ቀን ይሆናል፡፡ ትናንት መውለዷን እንደ እርግማን ትቆጥር ለነበረች እናት፣ መኖር እየጓጓ፤ ነገን እያለመ ህልሙ ቀዠት ብቻ ሆኖ ለቀረበት የአገሬ ወጣት፣ ስለነፃነት በተናገረበት አንደበቱ ምነው አፌን በቆረጠው ባልተነፈስኩ እስኪል ድረስ በአስቃቂና ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ በየሜዳው ይረሸን ለነበረ የአገሬ ህዝብ የተወለደበት አልያም ጉልቻ የቀየሰበት ቀን ሳይሆን የእሱ ምርጡና ብቸኛው የማይረሳና የቀናቶች ሁሉ አውራ ቀን ግንቦት 20 ነው፡፡

ሁላችንም በታሪክ አንዳንዶቻችን ደግሞ በተግባር እንዳየነው አምባገነኑ የደርግ ስርዓት የሰው ልጅ መፈጠሩን እስኪጠላ ድረስ በግፍ ይጨፈጭፍ የነበረው ህዝባችን ወንጀል ስለሰራ አልያም የአገሩን ህግ ስለተላለፈ አልነበረም፡፡ ወንጀል ሰርቷልስ ቢባል ህዝብ እንደ ህዝብ ወንጀል የሚሰራበት ሁኔታ ከየት ይመጣል ጎበዝ። ይልቁንም ተገዳዳሪ የሆነና የህዝብን ሁለንተናዊ ነፃነት ሊያስከብር የሚችል ተራማጅ አስተሳሰብ በመያዝና በደርግ መንግስት እይታ ከወታደራዊ ደርግ መንግስት የተለየ አመለካከት በማራመድ አሊያም ሊያራምድ አስቦ ይሆናል በሚል ነበር ያ ሁሉ ሰቆቃ በላዩ ላይ የሚዘንበው ደርግ የተለየ አመለካከት አላቸው ወይም ሊኖራቸው ይችላል ብሎ የሚያስባቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች የሚያስተናግድ ተፈጥሮአዊ ቁመና ስላልነበረውና እንቅስቃሴዎቹ ሁላ ስልጣንን ከማስጠበቅ ጋር የተያያዙ ስለነበር በህዝባችን ዘንድ ተነግሮ የማያልቅ ግፍና መከራ አደርሷል፡፡  

የደርግን ትእዛዝና ፍላጎት ተላልፎ መገኘትና የፈለጉትን ሃሳብ ማራመድ የገዥውን መንግስት ህገወጥ እንቅስቃሴ መቃወምና ይህንንም በፅሁፍ፣ በጋዜጣ አልያም በሬዲዮና በቴሌቭዥን ወይም በተለያዩ የስብሰባ ቦታዎች በንግግርና በተለያየ መንገድ ማስተጋባት ይቅርና ማሰብ በራሱ ለእስር፣ እንግልትና ኢሰብአዊ ግፍና በደል ወዳለበት የመጨረሻ ምዕራፍ ያሸጋግር ነበር።

ይህን በአፍሪካ እንኳ ተወዳዳሪ የሌለው የጦር መሳሪያ ባለቤት የነበረውን የደርግ “መንግስት”ና በአገር ውስጥም ጨፍጫፊና ሰብአዊነት የማይሰማው መንግስት ከአገራችን ህዝቦች ጫንቃ ላይ አውርዶ ማሽቀንጠር እና በምትኩ ህዝባዊ መንግስት ማቋቋም በበርካቶች ዘንድ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ ግፍና ጭቆናውን መሸከም ረሃብና ጥሙን መቋቋም ያቃተው የአገሬ ህዝብ ታዲያ በጥቂት ቆራጥ የህዝብ ልጆች የተፋፋመውን ደርግን የመጣል ህዝባዊ ትግል በሙሉ ልብ በመደገፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የደርግ አገዛዝን ታሪክ ለማድረግ በቅተዋል፡፡ ወትሮም የህዝብን ሃያልነት በቅጡ የማይገነዘበው የደርግ “መንግስት”ም ግራ እስኪገባው ድርስ የሽንፈት ካባን ሊከናነብ የግድ ሆኗል፡፡

የአገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታግለው ባታገሏቸው የነፃነት ተጋዮች አዲስ የህይወት ምዕራፍን ለመጀመር በቅተዋል፡፡ እናት በመውለዷ ከመሳቀቅ፤ የአገሬ ወጣት ደግሞ ትናንትን ማለም ከሚያጨናግፈው፤ የአገሬ ህዝብ በነፃነት ከመልማትና ከማደግ፣ ከመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ ከሚገድብው አምባገነን የደርግ ስርዓት ባደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ላይገናኝ መቆራረጥ ችሏል፡፡ ግንቦት 20! 1983 ለአገራችን ህዝቦች የነፃነት ጎህ የቀደደበት እለት በመሆኑ ለህዝባችን የቀናቶች ሁሉ አውራ ነው! ይህ የተቀደሰ ቀን የአሮጌው ስርዓት መዝጊያና የአዲሱ የህዳሴ ጉዞአችን መጀመሪያም ነውና በሀገራችን ታሪክ ድርብ ድርብርብ ቦታ ይዞ ይኖራል።

ኢህአዴግ አምባገነኑ የደርግ ስርዓት ከገረሰሰበት እለት ጀምሮ አገራችንን ወደ ተሻለ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ በርካታ እርምጃዎችን በመውሰድ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በአንድ አካል የሚሰጡ አልያም የሚነፈጉ ሳይሆን በህገመንግስቱ በተደነገገው መሰረት የሚፈፀሙ እንዲሆን አድርጓል፡፡ እነዚህ መብቶች የህዝቦች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ በሆነው ህገ መንግስት ላይ በግልፅ በመስፈራቸው ሁሉም በእኩል የሚጠብቃቸው፣ የሚያከብራቸውና የሚጠቀምባቸው መሆን ችለዋል፡፡

ባለፉት 24 ዓመታትም ዜጎች በነፃነት የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመደራጀት፣ የመምረጥና የመመረጥ፣ የመልማትና፣ ጤናቸው፣ ደህንነታቸውና መሰል ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የመጠቀም መብታቸው በመጠበቁ በተጨባጭ ለውጦች መመዝገብ ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና፣ ህዝቦች በቋንቋቸው የመናገር፣ የመፃፍ ቋንቋቸውን የማሳደግ፣ እና ባህላቸውን የመግለፅ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብታቸው ህገመንግስታዊ ዋስትና አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በህገመንግስት ያረጋገጡትን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ሳይሸራረፍ እንዲከበር በማድረግ አገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚያለሟት የጋራ አገር አድርግው ፈቅደውና አምነው በመቀበል የሚኖሩባት የእኩልነትና የመከባበር አገር ለመሆን በቅታለች፡፡

የሃይማኖት ነፃነት የተከበረባት፣ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው ተምረው ቋንቋቸውንና ባህላቸውን አሳድገው በማንነታቸው ሳያፍሩና ሳይሸማቀቁ በኩራትና በክብር የሚኖሩባት አገር የተገነባቸው ኢህአዴግ አገር የማስተዳደር ስልጣን ከተረከበበትና የአገራችን ብሄሮችና፣ ብሄረሰቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸው ከተረጋገጠበት ከግንቦት 20 1983 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡

ዛሬ በአገራችን የምናየው ዴሞክራሲ፣ ሰላም፣ ልማትና እድገት የመጣው ህዝባችን ፊቱን ወደ ልማት በማዞሩና የህዝብ ተሳትፎን የሚያጠናክሩ፤ ህዝቡ የልማቱ ባለቤት በማድረግ የህዝብ አቅምን በስፋት የሚጠቀሙ የልማት አቅጣጫዎች በኢህአዴግ መሪነት በመቀየሳቸው ነው፡፡ ዛሬ አገራችን ባለፉት 24 ዓመታት ያለፈችበትን ገፅታ ብንመለከተ ሰላሟ የተረጋገጠባት፣ የዜጎቿ ኑሮ በዘላቂነት እየተቀየረ ያለና በፈጣን የእድገት ማዕበል ውስጥ እየተምዘገዘገች ያለች አገር ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ ከራሳችን አልፈን ለሌሎችም በጥሩ ሁኔታ ምሳሌ ለመሆን የበቃችው ኢህአዴግ በተከተለው ትክክለኛ ፖሊሲና ህዝባችን ባደረገው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ነው።  

ዛሬ አገራችን  በርሃብ፣ በጦርነትና በተመፅዋችነት የምትጠራና የምትታወቅ አገር ሳትሆን የራሷን ሰላም ከማስጠበቅ አልፋ ለአፍሪካ ወንድምና እህት ህዝቦች ሰላም የምትሰራ፣ በርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመተማመን ላይ የተመሰረት አንድነት ፈጥረው ለአገራችው እድገትና ብልፅግና እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ የሚተጉባት አገር፣ በምግብ እህል ራስን ለመቻል በተቀየሰው የልማት አቅጣጫ በተቀዳጀነው ድል ከርሃብ ምሳሌነት እየወጣን እጅግ ፈጣን እድገት ከሚያስመዘግቡ ጥቂት የዓለማችን ሀገራት መካከል በክብር የሚትጠራ ብሩህ ተስፋ ያላት አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ 

ዜጎች የግንቦት 20 ፍሬ በሆነውና የመምረጥና የመመረጥ ህገመንግስታዊ መብት በመጠቀም ላለፉት 24 ዓመታት ከመላው ህዝባችን ጋር በመሆን አገራችንን ወደ እድገትና ብልፅግና እንድትገሰግስ ያደረጋትን ኢህአዴግን ምርጫቸው በማድረግ ባረጋገጡበት ማግስት ይህንን የድልና የነፃነት ቀን ማክበር ለመላው የአገራችን ህዝብም ሆነ ለልማት አጋሮቻችን ድርብ ድል ነው።

በእርግጥም ህይወታቸውንና አካላቸውን መስዋዕት አድርገው የዛሬዋን ብሩህ ጮራ እንድናጣጥም ያደረጉን ሰማዕታት ያጎናፀፉንን ድል ጠብቀን በጋራ ጥረት የአገራችንን ሰላም፣ ልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ወደ ተሻለ የለውጥ ደረጃ የምናደርስበት ነውና ግንቦት 20 ቃልኪዳናችንንም የምናድስበት ልዩ ቀን ሊሆን ይገባል፡፡ በመሆኑም ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች በጋራ የጀመርነው አይቀሬው የህዳሴ ጉዞአችንን ይበልጥ በማፋጠን ድሮ ወደነበርነበት ገናና ታሪካችን ለመደረስ አሁንም ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል።

No comments:

Post a Comment