EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 31 May 2015

ግንቦት 20ን የምናከብረው ስኬታችንን ይበልጥ ለማድመቅ ነው!!

የአገራችን ህዝቦች በጋራ ትግላቸው በተቀዳጁት ድል በቅብብሎሽ ሲተላለፍ ከነበረው የፀረ ዴሞክራቶች አገዛዝ ጭቆናና እንግልት ተላቅቀው የስልጣን ባለቤትነታቸውን ለ5ኛ ጊዜ በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ባረጋገጡበት ማግስት ያከበርነው 24ኛው አመት የግንቦት 20 በዓል ለመላው አገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ታላቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ግንቦት 20 ባለፉት ስርዓቶች ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ አስችሏል።
ኢህአዴግ በመራ የህዝቦች የትጥቅ ትግል አፋኙ የደርግ ስርዓት ተገርስሶ የህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ተረጋግጣል፡፡ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመሬት ባለቤት መሆን ብቻ ሳይሆን በመሬታቸው ያመረቱትን ምርት የመጠቀም ሙሉ ነፃነት ያጎናፀፈው ግንቦት 20 የተጎናፀፉት ድልም ነው፡፡ በዚህ ድል ላይ የተገነባችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቦቿ ለዘመናት ሲናፍቁት ወደኖሩት የፀረ ድህነት ትግል ፊታቸውን በማዞራቸው ላለፉት 24 አመታት በሁሉም መስክ ከቁልቁለት ጉዞ ሽቅብ መውጣት ጀምራለች፡፡
በአገራችን ስልጣን በጠመንጃ አፈሙዝ የሚያዝበት ምዕራፍ ተዘግቶ በምትኩ ዜጎች በይሁንታቸው ባፀደቁት ህገ መንግስት አማካኝነት የመሾምና የመሻር መብታቸው ተረጋግጣል፡፡ በግንቦት 20 በተገኘው ድል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በየአምስት አመቱ ጊዜያቸውን የጠበቁ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ አጠቃላይ ምርጫዎችን በማካሄድ ህገ መንግስታቸው ያጎናጸፋቸውን መብት በተግባር እያጣጣሙ ናቸው፡፡
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በግዳጅ አንድነት ጥላ ስር ሆነው ሲደርስባቸው ከነበረ ጭቆና ተላቅቀው በመፈቃቀድ ላይ በተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲኖሩ፣ በቋንቋቸው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋቸውን የማሳደግ እና ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብታቸው የተከበረው በግንቦት 20 ድል ነው።
በግንቦት 20 ድል በተገኘው ውጤት ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደርም ችለዋል። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብት ያለገደብ እንዲከበር ያደረገ ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲበሰር ሆኗል። ህዝቦችን በአስተዳደራዊ መንገድና በሃይል ለማዋሃድ የተፈፀሙ አፈናዎች በህዝቦች መራራ ትግል ተወግደው የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሁሉን አቀፍ እኩልነትና ብዝሃነት የተረጋገጠበት የፌደራል ስርዓት ባለቤት ሆነናል። በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በማጎልበት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማጠናከር እየሰራን ያለንውም ከግንቦት 20 ማግስት ጀምረን ነው፡፡
በአገራችን መንግስትን የሚቃወሙ መልእክቶችን መናገርና መፃፍ ቀርቶ ዜጎች ለመቃወም አስባችኋል እየተባሉ ከሚታሰሩበት፣ ከሚገረፉበትና ህይወታቸውን ከሚያጡበት አስከፊ አገዛዝ ወጥተው የአመለካከትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸው ህገ መንግስታዊ ዋስትና እንዲኖረው ያደረገው ግንቦት 20 ነው።
ግንቦት 20 ለዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን ከፍተኛ ሚና ያላቸው ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ በየደረጃው ያሉ የህዝብ ምክር ቤቶች፣ የህዝብ እንባ ጠባቂና የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ተቋማት ለማቋቋምና ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ታላቅ አስተዋፆም አበርክቷል፡፡ መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ በወቅቱ እንዲሰጡ የሚያስችል ግልፅ አሰራር የተዘረጋው ግንቦት 20 በፈጠረው ስርዓት ነው።
ለራሳቸው ሀይማኖት ህገ መንግስታዊ ሽፋን ሰጥተውና ይፋ የአገሪቱ የመንግስት ሀይማኖት አድርገው በሌላው ላይ ተጽእኖ ሲያደርጉ የቆዩ ስርአቶች እንዲሁም ሁሉንም እምነትና ሀይማኖት በጎታችነት በመፈረጅ ለማጥፋት አቋም ወስዶ ሲንቀሳቀስ የነበረው ስርዓት ላይመለስ እንዲወገድም አስችሏል። በምትኩም ሁሉንም ሃይማኖቶችና እምነቶች እኩል የሚመለከትና ሃይማኖትንና የመንግስት አስተዳደርን ነጣጥሎ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚያስተናግድ ስርዓት እንዲፈጠር ግንቦት 20 መሰረት ሆኗል።
የአገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል የህግ መብትና ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው መሰረት የተጣለው በግንቦት 20 ህዝባዊ ድል ነው። ባለፉት ስርዓቶች በህግ ሳይቀር የእኩልነት መብታቸውና ነፃነታቸው ተነፍጎ የሰቆቃ ህይወት እንዲገፉ ተደርገው የነበሩት ሴቶች ተጠቃሚነታቸው አድልኦ እንዳይደረግበት አስችሏል፡፡ የሕግ ማዕቀፎች እንዲታረሙ፣ በዴሞክራሲያዊ የሕግ ማዕቀፎች እንዲተኩም መሰረት ሆኗል። ለጦርነት ብቻ ሲፈለጉ የነበሩ የአገራችን ወጣቶችም በትምህርትና ስልጠና ራሳቸውን እንዲያበለፅጉ በማድረግና በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሳተፉ በማስቻል በአገር ግንባታ ሂደቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የሆኑትና ለራሳቸውና ለአገራቸው አስተዋፅኦ ማድረግ የቻሉት በግንቦት 20 በተገኘው ታላቅ ድል ነው።
ግንቦት 20 በድርቅና በረሃብ ብሎም በእርስ በርስ ጦርነት የምትታወቀው አገራችን ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ከሚጠቀሱ ጥቂት አገሮች ተርታ እንድትጠቀስም መሰረት ሆኗል። አገራችንን ትላንት በድህነቷና ኋላቀርነቷ ተምሳሌት ያደርጓት የነበሩ መንግስታትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በልማቷ ባስገኘችው ስኬት እውንነት የረሃብ ተምሳሌትነቷን ከመዝገባቸው ፍቀው ተስፋ ያላትና በእድገት እየገሰገሰች ያለች ሀገር መሆኗን መመስከር የጀመሩት የድህነቱን ዘበኛ አስወግደን ጠላታችን ድህነትን እንድንፋለም ባስቻለን የግንቦት 20 ድል ነው።
በተጎናፀፍነው ድል የዜጎቻችን ዓመታዊ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በ1983 ከነበረበት 70 ዶላር አሁን ወደ 632 ዶላር ደርሷል፡፡ ከምግብ እህል ተመፅዋችነት ተላቀን በአመት ከ250 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እህል በዋና ዋና ሰብሎች በማምረት በምግብ እህል ራሳችንን ችለናል፡፡
በመሰረተ ልማት ግንባታ በተለይም በቤቶች ልማት፣ በመንገድ፣ በባቡር፣ በኃይል፣ በውሃና አየር ትራንስፖርት፣ በማዳበሪያና ስኳር ፋብሪካ እንዲሁም በጤናና የትምህርት ተቋማት ግንባታዎች ያስመዘገብናቸው ስኬቶች ግንቦት 20 ባጎናፀፈን ድል የተገኙ ናቸው።
በተለይ መላው የአገራችን ህዝቦች በባለቤትነት ለሚገነቡት የጋራ ፕሮጀክት ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የህዝባችንን ተጠቃሚነት በማሳደግ በቂ ካፒታል መፍጠር የቻልነው፣ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር ለማድረግ በሁሉም ልማቶቻችን በቂ ክምችት የፈጠርነው የድህነቱን ዘበኛ በግንቦት 20 ህዝባዊ ድል በማሸነፋችንና ትኩረታችንን ወደ ፀረ ድህነት ትግል በማድረጋችን ነው።
በግንቦት 20 ህዝባዊ ድል ላለፉት 24 ዓመታት ታሪካችንን ቀይረን ስኬታማ የህዳሴ ጉዞ ጀምረናል። እንደ ሀገር በእርዳታ ላይ ከተመሰረተ ግንኙነት ተላቅቀን ትብብር ላይ ወደ ተመሰረተ የኢኮኖሚ አጋርነት መሸጋገር ችለናል። ያለፈው አሉታዊ ታሪካችን ተሽሮ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም መጓዝ የቻልነው፣ ከራሳችን አልፈን በሁለት ተቀናቃኝ ሀይሎች እኩል በመመረጥ በሰላም ማስከበር የተሰማራንው በጥቅሉ በሰላም ማስከበር መስክ ከዓለም አራተኛ ደረጃን የያዝነው ግንቦት 20 የተጎናፀፍነውን ድል መርሆ ተከትለን በመጓዛችን ነው።
በአጠቃላይ ባለፉት 24 አመታት ልትበታተን ከነበረች ሀገር ተነስተን አስተማማኝ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ችለናል፡፡ የሀገራችንን ህዳሴ የማረጋገጥ ጉዞም ጀምረናል። ዜጎቻችንም የዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ደረጃን ሙሉ በሙሉ የሚቀዳጁበትን እቅድ ቀይሰን በተግባር መጓዝ ቀጥለናል።
24ኛ አመት የግንቦት 20 በዓልን ስናከብርም ከዘላቂ ሰላማችን፣ ልማታችንና የዴሞክራሲ ጉዞአችን የሚያደናቅፉንን መሰናክሎች በጋራና በተቀናጀ ትግል ለማለፍ ቆርጠን በመነሳት የህዳሴ ጉዟችንን በጀመርነው ልማት አጠናክረን በመቀጠል ስኬታችንን ይበልጥ ለማድመቅ ቃል በመግባት መሆን ይኖርበታል።

ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት!

No comments:

Post a Comment