EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday, 9 April 2015

ቃለ ምልልስ በኦሕዴድ ታሪክና ሚና ዙሪያ

ጓድ አባይ ፀሃዬ የህ.ወ.ሓ.ት/ኢህአዴግ መስራች አባል፣ አንጋፋ ታጋይና በአሁኑ ጊዜ በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማእከል ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡  
በኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ ታሪክና ሚና ዙሪያ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ቃለ ምልልሱ እንደሚከተለው ቀርቧል፣ እንድታነቡት እንጋብዛለን።
ዋኢማ ---በትጥቅ ትግሉ ዘመን ኦህዴድ የኢህአዴግ አንድ አባል ድርጅት ሆኖ መቆሙ የነበረው ፋይዳ ምን ነበር? በዚህ ዙሪያ እንደመግቢያ፡፡ 

ጓድ አባይ ፀሐዬ --- የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ አንድ የኢህአዴግ አባል ድርጅት ሆኖ በመጋቢት 1982 ዓ.ም መደራጀቱ ፋይዳው ከዛ በፊት የኦሮሞ ህዝብ በዴሞክራሲያዊ አላማ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝብ አስተሳስሮ የሚያታግለውና የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በማጣቱ የተፈጠረ ድርጅት ነው፡፡ ከዛ በፊት የነበረ የኦሮሞ ህዝብ ትግል የብሄር ጭቆናው የሌላው በደልም ከተጀመረበት /ከተፈጠረበት ግዜ ጀምሮ ሲታገል ቆይቷል። የኦሮሞ ህዝብ ትግሉን አላቋረጠም። ለብሄራዊ መብቱም ለአጠቃላይ የኢኮኖሚያዊና ዴሞክራሲያዊ አጠቃላይ መብቱም፡፡ ግን ከዛ በፊት የነበሩ ድርጅቶች የተለያዩ በኦሮሞ ህዝብ ስም የተደራጁ ድርጅቶች ቢኖሩም አንደኛ ጠንካራ የህዝብ ድጋፍ እና ጠንካራ የህዝብ ማደራጀት ስራ አልነበረባቸውም፡፡
ወደ ህዝብ ገብተው ህዝቡን አደራጅተው ከህዝቡ ጋር ሆነው የህዝቡን ስሜት አዳምጠው ሀይል የፈጠሩ አቅም የፈጠሩ ጠንካራ ድርጅት፣ ጠንካራ የትጥቅ ትግል ሰራዊት የፈጠሩ አልነበሩም፡፡ ስለዚህ እየተደነቃቀፉ እየተኮላሹ ወደ አጎራባች ሀገሮች ወጣ ገባ እያሉ ነው ያሳለፉት ጊዜውን በአብዛኛው፡፡ ሁለተኛ መላውን የአማራ ህዝብና ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደጠላት የሚወስዱ የነበሩ ድርጅቶች ናቸው የነበሩት፡፡ ይህ ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ ብሄራዊ መብትና ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ ጥቅሞች የሚያስከብር አልነበረም፡፡
ስለዚህ የደርግ አቅም እየተዳከመ ሲመጣ በሰሜን ማለትም በትግራይና በአማራ ህዝብ ትግል በሌላ አካባቢም ህዝቡ ማለትም የደቡብ ህዝቦች፣ የሶማልያ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋር ሁሉም ይታገል ስለነበር የኦሮሞ ህዝብ ያልተካተተበት፣ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ደግሞ ከሰሜን ትግል ካልተቀናጀ ችግር ይፈጥራል ደርግ ቢወድቅም፡፡ ደርግ ለመጣልም ይህ ድርጅት ቢቀናጅ ነው የሚሻለው በሚል ነው ኦህዴድ የተፈጠረው፡፡ እና ይህን የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ፣ የኦሮሞ ህዝብን የዴሞክራሲያዊ ድርጅት መፈጠር ጥያቄ የመለሰ ለኢትዮጵያ የህዝቦች አንድነትና ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መፈጠር ምላሽ የሚሰጥ፣ ትግሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተሻለ እንዲቀናጅና ከደርግ ውድቀት በኋላም ሰላማዊ የሆነ የሽግግር መድረክ እንዲፈጠር ትልቅ አስተዋፆ የነበረው ነው የሚመስለኝ የድርጅቱ መፈጠር፡፡
{የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/} አንደኛ በደርግ ውድቀት ዋዜማ እንግዲህ በግንቦት 20/1983 ዓ.ም ነው ደርግ የተወገደው፣ መጋቢት 1982ዓ.ም ደግሞ ኦህዴድ ተፈጥሯል፣ በዚህ አንድ አመት ከምናምን ግዚያት ውስጥ የኦህዴድ አመራር አባላት ከፊሎቹ ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ አሁን ብአዴን የምንለው ኢህዴን ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ በርካታ በኋላ የተቀላቀሉ ናቸው። ይህ ሓይል መፈጠሩ የኦሮሞ ህዝብ  በወለጋ፣ ሰላሌ፣ ደራ፣ ፍቼም አካባቢ ያለው የኦሮሞ ህዝብ በትግሉ እንዲሳተፍ፣ እንዲሁም በደርግ መደምሰስ የመጨረሻ ርብርብ ላይ እንዲሳተፍ ሰራዊት ፈጥረው፣ እስከ አምስት ሺ የሚሆን ሰራዊት አሰልፈው ጦርነት ውስጥ የተሳተፉበት፣ ጦርነት ላይ ከመሳተፍ በላይ ደግሞ የወለጋ፣ ደራ፣ ሰላሌና ፍቼ ህዝብ በማደራጀት፣ ዓላማውን በማስረዳት፣ የሰላምና መረጋጋት ስራ በመፍጠር ትልቅ አስተዋፆ ነው ያደረጉት፡፡ በዛ ገና  ጀማሪ እድሜያቸው ማለት ነው፡፡
ሁለተኛው ከኢህአዴግ ጋር ተሳስረው፣ ከህወሃትም ብአዴንም ጋር ተሳስረው የኢህአደግ አባል ድርጅት ሆነው መፈጠራቸው ምን ጠቀማቸው? ካልን የኢህአደግ የትግል ተሞክሮ ጠቀማቸው፡፡ እንዴት ሰራዊት ይደራጃል? ህዝብ እንዴት ይደራጃል? እንደሌሎቹ ከዛ በፊት የነበሩ የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም እናስከብራለን የሚሉ ድርጅቶች በአንድ ጠባብ የሆነ አካባቢ ላይ ታጥረው አልቀሩም፡፡ ኢህአደግ ነፃ ያወጣው ሰፊ መሬት አለ፡፡ ትግራይና አማራ ክልል ኢህአዴግ የፈጠረው ትልቅ ሰራዊት ነበር። የኢሕአዴግ ልምድ አለ፣ የኢሕአዴግ የፖለቲካ አቋሞች የፖለቲካ አስተሳሰቦች ሰፊ ልምድ አለ። ይህን ሁሉ አቅም ይዘው ስለጀመሩ ጠቀማቸው። ሰሜን ላይ ከኢህአዴግ ሆነው ስለጀመሩ ቶሎ የጠላት ጥቃት አደጋ እንዳይደርስባቸው ኢህአዴግ አገዘ። የተሻለ ልምድና አቅም፣ የተሻለ ፖለቲካዊ አመለካከት፣ ለኢትዮጵያ የህዝቦች አንድነት በሳልና ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ይዘው እንዲጀምሩ አስቻላቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ቶሎ የተጠናከሩት፡፡
ዋኢማ --- የኦህዴድ መፈጠር በኢትዮጵያ የልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የተጫወተው ሚና እንዴት ይገልፁታል?
ጓድ አባይ ፀሐዬ --- ከደርግ ውድቀት በኋላም የተጫወቱት ትልቅ ሚና አለ፡፡ አንደኛ ያኔ የሽግግር ወቅት ሁሉም ፀረ ደርግ ሐይሎች የሚሳተፉበት የሽግግር መንግስት እንመስርት ብሎ ኢህአዴግ ጥሪ ሲያደርግ ለሁሉም ኦነግም ተሳትፎ ነበር፡፡ አምስቱም ሌሎች የኦሮሞ ህዝብን እንወክላለን የሚሉ ድርጅቶችም እንዲሳተፉ ነው የተደረገው፡፡ ሁሉንም ነው የጋበዘው ኢህአዴግ፡፡ ኦህዴድ አለኝ ከኔ ጋር እሱ ይበቃኛል አላለም፡፡ እንዳውም የበለጠ ቦታ የተሰጠው ከኦህዴድ ይልቅ ለኦነግ ነው፡፡ በሽግግር ወቅት የምክር ቤት ቦታ፣ የሚኒስትሮች ቦታም በርካታ ወንበር የተሰጠው ኦነግ ነው፡፡ ለምን ቢባል የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አዲሲቷን ኢትዮጵያ አብረን እንመስርት የሚል አቋም እንዲወስድ እነ ኦነግና ሌሎች ያራምዱት የነበሩት የጠባብ አስተሳሰብ ለኦሮሞ ህዝብ እንደማይጠቅመው እንዲረዳ ነበር የኢህአደግ ጭንቀቱና ልፋቱ ፡፡ በዚህ ዙሪያ ኦህዴድ ያኔ በትንሽ እድሜውና በትንሽ አቅሙ ከኦነግ ጋር ተወዳድሮ በራሱ በሁለቱም እግሩ ቆሞ ዴሞክራሲያዊ አንድነት በእኩልነትና ፍላጎት የተመሰረተች የህዝቦች አንድነት ያላት አንድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ናት የምትጠቅመን እንጂ መገንጠል አይጠቅምም ብሎ ከኦነግ ጋርም ከሌሎቹ ጠባብ ድርጅች ጋር ለመወዳደር እና ህዝቡን ለማሳመን ቻለ ፡፡
ይህን ትግል ሲያደርግ ከኦነግ ሲደርስበት የነበረ ግድያ፣ ድብደባ፣ እንግልት፣ የደጋፊዎቹ መጨፍጨፍ በደል ተቋቁሞ በትእግስት ወደ ጦርነት እንዳንሄድ ተብሎ በኦህዴድም በኢህአዲግ አቋም ተይዞ በትእግስት፣ ቢፈልግ ኦነግ ይግደላቸው፣ ይስቅላቸው አካላቸው ያጉድላቸው አባላቶቻችን ደጋፊዎቻችን እኛ የሰላም ኃይል መሆናችን፣ የዲሞክራሲ ኃይል መሆናችን ለኦሮሞ ህዝብ እናሳየዋለን፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ራሱ ይፈርደናል፣ የሚጠቅመውና የሚያዋጣው የትኛው መንገድ እንደሆነ ይረዳዋል ብሎ በከፍተኛ ትእግስት፣ በከፍተኛ የህዝብ ወገንተኝነት ከኢህአደግ ጋር ሆኖ የኦሮሞን ህዝብ መብትና ጥቅም ራሱ የኦሮሞ ህዝብ እንዲወስንና እንዲረዳ፣ ተረድቶም ኦነግ የማያዋጣው መሆኑን ኦህዴድ/ኢህአዴግ እንደሚያዋጣው፣ የኢትዮጵያ አንድነት በፍላጎትና በእኩልነት ሲመሰረት እንደሚጠቅመው እንዲረዳና ይህን አቋም እንዲይዝ ትልቅ ሚና የተጫወተ ከእድሜው  በላይ እና ከነበረው አቅም በላይ የሆነ ትልቅ ሚና ለዴሞክራሲያዊ አንድነትና ለኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት አስተዋጽኦ ያደረገ ድርጅት ነው ኦህዴድ፡፡
ህገመንግስቱ ረቅቆ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ደግሞ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ሲቋቋም እስከአሁን ድረስ የኦሮሞን ህዝብ ይህን ያስፈልገዋል፣ ይህን መብት ተረግጧል የሚሉትን ነበር በሙሉ የኦነግም የሌሎችም በሙሉ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እንደውም  ከዛ ባሻገር እንዲሄዱ ነው ኦህዴድ ትልቅ ሚና የተጫወተው፡፡  የኦሮሞ ህዝብ ባህልና ታሪክ ተከብሯል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ቋንቋ የስራ ቋንቋ እንዲሆን፣ የት/ት ቤት ቋንቋ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ የነበረው የተነጠቀው መሬቱና ምርቱ የራሱ እንዲሆንና ግብርናው የኑሮው ማሻሻያ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ኦሮምያ እየለማ ነው። የኦሮሞ ገጠር በኦሮምያ ውስጥ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሰፊ የኢንዱስትሪና የከተማ እድገት፣ ሰፊ ሌሎች የመሰረተ ልማትና ሌሎች ልማቶች እንዲከናወኑ ኦህዴድ ከኢህአዴግ ጋር ሆኖ ትልቅ ድርሻ ተጫቷል፡፡ ኦህዴድ በኦሮሚያ ውስጥ የኦነግና የሌሎች ጠባብ ኃይሎች ፀረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ከህዘብ ጋር ሆኖ በመመከት የተረጋጋ ሰላም እንዲኖረው ለልማት፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲቆም የኦሮሚያን ህዝብ ማድረግ ችሏል፡፡

ስለዚህ አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተፈጠረው  ሰላምና ዴሞክራሲያዊ አንድነትም በኦሮምያ ለተገኘው የኦሮሞ ህዝብና ሁሉም የብሔር መብቶች መከበርና ልማትና ዴሞክራሲ መገኘት ኦህዴድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ፣ ታሪክ የሰራ፣ ሀቀኛ የኦሮሞ ሀዝብ ጥቅምና መብት ያስከበረ፣ ለዚህም ከባድ መስዋትነት የከፈለ፣ መራራ ትግል ያደረገ፣ እውነተኛ የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም አስከባሪ እና ለኢትዮጵያ ልማትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት የቆመ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ የጎላ አስተዋፆ ተጨውቷል ብዬ ነው የማምነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብም ከተግባሩ አይቶ ኦህዴድ/ኢህአዴግ ሊደግፍ ያስቻለው በዚህ መንግድ መምራት ስለተቻለ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment