EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 6 April 2015

ኢህአዴግን መምረጥ የከተሞቻችንን የህዳሴ ጉዞን ማስቀጠል ነው!




የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
የሀገራችን ከተሞች የእድሜያቸውን ያክል ለውጥ የሚታይባቸው አልነበሩም፡፡ የሀገራችን መዲና አዲስ አበባን ጨምሮ ሁሉም ከተሞች በሚባል ደረጃ በገዥዎች የተሳሳተ ፖሊሲና አመራር ለልማትና ለኑሮ የማይመቹና ዕድገት የራቃቸው ሆነው ቆይተዋል፡፡ ባደጉት ሀገሮች ካሉት ከተሞች ብቻ ሳይሆን ከተሞችን የልማት ማዕከል በማድረግ ለውጥ የጀመሩ ታዳጊ ሀገራት ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች ጋር የሚነፃፀር የከተማ ይዘትና ገፅታ አልነበራቸውም፡፡ 

ከተሞቻችን ለገጠሩ ህዝባችንም ሆነ ለከተማው ህብረተሰብ በአስተዳደር ማዕከልነት ከሚሰጡት ፍትሃዊነት የጎደለው ግልጋሎት ባሻገር ይህ ነው የሚባል ልማትና እድገት ሳያመጡ በርካታ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የሀገራችን ከተሞች ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታ ችግር የሚታይባቸውና በራሳቸው ልማት ሳይሆን በገጠሩ ህዝብ ላይ ጥገኛ ሆነው እንዲቀጥሉ በመደረጋቸው የነዋሪዎቻቸውን የመሰረተ ልማት፣ የስራ እድልና የለውጥ ፍላጎት ለማሟላት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡

የድህነትና ኋላቀርነት ምንጭ የነበረውን የአፈና ስርዓት ባስወገደ ማግስት አዲስ የለውጥ ምዕራፍ የከፈተው በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን የቀየሰው የከተማ ልማት ፖሊሲ ነባር ከተሞች ወደ አዲስ የለውጥ ንቅናቄ እንዲገቡና በከፊል በአዲስ መልክ ፈርሰው እንዲገነቡ፣ የገጠር ልማቱን በመከተልም አዳዲስ ከተሞች እንዲያብቡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የአስተዳደር ማእከላት ሆነው የቆዩ ከተሞቻችንን ከኢንዱትሪ ልማት ጋር በማስተሳሰር ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጠርባቸው፣ የከፍተኛ ኮንስትራክሽን ማዕከላት እንዲሆኑና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለማድረግ ተችሏል፡፡ 

በኢህአዴግ የለውጥ ፖሊሲና በነዋሪዎቻቸው ንቁ ተሳትፎ ከተሞቻችን የህዳሴያችን ጅምር ማሳያና የቀጣይ ህዳሴያችን የለውጥ ማዕከላት እየሆኑ ነው፡፡ ከገጠር ልማትና ኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር በተቀናጀ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ በተመሰረተ ልማት አብረው የሚለሙበትና የሚያድጉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለዚህም ነው በርካታ ነባር ከተሞች ፈርሰው እየተገነቡ፣ በከተማ ላይ አዲስ ከተማ የመገንባት ያህል በከፍተኛ ደረጃ እየሰፉ የሚገኙት፡፡ ከነባር ከተሞች ፈጣን እድገት ጎን ለጎንም የገጠር ልማት ስኬትን በመከተል በርካታ አዳዲስ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከተሞች እየለሙና እየተስፋፉ ነው፡፡ 

ኢህአዴግ የሀገራችን ከተሞች ዕድገትና የነዋሪዎች ጥቅም የሚረጋገጠው ከገጠሩ ልማት ጋር ሲተሳሰር መሆኑን አፅንኦት ሰጥቶ የገጠሩን ልማት የሚደግፉ የንግድና የኢንዱስትሪ ልማት ስራዎች የሚሰሩባቸው ከተሞች በየእርከኑ እንዲቋቋሙ አድርጓል። በዘፈቀደ ሲካሄድ የቆየውን የከተሞች አሰፋፈርና አከታተም ግልፅ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረፅና የመካከለኛና የረዥም ጊዜ የከተሞች ፕላንና ደረጃዎች ምደባ በማካሄድ የሀገራዊ ልማትና ለውጥ ማዕከላት እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ፈጣን ልማቱን በመከተልም በፍጥነት እያደጉ ነው፡፡ የአዳማ፣ ሀዋሳ፣ መቐለ፣ ባህር ዳር ከተሞች የዚህ ፈጣን ዕድገት ማሳያ ናቸው፡፡

በከተሞች የመሬትና የመሰረተ ልማት አቅርቦት በአካባቢው ለሚፈጠሩ የንግድና ምርት ተቋማት ቅድሚያ በሚሰጥና የህዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አቅጣጫ እንዲመራ ተደርጓል፡፡ ለዚሁም ሲባል የከተማ መሬትን ለኢኮኖሚ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት በብቃት ለመጠቀም የሚያስችል የሊዝ ፖሊሲ በመቅረፅና በአፈፃፀም ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት የባለሃብቶችን የልማት ተሳትፎና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ ፖሊሲ ከልማት ተገልለው የነበሩ ሀገራዊ ባለሃብቶች በከተሞች ልማት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏል፡፡ 

የከተሞች የልምድ ልውውጥ መድረክ በመፍጠር /የከተሞች ቀን/ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋትና በየደረጃው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሰፊ ጥረት ተደርጓል፡፡ በከተሞች ቀን ስኬታማ ተሞክሮዎችን ለማስፋትና የአፈፃፀም ክፍተት የታየባቸውን በአፋጣኝ ለማሻሻል የሚያስችል የትብብርና የውድድር መንፈስ ተፈጥሯል፡፡ በቀጣይም ዘመናዊና ለነዋሪዎች የተመቹ ከተሞች ለመገንባት በሚያስችል አቅጣጫ ይኸው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ 

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን ተግባራዊ ባደረገው የከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራተጂ የሀገራችን ከተሞች በኢንዱስትሪ ልማት፣ በኮንስትራክሽን፣ በቤቶች ግንባታ፣  በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ልማትና የአካባቢ ልማት ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር የነዋሪዎቻቸውን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡ በሀገር ደረጃ ባለፉት አራት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አመታት ከታቀደው በላቀ ደረጃ ለ8.3 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ተችሏል፡፡

የመንገድ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የእርስ በርስና ከገጠር ልማት ጋር ትስስርን በመፍጠር የፍትሃዊና ተመጣጣኝ ዕድገት ማሳያዎች እየሆኑ ነው፡፡  በዘርፈ ብዙ የከተማ ልማት ፕሮጀክቶች በርካታ የከተሞቻችን ወጣቶችና ሴቶች ከስራ ጠባቂነት በመላቀቅና ስራ ፈጣሪ ሆነው ራሳቸውንና ሀገራቸውን በመጥቀም ለሀገራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ያስቻሉ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ኢህአዴግ የከተሞችን ልማት ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር በተቀናጀ መልኩ እንዲፈፀም በማድረግ የግል ባለሃብቶች በከተሞች ልማትና ሀገራዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ አስችሏል፡፡ ለኢንዱስትሪ ልማት ወሳኝ የሆነ የሰው ኃይል አቅም የሚፈጥሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያግዙ የምርምር ተቋማትና  ኢንስቲትዩቶችን በመዲናችንና በአብዛኛዎቹ ከተሞች በማቋቋም ሰፊ የአቅም ግንባታ ስራዎችን አከናውኗል፡፡ የኢንዱስትሪ ልማት መሰረት የሆኑ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ለማስፋፋትና ለማጠናከርም የማምረቻና መሸጫ ቦታ በማዘጋጀት፣ ሼዶችን በመገንባትና  የገበያ አቅማቸውን በማጠናከር ሰፊ ድጋፍ አድርጓል፣ አሁንም እያደረገ ነው፡፡ ተቋማቱ ወደ መካከለኛ ኢንደስትሪ ለመሸጋገር የሚያስችላቸውን የጥራትና የተወዳዳሪነት አቅም እንዲያጎለብቱ የቴክኒክና የንግድ ክህሎት ስልጠናዎችን ሰጥቷል። የሀገር ውስጥና የውጭ ገበያ ትስስር እንዲኖራቸውም ድጋፍ አድርጓል።

ኢህአዴግ ከተሞች ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዲኖራቸው የሚያስችል አመራር ሰጥቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በውጭ የኮንስትራክሽን ተቋማት ይሰሩ የነበሩ ፕሮጀክቶች በሀገር ውስጥ ተቋራጮች በብቃት የሚሰሩበትና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ የሚገኙ የመንገድና የዘመናዊ ህንፃዎች ግንባታዎች፣ በየክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ ስቴዲየሞች የሀገራችን የኮንስትራክሽን ዘርፍ በፈጣን ዕድገት ላይ እንደሚገኝ ያረጋግጣሉ፡፡ ይህ ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበውም በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ትኩረት በመስጠቱና ባለሙያዎች በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በቂ እውቀት እንዲቀስሙና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ  በተቀየሱ ትክክለኛ ፖሊሲዎች ተግባራዊነት ነው፡፡


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ኢህአዴግ በከተማ ልማት ያከናወነው ተግባር ውጤታማነት ሌላው መገለጫ በቤቶች ልማት ዘርፍ የተመዘገበው ስኬትና በዜጎች ህይወት ላይ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ነው። የመኖሪያ ቤት ችግር የከተሞች ቁልፍ ችግር መሆኑን በማገናዘብ በተቀረፀው የተቀናጀ የመኖሪያ ቤቶች ልማት ፖሊሲና ፕሮግራም የግል ባለሃብቶች፣ መንግስትና በግል ቤት መስራት የሚችሉ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በርካታ ባለሃብቶች በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የቀየሰውን ትክክለኛ ፖሊሲ በመጠቀም ትላልቅ የሪል ስቴት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረጋቸው የመግዛት አቅም ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ 

በግል በሊዝ ቦታ ተረክበው መስራት የሚችሉም በራሳቸው ጥረት ውጤታማ ሆነዋል፡፡ በማህበራት የተደራጁ በርካታ ዜጎችም የቤት ልማት ፖሊሲው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በመንግስት የተሰሩትና እየተሰሩ ባሉት የቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች ዜጎች በተመጣጣኝና በረዥም ጊዜ ክፍያ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ሆነዋል፣ አሁንም እየሆኑ ነው፡፡ የቤቶች ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ በሆነባቸው ባለፉት አስር አመታት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ተጠናቀው ለነዋሪዎች የተላለፉ ሲሆን አሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ 

የተቀናጀ የቤቶች ልማት ፖሊሲው ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እድገትም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ሀገር በቀል ተቋማትና አንቀሳቃሾች በየጊዜው ቁጥራቸው እየጨመረና አቅማቸው እየጎለበተ ይገኛሉ፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተሳታፊ የሆኑ የከተማ ነዋሪዎችና የኮንስትራክሽን ባለሙያዎችም በዚህ ኢንዱስትሪ ስር ታቅፈው የልማቱ ባለቤትና ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
 

ሁሌም ለሴቶች እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት በፅናት የቆመው ኢህአዴግ ሴቶች በቤቶች ልማትና በከተሞቻችን በሚካሄዱ የተለያዩ የልማት መስኮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትጋት ሰርቷል፣ አሁንም እየሰራ ነው፡፡ ከ800 ሺህ በላይ ቤተሰቦችን የመጠለያ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ በተቻለው የቤቶች ልማት ፕሮግራም የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በቅርቡም የመንግስት ሰራተኞችን ተጠቃሚነት የሚያጋግጥ አሰራር በመዘርጋቱ ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን በተሻለ ብቃት እንዲወጡና ባበረከቱት አስተዋፅኦ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ኢህአዴግ የከተማ ነዋሪዎችን የገቢ አቅም ለማሳደግና ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ከቀረፃቸው ስኬታማ ፖሊሲዎች ጎን ለጎን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በዝቅተኛ የመሬት ሊዝ ዋጋና በአነስተኛ የወለድ መጠን በረጅም ጊዜ ክፍያ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ አድርጓል። በዚህም የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን አቃልሏል፡፡ ባለፉት አመታት ሲያጋጥም የነበረውን የዋጋ ንረት ተከትሎ ያጋጠመውን የኑሮ ውድነት ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል ስኬታማ ስራ ተሰርቷል፡፡
የችግሩ ምንጭ የሆነውን የገቢ አቅም ማነስ ለማሻሻል የሚያስችሉ እቅዶችን ተግባራዊ ከማድረግ ጎን ለጎን ጊዜያዊ ችግሮችን በብቃት ለመፍታት ተችሏል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በከተሞች ከስራ አጥነትና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚታዩትን ችግሮች በአፋጣኝ ለመፍታት እንዲቻል ህዝቡን በተደራጀ መንገድ በማሳተፍ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ኢህአዴግ ፈጣን ለውጥ የማምጣት ብቃቱን በመጠቀም እነዚህን ጊዜያዊ ችግሮች ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፣ ትኩረት ሰጥቶ በተንቀሳቀሰባቸው መስኮችም ስኬታማ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ጥረት የህዝብ እርካታ እስኪረጋገጥ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
የሀገራችን ከተሞች ነዋሪዎቻቸውን ተጠቃሚ ከማድረግ አልፈው የአፍሪካ ሀገሮችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻቸው የሚመክሩባቸውና የሚገናኙባቸው መዳረሻዎች እስከመሆን ደርሰዋል። ከተሞቻችን በነዋሪዎቻቸው የላቀ ተሳትፎ ደረጃ በደረጃ እያሟሉ በመጡት የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ባፀኑት አስተማማኝ ሰላም ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭነታቸው እየላቀ፣ ተፈላጊነታቸውም እየጨመረ መጥቷል። 

የሀገራችን ከተሞች ማንንም ሊስብ የሚችል ሰላምና ለልማት ምቹ የሆነ ፖሊሲ ያላቸው በመሆኑ የውጭ ባለሃብቶችን ቀዳሚ ትኩረት አግኝተዋል፤ የወቅቱ የዓለማችን ኢንደስትሪ የሚፈልገው የግብርና ግብዓት ገጠሩን ከከተማ ባስተሳሰረ ልማታችን በመፈጠሩም በርካታ ባለሃብቶች ሊሰሩባቸው ከሚመርጧቸው የዓለማችን ሀገሮች የኢትዮጵያን ተመራጭነት ማጉላት ችለዋል።

ከተሞቻችን የእስካሁኑን ስኬት የበለጠ በማጎልበት ለነዋሪዎቻቸው ተጠቃሚነት ከዚህም በላቀ ሁኔታ ማደግና ምቹነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ኢህአዴግ ያምናል። ስለሆነም የሀገራችን ህዝቦች ከተማና ገጠሩን ባስተሳሰረ ሁለንተናዊ ልማት እድገት እያስመዘገበና ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ ያለውን ኢህአዴግ በመምረጥ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ እንዲያስቀጥሉ ኢህአዴግ ጥሪ ያቀርባል።

ኢህአዴግን መምረጥ የከተሞች ልማትን ማስቀጠልና የነዋሪዎቻቸውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው! 

ኢህአዴግን መምረጥ የከተሞቻችንን ህዳሴ ማሳካት ነው!!

ኢህአዴግን ይምረጡ!!

No comments:

Post a Comment