EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 15 April 2015

ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ልማት መፋጠን - ኢህአዴግ!




የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን ሀገራችንን ከድህነትና ኋላቀርነት በማላቀቅ ፈጣን ዕድገት ለማምጣት የቀየሳቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በብቃት ለማስፈፀም ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል። በዚህም ከአስር ዓመታት ለሚልቁ ጊዜያት በአማካይ ከ10 በመቶ በላይ ዓመታዊ እድገትን በማስመዝገብ በስኬት መጓዝ ችሏል። በውጤቱም ሀገራችን እጅግ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ የዓለማችን ጥቂት ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች፡፡

በዕድገቱ ውስጥ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ማደግ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት መስፋፋት እንዲሁም የዩኒቨርስቲዎቻችን ቁጥር ማሻቀብ የፈጠሩትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የምናደርገውን ሽግግር ለማሳካት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ ተቀርፆ እሱን ለማስፈፀም ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ 

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ሀገራችን ያላትን ውሱን ካፒታልና ሰፊ የሰው ኃይል በአግባቡ ለመጠቀም እያስቻለ ሲሆን በከተሞች ያለውን የሥራ አጥነት ችግር በመቅረፍም ከግብርና ቀጥሎ ሰፊ የሰው ኃይልን የሚያቅፍ መስክ ሆኗል፡፡ የዘርፉ ልማትና የስራ እድል የመፍጠር አቅም ለማሳደግ እንዲቻልም በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ ይህ ዘርፍ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ በማድረግ ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችል በመሆኑም ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ከ293 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ የስራ ቦታ፣ 617 ህንፃዎችንና ከ20 ሺህ በላይ ሼዶችን በማዘጋጀት ለመስሪያና መሸጫ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ ለኢንተርፕራይዞቹ እድገት ወሳኝ የሆነውን ብድር በማቅረብ ረገድም ከ1ነጥብ1 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ አንቀሳቃሾች ከ12ነጥብ3 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር አግኘተዋል።

የኢንተርፕራይዞቹ አንቀሳቃሾችም መንግስት የፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከ13ነጥብ3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመቆጠብ ችለዋል፡፡ እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ቀላል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚሰሩ በመሆናቸው የአዳዲስ ፈጠራዎችና ባለሙያዎች መፍለቂያም እየሆኑ ነው፡፡ ባለፉት አራት አመታት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአንቀሳቃሾች ለማሸጋገር በተሰሩ ስራዎች ከአራት ሺህ በላይ የመስሪያ ሞዴሎች በናሙናነት ተመርተው ከሶስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ለኢንተርፕራይዞች ተሸጋግረዋል፡፡ ይህም የከተሞች ልማትንና የቴክኖሎጂ አቅምን ያጎለበተ ነው፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በምርትና አገልግሎት ስራዎች እንዲሰማሩ፣ መንግስታዊ ድጋፎችን በአግባቡ እንዲያገኙና በሌሎች ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎቶች በተቀናጀ፣ ግልፅና ቀልጣፋ በሆነ መልክ በአንድ ስፍራ እንዲያገኙ ለማስቻል በተደረገው ጥረት በመላ ሀገሪቱ 1ሺ341 የአንድ ማዕከል መስጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የትምህርት እድል ላገኙትም ሆነ ላላገኙት የህብረተሰብ ክፍሎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማረጋገጥ የሚያስችል ዘርፍ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የስራ እድልን በመፍጠር የዜጎችን ገቢ ለማሻሻልና ድህነትን ለመቀነስ የተከናወኑት ተግባራትና የተመዘገበው ውጤትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ብቻ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከ783 ሺህ በላይ ዜጎች፣ በማእድንና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ከ693 ሺህ በላይ ዜጎች፣ በከተማ ግብርና እና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ከ750 ሺህ በላይ ዜጎች፣ በንግድ ዘርፍ ከ785 ሺህ በላይ ዜጎች፣ በአገልግሎት ዘርፍ ከ924 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡ በመንግስት ሜጋ ፕሮጀክቶችም ከ3ነጥብ3 ሚሊየን በላይ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በዘርፉ ለሦስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል ተብሎ የታቀደ ሲሆን በአራት አመት ተኩል ውስጥ ብቻ ከ8ነጥብ3 ሚሊየን በላይ ዜጎች በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የስራ እድል በመፍጠር የላቀ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ ከተፈጠረው የስራ ዕድል ውስጥም የሴቶች ተሳትፎ የ41 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በዝቅተኛ ካፒታልና በሰፊ የሰው ኃይል እውቀትና ጉልበት በመጠቀም ስኬታማ ከመሆናቸው ባሻገር በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በአብዛኛው የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃን የሚጠቀሙ መሆናቸው ለሀገራዊ ልማታችን ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረቱም ባሻገር በሀገር ውስጥ የጥሬ እቃ አቅርቦት ምርት እንዲጨምርና በዚሁ ስራ ላይ የሚሰማሩ ዜጎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ ነው፡፡ የእነዚህ ተቋማት ምርቶች ከውጭ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ረገድም የማይናቅ ድርሻ እየተጫወቱ ነው፡፡ 

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተለይም በቆዳና የቆዳ ውጤቶች ስራ ላይ የተሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ምርት የሆኑ ጫማዎች፣ ቀበቶዎች ቦርሳዎችን የመሳሰሉ ምርቶች በሀገር ውስጥ ሰፊ ተቀባይነትን እያገኙ መምጣታቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የዘርፉ አንቀሳቃሾች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገ መሆኑን ጨምሮ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የሀገር ውስጥ ገበያ ትስስር የተፈጠረ ሲሆን የቆዳ ውጤቶችንና ጨርቃ ጨርቅና አልባሳትን እንዲሁም የእደ ጥበብ ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ74 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ1ነጥብ4 ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ተችሏል፡፡

በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን በዘርፉ እያስመዘገበው ያለው ስኬት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪያችን ቁልፍ የምርትና የእድገት መሰረት እንደሚሆኑ፣ በሂደትም ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በምናደርገው መዋቅራዊ ሽግግር ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ አመላካች ነው፡፡ ለኢንዱስትሪው ልማት አስተማማኝና ሰፊ መሰረት ሆነው የሚያገለግሉትን እነዚህን ኢንተርፕራይዞች በላቀ ደረጃ ውጤታማ ለማድረግም በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩት አንቀሳቃሾች የብድር፣ የሥልጠና የመስሪያና መሸጫ ቦታ አቅርቦት በቅድሚያ እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ 

ይህንኑ ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም ባለፉት ዓመታት ከ3 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች እያንዳንዳቸው ከ1ነጥብ5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ታዳጊ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ በተለይም የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች በርካታ ግብዓቶችን የሚያቀርቡ መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ ከኢፌዴሪ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር የተለያዩ ማሽነሪዎች መለዋወጫ የሚያመርቱ 31 ወርክሾፖች በትግራይ፣ አማራ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡


የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ባሻገር ለተደራጀ የህዝብ ትግልም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢህአዴግ የሚያካሂደውን የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ለማሳካት የሚያስችሉ ተቋማት መሆናቸውም የስኬቱ ሌላው መገለጫ ነው፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ዜጎች በራሳቸው ገቢና ሃብት በመተማመን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን በመታገል የመንግስት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ግፊት እያደረጉ ነው፡፡ዜጎች በዝቅተኛ ካፒታል፣ በራሳቸው እውቀትና ጉልበት የሚያስመዘግቡት ስኬት በአቋራጭ ሃብት ለማካበት የሚደረገውን የኪራይ ሰብሳቢዎች መሯሯጥ በማሸነፍና የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተሳሰብን በመናድ በምትኩ ልማታዊ ባለሃብቶችን ለመፍጠር የሚያስችል ነው፡፡ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ኪራይ ሰብሳቢነትን የሚጠየፍና በግል ጥረትና ልፋት በሚገኝ ልማትና ለውጥ የሚኮራ ትውልድ በመገንባት የልማታዊነት አመለካከት አብነታዊ ተቋማት ናቸው፡፡

ዜጎች ተቀራርቦ አብሮ የመስራት ባህልን እንዲያዳብሩና ማህበራዊ ግንኙነቶቻቸውን እንዲያጎለብቱ በማስቻል ረገድም ከፍተኛ ማህበራዊ ፋይዳ ያላቸው ተቋማት ናቸው፡፡ ሥራን የማማረጥና የመናቅ አመለካከትን በመናድ የስራ ክቡርነት አስተሳሰብን በመገንባት በወጣቱ ትውልድ ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው፡፡ ዛሬ የከፍተኛ ተቋማት ምሩቃን ስራን ሳያማርጡ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው የሃብት ባለቤት እየሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች የዘርፉን ልማት ለማጣጣል ሰፊ ቅስቀሳ ባካሄዱባቸው ባለፉት አራት ዓመታት 300 ሺህ የሚሆኑ የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ምሩቃን ተደራጅተውና አስፈላጊውን የክህሎት ስልጠና ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

በጋራ ሰርቶ በተባበረ ክንድ ሀገርን ማሳደግ እንደሚቻል ከመረዳት አልፎ ሌሎችንም የማስገንዘብ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ኢንተርፕራይዞች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በዚህም በኢንተርፕራይዞቹ አንቀሳቃሾች አልፎ አልፎ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን ከመዋጋት ባሻገር በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚታዩትን ችግሮች በመጋፈጥ ለመልካም አስተዳደር መጎልበት አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው፡፡ በመጠነኛ የመንግስት ድጋፍ የራስን እውቀትና ጉልበት በመጠቀም ደረጃ በደረጃ ማደግ በሚያስችል ስርዓት ውስጥ እየጎለበቱ የሚገኙት እነዚህ ኢንተርፕራይዞች የኪራይ ሰብሳቢነት እንዲወገድና በሀገሪቱ ውስጥ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የበኩላቸውን ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ተቃዋሚዎች እንደሌሎቹ መስኮች ሁሉ በዘርፉም በሚከተሉት የተሳሳተ ፖሊሲ የዘርፉ ልማት አማራጭ የሥራ መስክ በመጥፋቱ የሚገባበት ነው የሚል ውዥንብር ያስፋፋሉ፡፡ ይህ የተሳሳተ አቋም ወደ ህዋ የሚመጥቁ ማሽኖች ጭምር የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ መለዋወጫዎችና እቃዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የሚሰሩ መሆናቸውን ካለማወቅ አሊያም የኢህአዴግን ፖሊሲ በጭፍን ከመቃወም የመነጨ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የበለፀጉ ሀገራትም ጭምር የዕድገታቸው ዋነኛ ቁልፍ አሁንም ድረስ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት መሆኑ የአደባባይ ሃቅ መሆኑን መገንዘብ አልቻሉም፡፡ 

በኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ልማት የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰችውና እንደ ቶዮታና ሶኒ ያሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎችን ያፈለቀቸው ጃፓን ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የማኑፋክቸሪንግ ምርቷ የሚመረተው በጥቃቅንና አነስተኛ የማኑፋክቸሪንግ ተቋማት መሆኑ የዚህ እውነታ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ዋንኛ የስራ እድል ፈጣሪ ሃይሎች የሚሆኑትም እንደኛ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በበለፀጉ ሀገራትም ጭምር ነው፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን የህዳሴው ጉዟችን ሲጠናቀቅም በኢንዱስትሪ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዋናዎቹ አምራች ኃይሎች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

ለዚህም ነው በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት አንዱ የህዳሴያችን መሰረት እንዲሆን ያደረገው፡፡ ኢህአዴግ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠርና የሃብት ባለቤት በማድረግ ፈጣን እድገት እያስመዘገበ ያለውን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ 

ኢህአዴግን መምረጥ የኢንተርፕራይዞቹን ስኬት በማሳደግና ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የምናደርገውን ሽግግር በማፋጠን የህዳሴ ጉዟችን ማስቀጠል ነው!

No comments:

Post a Comment