EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 1 April 2015

በምግብ እህል እራሳችን መቻላችን የፖሊሲያችን ትክክለኛነት ማረጋገጫ ነው!!




ኢህአዴግ በተከተለው ትክክለኛ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህዝቦች ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ወርቃማ ስኬቶች ተመዝግበዋል!!

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
ኢሕአዴግ ከጅምሩ ያስቀመጠው የኢኮኖሚ ልማት አላማ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ አገራችንን ከተመጽዋችነት የሚያላቅቅ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማረጋገጥ የዳበረ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ መገንባት ነው፡፡ ማንኛውንም አይነት የኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ ካፒታል፣ ሰራተኛ የሰው ሃይል፣ መሬትና እነዚህን በውጤታማነት አቀናጅቶ መጠቀም የሚችል አመራር ያስፈልጋል። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የካፒታል እጥረት መኖሩና የካፒታል እጥረቱም በአጭር ጊዜ እንደማይፈታም ግልጽ ነው፡፡ በአንጻሩ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ታታሪ የሰው ኃይልና ለልማት የተመቸ በቂ መሬት አለ። ይህም በመሆኑ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቀውን ኢንዱስትሪን ማእከል ያደረገ ልማት የትም እንደማያደረስን የታወቀ ነበር፡፡
በዚህም ምክኒያት ያለንን ሰፊ የሰው ጉልበትና መሬትን እንዲሁም ውስን ካፒታል በመጠቀም የህዝቡ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የልማት ስትራቴጂ መከተል የግድ ይል ነበር፡፡ ለዚህም ነው ያለንን አቅም ተጠቅመን አገራችን ከብተና ሊታደግ የሚችል ገጠርንና ግብርና ማእከል ያደረግ ስትራቴጂ በመከተል ልማታችን የጀመርነው፡፡ ግብርናና ገጠርን ማእከል ያደረገ የልማት ፖሊሲ የተከተልነው የለገጠሩንም ሆነ የከተማውን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ ስለነበረ ነው፡፡ የግብርና መር የልማት ስትራቴያች የተከተልነው ለኢንዱስትሪውና ለአገልግሎት ዘርፉም እድገትም  ወሳኝ ሚና የሚጫወት ስለነበረም ነው፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
ኢህአዴግ የቀረጸውን ፖሊሲና ስትራቴጂ በሚመራው ልማታዊ መንግስት በቁርጠኛነት በመፈጸሙ የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዘግበዋል፡፡   ግብርናው ከኋላ ቀር የአስተራረስ ስርዓት በመላቀቅ ምርታማነታችንን ሊያሳድግ እንዲችል በባለሙያና በቴክኖሎጂ የሚደገፍበትን ስርዓት በመዘርጋት ተንቀሳቅሷል፡፡ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆችን በማቋቋም የግብርና ድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎች በማፍራት የግብርና ልማት ስራችንን ከዘልማዳዊ አሰራር ወጥቶ በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ጥረት ተደርጓል፡፡ አርሶ አደሩ በግብርና ኤክስንቴንሽን ፕሮግራም ተደግፎ መሬቱ ላይ እሴት የሚጨምሩ እንደ ማዳበሪያ ምርጥ ዘር ፀረ አረምና ፀረ ተባይ ያሉ ግብዓቶች በመጠቀሙ በግብርና ምርታማነት ላይ እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡ በዚህም በ1983 . በዋና ዋና ሰብሎች 52 ሚሊዮን ኩንታል የነበረውን አገራዊ ምርታችን 269 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ ተችሏል፡፡ ባለፉት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዳችን አራት አመታት ብቻ በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ 88 ሚሊዮን ኩንታል የምርት ጭማሪ ተገኝቷል፡፡ ከአጠቃላይ የምርት ጭማሪው 95 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመረተው ደግሞ በአነስተኛ የአርሶ አደሩ እርሻ አማካኝነት መሆኑ ኢህአዴግ የተከተለውን  ፖሊሲው ትክክለኛነት ያረጋገጠ ነው፡፡

የተከተልነው ፖሊሲ የጥቂቶችን ጥቅም የቆመ ሳይሆን የብዙሃኑን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ባለፉት አመታት በሰራናቸው ስራዎች በድህነት ሲኖር የነበረው ህዝብ ቁጥር እየቀነሰ ይገኛል፡፡ በ1988 . በገጠር ከሚኖረው ህዝብ 47 ነጥብ 5 በመቶ በድህነት ውስጥ ይኖር የነበረ ህዝባችን ቁጥር አሁን ላይ ወደ 24 በመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡ 
በተሃድሷችን ማግስት ፖሊሲው ሲነደፍ 14 ሚሊዮን ገደማ የነበረው የተረጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ ባደረግነው ርብርብ ቁጥሩ በየዓመቱ እየቀነሰ መጥቶ 2006 ዓመት ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ወርዷል፡፡ ይህ አገራችንን በርሃብና እጇን ለልመና ብቻ የምትዘረጋ አገር አድርገው ለሚስሏት አካላት ማደግ እንደምንችል መልዕክት ያስተላለፍንበትና እይታቸውንም እንዲቀይሩ ያደርግንበት ጭምር ነው፡፡ ኢህአዴግ በቀጣይነት የተረጂዎችን ቁጥር ዜሮ ለማድረስ ሳይታክት ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ሲገልፅ ነገም ከህዝባችን ጋር የድህነትን ተራራ በተባበረ ክንድ ማፈራረስ እንደሚቻል በፅናት በማመን ነው፡፡ በአገራችን እየተረጋገጠ ያለው የግብርና ምርትና ምርታማነት ሀዝቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ተጠቃሚዎች በተጨባጭ ከህይወታቸው ለውጥ ከመጣው ለውጥ ጋር አያይዘው የሚመሰክሩት ሃቅ ነው፡፡ 
ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነትና ከድርቅ ተጽዕኖ ለማላቀቅ ለመስኖ ልማት በሰጠነው ትኩረት ከህዝባችን ጋር በመሆን ስኬቶች በማስመዝገብ ላይ እንገኛለን!!

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣
ሀገራችን በመስኖ የሚለማ ሰፊ መሬት አላት። ይሁንና መስኖ 1984 . በፊት ትኩረት ያልተሰጠውና አጠቃላይ ሽፋኑም 61 ሄክታር የማይበልጥ ነበር። ኢህአዴግ ባለፉት አመታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ የመስኖ ልማቱ እየተስፋፋ መምጣት ችሏል። በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቷ 5 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ከኩሬ፣ ከዝናብ፣ ከወንዝ ጠለፋና በጉድጓድ ቁፋሮ ላይ የተመሰረተ የመስኖ ውሃ አማራጭ ይጠቀማሉ። አርሶ አደሮቹ የውሃ አማራጮቹን ተጠቅመው መስኖ በማልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ናቸው።
በኢህአዴግና በአጋር ድርጅቶች በተሰሩ ስራዎች የአርብቶ አደሮች ተጠቃሚነትም የሚያረጋግጡ ስኬቶች እተመዘገቡ ነው፡፡ አርብቶ አደሮቻችን ውሃ ባለባቸው አካባቢዎች በቋሚነት በመስፈራቸው ተረጋግተው መኖር ጀምረዋል። ይህ ደግሞ ለአርብቶ አደሩ ህዝባችን የማህበራዊ ተቋማትን ለመገንባት፣ የሙያና የአመራር ድጋፍ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።
የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ሃብትን መሠረት ያደረገ የመንደር ማሰባሰብ ስራን በማከናወን ተበታትኖ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር አስቸጋሪ ኑሮ የሚገፋውን አርብቶ አደር አንድ ስፍራ ተረጋግቶ ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት ኑሮ እንዲቀየር በስትራቴጂያችን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል። አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በምንፈፅማቸው ስራዎች ዙሪያ የተቃውሞ ድምፃቸውን የሚያሰሙ ኃይሎች የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም መተግበር ባህላዊ የአኗኗር ዘይቤን ያጠፋል ብለው ይከራከራሉ። 

አገራችን ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት ቁጥር ካላቸው አገሮች አንዷ ነች፡፡ ይሁን እንጂ የብዛቱን ያክል በኢኮኖሚ ላይ ፋይዳ ባለው ሁኔታ ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል፡፡  የእንስሳት ሃብት ልማት ዘመናዊ በሆነ የአረባብ ዘዴ በመጠቀም ኢኮኖሚያችንን የምናሳድግብት አንድ መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ግልፅ አቅጣጫ በማስቀመጥ የእንስሳት ዝርያዎችን በማቅረብና በማሻሻል፣ መኖና ውሃ በማቅረብ፣ የእንስሳት ጤና እንክብካቤን በማስፋፋት ተንቀሳቀስናል። በዚህም በዘርፉ ስኬቶች መመዝገብ ጀምረዋል፡፡ ይሁንና አሁንም  ከዘርፉ ማግኘት የሚገባንን ኢኮኖሚያዊ ጠቃሜታ በሚፈለገው ደረጃ  ያላረጋገጥ በመሆኑ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የጀመርነው ስራ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡ የእንስሳት ልማት ስራውን ከተፋሰስ ልማቱ ጋር በማስተሳሰር የልቅ ግጦሽን ደረጃ በደረጃ በማስቀረትና ይህንኑ ለማሳካትም ተያይዘው መፈፀም ያለባቸው የዝርያ ማሻሻል፣ የመኖ ልማትና የእንስሳት ጤና ሥራዎች አጠናክር እንቀጥላለን፡፡
በተፈጥሮ ሃብት ልማት የተመዘገቡት ስኬቶች የህዝባችን የተባበረ ክንድና የኢህአዴግ የጠራ ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው!!

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣
የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራችን የግብርናችን መሠረትና የህዝባችን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ኢህአዴግ ይገነዘባል። በመሆኑም ለውድመት ተዳርጎ የቆየው የተፈጥሮ ሃብታችን መልሶ እንዲያገግም በአፈርና ውሃ ጥበቃ ትኩረት በመስጠት ከህዝባችን ጋር በጋራ ሲረባረብ ቆይቷል። የአረጓዴ ልማት ስትራቴጂ ቀርጸን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የሚያስችል አቅጣጫ በመከተል ላይ እንገኛለን
የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራችን በሀዝብ ፍላጎት ላይ በተመሰረተ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት ብቻ በአማካይ 16 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ የተሳተፈበት ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ፈጥሮ ሃብት ላይ ባደረግነው ርብርብ ደርቀው የነበሩ ምንጮችና ሀይቆች ወደ ነበሩበት መመለስ ጀምረዋል። ጠፍተው የነበሩ አገር በቀል ዛፎች መብቀል ጀምረዋል፡፡
1999 . ባወጣነው የደን ፖሊሲ፤ የግል ደን ልማትና ጥበቃ፣ የደን ልማት ቴክኖሎጂና የደን ገበያ ልማት እንዲስፋፉ እንዲሁም የደን ሃብት ከተለያዩ ጥፋቶች እንደጠበቅ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል። የተሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ በተከናወኑት ስራዎች በአሁኑ ወቅት የሀገራችን የደን ሽፋን እጅግ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ አሽቆልቁሎ ከነበረበት 3 በመቶ ወደ 15.5 በመቶ አድጓል። በዚህ የተነሳ ከየአካባቢዎች ሸሽተው የነበሩ የዱር አራዊቶችም ተመልሰው መታየት ጀምረዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራችን የህዝብ ተጠቃሚነትንም እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ በቀጣይነት ልማቱን ይበልጥ ለማስፋፋትና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በስልጠና የታገዘ ድጋፍ የመስጠትና ደጋፊ ቴክኖሎጂዎችን የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣
በአጠቃላይ በግብር ልማት መስኮች አንፀባራቂ ድል ማስመዝገብ የቻልነው መላ አርሶ አደራችንና አርብቶ አደራችን ፊታቸውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማት እንዲያዞሩ ያደረገ ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሰን በመረባረባችን ነው።  የአገራችን ተቃዋሚዎች ይህን የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ የግብርና ልማት በገሃድ የሚታይ እውነታ በመካድ ሲያጥላሉት ይታያል፡፡ አማራጭ ብለው የሚያቀርቡት ሃሳብም ብዙሃንኑ የሚጠቅም ሳይሆን ለጥቂቶች የወገነ ነው፡፡ 

ለዚህም ነው ኢህአዴግ መምረጥ የህዝብ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ፣ ፈጣንና ቀጣይነት ልማት ማስቀጠል ነው የምንለው፡፡ ለዚህም ነው የአገራችን ህዝቦች ዋነኛ ጠላታቸው በሆነው ድህነትን ላይ የጀመሩትን ትግል አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚቻለው በኢህአዴግ ትክክለኛ መስመር፣ ፖሊሲና ቁርጠኛ አመራር ነው የምንለው፡፡ 

በግብርናና ገጠር ልማት የተመዘገበውን አንፀባራቂ ድል በመጠበቅና አጠናክሮ በማስቀጠል የአገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ኢሕአዴግን ይምረጡ!!

No comments:

Post a Comment