ኢህአዴግ
በሀገራችን የመሰረተ ልማት መስፋፋት ለአጠቃላይ አገራዊ ልማት ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ ከግምት በማስገባት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ
በትጋት እየሰራ ይገኛል። መሰረተ ልማት በሀገራችን አንድ ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር፣ የአገራችን ኢኮኖሚ በአለም ተወዳዳሪ
እንዲሆን በማድረግና በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገት ለማምጣት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ኢህአዴግ በሚመራው ልማታዊና
ዴሞክራሲዊ መንግስት ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
እንደሚታወቀው
ከዛሬ 23 አመት በፊት የሀገራችን መሰረተ ልማት ለአብዛኛው ህዝብ ተደራሽ ያልነበረ፣ የነበሩትም በጥገና እጦት ተገቢውን
አገልግሎት መስጠት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ የደረሱበት ሁኔታ ነበር፡፡ የ24 አመታት ጉዟችን የጀመረው እጅግ ከፍተኛ የሚባል
የመሰረተ ልማት ክፍታት ከነበረው ሀገራዊ ሁኔታ በመሆኑ በዘርፉ ያስመዘገብነው ውጤት የሞት የሽረት ትግል የጠየቀ ነበር፡፡ የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራ ከፍተኛ የካፒታል፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና
ማሽነሪ የሚጠይቅና በሀገራችን እነዚህ ሁኔታዎች ተሟልተው የማይገኙበት መሆኑ ሌላው ፈታኝ ሁኔታ እንደነበር ማንም በቀላሉ
የሚገነዘበው እውነታ ነው። የመሰረተ ልማት ስራ በአብዛኛው በግል ባለሃብቱ ሊሞላ ስለማይችል በመንግስት ትክሻ ላይም የወደቀ
ነበር፡፡ በኢህአዴግ በሚመራው መንግስት የመሰረተ ልማት ለአጠቃላይ ልማታችን ካለው ቁልፍ ሚና አኳያ የነበሩ ፈታኝ ሁኔታዎችን
በጽናት በማለፍ በዘርፉ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡
በመሰረተ
ልማት ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል በመንገድና በሌሎች የትራንስፖርት መስኮች የተመዘገበው ተጠቃሽ ነው፡፡ በትራንስፖርት መሰረተ ልማት
የተመዘገበው ስኬት ኢህአዴግ በእርግጥም ልማትን ለማረጋገጥ ከሰፊው
ህዝብ ጋር ሆኖ ሌት ተቀን የሚተጋ፣ ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ ለማድረግ የቆረጠ እንደሆነ ማሳያ ተደርጎ የሚቀርብ ነው።
ኢህአዴግ መላ ሀገሪቱን በትራንስፖርት መረብ በማስተሳሰር አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ
በመንገድ፣ በአየር፣ በባቡርና በመርከብ ትራንስፖርት ልማት ዘርፍ አንጸባራቂ ድል አስመዝግቧል።
የመንገድ
ግንባታ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ ቢሆንም ዘርፉ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመነሳት የኢትዮጵያን የመንገድ አውታር
መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር የመገንባት ራዕይ ሰንቆ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም መሰረት በ1983ዓ.ም
በመላ ሀገሪቱ 18 ሺ 81 ኪሎ ሜትር ብቻ የነበረው የመንገድ አውታር በአሁኑ ወቅት በብዙ እጥፍ አድጎ ከ105
ሺ ኪ.ሜ በላይ
ሆኗል። ባለፉት 24 ዓመታት የመንገድ አውታር በአማካይ በዓመት
ከ16% በላይ እያደገ መጥቷል፡፡ ያለፉት አራት ዓመታትን ብቻ ለይተን ካየን ደግሞ የሀገሪቱ የመንገድ አውታር ከእጥፍ በላይ
አድጓል፡፡ 10 ሺ 765 የገጠር ቀበሌዎችን ከዋና መንገዶች ጋር ማገናኘት ተችሏል። በዚህም
አርሶ አደሩ ለምርቱ የሚፈልገውን ግብዓትም ሆነ የሚያመርተውን ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል።
ባለፉት
አመታት ከፍተኛ ለውጥ በመመዝገብ ላይ ከሚገኝባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የባቡር ትራንስፖርት ልማት ስራ ነው። ምንም እንኳን ሀገራችን
ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የጀመረች ቢሆንም ዘርፉ በበርካታ ተግዳሮቶች ተተብትቦ
ቆይቶ በመጨረሻም ተንገራግጮ ቆሞ ነበር። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ 2 ሺህ 395 ኪሎ
ሜትር የባቡር መስመር ለመዘርጋት ታቅዶ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው። የአዲስ አባባ የቀላል ባቡር ፕሮጄክት ከ95 በመቶ በላይ
ተጠናቅቆ የፍተሻና ሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ ጂቡቲ መስመር የተጀመረው የባቡር መንገድ ግንባታም በተያዘለት
እቅድ እየተፈፀመ ይገኛል። የባቡር መስመር ዝርጋታው የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በማቃለል እንዲሁም በኢኮኖሚያችን በተለይ
የወጪና የገቢ ንግድ በማፋጠን ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል። የባቡር ልማት ከፍተኛ ካፒታልና ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ በመሆኑ የባቡር
ፕሮጀክቶቻችን እየገጠማቸው ያለውን የፋይናንስ እጥረት ፈተናዎች እየፈታን በመረባረብ ላይ እንገኛለን፡፡
በ24 አመታት ጉዟችን እመርታዊ ለውጥ
ከተመዘገበባቸው የመሰረተ ልማት ዘርፎች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ልማታችን አንዱ ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት
በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ የሚዘልቅ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ የዜጎችን ህይወት
ለመቀየርና የአኗኗር ዘይቤአቸውን ለማዘመን፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ
ምርት ለማቅረብና ዘላቂ
የኢንዱስትሪ ዕድገት ለማረጋገጥ ያለው ድርሻ የላቀ መሆኑን
የሚያምነው ኢህአዴግ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቁርጠኝነት እየፈታ እመርታዊ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ
ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል ልማታችን የየወቅቱን
ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የሀገራችንን ፈጣን ዕድገት ቀጣይነት በሚያረጋግጥ መልኩ ራዕይ የሰንቀ ነው።
በሀገራችን የኤሌክትሪክ ሀኃል ማቅረብ ከተጀመረ
ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ቢቆጠርም እስከ 1983 ዓ.ም በሀገራችን የነበረው የኃይል አቅም ከ370 ሜጋ ዋት ያልበለጠ ነበር። በዚህ ምክንያትም ትንንሽ ከተሞችና
ገጠሮች ቀርቶ ለዋና ዋና ከተሞችም ቢሆን የኤሌክትሪክ
ኃይል አቅርቦትን በተሟላ መልኩ ማቅረብ የማይታሰብ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። በአሁኑ
ወቅት 2 ሺህ 313 ሜጋ ዋት ማመንጨት የተቻለ ሲሆን በያዝነው አመት መጨረሻ ግንባታው የሚጠናቀቀው የጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ
ኃይል ማመንጫ 1 ሺህ 870 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ከ4 ሺህ በላይ ከፍ ያደርገዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ
ኃይል ማመንጫ ግድብ ጨምሮ የሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታ ሲጠናቀቅ ሀገራችን 10 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት ደረጃ ላይ ትደርሳለች።
ከኃይል
ልማታችን እጅግ ገዝፎ የሚታየው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአይቻልም አስተሳሰብን የሰበረ፣ ታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ
ዜናዊ እንዳለውም መሃንዲሶቹም፣ ግንበኞችም፣ የፋይናንስ ምንጮችም እራሳችን ሆነን እየገነባነው ያለ የህዳሴያችን ታላቅ ፕሮጀክት
ነው። ህዝቡ ከዳር ዳር ተነቃንቆ ለግድቡ ግንባታ አቅሙ የፈቀደውን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። ይህም ለሀገራችን በጎ
የማያስቡ አካላትን አስደንግጧል። የግድቡ መሰረት ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ የማጥላላት ዘመቻ በማድረግ ላይ የሚገኙት የውጭ ኃይሎችና
የሀገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸው ምን ያህል ከህዝብ ፍላጎት ያፈነገጠ አስተሳሰብ እንዳላቸው ያጋለጠ ታላቅ ፕሮጀክትም ሆኗል።
ከኤሌክትሪክ ኃይል ልማታችን
ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው የሚያምነው ድርጅታችን ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ “የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁሉም” በሚል መርሀ የገጠር ኤሌክትሪፌኬሽን
ፕሮግራም በመንደፍ ከተወሰኑ ከተሞች ውጪ የማይታሰብ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለገጠሩ ህዝባችንም እንዲዳረስ
በማድረግ ላይ ነው። ፕሮግራሙ ሲጀመር ከ648 ያልበለጡ ተጠቃሚ ከተሞችና ከ17 በመቶ ሽፋን ያልበለጠ የነበረው በአሁኑ ሰዓት 5
ሺህ 100 በላይ የከተማና የገጠር ቀበሌዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ሽፋኑም 54 በመቶ ያህል ለማድረስ ተችሏል።
በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ያስመዘገብናቸው ስኬቶች አልጋ በአልጋ የተገኙ
ሳይሆን በርካታ ፈተናዎችንና ችግሮችን ተጋፍጦ በማለፍ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ዘርፉ የሚፈልገው ከፍተኛ ካፒታል አኳያ የፋይናንስ
እጥረት ዋነኛው ፈተና ነበር፡፡ የኒዮሊበራል ኃይሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቻችን የውጭ ብድር እንዳያገኙ
ባደረገበትና በእራሳችን አቅም የገነባናቸው ከመሆኑ አኳያ ሲታይ ኢህአዴግ እና የሚመራው መንግስት ለልማቱ የሰጡት ትኩረት ከፍተኛ
መሆኑን ያሳያል፡፡
በኤሌክትሪክ አገልግሎት በአንድ በኩል ልማቱ ተደራሽ ባልሆኑባቸው
አካባቢዎች የልማቱ ተጠቃሚ የመሆን ጥያቄ በሌላ በኩል አገልግሎቱ በተዳረሰባቸው አካባቢዎች ከኃይል መቆራረጥ ጋር ተያይዞ
ቅሬታዎች እንዳሉ ኢህአዴግ ይገነዘባል፡፡ የህዝቡን ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ለመፍታት ልማቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም
ይገነዘባል፡፡ የኃይል መቆራረጡንም በአስተማማኝ መፍታት የሚያስችል እቅድና አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ችግሩን
ለመፍታት ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ
ከተንቀሳቀሰባቸው የመሰረተ ልማት መስኮች ሌላው የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ የተፋጠነ
የንግድ ልውውጥ ለማረጋገጥ፣ መንግስት የሚሠጣቸውን አገልግሎቶች ቀልጣፋ ለማድረግና የመንግስትን አሰራር ግልጽ ለማድረግ
የሚጫወተው ሚናም የጎላ ነው፡፡ ወጣቶች፣ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ዘመናዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ለራሳቸውና ለሀገራቸው
አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ያስችላል፡፡ በአጠቃላይ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለልማታዊና ዲሞክራሲ ግባችን መሳካት
ከፍተኛ ድርሻ በማበርከት የህዝብ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን
በማመን ኢህአዴግ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል፡፡
በ1982 ዓ.ም
በመላ ሀገሪቱ የነበረው የቴሌኮም ደንበኞች ቁጥር 56
ሺህ 557 ብቻ ነበር። አሁን በተንቀሳቃሽ ስልክ ብቻ 33 ሚሊዮን፣ በመደበኛ ቴሌፎን ደግሞ 820 ሺህ እንዲሁም በዳታና በኢንተርኔት አገልግሎት 8 ሚሊዮን ደንበኞች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከምንም የተነሳው የገጠር ቴሌኮም ሽፋን በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ ይህም የሀገራችን አርሶ አደሮችና
አርብቶ አደሮች ከፈጣን ሀገራዊ ዕድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ ነው።
የውጭ የኒዮሊበራል ኃይሉና የውስጥ ተላላኪዎች መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን ወደ ግል እንዲያዞር ያልፈነቀሉት
ድንጋይ የለም። አብዛኛዎቹ የሀገራችን ተቃዋሚዎችም የቴሌኮም አገልግሎት ለግሉ ዘርፍ እንዲሸጥ አቋም ያላቸው ናቸው፡፡ የሀገር
ውስጥ ባለሀብት አቅም ባልጠነከረበት፣ ዘርፉ የሚጠይቀው መሰረተ ልማት ባልተሟላበት እንዲሁም የህብረተሰቡ የመግዛት አቅም ገና
ባልዳበረበት ነባራዊ ሁኔታ ተቃዋሚዎች ይህን መሰል አቋም መያዛቸው ውግንናቸው ከህዝብ ጋር እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ በቂ ማሳያ
ነው። መንግስት በልማቱ በመሳተፉ ከፍተኛ የቴሌኮሙዩኒኬሽን መሰረተ ልማት በመዘርጋት በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበው በተለይ
ከልማቱ ርቆ የቆየውን የገጠር ህዝብ ጭምር ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለው፡፡
የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ተደራሽነትን በዘላቂነት
ማረጋገጥ ማለት የገጠርና የከተማ ህዝባችን ከሀገሪቱ እድገት
ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ የሀገራችንን እድገት ቀጣይነት የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ኢህአዴግ የገፀ ምድርና
የከርሰ ምድር የውሃ ሃብቶቻችንን በአግባቡ በማልማትና በማጎልበት የህዝባችንን የኑሮ ደረጃ በቀጣይነት ለማሻሻል በሚያስችል
መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል ዘርፈ ብዙ ስራዎችን አከናውኗል፣ በማከናወን ላይም ይገኛል። የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና
ተደራሽነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ስኬት
ተመዝግቧል፡፡ በዘርፉ በተካሄደው ልማት የሴቶችን የስራ ጫና በማቃለል እንዲሁም ዜጎቻችን ከውሃ ወለድ በሽታዎች ጋር ተያይዞ
ይገጥም የነበረው የጤና ጠንቅም እየቀነሰ ይገኛል።
ዘርፉ ከነበረበትና
አሁን ከደረሰበት
አንፃር
ሲመዘን
ጉልህ የሚባል
ስኬት ተመዝግቦበታል፡፡
ሆኖም ፈጣኑ እድገታችን ሰፊና የማይቋረጥ
ፍላጎት
የሚጠይቅ
ከመሆኑ
ጋር ተያይዞ
አሁንም
ሰፊና ተከታታይ
ስራ የሚፈልግ
ዘርፍ ነው፡፡
አሁንም በልማቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ ዜጎች ያሉ መሆናቸውና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ
ከሆኑትም በከተሞች እየመጣ ካለው ከፍተኛ ልማት ጋር ተያይዞ የአገልግሎት መቆራረጥ የሚያጋጥም መሆኑን በመገንዘብ ችግሩን
ለመቅረፍ ርብርብ በመደረግ ላይ ሲሆን ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ግዙፍ
የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ስናካሂድ ልማታችን ከጎረቤቶቻችን ጋር የሚኖረውን ትስስርም ከግምት ውስጥ አስገብተናል። የባቡር
መስመር ዝርጋታችንን ስናስብ ሀገራችንን ከጅቡቲ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከኬንያ ጋር በማስተሳሰር የወጪና የገቢ ንግዳችንን
እንዲያሳልጥና ከሀገራት ጋር ያለን ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገርን ታሳቢ በማድረግ ነው። የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቻችን
ፋይዳ አገራችንን ከብክለት ነፃ የሆነ ኃይል በማምረት ከራሷ አልፋ ለጎረቤቶቿ ኃይል የምታቀርብ ጠንካራ ሀገር መገንባት ነው።
የአውራ መንገዶች ግንባታችን ጎረቤቶቻችን ጋር በየብስ ትራንስፖርት በማስተሳሰር ላይ ይገኛል። አየር መንገዳችን ከአካባቢው
አልፎ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት በማስተሳሰር ላይ የሚገኝ የሀገራችንንና የአህጉራችን ኩራት ሆኗል።
ሀገራችንን
በመሰረተ ልማት ከጎረቤቶቿ ጋር የሚኖራት ትስስር የሀገራችን
ልማት እነሱንም ጭምር የሚጠቅም መሆኑን በተግባር አይተው ከእኛ ጋር አብሮ ማደግን እንዲያልሙ እኛም ከፍተኛ የሆነ የውጭ
ምንዛሪ በማግኘት ለቀጣይ ዕድገት ተጨማሪ አቅም እንድናገኝ ያስችለናል። በሀገራችንና በቀጣናው ሀገራት መካከል በመተማመን ላይ
የተመሰረተ፣ ለሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት የሚሰጥ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠርም ያስችላል።
የሀገራችን
ተቃዋሚዎች ከመሰረተ ልማት ግንባታዎች በተለይም ከቴሌኮምና ከመብራት ጋር በተያያዘ በጊዜያዊነት የሚያጋጥመውን የአገልግሎት
መቆራረጥ ችግር እንደ መሰረታዊ የፖሊሲ ችግር አድርገው አጣመው በማቅረብ መንግስት የሚያደርጋቸውን የልማት ስራዎች ጥላሸት
መቀባት የተለመደ ተግባራቸው ሆኗል። መንግስት ከመሰረተ ልማት
ግንባታዎች እጁን እንዲያወጣ ከውጪ አዛዦቻቸው ጋር በመሆን የተለያየ ጫናዎችን ለመፍጠር ይሞክራሉ። የሀገራችን ተቃዋሚዎች ህዝቡ
በገሃድ የሚያውቃቸውን በመሰረተ ልማት የተመዘገቡ ስኬቶችን ሸምጥጠው ይክዳሉ፡፡ አማራጭ ብለው የሚያቀርቡትም ሀገራችን የውጭ ኃይሎች
መፈንጫ እንድትሆን የሚያደረግና የተጀመረውን ለውጥ ወደኋላ የሚመልስ የውድቀት መንገድ ነው፡፡
ሁሌም
ተጠሪነቱና አገልጋይነቱ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ብቻ የሆነው ኢህአዴግ ግን አሁንም በጠራ መስመሩ እየተመራ በስኬት ጎዳና ላይ በመገስገስ
ለተሻለ ለውጥና ስኬት እንደሚሰራ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል።
ኢህአዴግ
እንደሌሎች ዘርፎች ሁሉ በመሰረተ ልማቱም ረገድ ያሉትንን እጥረቶች ከመላ ህዝባችንን ጋር በመሆን እንደሚፈታቸው እርግጠኛ ነው።
በቴሌኮም አገልግሎት ዙሪያ ሲያጋጥም የነበረው መቆራረጥ ከሞላ ጎደል የፈታንበትና አሁንም የሰለጠኑ ሀገሮች የሚጠቀምበትን በዘርፉ
አራተኛ ትውልድ ቴክኖሎጂ መዘርጋት መጀመራችን ከጊዜያዊ ችግሮች ማዶ ዘላቂ መፍትሄዎችን ቀርጸን የመተግበር ብቃታችንን የሚያሳይ
ነው። በመብራት ኃይል መሰረተ ልማት በኩል የሚታየውም የኃይል መቆራረጥ በህዝባችን ቅሬታ እንደፈጠረ ኢህአዴግ ይገነዘባል። ችግሩን በአስተማማኝ
ሁኔታ ለመፍታት የሚስችል እቅድ ተዘጋጅቶ ችግሮችን ለመፈታት የሚያስችል
ስራ እየተሰራ ሲሆን ልማቱን በማፋጠን ችግሮቹን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍታት ኢህአዴግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ሊያረጋግጥላችሁ
ይወዳል፡፡
ኢህአዴግ
በሌሎችም መሰረተ ልማት ስራዎቻችን የሚታዩ የጥራት ጉድለቶችንም በአግባቡ በመረዳት መፍትሄዎችን አስቀምጦ በመረባረብ ላይ
ይገኛል። እነዚህ ችግሮች በፈጣኑ እድገታችን ውስጥ የሚጠበቁና አንዳንዶቹም በአፈፃፀም ሂደት የሚፈጠሩ እንጂ የፖሊሲና የአቅጣጫ
ችግር እንዳልሆኑ በመረዳት ህዝባችንም ከጎናችን በመሆኑ ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ የሚቀረፉበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ኢህአዴግ
ያረጋግጣል።
በመሰረተ
ልማት አንጸባራቂ ስኬቶችን ያስመዘገበውንና የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ቁርጠኛ የሆነውን ኢህአዴግን በመምረጥ የህዳሴ ጉዟችን
አጠናክረን እናስቀጥል፡፡
ኢህአዴግን ይምረጡ፣ ምልክታችንም ታታሪዋ
ጣፋጩን ማርን የምትሰራው ንብ ነች!!
No comments:
Post a Comment