በህዝቦች የተደራጀ የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ተመስርቶ
መልካም
አስተዳደርን
ለማስፈን በመትጋት ላይ ያለ ድርጅት -ኢሕአዴግ!
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ባለፉት ስርዓቶች ዜጎች በዘር፣
በሃይማኖት፣ በብሄር፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በሀብትና በሌላ አቋማቸው ምክንያት ሲደርሱባቸው በነበሩ የተለያዩ
ጭቆናዎች ለከፋ እንግልትና ስቃይ ሲጋለጡ ቆይተዋል። በአካባቢያቸውና በአገራቸው ጉዳይ ላይ በጋራ የመወሰን ብሎም በአገሪቱ ከሚፈራው
ሃብት እኩል የመጠቀም መብት ያልነበራቸው በመሆኑ በገዛ ቀዬያቸውና አገራቸው ለሚከናወኑ ጉዳዮች ሁሉ ባይተዋር ሆነው ኖረዋል። በዚህም
ሳቢያ እንኳንስ በአገራቸው ጉዳይ ሊሳተፉና ጥቅሞቻቸውን ሊያስከብሩ እንዲሁም የጋራ መግባባት ሊፈጥሩ ቀርቶ በህይወት የመኖር መብታቸውን
ማረጋገጥ ያልቻሉ በመሆናቸው ጨቋኞቹን ስርዓቶች ለማስወገድ የትጥቅ ትግልን ብቸኛ አማራጭ አድርገው የስልጣን ባለቤትነታቸውን ለማረጋገጥ
እልህ አስጨራሽ ትግል አካሂደዋል፤ ከፍተኛ መስዋዕትነትም ከፍለዋል።
ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶቻቸውን
በማስከበር በጋራ ሀብታቸው ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል እድል የተነፈጋቸው የሀገራችን ህዝቦች ያደረጉት ትግል ለፍሬ ከበቃ በኋላ
በኢትዮጵያ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች የአገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መሆናቸው በቃል ኪዳናቸው ሰነድ በሆነው ህገ መንግስት
ላይ በይፋ ተደንግጓል። ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በተግባር እንደታየውም ሁሉም ዜጎች በአገራቸው ያለምንም ልዩነት እኩል የመሳተፍና
እኩል የመጠቀም መብታቸው ዋስትና አግኝቷል።
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ እንዳለፉት ስርዓቶች በኃይልና በእኔ አውቅልሃለሁ ባይነት
ሳይሆን ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማካኝነት በሚያስተላልፈው ውሳኔ የህዝቡን ይሁንታ ያገኘ ሃይል ብቻ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበት
ስርዓት ተዘርግቷል። ዜጎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ከሚኖራቸው የስልጣን ባለቤትነት በመለስ በአካባቢያዊ ጉዳዮቻቸው ላይ በጋራ
የሚመክሩባቸውና ውሳኔ የሚያሳልፉባቸው መድረኮችም ተፈጥረዋል። ለረጅም ዘመናት የአገራችን ህዝቦች የመልካም አስተዳደርና የፖለቲካ
ጥያቄ ሆኖ የቆየውን አንዱ ከሌላው የበላይ ሆኖ የመጠቀም ዝንባሌና በተቃራኒው ሌላው የበይ ተመልካች ሆኖ የሚጎዳበትን አድሏዊ አሰራር
ከመሰረቱ በማስወገድ ዜጎችን በአገራቸው፣ በክልሎቻቸው፣ በከተሞቻቸውና በአካባቢያቸው የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ወሳኝ
መሆን የቻሉበት አስተማማኝ ስርዓት የተገነባው በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ነው።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ባለፉት 23 ዓመታት የአገራችን ህዝቦች በተሳትፎአቸው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በማስከበርና
አገራቸውን በተሻለ ፍጥነት በማሳደግ ዘላቂ ልማትና እድገታቸውን እንዲያጠናክሩ የህዝቦች ተሳትፎ የዳበረበት መልካም አስተዳደርን
ለማስፈን በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። አጥጋቢ ውጤቶችም ተገኝተዋል። በእነዚህ ዓመታት የሀገራችንን ልማትና ዴሞክራሲ በጠንካራ
መሰረት ላይ መገንባት ያስቻለና ህዝቦችን ተሳታፊ ያደረገ የመልካም አስተዳደር ግንባታ በየደረጃውና በየአካባቢው ተካሂዷል።
የህዝቡ ተጠቃሚነት በራሱ በህዝቡ ተሳትፎና ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎለብት የህዝብ አደረጃጀቶች ከቀበሌ
እስከ ፌዴራል ፓርላማ በስፋት ተደራጅተዋል። ዜጎች በአካባቢያቸው
የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በመሆንና ውሳኔ በማሳረፍ የመብቶቻቸው ባለቤት ራሳቸው
መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
የገጠሩ ህዝባችን ተሳትፎ ጎልቶ
ከሚስተዋልባቸው አደረጃጀቶች የልማትና የ1ለ5 አደረጃጀቶች ይጠቀሳሉ። በዚህ የልማት ሰራዊት አደረጃጀት በተለይ አርሶ አደሩ የልማት
ተሞክሮ ልውውጥ በማድረግ በየመንደሩ በልማትና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያየና ውሳኔ እየሰጠ ለራሱና ለአካባቢው ልማት
መጎልበት የበኩሉን እንዲወጣ በመደረግ ላይ ነው። በእነዚህ አደረጃጀቶች አማካኝነት በአገራችን ገጠሮችና ከተሞች ህዝቡ በመልካም
አስተዳደር ጉዳዮች በዕቅድ ዝግጅት፣ በተግባር አፈፃፀም፣ በክትትልና ድጋፍ ራሱ ተሳታፊ ሆኖ የሚወስንባቸው ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።
ባለፉት አመታት በገጠር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራው በአመት በአማካይ 16 ሚሊዮን ህዝብ በአማካይ እስከ 30 ቀናት በፍላጎቱ ተደራጅቶ
ተአምር የሚባል ስኬት አስመዝግቧል፡፡ በገጠር መንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም እንደዚሁ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ውጤታማ
ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በከተሞችም ነዋሪዎች በነዋሪዎች ፎረምና ሌሎች አደረጃጀቶች አማካኝነት በአካባቢያቸው ልማትና አስተዳደራዊ
ጉዳዮች በጋራ በመወያየት፣ ውሳኔ በመስጠትና በመሳተፍ የልማት ስራዎችን እያከናወኑ ነው። በከተሞች አብዛኛዎቹ የመንገድ እና ሌሎች
መሰረተ ልማቶች በከተማ ነዋሪዎች ተሳትፎ እየተካሄዱ ሲሆን በፅዳትና ውበት፣ በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የፀጥታ ማስከበር ስራዎች
ነዋሪዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
የመልካም አስተዳደር ማስፈን ስራን ስኬታማ ለማድረግ በአመለካከት፣ በአቅምና
ከሁሉም በላይ በህዝቦች ተሳትፎ የደረጀ እንቅስቃሴና ግንባታ ማድረግን ይጠይቃል። ከዚህም አኳያ የተግባር አፈፃፀሙ በርካታ
ዓመታትን የሚጠይቅ መሆኑን ጨምሮ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩ እንዲሁም ሀገራችን ካለባት የማስፈፀም አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ዘላዊ
መፍትሄ ሊበጅላቸው የሚገባ ጉዳዮች እንዳሉ አያጠራጥርም። መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉና በሂደት
የሚከናወኑ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግስት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችልም
ኢህአዴግ በጥልቅ ያምናል። ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት ያለው የመልካም አስተተዳደር ትግበራ አፈፃፀማችን የአቅም ውስንነትን ተሻግሮ
መሻሻል እያሳየ እንደሆነ ቢገነዘብም የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሁንም እንዳሉ በመረዳት ችግሮቹን ለመፍታት ከህዝቡ ጋር
በመሆን እየሰራ ይገኛል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተሟላ ሁኔታ መቅረፍ የምንችለው በየጊዜው እያደገ
የሚሄደውን የህዝባችንን የመልማት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ልማታችንን ከዚህም በላይ ማፋጠን ስንችል እንደሆነ ኢሕአዴግ ያምናል።
ከመልማት ፍላጎት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ከህዝቡ ጋር በመወያየት በእቅድ ለመፍታት የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን
መቀጠል እንዳለብንም እንገነዘባለን። ከፍተኛ ልማት እየተካሄደባት ባለችውና ህዝቡ በስፋት ተሳታፊ በሆነበት አገራችን ልማቱ
የሚመልሰው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች
በአስቸኳይ መፈታት እንዳለባቸው ተገንዝቦ ኢሕአዴግ ለመፍትሄው እየሰራ ይገኛል። ችግሮቹ በተፋጠነ ልማትና በጠነከረ የህዝቦች
ተሳትፎ ምላሽ እንደሚያገኙም ያምናል።
ኢሕአዴግ እጅግ በርካታና የተወሳሰቡ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ካለፉት ስርዓቶች
የተረከበ ቢሆንም ስር ሰድዶ የቆየውን የአስተሳሰብና የተግባር ችግር መቅረፍ ሰፊ ጊዜ ይጠይቃል ብሎ ሳይወሰን ችግሮቹን ለማስወገድ
በየደረጃው ተገቢ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን እርምጃዎች ወስዷል፤ በመውሰድ ላይም ይገኛል። ከአስተሳሰብ አኳያ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖሊቲካዊ
ኢኮኖሚን በልማታዊነት ለመተካት እያደረገ ያለው ጥረትም ከወዲሁ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገብ ጀምሯል፤ ይሕ ወደፊትም ተጠናክሮ
ይቀጥላል።
እነዚህ ዕውነታዎች መልካም አስተዳደር በሂደት ስር የሚሰድ እንዲሁም እያበበ የሚጎመራ
መሆኑን የሚያላክቱ እንጂ በተቃዋሚው ጎራ ሲነገር እንደሚሰማው ሁሉ ነገር ያልተሰራ ወይም ሁሉም ነገር ዛሬ መፈታት ይችላል
የሚል በጥናትና ሳይንሳዊ ትንታኔ ላይ ያልተመሰረተ “የሱሪ በአንገት” ብሂል ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል የሚያረጋግጡ ናቸው። በሀገራችን እየተገነባ ያለው የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስርዓት
በጊዜ ዑደት ውሰጥ አሁን ካለውም በላይ እየጎመራ መሄዱ እንዳለበት ኢህአዴግ ጽኑ አቋም አለው። በተለይ የልማታችን
መፋጠን በየዘርፉ ያለውን አገልግሎት በማሻሻልና ተደራሽነቱን በማሳደግ የህዝባችን ተጠቃሚነት ይበልጥ እንደሚረጋገጥ ኢህአዴግ
በፅኑ በመረዳት በዘርፉ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል። ለዚህም መላው ህዝብ ዛሬም እንደትላንቱ ለመልካም አስተዳደር
መስፈን ከኢህአዴግ ጋር በመሆን እንዲረባረብ ጥሪውን ያቀርባል።
ልማታችን በማፋጠን፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራር በማጠናከር ከመላ የአገራችን
ህዝቦች ጋር በመሆን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተዘገጀውን ኢህአዴግን ይምረጡ
ምልክታችን መልካም መዓዛ ካለው አበባ ጣፋጭ ማር የምታመርተው ታታሪዋ ንብ ነች።
No comments:
Post a Comment