የመልካም አስተደዳር ስኬቶችን በማጎልበት ድክመቶችን በማረም ለቀጣይ ለውጥ የተዘጋጀ ድርጅት - ኢህአዴግ
ኢህአዴግ መልካም አስተዳደር በሀገራችን ፈጣን ልማት ለማረጋገጥና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደታችንን ለማሳካት ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አበክሮ ይገነዘባል። ልማት፣ ሰላም ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ለሀገራችን ህዝቦች ለምርጫ የማይቀርቡ የህልውና ጉዳዮች መሆናቸውንም በፅናት ያምናል። ለዚህም ነው ድርጅታችን ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት ልማት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን አጣምሮ ተግባራዊ በማድረግ የሀገራችንን ገፅታና የዜጐቿን ህይወት በመቀየር ላይ የሚገኘው።
በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን አሟልቶ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ኢህአዴግ በፕሮግራሙ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ መልካም አስተዳደር በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው መርሆዎች ያሉት ሲሆን ዋና ዋናዎቹም የህዝብ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ የህግ የበላይነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሁም ቀልጣፋነትና ውጤታማነት ናቸው፡፡
በሀገራችን እነዚህ መሰረታዊ የመልካም አስተዳደር መርሆዎች ባለፉት ስርአቶች ፈጽመው የማይታሰቡና የተገደቡ ነበሩ፡፡ በነገስታቱ ዘመን በህገ መንግስታቸው ጭምር ነገስታቱን መውቀስም መክሰስም እንደማይቻል የተደነገገበትና “ንጉስ አይከሰሰም ሰማይ አይታረስም” በሚል መርህ የመሪዎች ግልፀኝነትና ተጠያቂነት ፈጽሞ የማይጠበቅበት ሁኔታ ነበር። በወታደራዊው የአገዛዝ ዘመንም አስተዳዳሪዎችን መቃወም፣ በፈለጉት አግባብ ተደራጅቶ የተለያዩ ሃሳቦችን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መግለፅ ቀርቶ ልዩነትን ማሰብ በራሱ በጸረ አብዮተኛነት አስፈርጆ ህይወት ያሳጣ ነበር። ይህ ታሪካዊ እውነታ የሚነግረን በነገስታቱም ሆነ በወታደራዊ አምባገነኖቹ የአገዛዝ ዘመን የሀገራችን የመልካም አስተዳደር ችግር የጀመረው ዴሞክራሲን በማፈንና በመርገጥ እንደነበር ነው።
በአንፃሩ በኢህአዴግ መሪነት እተገነባ የሚገኘው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአታችን በሀገራችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በትጋት መስራት የጀመረው የዜጐችን የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች በአግባቡ በመመለስ ነው። በሀገራችን ልዩ ነባራዊ ሁኔታ በእርግጥም የአፈናና ስርአቱ እንደተገረሰሰ ህዝቡ ውስጥ ለዘመናት ሲብላሉ የቆዩትን የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ልማትም ሆነ መልካም አስተዳደር በቅጡ ሊጀመር ይቅርና ሊታሰብ አይችልም ነበር። በዚህ ምክንያት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአታችን ፈጣኑን ልማትም ሆነ ስለመልካም አስተዳደር ማሰብ የጀመረው ለህዝቦች የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች አስተማማኝ ምላሽ በመስጠት ነው። ይህም በመሆኑ ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ የሆነው የህዝቦችንና የዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ዋስትና የሚሰጥ ህገ መንግስታዊ ስርአት በህዝቦች ነፃ ፈቃድ እንዲፀድቅ፡፡
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
የህግ የበላይነት የዴሞክራሲያችን አንዱ ምሰሶ መሆኑን በማመን ኢህአዴግ በመስመሩና በፖሊሲዎቹ በግልጽ አስቀምጦ ለተግባራዊነቱ ተረባርቧል፡፡ ያለአግባብ መጠቀም ያለንን ውስን ሃብት ለልማት ለማዋል እንዳንችል እንቅፋት የሚፈጥር መሆኑንና ተጠያቂነት የሚያስከትል አሰራር መከተል እንደሚያስፈልግም ይገነዘባል። በእስካሁኑ ጉዟችን የታዩ የመልካም አስተዳደር ስኬቶችና እጥረቶችን አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የመልካም አስተዳደር መርሆዎች መሰረት አድርጎ በሚዛኑ መመልከት ጥንካሬዎቻችን አጠናክረን እጥረቶቻችን አርመን ለቀጣይ ለውጥ እንድንተጋ የሚያስችል ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ድርጅታችን ኢህአዴግ ከህዝቦቻችን ጋር በመሆን በ24 አመታት ጉዟችን በመልካም አስተዳደር ስኬቶችን ያስመዘገበውን ያህል ገና ያልፈታናቸው እጥረቶች እንዳሉም ይገነዘባል፡፡ እነዚህን የመልካም አስተደዳር ስኬቶችን አጠናክሮ ለመቀጠልም ሆነ እጥረቶችን ለማረም ታዲያ ህዝቡ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ኢህአዴግ በጽናት ያምናል፡፡ ያለ ህዝብ ተሳትፎ ዴሞክራሲና ልማት ማምጣት እንደማይቻል እንዲሁም የህዝብ ተጠቃሚነት ያላረጋገጠ ዴሞክራሲና ልማት ዘላቂነት እንደሌለው ኢህአዴግ ከጅምሩ አቋም የወሰደበት ጉዳይ ነው፡፡
የህዝብ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መልካም አስተዳደር ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ ለዚህም ነው የኢህአዴግ ሁሉም ፖሊሲዎቹ ዋነኛ ማእከል የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሆነው፡፡ በሀገራችን ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ከተረጋገጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የኢፌዲሪ ህገ መንግስትን የማርቀቅና የማጽደቅ ሂደት ነበር፡፡ የህገ መንግስቱ የማርቀቅና የማጽደቅ ሂደት ካለፉት ስርአቶች ህገ መንግስቶች በእጅጉ በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የህዝቦች ተሳትፎና ባለቤትነት የተረጋገጠበት ነበር፡፡ ሁሉም ህብረተሰብ በየአካባቢው በመሰረታዊ የህገ መንግስቱ ጉዳዮች በቀረቡ አማራጮች ላይ ተወያይቶ ድምጽ እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡ የህዝቡን ፍላጎቶች መሰረት ተደርጎ በተዘጋጀው ረቂቅም ህዝቡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወካዮቹን መርጦ የህገ መንግስት ጉባኤ ተቋቋሞ ጥልቀት ያለው ውይይት ካደረገ በኋላ ህገ መንግስቱ ጸድቋል፡፡ የሀገራችን ህዝቦች በከፍተኛ ተሳትፎና ባለቤትነት ያጸቁት ህገ መንግስት ከሌሎች የዴሞክራሲ ሀገራት ከተለመደው የውክልና ተሳትፎ በተጨማሪ ቀጥተኛ ተሳትፎንም አካቶ ይዟል። ይህም የሚያሳየው በሀገራችን በመገንባት ላይ የሚገኘው ስርአት ከጅምሩ የህዝብ ተሳትፎና ባለቤትነት የተረጋገጠበት መሆኑን ነው፡፡
ኢህአዴግ የህዝብ ተሳትፎ ለእውነተኛ ለውጥ ግብአት የሚሆነው የነቃ፣ ነፃና የተደራጀ ሆኖ ሲፈፀም ብቻ መሆኑን አጥብቆ ያምናል። በመሆኑም ድርጅታችን የህዝቡ ተሳትፎ በነፃ ፍላጐትና ውሳኔ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት በሁሉም ፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ አስቀምጧል። በተግባርም ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት የህዝቡ ተሳትፎ ንቁ፤ ነፃና የተደራጀ እንዲሆን ብዙ ሰርቷል። ይህም በመሆኑ ነው ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት ያወጧቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ወደ ተጨባጭ እቅድ በመቀየር ተጨባጭ ስኬት ማስመዝገብ የተቻለው፡፡ ባለፉት 12 አመታት በሀገራችን የተመዘገበው ፈጣንና ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኘው የኢኮኖሚ እድገት ከትክክለኛ ፖሊሲና ከከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ውጪ ሊታሰብ እንኳን የሚችል አይደለም።
በገጠር አርሶ አደሩ አካባቢያዊ እውቀቱን፣ ጉልበቱንና የተፈጥሮ ሃብቱን አዋህዶ ጥቅም ላይ በማዋል በግብርና ልማታችን ላይ ታይቶ የማይታወቅ እመርታ አስመዝግቧል። ባለፉት አመታት አርሶ አደሩ በተፋሰስ ልማትና በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ ያፈሰሰው ጉልበትና ያስገኘው ውጤት የሀገራችንን ታሪክ የሚቀይር ተጨባጭ አቅም ሆኗል። ከተሞቻችን አፍርሰን ዳግም የመገንባት ያህል እያካሄድን ባለነው ሁለገብ የልማት ርብርብ ውስጥ የነዋሪዎቹ የገንዘብና የጉልበት አስተዋፅኦ መንግስት ከሚመድበው መዋእለ ነዋይ የማይተናነስ እየሆነ መጥቷል። በገጠርና በከተሞች ባለፈ ታሪካችን ከጥቅም ርቀው የቆዩት ሴቶችና ወጣቶች በሁሉም መስክ በተደራጀ መንገድ እየተሳተፉ የስርአቱ ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል። ባለፉት ጥቂት አመታት ደግሞ በልማት ሰራዊት እና በሌሎች የህዝብ አደረጃጀቶች አማካኝነት በገጠርና በከተማ የህዝቡን የተደራጀ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። በሂደቱም አመርቂ ውጤት አግኝተናል።
በትክክለኛ ፖሊሲ፣ ብቃት ባለው አመራርና በህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች የተረጂነት ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ በማድረግ፣ በርካታ ዜጎች ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ወጥተው ሃብት ማፍራት መጀመራቸው እንዲሁም የመሰረት ልማትና የማህበራዊ ልማት ለአብዛኛው ህዝብ ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው፡፡ በእነዚህ አመታት የተገኙ ስኬቶች ሀገራችን ከነበረችበት አስከፊ ድህነት፣ ኋላቀርነትና የሰላም እጦት አኳያ ሲታይ በቀላሉ የማይታዩና ለወደፊቱም ድህነትን አስወግደን የሁሉም ዜጎች ተጠቃሚነት በሚፈለገው ደረጃ ለማረጋገጥ እንደምንችል ብሩህ ተስፋ የፈነጠቁ ሆነዋል፡፡
ኢህአዴግ የህዝብ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ በእስካሁኑ ስኬቶች ተኩራርቶና ረክቶ የሚቆም ሳይሆን የህዝቦችን ተጠቃሚነት በተሟላ ሁኔታ ለማረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ በትጋትና በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባው ያምናል፡፡ በሀገራችን አሁንም ድህነት ሙሉ በሙሉ ያልተወገደ በመሆኑ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች መኖራቸውን፣ አሁንም ስራ ያልያዙ ወጣቶች መኖራቸውን እንዲሁም የመሰረተ ልማትና የማህበራዊ ልማት ጥራቱን ጠብቆ ለሁሉም ያልተዳረሰ መሆኑን ይገነዘባል፡፡ ኢህአዴግና የሀገራችን ህዝቦች እነዚህን ችግሮች የመቅረፍ ብቃት እንዳላቸው ያለፉት ስኬቶቻቸው ዋነኛ ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡ የእስካሁኑ ጉዟችን የሚያሳየው አሁንም ጠንክረን ከሰራን የማንፈታው ችግር እንደማይኖርና በድህነት ላይ የጀመርነውን ትግል በድል እንደምንወጣ ያሳያል፡፡
የተከበራችሁ
የሀገራችን
ህዝቦች፣
ግልፅነት፣ ተጠያቂነት የህግ የበላይነትና ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት ከህዝቦች ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተጨማሪ የሚታዩ አለም አቀፍ የጋራ ተቀባይነት ያላቸው የመልካም አስተዳዳር መመዘኛዎች ናቸው። በዚህ ምክንያት ህገ-መንግስታችን የመንግስት አመራርና አሰራር ለህዝቡ ግልፅ እንዲሆን ደንግጓል። በህገ-መንግስቱ መሰረት መንግስት በህዝብ ይጠየቃል። ዜጐች በቀጥታና በምርጫ በሚያደራጇቸው የህዝብ ምክር ቤቶች አማካኝነት መንግስትን ይቆጣጠራሉ።
በድርጅታችን የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የዜጐችንና የመንግስት ግንኙነት በግልፅነትና በተጠያቂነት መርሆዎች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አበክሮ ሰርቷል። በሀገራችን የመጀመሪያው በህዝብ የተመረጠ መንግስት ስልጣን ከያዘ ከ1987 ጀምሮ ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚና አስፈፃሚ በመባል የሚታወቁት ሦስቱ የመንግስት አካላት የየራሳቸውን ህገ-መንግስታዊ ተልእኮ በግልፅነትና በተጠያቂነት መንፈስ መፈፀም በሚችሉበት ሁኔታ ተደራጅተዋል። እነዚህ አካላት በተለይም ደግሞ ከተሃድሶ በኋላ አንዱ ሌላውን በብቃት መደገፍና መቆጣጠር በሚችሉበት መንገድ እንዲጠናከሩ ሆነዋል።
ዛሬ በመላ ሀገራችን ከቀበሌ እስከ ፌደራል ፓርላማ በተደራጁ የህዝብ ምክር ቤቶች ውስጥ ከ4 ሚሊዮን የማያንሱ ዜጐች ይሳተፋሉ። ድርጅታችን በየደረጃው በተደራጁ የህዝብ ም/ቤቶች በተለይም ደግሞ በቀበሌና በወረዳ ምክር ቤቶች ውስጥ የዜጐች ተሳትፎ በዚህ ደረጃ እንዲሰፋ ያደረገው የህዝቡን የመወሰን አቅም ከፍ ለማድረግና በተባበረ አቅም አስፈፃሚውን የመቆጣጠር ጉልበት እንዲኖረው ለማስቻል ነው። በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ም/ቤቶች የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደቱ የሚመራባቸውን ህጐች ያወጣሉ፣ እቅዶችን በብቃትና በጥራት ለማስፈፀም የሚያስችለውን በጀት ያፀድቃሉ። የህዝቡ የተናጠልና የተደራጀ እንቅስቃሴ የሚመራው ምክር ቤቶቹ በሚያወጧቸው አቅጣጫዎች ነው። አስፈፃሚ አካላት ከላይ እስከታች ለም/ቤቶቹ ወቅቱን የጠበቀ ሪፖርት ያቀርባሉ። በየደረጃው በተደራጁ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ተመድበው የሚያገልግሉ ዳኞች የሚሾሙትና የሚሻሩትም በምክር ቤቶቹ ነው። በዚህ ሳቢያ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የሁሉም የመንግስት አካላት የበላይና የህዝቡ የሉአላዊነት መገለጫ ሆነው እየሰሩ ናቸው።
በድርጅታችን የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በየደረጃው የተደራጁ የህዝብ ም/ቤቶች በህገ-መንግስታችን የተጣለባቸውን ይህንን ከባድ ሃላፊነት በብቃት ሲወጡ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደቱ ተደማሪ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይቀጥላል ብሎ ያምናል። የህዝብ ምክር ቤቶች በሁሉም የመንግስት አካላት ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ሲችሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተቀረፉ እንደሚሄዱም በአፅንኦት ይገነዘባል። ከዚህ በመነሳትም የህዝብ ምክር ቤቶች በአመራር፣ በአደረጃጀትና በአሰራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጠናከሩና በዕለት ተዕለት አፈፃፀማቸው ውጤታማ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት ሰርቷል። ምክር ቤቶቹ ባለፉት አምስት አመታት አስፈፃሚውን ለመደገፍና ለመቆጣጠር ያሳዩት ተነሳሽነትና የተገኘው ተጨባጭ ውጤት የዚህ ማሳያ ነው።
የተከበራችሁ
የሀገራችን
ህዝቦች
በየትኛውም መንግስት የአመራርና የአሰራር ሂደት ውስጥ የአገልግሎት ቅልጥፍናና ፍትሃዊነትን በማዛባት ስርዓቱንና ህዝቡን ለመልካም አስተዳደር ጉድለትና ለብልሹ አሰራር ከሚያጋልጡ ችግሮች አንዱ ሙስና ነው። ድርጅታችን እየገነባን ላለነው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ዋነኛ አደጋ በማንኛውም አጋጣሚና የስራ ሂደት ውስጥ እሴት ሳይጨምሩ የመጠቀም ወይም የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር መሆኑን ለይቶ የሞት ሽረት ትግል ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። በተለይም ባለፉት አምስት አመታት ስርአታችንን ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጋልጡት የስራና የስምሪት መስኮች ተለይተዋል። የገጠርና የከተሞች የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም፣ የግዢ ስርአታችን እንዲሁም የግብር አስተዳደር እና የንግድና የኮንስትራክሽን ዘርፎች መሆናቸውን ለይቶ ውጤታማ ትግል አካሂዷል። በመሆኑም በከተሞች የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ የሚታየውን ህገ-ወጥ ወረራና የሙስና ችግር ለመቅረፍ የተዘጋጀው አዲሱ የሊዝ አዋጅ አመርቂ ውጤት አስገኝቷል። በሌሎቹ የስራ ዘርፎች እየተወሰዱ ያሉ ቀጣይነት ያላቸው የማሻሻያ እርምጃዎችም ለውጤት እየበቁ ናቸው።
ሙስናን አስተማማኝ በሆነ መንገድ መዋጋት የሚቻለው በአመራሩና በአጠቃላይ ህዝቡ ዘንድ በሚፈጠር የአስተሳሰብ ለውጥ ነው። ድርጅታችን ሙስናን የልማታችንና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን እንቅፋት በማይሆንበት ደረጃ ማስወገድ የሚቻለውም የህዝቡን ሁለገብ ተሳትፎ በማረጋገጥ እንደሆነ ያምናል። ሙስናን በመከላከል ሂደት የህዝቡን ተሳትፎ አሟልቶ ማረጋገጥ የሚቻለውና ትግሉ ለፍሬ የሚበቃው ደግሞ ሙስናን የሚጠየፍ ህብረተሰብ በመገንባት እንደሆነ አበክሮ ይገነዘባል። ስለሆነም ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት ስራ ላይ በዋለው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በተቀረፀው የስነ-ዜጋና የስነ-ምግባር ትምህርት አማካኝነት በተለይም ሀገር ተረካቢ በሆኑ ህፃናትና ወጣቶች ላይ ውጤታማ አስተምህሮ ሰርቷል።
በስርአታችን ውስጥ በዚህ መልክ የሚካሄደውን የአስተሳሰብ ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ ሙስና ተከስቶ ሲገኝም አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብና የማስቀጣት ስራችን የመከላከል ስራውን በሚያግዝ መልኩ እየተፈፀመ ነው። በድርጅታችን የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን በሙሰኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ አያውቅም። በዚህ መንገድ የተወሰዱ ተከታታይ እርምጃዎች በሙስና አማካኝነት የሚፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታን በልማታዊ መንገድ እንድንቀጥል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፣
ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን መርሆዎች ከህዝባዊ አላማዎቹና ከሀገራችን ልዩ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ በስራ ላይ በማዋል ዜጐች የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሌት ከቀን ሰርቷል፤ አሁንም እየሰራ ነው። በሂደቱም እስካሁን በዝርዝር ያየናቸው ውጤቶች በየዘርፉ ተመዝግበዋል። አሁንም በየዘርፉ የተመዘገቡት በጐ ፍፃሜዎቻችን እንደተጠበቁ ሆነው ድርጅታችን በውጤታማ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ትግላችን ውስጥ እያጋጠሙ ካሉ ፈተናዎች አንዱና ቀዳሚው የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን ይረዳል። ከመሰረተ ልማት አገልግሎት አንፃር የመብራት፣ የውሃ፣ ስልክ እንዲሁም በግብርና በታክስ፣ በመንግስታዊ አግልግሎቶች እና በመሳሰሉት በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መኖራቸውን ኢህአዴግ ይገነዘባል፡፡
አጠቃላይ የህዝቡ ጥያቄዎች ሲታዩ በአንድ በኩል የልማት ጥያቄ ገጽታ ያላቸውና ካለን አቅም አኳያ ደረጃ በደረጃ መፈታት የሚገባቸው ሲሆኑ በሌላ በኩል ከአመራሩና ከፈጻሚው አካል አግልግሎት አሰጣጥ መጓደል የሚከሰቱ ናቸው፡፡ መንግስት በፌዴራልና በክልሎች ደረጃ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ንቅናቄ በመፍጠር እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየሰራ ይገኛል። የመልካም አስተዳዳር ችግር ምንጭ ተደርገው የተለዩ ተቋማት ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት የተደራጀ እቅድ እያወጡ ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። አንዳንዶቹ ለውጥ ማምጣት ጀምረዋል። ይሁን እንጂ አሁንም በብዙዎቹ የህዝብ እርካታ በሚፈለገው ደረጃ አልተረጋገጠም፡፡ ስለሆነም ልማትን በማፋጠን የሚፈቱትን የህዝብ ጥያቄዎች ከህዝቡ ጋር በመወያየት ቅደም ተከተል አውጥቶ መፍትሄ ለመስጠት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከልማት ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በየደረጃው ካለው አመራርና ሰራተኛ የአገልጋይነት መንፈስ መጓደልና ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የሚመነጩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ። እነዚህን ችግሮች የግልጸኝነትና የተጠያቂነት አሰራር በማጠናከርና በሂደቱም የህዝቡን የተሟላ ተሳትፎ በማረጋገጥ መፍታት ጊዜ የማይሰጠው መሆኑን ኢህአዴግ ይገነዘባል። ለዚህም ተግቶ እንደሚሰራ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡
የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተሟላ ሁኔታ የመፍታት ብቃት ያላቸው ኢህአዴግና የሀገራችን ህዝቦች መሆናቸው ያለፉት ሁለት አሰርት አመታት ጉዞዎቻችን ያሳያሉ፡፡ ኢህአዴግ በየጊዜው ከሚያስመዘግባቸው ስኬቶቹ ብቻ ሳይሆኑ ከስህተቶቹም እየተማረ ለድል የበቃ ድርጅት ነው። የሀገራችን ተቃዋሚዎች ግን የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ ችግሮችን በፈጠራ ወሬዎች በማጀብ ማራገብ የቀን ተቀን ተግባራቸው ሆኗል፡፡ የሀገራችን ህዝቦች በገሃድ የሚያውቁቱን እውነታ ክደው ሀገራችን ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደገባች አስመስለው ሲስሏት ይታያሉ፡፡ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ብዙዎቹ ካለፈው ስህተታቸው ሳይማሩ አሁንም በእራሳቸው ውስጣዊ ዴሞክራሲ ማረጋገጥ አቅቷቸው ሲተራመሱ እየዋሉ ለህዝቦች የመልካም አስተዳደር አረጋጋጭ ሆነው ለመቅረብ ይሞክራሉ። ይህም በመሆኑ የሀገራችን ተቀዋሚዎች የመልካም አስተዳደር አማራጭ እንደማይሆኑ በቀላሉ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡
ህዝባዊ ባህሪ የተላበሰው ኢህአዴግ ሁልጊዜም የውስጥ ድክመቶችን ታግሎ እያረመ አሁን ሀገራችን ከደረሰችበት ሁለንተናዊ ለውጥ ያደረሰ መሆኑ የሀገራችን ህዝቦች የምትገነዘቡት ነው፡፡ ለዚህም ነው የመልካም አስተዳደርን በማረጋገጥ የህዝብ እርካታን አላረጋገጥኩም ብሎ ችግሩን ወደ ውስጡ የሚያየው፡፡ ለዚህም ነው በሀገራችን በለውጥ ጎዳና እየተጓዘች ባለችበት በአሁኑ ጊዜ እየታዩ ያሉ ችግሮቹን ሊፈቱ የሚችሉት በኢህአዴግና በሀገራችን ህዝቦች የጋራ ትግል ነው የምንለው፡፡
ኢህአዴግን መምረጥ የህዝቡን ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መልካም አስተዳደር ማስፈን ነው።
ኢህአዴግን ይምረጡ! ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተውን ታታሪዋ ንብ ነች!!
No comments:
Post a Comment