EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 17 April 2015

በኢህአዴግ መስመር ለኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ሆነናል!!




የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
በኢህአዴግ የተመራው የሀገራችን ህዝቦች ትግል ግብ የድህነትና ኋላቀርነት ጠበቃ የነበረውን የደርግ ስርዓት በማስወገድ የበለፀገች ሀገር መገንባት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ የሀገር እድገትና ለውጥ ደግሞ ከእልህ አስጨራሽ ትግልና መስዋእትነት ባሻገር ትክክለኛ ፖሊሲና የዜጎችን እውቀት፣ ጉልበትና ሃብት በማቀናጀት በብቃት ለሀገር ልማት እንዲውል ማድረግ የግድ ይላል፡፡

የልማትና ኢንቨስትመንት ፖሊሲያችን ታሳቢ ያደረገው የደርግ የአፈና ስርዓት የዜጎች የማሰብ ነፃነት ብቻ ሳይሆን ሃብት የማፍራት መብትንም በመገደብ የሀገራችን ኢኮኖሚ በእዝ ፖሊሲ ቁልቁል እንዲጓዝና ተንገራግጮ እንዲቆም ያደረው መሆኑን ነው፡፡ ማንኛውም በግል ንግድም ሆነ አገልግሎት ስራ ለመሰማራት የሚፈልግ ዜጋ ቢሮክራሲያዊ ውጣ ውረዱ እንደተጠበቀ ሆኖ የካፒታል ጣራው ከግማሽ ሚሊዮን እንዳይዘል ገደብ የተጣለበት ነበር፡፡ ይህም ዜጎች የፈጠራና የማደግ ተስፋቸውና ፍላጎታቸው እንዲሸበብ በማድረግ ለሀገራዊ ልማት አስተዋፅኦ ማድረግ ይችል የነበረው የግሉ ኢንቨስትመንት እንዲቀጭጭና ባለበት እንዲረግጥ በሂደትም ለሀገራዊ ልማት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እንዲሟሽሽ ተደርጓል፡፡ የግል ኢንቨስትመንት በመገደቡም በውጭ ኢንቨስትመንትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ይቅርና በዜጎች አቅምም ሃብት ማመንጨት የሚያስችል ኢኮኖሚ መገንባት አልተቻለም፡፡ በዚህም በከተማም ሆነ በገጠር ከእርስ በእርሱ ጦርነት አፈሳ የተረፈው ሰፊው አምራች የህብረተሰብ ክፍል በስራ አጥነት ችግር እንዲሰቃይና በየጊዜው ችግሩ እንዲባባስ ተደርጓል፡፡
ኢህአዴግ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ከመፍጠርና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት ከመጣል እኩል ኢኮኖሚውን ከውድቀት በማውጣት ሀገራችንን ከድህነት የሚታደግ አዲስ የልማትና የሀገራዊ እድገት ፖሊሲ ተግባራዊ የማድረግ ተልዕኮ ነው የተሸከመው፡፡ ተልዕኮው በጦርነት በድርቅና በሁለንተናዊ ኋላቀርነት ውስጥ በነበረች ሀገር መፈፀም ምን ያህል ከባድ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ይህ ተልዕኮ ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም ሀገር ለመለወጥ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለው ኢህአዴግ ችግሩን በብቃት የሚፈታ ፖሊሲ በመቀየስ በተነፃፃሪ በአጭር ጊዜ ለመፍታት ወደ አዲስ የትግል ምዕራፍ በመግባት የለውጥ ጉዞውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ኢህአዴግ የሀገራችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በነፃ የገበያ ስርዓት መመራት እንዳለበት በፕሮግራሙ ላይ በግልፅ በማስቀመጥና በግብርና ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ልማት የሚያረጋግጥ፣ መንግስት የገበያ ጉድለት ባለባቸው ዘርፎች ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የሚያስችል ፖሊሲ በመቅረፅ ለፈጣን ሀገራዊ ልማት ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም የሀገራችን ባለሃብቶች የለውጡ ባለቤቶች የሚሆኑበት፣ የውጭ ባለሃብቶችም የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በቀላሉ መሰማራት በማይችሉባቸው በዋነኛነት የውጭ ምንዛሪ በማያስገኙ ወይም በማያድኑ ዘርፎች የሚሳተፉበት የኢንቨስትመንት ስርዓት በመቅረፅ ተግባራዊ አድርጓል፡፡
ኢህአዴግ በሀገራችን ፈጣንና ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት ይቻል ዘንድ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ሰፊ የሰው ኃይል ተሰማርቶበት በሚገኝበት ገጠርና ግብርና ላይ መመስረት እንዳለበት ያምናል፡፡ በገጠሩ ያለውን ሰፊ የሰው ጉልበት፣ የተፈጥሮ ሃብትና መሬት በመጠቀም፣ በአነስተኛ ደረጃ ያለውን ካፒታል በቀጣይነት ማሳደግ ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን በግልፅ አስቀምጧል፡፡ በገጠርና ግብርና ላይ የሚመዘገብ ፈጣን ለውጥ እዚያው ሳለ የከተማ ነዋሪውን ህዝብ ጨምሮ አብዛኛው የሀገራችን ህዝቦች ከልማቱ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል እድል ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ የካፒታል አቅማችንን ለማሳደግና የከተሞች ልማት ለማፋጠን ጉልበትን በሰፊው የሚጠቀምና የመሬት ሃብታችንን በብቃት ለማልማት የሚያስችል አቅጣጫ ከመከተል ውጭ አማራጭ እንደሌለን ያገናዘበ የልማት ፖሊሲ ተቀርፆ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ የኢንቨስትመንት ፖሊሲያችንም ይህንኑ በሚያጠናክርና የሀገር ውስጥ ባለሃብት የለውጡ ዋነኛ ባለቤት በሚያደርግ መርህ እንዲመራ ተደርጓል፡፡
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
የሀገራችን የግል ባለሃብት የኢንዱስትሪ ልማት አንቀሳቃሽ ሞተር ሆኖ የካፒታልና የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ የሚያስችል ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ፖሊሲያችን በሀገር በቀል ባለሃብቱ ላይ አንዳችም የኢንቨስትመንት ጣሪያ አያስቀምጥም፡፡ ማንኛውም የሀገራችን ዜጋ ባለበት ክልልም ሆነ ከዚያ ውጭ ባሉት ክልሎች መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ የካፒታል ጣሪያ አይጣልበትም፡፡ ይህም በግማሽ ሚሊዮን ተገድበው የቆዩ በርካታ የሀገር ውስጥ የግል ባለሃብቶች የበርካታ ፋብሪካዎችና የንግድ ተቋማት ባለቤቶችና ሚሊየነሮች ለማድረግ ያስቻለ ነው፡፡ የውጭ ባለሃብቶችም የሀገራችን የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢንቨስትመንት ተሳትፏቸው እያደገ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በአፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ መጠን ከሚፈስባቸው ግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ሆናለች፡፡
የኢንቨስትመንት ፖሊሲያችን የመንግስት፣ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችና የውጭ ባለሃብቶችን አቅም በማቀናጀት ፈጣን የኮንስትራክሽን፣ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡ የመንግስት ሚና በዋነኛነት በግል ባለሃብት ሊሰሩ በማይችሉ ዘርፎችና በመሰረተ-ልማት ያተኮረ ሲሆን የሀገራችን ባለሃብቶች ከጥቂት ዘርፎች ውጭ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች በስፋት እንዲንቀሳቀሱ ያስቻለ ፖሊሲ ነው፡፡ የውጭ ባለሃብቶችም በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በቀላሉ በማይሰሩ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በሚያረጋግጡ፣ ከፍተኛ ካፒታልና ሰፊ የሰው ኃይል ሊቀጥሩ በሚችሉ የኢንቨስትመንት መስኮች በስፋት እየተሳተፉ ነው፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን የገበያ ክፍተት ባለባቸው የልማት ዘርፎች ከፍተኛ ካፒታል በመመደብ ልማትን የማረጋገጥ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የፌዴራል መንግስቱ ከአንድ በላይ ክልሎችን የሚያቋርጡ አውራ መንገዶች በማልማት ሰፊ ርቀት ተጉዟል፤ የባቡር ትራንስፖርት ግንባታም እያካሄደ ነው፡፡ በሁሉም ክልሎች የመንገድ፣ የአየርና የባቡር ትራንስፖርት በማስፋፋት በየትኛውም የሀገራችን ጫፎች የሚገኙ ዜጎች ከሃገሪቱ ሃብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ በተለይም በማደግ ላይ በሚገኙ አካባቢዎች ባለሃብቱ በቀላሉና በተመጣጣኝ ወጪ በመረጠው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተንቀሳቅሶ መስራት እንዲችል ግዙፍ ካፒታል የሚጠይቁ የመሰረተ-ልማት ኢንቨስትመንት እያከናወነ ነው፡፡ አንድ የጋራ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት መርህን በመከተልም ታላላቅ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የስኳር፣ የማዳበሪያ፣ የብረታ ብረት፣ የግድብና መስኖ የኬሚካል መድኃኒት ፋብሪካዎችንና ሌሎችንም አምራች ኢንዱስትሪዎች በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡
የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ የበለጠ ለማሳደግ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርጓል፡፡ በተለይም ምርትን ወደ ውጭ በሚልኩ የአግሮ ኢንዱስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎችን ለማበረታታት የተቀየሱት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ከፍተኛ ውጤት እያሳዩ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት ስኬቱ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተመዘገቡ ባሉት ውጤቶችም በግልፅ እየታየ በመሆኑ ብዙዎች የሚጓጉለት መስክ ሆኗል፡፡ እነዚህ ዘርፎች ለሀገራዊ እድገት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱም በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን የቀረፀው የኢንቨስትመንት ፖሊሲና ተግባራዊ አፈፃፀሙ ውጤታማ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ከሀገር ውጥ ባለሃብቶች ጎን ለጎን የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው፡፡ የዓለማችን ከፍተኛና ታዋቂ ባለሃብቶች በሀገራችን የሆልቲካልቸር፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳ፣ የኮንስትራክሽን፣ የመጠጥ ኢንዱስትሪ ለመሳተፍ ያስመዘገቡት ካፒታልና ፋብሪካዎች በማቋቋም እያስመዘገቡት ያሉት ውጤት ሀገራችን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅም እያደገ መሆኑን፣ በአፍሪካም ተመራጭ ሀገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
የኢንቨስትመንት ፖሊሲው ስኬት ለሀገራዊ ዕድገታችንና ለዜጎች ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑም በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎችና ሰራተኞች የሚያረጋግጡት እውነታ ነው፡፡ በአግሮ ኢንዱስትሪና በአገልግሎት በተለይም የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት በመስፋፋቱ ዘርፉ ለበርካታ ዜጎቻችን የስራ እድልና የገቢ ምንጭ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በየዓመቱ በጎብኚዎች ብዛትም ሆነ በሚያስገባው ገቢ እያደገ መጥቷል፡፡ የባለፈውን ዓመት አፈፃፀም ብቻ እንኳን ወስደን ብናይ ከአንድ መቶ ሺህ ከሚጠጉ ጎብኝዎች ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ተገኝቷል፡፡ ይህም ሀገራችን በየዓመቱ ከቡና ወይም ከሰሊጥ ምርት ከምታገኘው ገቢ ጋር ተመጣጣኝ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና የመጠጥ እንዲሁም የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከማስፋፋት ጎን ለጎን የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም እየጎለበተና ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑም የኢንቨስትመንት ፖሊሲያችን ስኬት ሌላው ማረጋገጫ ነው፡፡
በኢህአዴግ የሚመራው መንግስታችን እጅግ ፈጣን ከሆነው ልማታችን ጋር የተያያዙና ከፍላጎት መጨመር ጋር የተሳሰሩ የአገልግሎትና የመሰረተ-ልማት አቅርቦት ክፍተቶች እንደሚያጋጥሙ ይገነዘባል፡፡ ይህ ሁኔታ ከምንም በላይ የኢንቨስትመንት ፍሰትንና ፈጣን ልማታችንን የሚጎዳ መሆኑን በመገንዘብ ከአጭር፣ ከመካከለኛና ከረዥም ጊዜ አኳያ ለመፍታት ከባለሃብቱና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተቀናጀ መፍትሄ በመስጠት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል በመረባረብ ላይ ነው፡፡ 
የኃይል አቅርቦቱን በስትራቴጂካዊ መልኩ ለመፍታት ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ሌት ተቀን በመረባረብ ላይ የሚገኝ ሲሆን የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ዓለም የደረሰበትን የመጨረሻ አራተኛ ትውልድ (4G) ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የመሬት አቅርቦት ተግዳሮትን ለመፍታት የመሬት ባንክ በማደራጀት ፈጣን መፍትሄ እየሰጠ ሲሆን ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚታዩ ተግዳሮቶችን ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግና የብድርና የግብር አከፋፈል ስርዓት የሚያቀላጥፉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ 
ኢህአዴግ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቱን አቅም ወደ ላቀ ብቃት በማሸጋገርና ልማቱን በማፋጠን የሃገር ልማትና የዜጎች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በቁርጠኝነት መንቀሳቀሱን ይቀጥላል፡፡ ኢህአዴግን መምረጥ ሀገራችን እያስመዘገበች ያለችውን ፈጣን ልማት ለማስቀጠል በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ኢንቨስትመንት በማስፋት የሀገራችንን ህዳሴ ማሳካት ነው፡፡
ህዳሴያችን በኢህአዴግ፣ በባለሃብቶችና በመላው ህዝባችን የተቀናጀ ትግል እውን ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment