EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 29 March 2015

ስኬታማው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ

ኢህአዴግ የተከተለው ትክክለኛ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ በግብርናና ገጠር ልማት አንጸባራቂ ስኬቶች እንዲመዘገቡ አስችሏል!!
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ባለፉት 23 አመታት በኢህአዴግ ትክክለኛ ፖሊሲና ቁርጠኛ አመራር እመርታዊ ስኬቶችና ለውጦች ከተመዘገገበባቸው መስኮች ውስጥ የግብርናና የገጠር ልማት አንዱ ነው፡፡ ያለፉት ስርአቶች በተከተሉት ጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝና የተሳሳተ ፖሊሲ ለአራችን እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችል የነበረውን የግብርና ዘርፍ አምክነውታል፣ የአገራችን ህዝቦችንም ለስቃይና ለሰቆቃ ኑሮ ዳርገዋቸው ነበር፡፡ እንደሚታወቀው የፊውዳል ስርዓት ማቆጥቆጥን ተከትሎ መሬት በአገራችን ቁልፍ የኢኮኖሚ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል። በፊውዳሉ ስርዓት የገዢ መደቦች የፖለቲካ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የአርሶ አደሩን መብት ረግጠው ጉልበቱንና ምርቱን በመመዝበር የመከራ ህይወትን ሲገፋ ኖሯል። አርሶ አደሮች ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያመረቱትን ምርት በፊውዳሎች እየተቀሙ የበይ ተመልካች ሆነው ለረጅም ዘመናት ኖረዋል፡፡ የንጉሱ ስርአት እንዲወገድ ካደረጉት የህዝቦች መሰረታዊ ጥያቄዎች ውስጥ የመሬት ላራሹ ጥያቄ አንዱ ነበር፡፡ 
የአገራችንን ህዝቦች የትግል ውጤት በሃይል ቀምቶ በፊውዳሉ ስርዓት እግር የተተካው የደርግ አገዛዝ የመሬት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ ጥያቄ መሆኑን ስለተረዳ ለይስሙላ “መሬት ላራሹ” ብሎ ቢያውጅም በተጨባጭ የፈፀመው የዚህን ተቃራኒ ነበር። ደርግ የወሰደው ጥገናዊ ለውጥ የህዝቦችን የመብት ጥያቄዎች ሳይመልስ የተካሄደ በመሆኑ ቅርጹንና መልኩን ቀይሮ ጭቆናውን ያስቀጠለ ነበር፡፡ ደርግ የአርሶ አደሩ ጉልበትና ምርት በመበዝበዝ በአንድ በኩል የአርሶ አደሩ አቅም እንዲዳከም በሌላ በኩል የራሱን ወታደራዊ አቅም እንዲጎለብት አቅዶ ሰርቷል። በየአካባቢው የእርሻ ሰብል ግብይት ድርጅቶችን በማቋቋም አርሶ አደሩን ያመረተውን ምርት ኮታና የዋጋ ተመን በማውጣት በርካሽ ዋጋ ለመንግስት እንዲሸጥ፣ ኋላም የራሱን ምርት መልሶ ከመንግስት በውድ ዋጋ እንዲገዛ ግዳጅ ጥሎበት ነበር። በወቅቱ መንግስት ባወጣው የዋጋ ተመንና ኮታ መሰረት ከአርሶ አደሩ የገዛውን ምርት በእጥፍ እያተረፈ ሲሸጠው የነበረ ሲሆን ይህም ስርአቱ ምን ያህል በዝባዥ እንደነበረ ያሳያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ህዝቡ በማያምንባቸው ለጦርነት የሚውል ገንዘብ እንዲያዋጣ ይገደድ ነበር፡፡ በተጨማሪም የፊውዳሉም ሆነ የደርግ ስርዓት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአገራችንን አርሶ አደሮች ህይወት ሊቀይሩ የሚችል ትክክለኛ ፖሊሲና የአመራር ድጋፍ መስጠት የሚችሉም የሚፈልጉም አልነበሩም።

የእነዚህ ችግሮች ድምር ውጤት አርሶ አደሩ ለበርካታ ዓመታት በአስከፊ ችግር ውስጥ እንዲቆይ፣ የግብርናው ዘርፍም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የአመራረት ዘይቤ እንዳይላቀቅ አድርጎታል፡፡  ይህ ያለፉት መንግሥታት የተሳሳተ አቅጣጫ አርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን መላ የአገራችንን ህዝቦች ወደ አዘቅት የከተተ በመሆኑ የረጅም ጊዜ ስልጣኔ ታሪክ ባለቤት የነበረችው ሀገራችን በአስከፊ ድህነት፣ ኋላቀርነትና ድንቁርና ልትማቅቅ ግድ ሆኖባታል። ለዚህም ነው ይህን አስከፊ አገራዊ ገጽታና በህዝቦች ላይ የደረሰ ዘግናኝ በደል ለመቀየር የአገራችን ህዝቦች የትውልዶችን ቅብበሎሽ በጠየቀና ከፍተኛ መስዋዕትነት በተከፈለበት ትግል ስርቶቹን ያስወገዷቸው።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ለረጅም ዘመናት ከኖርንበት ድህነት ለመውጣት ከህዝብ ጉልበትና ከመሬት የተሻለ የልማት ግብዓት ሊኖር እንደማይችል ኢህአዴግ በጥብቅ ያምናል። ኢህአዴግ ይህን ነባራዊ ሀቅ በሚገባ በማጤን በፕሮግራሙ ሰፊውን የአገራችንን አርሶ አደርና አርብቶ አደር ለሚያሳትፈው የግብርናና ገጠር ልማት ዘርፍ አመቺ መደላድል መፍጠር እንደሚገባ አስቀምጧል።
ህገ መንግስታችን የኢትዮጵያን ህዝቦችን ታሪክና ለዘመናት በመሬት ሳቢያ የደረሰባቸውን በደል እንዲሁም  በአገራችን ህዝቦች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ መሬት ያለውን ልዩ ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት መሬት የሚመራበት ፖሊሲ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሆን አድርጓል። የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሃብት የባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ሆኖ የአርሶ አደሮችና የአርብቶ አደሮችን የመጠቀም መብት ያረጋገጠ እንዲሆን ህገ መንግስቱ ደንግጓል። አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ለኑሯቸው የሚያስፈልጋቸውን መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው የተከበረ መሆኑም በግልጽ ተደንግጓል። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የመሬት ይዞታቸውን የማልማት፣ የመጠቀም፣  የማከራየትና የማውረስ መብታቸውንም ተጎናጽፈዋል። ህገ መንግስታችን “መሬት የማይሸጥ፣ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነው” በማለት መሬት በጣት ለሚቆጠሩ ባለፀጋዎች ብቻ ሳይሆን ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝቦች አስተማማኝና ዘላቂ የሃብት ምንጭ እንዲሆን ያደረገው። ይህ በመሆኑ በአገራችን መሬትን በመቆጣጠር በጫናና በተጽዕኖ ሊመጣ የሚችለው የፀረ ዴሞክራሲያዊነት በር ተዘግቷል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ኢሕአዴግ ያስቀመጠው የኢኮኖሚ ልማት አላማ ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ አገራችንን ከተመጽዋችነት የሚያላቅቅ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማረጋገጥ የዳበረ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ መገንባት ነው፡፡ ማንኛውንም አይነት የኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ ካፒታል፣ ሰራተኛ የሰው ሃይል፣ መሬትና እነዚህን በውጤታማነት አቀናጅቶ መጠቀም የሚችል አመራር ያስፈልጋል። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲታይ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የካፒታል እጥረት መኖሩና የካፒታል እጥረቱም በአጭር ጊዜ እንደማይፈታም ግልጽ ነው፡፡ በአንጻሩ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ታታሪ የሰው ኃይልና ለልማት የተመቸ በቂ መሬት አለ። ይህም በመሆኑ ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቀውን ኢንዱስትሪን ማእከል ያደረገ ልማት የትም እንደማያደረስን የታወቀ ነበር፡፡ በዚህም ምክኒያት ያለንን ሰፊ የሰው ጉልበትና መሬትን እንዲሁም ውስን ካፒታል በመጠቀም የህዝቡ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችል የልማት ስትራቴጂ መከተል የግድ ይል ነበር፡፡ ለዚህም ነው ያለንን አቅም ተጠቅመን አገራችን ከብተና ሊታደግ የሚችል ገጠርንና ግብርና ማእከል ያደረግ ስትራቴጂ በመከተል ልማታችን የጀመርነው፡፡
በ1993 የኢህአዴግ ተሃድሶ ተከትሎ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂያችን ነጥሮ ወጥቶ ተግባራዊ በመደረጉ በአገራችን ለተመዘገበው ፈጣንና ተከታታይ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ባለፉት 23 አመታት ያደረግነው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በቀደሙት ስርዓቶች የተረጂነትና የኋላቀርነት መገለጫ ተደርጎ ሲወሰድ የነበረው ግብርናችን የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር አልፎ በአገራዊ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና እንዲጫወት አስችሏል። የሰው ጉልበትን በስፋት በማነቃነቅና መሬትን በአግባቡ በመጠቀማችን ሀገራችን 12 ተከታታይ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበች ሲሆን ባለፉት አመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደጋችን እንደ ሀገር በምግብ እህል ራሳችንን ችለናል።
የተከተልነው ትክክለኛ ፖሊሲያችን ለህዝባችን የመስራትና የመለወጥ ፍላጎት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ ምርታማነታችን ከፍተኛ እድገት እየተመዘገበበት መጓዝ ችሏል። በ1983 ዓ.ም በዋና ዋና ሰብሎች 52 ሚሊየን ኩንታል የነበረውን ዓመታዊ የምርት መጠን ባለፈው አመት 269 ሚሊየን ኩንታል ማድረስ ችለናል። ከዚህ ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የተመረተው በአነስተኛ የአርሶ አደሩ እርሻ አማካኝነት መሆኑን ሲታሰብ ኢህአዴግ አርሶ አደሩና የግብርናው ዘርፍ የዕድገት ምንጭ እንዲሆን የተከተለውን ፖሊሲ ትክክለኛነት ያረጋግጣል፡፡
የግብርና ምርታችን እያደገ የመጣውን የህዝባችን ቁጥር ከመመገብ አልፎ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የኢኮኖሚ መሪነቱን ይዞ ዘልቋል። አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያው አቅም እንዲፈጥር አድርገናል፡፡ ለዚህም ስኬት ገበያ መር የአመራረት ስልት መከተላችንና ይህንኑ ለማገዝ የሚያስችሉ የባለሙያ፣ የተቀናጀ አመራርና የግብዓት አቅርቦት ማሟላታችን በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በ1994 ዓ.ም 14 ሚሊየን ገደማ የነበረው የተረጂዎች ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ መጥቶ ባለፈው ዓመት ወደ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ቀንሷል። በቀጣይም የተረጂዎችን ቁጥር ዜሮ ለማድረስ እየተረባረብን እንገኛለን። ይህም ህይወቱ በሚሰፈርለት እርዳታ ላይ ተመሰረቶ የነበረውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ድርቅ በተከሰተ ቁጥር የበርካታ ዜጎች ህይወት ሲቀጠፍበት የነበረውን ሁኔታ በማስቀረት ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት ነው፡፡  በ1988 .ም በገጠር ከሚኖረው ህዝብ 47 ነጥብ 5 በመቶው በድህነት ውስጥ ይኖር የነበረ ሲሆን የድህነትን ተራራ ለመናድ ባደረግነው ርብርብ ሀገራዊ የድህነት መጠኑ በ2005 .ም ወደ 26 በመቶ ወርዷል፡፡ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ደግሞ ቁጥሩ ወደ 22 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚወርድ ይጠበቃል።
ቀድሞ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የግብርና ዘይቤ ውስጥ የነበሩ በርካታ አርሶ አደሮች አሁን ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ወደ መገንባት ተሸጋግረዋል። በአለባበስ፣ በአመጋገብና በአኗኗር ለውጥ አምጥተዋል። ተንቀሳቃሽና መደበኛ ስልክ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ መገናኛ ብዙሃን መጠቀም ጀምረዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሃብት ማፍራት የጀመሩ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችም በየአካባቢው ተፈጥረዋል። ባፈሩት ሃብት በተለያዩ መስኮች የሚሳተፉ ኢንቨስተሮች ለመሆን በቅተዋል።
ግብርናው በሚያመነጨው ሃብትና ጥሬ ዕቃ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች በፍጥነት እያደጉ ናቸው። ኢኮኖሚያችን ገና ታዳጊ ቢሆንም በእነዚህ ድምር ውጤት ከአንዳንድ የበለጸጉ አገሮች በተሻለ ሁኔታ የሥራ አጥነትን ችግር ተቋቁመን በህዳሴ ጉዞ ወደፊት መገስገስ ቀጥለናል። የመሬት ፖሊሲያችን ለዘመናት የምንታወቅበት የረሃብ ታሪክ እንዲቀየር ከማድረጉም ባሻገር እንደርስበታለን ብለን ባስቀመጥነው ግብ አቅጣጫ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራችን ሽግግር መሰረት እየጣለ ነው።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ኢህአዴግ የተከተላቸው ትክክለኛ ፖሊሲዎች ተጨባጭ ስኬት ማስመዝገብ የቻሉት የአገራችን ህዝቦች ራሳቸው በባለቤትነት የሚያሳተፉበትና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት በመሆናቸው ነው። ኢሕአዴግ ከህዝባዊ ባህሪው በመነጨ የኒዮ ሊብራል ሃይሉንና የአገር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢ ወኪል የሆኑትን ተላላኪዎቻቸውን ጫና በመመከት ነው። የእነዚህ ሃይሎች ወኪል የሆኑት የአገራችን ተቃዋሚዎችም በተጨባጭ የመጣን ለውጥና እድገት ሸምጥጠው በመካድ እርስ በእርሳቸው የሚምታቱ መሰረተ ቢስ የጭፍን ጥላቻ ሃሳቦችን ሲያቀርቡ ይታያሉ። በአንድ በኩል አርሶ አደሩ መሬቱን ገንዘብ ላላቸው ሃብታሞች እንዳይሸጥ በመከልከል መብቱን ገደባችሁት በማለት ተቆርቋሪ መስለው ሊቀርቡ ይሞክራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መሬት ለባለሃብት እየተሸጠነው ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ከዚህ እርስ በእርሱ ከሚምታታ አቋማቸው መረዳት የሚቻለውም አማራጫቸው ባለፉት ስርቶች ተግባራዊ ሆኖ የወደቀው አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን በጥቂቶች የጭቆና ቀንበር እንዲጫንበት የሚያደርግ ስርዓትን የሚመልስ መሆኑን ነው፡፡     
በአገራችን መሬት በመንግስትና በህዝቡ እጅ ሆኖ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ  የመሬት ፖሊሲ መከተላችን ለአጠቃላይ ልማታችን ያለው ጠቀሜታ በተጨባጭ ተረጋግጧል፡፡ በኒዮ ሊብራል ጫና መሬትን በነፃ ገበያ ሰበብ እንደተራ ሸቀጥ እንዲሸጥ ያደረጉ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮችና ሌሎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ልማት ለማምጣት እንደ አንድ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ በእንደነዚህ አይነት አገሮች መሬት በተለያየ አጋጣሚ በግለሰቦችና ቡድኖች እጅ በመግባቱ አገሮች የምርት ክንውንንም ሆነ የመንገድ መሠረተ ልማትን የማስፋፋት፣ ለዜጎች የመኖሪያ ቤትና ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ገንብቶ ህዝባቸውን ተጠቃሚ የማድረግ ፍላጎታቸውን መወጣት አልቻሉም። መሬትን ለባለፀጎች ሃብት ማካበቻ እንዲሆን አሳልፈው በመስጠታቸው ወደ ኋላ ተመልሶ መሬትን ለህዝቦቻቸው ልማት የማዋሉን ጉዳይ የማይሞክሩት እየሆነባቸው ይገኛል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ኢህአዴግ የነደፋቸውና ተግባር ላይ ያዋላቸው እነዚሁ የትክክለኛ የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፎች ከገባንበት የድህነት አዙሪት ሰብረን እንድንወጣ፣ የአገራችንን ህዝቦች የድህነትና የተረጂነት መጠንን እንድንቀንስ እንዲሁም በከፍተኛ የእድገት ጎዳና እንድንራመድ አስችለውናል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገራችን ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከእርዳታ ወደ ትብብር ማዕቀፍና አብሮ በመልማት ላይ ያተኮረም ሆኗል። ለዚህም ግብርናችን ከፍተኛና ወሳኝ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
የግብርናና ገጠር ልማት ስራችን ለዘመናት ተረስቶ በነበረው አርብቶ አደሩም ህይወት ላይ ለውጥ እንዲያስመዘግብ ያደረገው ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ ለዘመናት ተገልለውና ተረስተው የቆዩ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የመሠረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ፍትሃዊ ልማትን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። የአርብቶ አደሮቻችን ዋነኛ ማነቆ የሆነውን የውሃ አቅርቦት ችግር መቅረፍ በመጀመራችን አርብቶ አደሩ ተረጋግቶ ለመኖር የሚያስችለው ሁኔታ መፈጠር ጀምሯል። በመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሞቻችን አርብቶ አደሮች አንድ ላይ ተረጋግተው እንዲኖሩና ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲቀየሩም ያደረገ ነው።
በገጠሩ አርሶ አደርም ሆነ አርብቶ አደር ህዝባችን ህይወት ላይ የመጡ ለውጦች የትክክለኛው ግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲያችን ስኬቶች ማሳያ ናቸው። በዚህ ሂደት ያስመዘገብነው እድገትና የጀመርነው የህዳሴ ጉዞ ሊሳካ የሚችለው የፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፎቻችንን ጠብቀን በመጓዝ ለውጤታማነቱ በስፋት ስንንቀሳቀስ ነው። ኢህአዴግ እንደ እስካሁኑ ሁሉ በግብርናና ገጠር ልማት ስራዎቻችን የገጠሩ ብቻ ሳይሆን የከተሜውም ተጠቃሚነት መረጋገጥ እንዲችል ለስኬት ያበቁንን የፖሊሲና ህዝብን ያሳተፉ የልማት ፕሮግራሞች ጠብቆ በመጓዝ የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ ይሰራል።
ኢህአዴግን በመምረጥ የህዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ የሚገኘውን ፈጣንና ተከታታይ ልማት እናስቀጥል!!

No comments:

Post a Comment