(በቢልልኝ ሀብታሙ)
አገራችን ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜያት
ነፃነትዋን አስጠብቃ የኖረች አገር እንደሆነች ሁሉ በዚህ የረጅም ጊዜያት ታሪክ ውስጥ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን በመሳሰሉ
ገፅታዎች ያላት ልምድ አነስተኛ ነው፡፡ በአገራችን ታሪክ ወጥ የሆነ ዴምክራሲያዊ ስርአት መገንባት ባለመቻሉ በየጊዜው የሚፈጠሩት
ተቀያያሪ ስርአቶች የጥቂቶች ጥቅም ማራመጃ እንጂ ለብዙሀን የሚጠቅም ስራ የሚሰራባቸው ነበሩ ማለት አይቻልም፡፡ በባለፉት ስርአቶች
የነበረን ተሞክሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የመንግስት ለውጦችን ማስተናገድ እንጂ ጠንካራ ስርአት የመገንባት አልነበረም፡፡
በሀገራችን የተደራጀ ጠንካራ
መንግስታዊ ስርአት መገንባት የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ኢህአዴግ አገሪቷን ማስተዳደር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ነው ቢባል
ማጋነን አይሆንም፡፡ እንደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ጀማሪነታችን ችግር አልነበረም ብሎ መካድ ባይቻልም ከችግሩ በብዙ እጥፍ ጎልተው
ሊወጡ የቻሉ በጎ አፈፃፀሞችን ማየታችንን ግን መካድ አይቻልም፡፡ ባለፉት ምርጫዎች ያሳለፍናቸውን ዴሞክራሲያዊ ሂደቶች በየጊዜው
እየተሻሻሉ መምጣታቸውን መገንዘብ የሚችል ቀና ህሊና ካለ ጠንካራ ዴሞከራሲያዊ ስርአት ልንገነባ የምንችልበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን
መረዳት አያዳግትም፡፡
ኢህአዴግ አገሪቷን ማስተዳደር
ከጀመረ ወዲህ ያለው የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ሂደት ለረጅም ጊዜ ፈራርሶና የነበረን አሮጌ ቤት አፅድቶ አንደገና የመገንባት
ሂደት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ስራ ውስጥ የተገባው በኢህአዴግ ፍላጎት ሳይሆን የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በፈጠረው አስገዳጅነት
ነው፡፡ ኢሕአዴግ ስልጣን የያዘበት ወቅት በሀገራችን የብሄር ቅራኔ እጅግ ተባብሶ በዜጎችና ህዝቦች መካከል ጥርጣሬና ያለመተማመን
የሰፈነበት ነበር። ሁሉም የነፃነት ጥያቄ እያነሱ ሀገሪቱ ለመበታተን ከቋፍ የደረሰችበት ወቅት ነበር። ከዚህ በመነሳት ነባራዊ ሁኔታው
ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመገንባት ጉዳይን የህልውና ጉዳይ አድርጎት ነበር ማለት ይቻላል።
ትልቅ ህንፃ ለመስራት ከታች
ጠንካራ መሰረት መኖር እንዳለበት ሁሉ የዴሞክራሲዊ ስርአቱን ለመገንባትም ጠንካራ መሰረት ተጥሏል፡፡ ይህ ሂደት በተጨባጭ የሚታዩ
ስኬቶች የተመዘገቡበት ቢሆንም ብዙ ድካምና መስዋዕትነት የጠየቀውን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ፍፁም እንደሌለ ሽምጥጥ አድርገው
የካዱም አልታጡም፡፡ ያም ሆኖ ዴሞክራሲ ሌሎችን ለማስደሰት ወይም ለማስኮረፍ
ሲባል የሚገነባ ሳይሆን በራሱ ተፈላጊ በመሆኑ በአገሪቱ
ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ እርግጥ ነው ምርጫን የመሳሰሉ አበይት የዴሞክራሲያ ሂደቶች
በመጡ ቁጥር ሆን ተብለው የሚፈፀሙ የሚመስሉ የዴሞክራሲዊ ስርአት ፀር የሆኑ የህግ ጥሰቶችን በማስወገድ ረገድ በሚፈለገው ልክ ውጤት
አልመጣም፡፡
የእነዚህ ምርጫንና ሌሎች አጋጣሚዎችን
ተገን አድርገው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አመለካከታቸውንና ተግባራቸውን የሚያንፀባርቁ አካላት እንቅስቃሴ ሶስት መሰረታዊ ገፅታዎችን የተላበሰ ነው። እነዚህ ገፅታዎች በጤነኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን አሉታዊ አስተዋፆ በተጓዳኝ በማሳየት ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡
ሀ. የዴሞክራሲያዊ ሂደቶችን ተአማኒነት ማሳጣት
የመጀመሪያው ገፅታ የዴሞክራሲያዊ
ሂደቶችን ተአማኒነት ለማሳጣት የሚደረጉ ጥረቶች አካል ነው፡፡ ለዚህ አላማ ማስፈፀሚያ በተለያዩ አቅጣጫ የሚበተኑ ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳዎችን
በመንዛት በአገሪቱ የሚደረገውን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ዋጋ በማሳጣት ዜጎችና የአገሪቷን እድገት የሚመኙ አካላት እምነት
እንዳይኖራቸው ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ መንግስት የህዝቡን የዴሞክራሲና መልካም አስተዳር ብሎም ሌሎች የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያደርገውን
ጥረት ለራሳቸው ጥገኛ አላማ ሊውል በሚችል መልኩ በመለወጥ በአገሪቱ የተጀመረውን የተስፋ ጭላጭል ማጨለም ዋንኛ ተግባራቸው ከሆነ
ሰነባብቷል፡፡
በህዝብ ሰፊ ተሳትፎና በመንግስት
ያላሰለሰ ጥረት የመጡትን ለውጦች ልቦናቸው ቢያምንበትም ሆነ ብለው የምላስ ክህደት ውስጥ በመግባት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲፈጠርና
በዚህ የተነሳም የህዝብና የመንግስት አንድነት ተዳክሞ በሚፈጠረው ክፍተት የራስን ግላዊ አጀንዳ ማራመድን አላማቸው አድርገዋል፡፡
ይህን እኩይ አላማ በሰነቀው ጥረታቸውም በአገሪቱ የሚገኙ ዜጎች በመንግስት
ላይ እምነት እንዲያጡ፣ ለዘመናት ተቻችሎ በአንድ ላይ የኖረው ህዝባችን እርስ በርሱ በጥርጣሬ እንዲተያይ በማድረግ ለከፋ ትርምስና
አገራዊ ቀውስ በመዳረግ በመሀሉ በሚፈጠር እድል የራስን ጠባብ አጀንዳ ማስፈፀም ፍላጎታቸው ነው፡፡
ለ. የአገሪቱን መልካም ገፅታ ማበላሸት
ሌላኛው የጥገኞች የትግል እንቅስቃሴ
መሰረት የሚያደርገው አገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበችውን መልካም ስም ጥላሸት በመቀባት የተበላሸ ገፅታን ማላበስ ነው፡፡
የሚሰማቸው ባያገኙም አንዳንድ ወገኖች በተለይም መሰረታቸውን በምዕራባዉያን አገራት ያደረጉ የፖለቲካ ኃይሎች በየአደባባዩና በየኤምባሲው በመግተልተል የአገሪቱን መልካም
ዝና ለማበላሸት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ይህ ጥረታቸው መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ለሚያደርገው ሰፊ የልማት
ርብርብ የሚያግዘውን አለም አቀፋዊ ትብብር ማሳጣትን ግብ ያደረገ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በዚህም ገንዘብ አታበደሩ ከማለት አንስቶ
ከአገሪቱ ጋር ያላችሁን ግንኙነት አቋርጡ እስከሚሉ ተማፅኖዎች የሚደርሱ እንቅስቃሴዎች አድርገዋል። ይህ ሃሳባቸው ቢሳካ ኖሮ አገሪቱ
በአለም አቀፍ የፖለቲካ መድረኮች ያላትን መልካም ዝና በማጉደፍ ከአለም አንድትገለል የሚያደርግ እኩይ ተግባር ነው፡፡ የነዚህ ወገኖች
መውተርተር ያመጣው ለውጥ ባይኖርም አንቅስቃሲያቸውን ለሚያስተውል አገር ወዳድ ዜጋ ግን ከትዝብት የሚጥላቸው ነው፡፡
ሐ. ሰላምን ማደፍረስ
ጥገኞች አላማቸውን ለማሳካት
ከሚጠቀሙበት መንገድ በመጨረሻ የሚነሳው አካሄድ በአገሪቱ ያለውን ሰላም ለማደፍረስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በዚህ ድርጊታቸውም
አንዱን ብሔር በተለየ መልኩ የተበደለ አድርጎ የማቅረብ ሌላኛውን ብሔር በገዥና በበዳይ ገፅታ በመሳል የግጭት አጀንዳ ለመፍጠር ይጥራሉ፡፡ የነዚህ አካላት እንቅስቃሴ የህዝቡን
ስሜት የሚነኩ ሀይማኖትና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በመጠቀም ችግሮችን የተለየ ገፅታ የማስያዝና አጋኖ የማቅረብ ስልትን ይጠቀማሉ። ይህ
አካሄዳቸው ግን የውበታችንና አንድነታችን ምንጭ የሆነውን ልዩነታችንን በስህተት ስሌት በማስላት እና ይህንኑ እንደክፈተት በመጠቀም
እርስ በርስ በማናከስ በሚፈጠረው አገራዊ ትርምስ በድብቅ የያዙትን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈጸም የታለመ እኩይ ድርጊት መሆኑን ህዝቡ
የሚረዳው ነው።
No comments:
Post a Comment