የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት ያረጋገጠ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲገነባ በቁርጠኝነት እየታገለ ያለ ህዝባዊ ድርጅት-ኢህአዴግ
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
የመድብለ ፓርቲ ስርዓት
ዋነኛ መገለጫ ህዝቦች የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት መሆናቸው ነው፡፡ ዜጎች በምርጫ ካርዳቸው አማካኝነት ይሁንታቸውን በሰጡት ፓርቲ
ብቻ የሚመሩበት ሁኔታ ሲኖር የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እውን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሕዝቡ አንዱን ፓርቲ ከሌሎቹ ፓርቲዎች አስበልጦ እንዲመራው
ሃላፊነት መስጠት የሚችለው ደግሞ የተለያዩ አማራጮችን ማቅረብ የሚችሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲኖሩ ነው፡፡ ስለሆነም በመድብለ ፓርቲ
ስርዓት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጮቻቸውን ለህዝብ የሚያቀርቡበት የተመቻቸ ሁኔታ መኖር አለበት፡፡
ከዚህ በተቃራኒ የአንድ ፓርቲ ስርዓት የሚባለው ግን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጫቸው ማቅረብ የማይችሉበትና ህዝቦችም
አማራጭ ሐሳብ አግኝተው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ዕድል የማያገኙበት ስርዓት ነው። እናም የአንድ ፓርቲ ስርዓት የፖለቲካ ልዩነቶች ማስተናገድ የማይችል በመሆኑ ከመድብለ ፓርቲ ስርዓት ማዕቀፍ
ውጭ ነው። በዚህ ስርዓት ውስጥ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚደራጁበት በምርጫም ተወዳድረው በህዝቡ ይሁንታ የመንግስት ስልጣንን የሚይዙበት አሰራር የተዘጋ ነው።
በሀገራችን ያለፉት ስርዓቶች የህዝቦችን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነትና
ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶችን አፍነው ቆይተዋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ሕዝቦች እነዚህን ስርዓቶች አሜን ብለው ሳይቀበሉ በየጊዜው
አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ እየከፈሉ በፅናት ታግለዋቸዋል፡፡ በዚህ የህዝቦች እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችን ሁሉን
አቀፍ መስዋዕትነትን የጠየቀውን ትግል በትክለኛ መስመር በመምራት የአንድ ፓርቲ አገዛዙን
በማስወገድ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና የብዙሃን ተሳትፎ የተረጋገጠበት የአስተሳሰብ ብዝሃነት እውን እንዲሆን
አድርጓል።
በኢህአዴግ መሪነት ለድል የበቃው የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና
ህዝቦች ትግል ያረጋገጠው እውነታ ቢኖር ህዝቦች የማያምኑበት ማንኛውም ዓይነት ስርዓት እንዲመራቸው እንደማይፈቅዱና በኃይል ሊገዛቸው
ቢፈልግም የኃይል አገዛዙ ዕድሜ እንደማይኖረው ነው፡፡ ኢህአዴግ በህዝባችን ተሳትፎና መስዋእትነት የጨቋኞችና አምባገነኖችን
አስተዳደር ከመሰረቱ በመናድና በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት የሀገራችን ዘላቂ ሰላም ከማረጋገጥ በተጨማሪ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችንም በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲጓዝ አድርጓል። በዚህም የህዝባችን
ብቸኛ የስልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት ማረጋገጥ ችሏል።
ህገ መንግስታችን ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መሰረት ሆኗል!
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
ኢህአዴግ የህዝቦችን ትግል በግንባር ቀደምነት በመምራት አምባገነኑን የደርግ ስርዓት ቢያስወግድም ከፍተኛ
መስዋእትነት ከፍሎ ያገኘውን ስልጣን ለብቻው መያዝን ምርጫው አላደረገም፡፡ ይልቁንም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም እና ሁሉም ሃይሎች በሽግግሩ እንዲሳተፉና የሀገሪቱ መፃኢ እጣ ፈንታ በጋራ የሚወስኑበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥሪ አድርጓል፡፡
የደርግን
ስርዓት ለመጣል ከየአቅጣጫው መሳሪያ ያነሱ የተለያዩ የታጠቁ ሃይሎችን
ጨምሮ የተለያዩ ፓርቲዎችን፣ ቡድኖችንና ግለሰቦችን በማካተት በአዲሲቱ ኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ላይ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉበት ሁኔታ ያመቻቸ የሽግግር መንግስት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡ ይህም ኢህአዴግ
ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት መስፈን መሰረት በመጣል ሂደት
ለነበረው ቁርጠኝነት መገለጫ ነው፡፡
በሽግግር መድረኩ ወቅት ሁሉም ተሳታፊ
አካላት ለሀገሪቱ ይበጃል ያሉትን ሃሳብ በማቅረብ ጠቃሚ
የሆነ ዴሞክራሲያዊ ውይይት አድርገዋል፡፡ ይህ ወቅት በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የቻሉ ሃሳቦች ገዢ በመሆን ተግባራዊ እየተደረጉ የሚሄዱበት የመንግስታዊ ስርዓት መሰረት የተጣለበትና አሃዳዊ የነበረው የመንግስት ስርዓት በመሰረቱ መቀየሩ በይፋ የታወጀበትም
ነበር፡፡ በወቅቱ በኢህአዴግ ግንባር ቀደም ተዋናይነት የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን በማዋቀር የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህልና እምነት እንዲሁም የሀገራችንን ራዕይ መሰረት ያደረገ ረቂቅ ህገ መንግስት ተዘጋጅቷል፡፡
በሽግግር መንግስቱ ወቅት
በተዘጋጀው
ረቂቅ ህገ መንግስት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ በተለያየ ደረጃ የሕብረተሰብ ተወካዮችን በማሳተፍ ሰፊ ውይይቶችን ከተደረጉ በኋላ የማሻሻያ ግብዓቶች ታክለውበት የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በስራ ላይ እንዲውል ማድረግም ተችሏል፡፡ በሕገ መንግስቱ ከተካተቱ አዳዲስ አስተሳሰቦችና
እምነቶች መካከልም የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ይገኝበታል። ሕገ መንግስታችን ለሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት
ዋስትና ሰጥቷል ስንልም ከያዛቸው ድንጋጌዎች በመነሳት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን በማያሻማ
መንገድ በመደንገግ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የህዝብ ሉዓላዊነት በተግባር አረጋግጧል፡፡
ህገ መንግስቱ በአንቀፅ 29 “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል” በማለት ከጅምሩ ልዩነቶች መደፍጠጥ እንደማይገባቸው ይደነግጋል፡፡ ዜጎች ይህን አስተሳሰባቸውን በጋራ በመሆን በተደራጀ
መንገድ ለማራመድ ከሚችሉባቸው መንገዶች አንዱ በፖለቲካ ፓርቲነት መደራጀት ነው፡፡ ይህም በህገ መንግስቱ ሙሉ እውቅና ያገኘ መብት ነው፡፡ ዜጎች ለተወሰነ አላማ መደራጀት ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፤ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብትም አላቸው፡፡ የዜጎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የመደራጀት መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና ማግኘቱን ተከትሎ የተለያየ ፖለቲካዊ አቋምን የያዙ በርካታ ሀገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች ተቋቁመው በነፃነት እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በአሁኑ
ጊዜም 75 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየደረጃው
እየተንቀሳቀሱ ሲሆን ይህም የሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን
የሚያረጋግጥ ነው።
በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር የሚያስፈልገው ሕዝቡ የተለያዩ አማራጮች እየቀረቡለት ከቀረቡ አማራጮች መካከል የሚበጀውን እየመረጠ ለስልጣን የሚያበቃበት ሁኔታ ለመፍጠር በመሆኑ ኢህአዴግ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታው በቁርጠኝነት እየሰራ መጥቷል። በኢህአዴግ መሪነት በሀገራችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ህገ መንግስታዊ እውቅና ከማግኘቱም በላይ በተግባርም ሰፊ የግል ህትመትና ኤፍ ኤም ሬዲዮ ሚዲያዎች መስፋፋት በመጀመራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጫቸውን ለህዝብ ማቅረብ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ያላቸው እነዚህ መብቶች በቡድንና በተናጠል የተፈቀዱና ጥበቃም የሚደረግላቸው ሲሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፓርቲ ልሳን ማውጣትና ለአባላቶቻቸው በነፃነት ማሰራጨት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ምርጫዎቻችን የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ስኬቶች ናቸው!!
የተከበራችሁ
የኢትዮጵያ ህዝቦች፤
የፖለቲካ ፓርቲዎች ግብ የሚሆነው የቀረፁትን ፕሮግራም ለመፈፀም የሚያስችላቸውን መንግስታዊ ስልጣን በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች መያዝ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ አስቀድሞ በተወሰነለት ጊዜ በመደበኛነት
የሚካሄድ
ምርጫ ሲኖር ብቻ
ነው፡፡ ስለሆነም በሀገራችን የሚካሄዱ ምርጫዎችን የሚመራና የሚያስተዳድር
ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውግንና ነፃና ገለልተኛ የሆነ ቦርድ በህገ መንግስቱ መሰረት ተቋቋቁሟል፡፡ ቦርዱ ሲቋቋም ተቃዋሚ ፓርቲዎች
ጭምር የቦርዱ አባላት የሚሆኑ ዕጩዎችን በማቅረብ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ የምርጫ ህጎቻችንም እንዲሁ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ
እንዲሆኑ ለማድረግ ሰፊ ስራ ተከናውኗል። በተለይ በሶስተኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ ማግስት ከፓርቲዎች ጋር በተደረጉ ሰፊ ውይይትችና
ምክክሮች የምርጫ ህጉ እንዲሻሻል በማድረግ የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ
ለማጠናከር በኢህአዴግ ግንባር ቀደም ተዋናይነት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። የቦርዱ አሰራርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየተጠናከረ
መጥቷል። እናም ቦርዱ በህገ መንግስቱ የተሰጠው ስልጣንና ተግባር በገለልተኝነት እያከናወነ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው።
ይሁንና
ህጋዊና ህገወጥ መንገዶችን እያጣቀሱ መጓዝን የመረጡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘወትር ቦርዱን በሀሰት መወንጀላቸውን ቀጥለውበታል፡፡
እነዚህ አፍራሽ ኃይሎች ቦርዱን ለማጠልሸት ሌት ተቀን የሚተጉት የራሳቸው ህገ ወጥ ተግባር ለመሸፈን በማሰብ እንደሆነ መላው የሀገራችን
ህዝቦች የሚገነዘቡት ጉዳይ ነው።
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 38 ማንኛውም ዜጋ በቀለም፤ በዘር፤ በሃይማኖት ወይም በአመለካከት ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለው በደነገገው መሰረት እስካሁን በሀገራችን አራት አጠቃላይና አካባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ ምርጫዎች የታየው የህዝብ ተሳትፎም
እጅግ ከፍተኛና በእርግጥም የህዝቡን ወሳኝነት በተግባር ያረጋገጠ ነው። ምርጫዎቹ ነፃ፤ ፍትሃዊ፤ ዴሞክራሲያዊና በመላው ህዝብ ተሳትፎ የተፈፀሙ ሲሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች መሆናችንን ያረጋገጡ ምርጫዎች ናቸው፡፡
ለአብነት በመጀመሪያውና ሁለተኛው ዙር ምርጫዎች የተወዳደሩ
ፓርቲዎች ብዛት እንደቅደም ተከተላቸው 57 እና 49 ሲሆኑ የፓርላማ መቀመጫ ያገኙ ፓርቲዎች ብዛትም እንደቅደምተከተላቸው 43 እና
42 ነበሩ፡፡ የ2002ቱን ምርጫም
እንዲሁ
ከተመዘገቡት 31 ሚልዮን 926ሺህ,520 ሰዎች መካከል
93.4 በመቶ ያክሉ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ተሳትፎው ከሌሎች አገሮች ልምድ ጋር ሲነፃፀርም እጅግ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡
በ2002 በተካሄደው
ምርጫ 63 የፖለቲካ ፓርቲዎች 2ሺህ 188 ዕጩዎች ለተወካዮች ምክር ቤት፤ 4ሺህ
746 ዕጩዎች ለክልል ምክር ቤቶች እና 45 ዕጩዎች በግል ተወዳድረዋል፡፡ ይህ ለአንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር በአማካይ ከአራት በላይ ዕጩዎች፤ ለአንድ የክልል ምክር ቤት ወንበር ደግሞ በአማካይ ሶስት ተወዳዳሪዎች መቅረባቸውንና ውድድሩ ጠንካራ እንደነበር ያመለክታል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም በምርጫው ሂደቶች ነፃ ሆነው
ዘግበዋል፡፡ በመጨረሻም ሕብረተሰቡ ከቀረቡለት አማራጮች ውስጥ የኢህአዴግ መስመር የሀገሪቱን ህዳሴ ማረጋገጥ የሚችል ብቸኛ መስመር
መሆኑን በመተማመን ድምፁን ለኢህአዴግ ሰጥቷል፡፡ ለዚህም ኢህአዴግ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ላቅ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
በቀደሙት ሶስት አጠቃላይ ምርጫዎች ኢህአዴግ በህዝባችን ይሁንታ በአብላጫ ድምፅ እያሸነፈ ከህዝቡ
የተሰጠው ከፍተኛ ኃላፊነት በቁርጠኝነትና በከፍተኛ ዲስፕሊን እየተወጣ መጥቷል። በምርጫ 2002 ደግሞ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከምክር ቤቶች የተገለሉበት ሁኔታ ሲፈጠር ኢህአዴግ ደግሞ በአንፃሩ
ከፍተኛ ይሁንታን አግኝቷል። ከህዝቡ የተሰጠው ከፍተኛ ኃላፊነት በመገንዘብም የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችሉ
ስኬታማ ስራዎች አከናውኗል። ኢህአዴግ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ
ስርዓቱን ለማጠናከር በቁርጠኝነት ሲሰራ የሀገራችን ተቃዋሚዎች ግን ህዝቡን ሊያሳምን የሚችል የፖሊሲ አማራጭ ማቅረብ ባለመቻላቸው የሀገራችን ህዝቦች ይሁንታ በተደጋጋሚ ተነፍገዋል፡፡ በመሆኑም ኢሕአዴግ የአውራ ፓርቲ መልክ ይዞ እንዲጓዝ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
የሀገራችን ህዝቦች የሀገሪቱን
ህዳሴ እውን ለማድረግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሌት ተቀን ለሚተጋው ኢህአዴግ ድምፃቸው ሰጥተው ተቃዋሚዎች ግን የሀገራችን ሰላም፣ ልማትና
ዴሞክራሲ ማረጋገጥ እንደማይችሉ በድምፀቸው ባረጋገጡበት ሁኔታ ተቃዋሚዎች የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ የተቀለበሰ ለማስመሰል ተረባርበዋል፡፡ ህዝቡ ለምን ድምፁን እንዳልሰጣቸው
ራሳቸውን በአግባቡ ፈትሸው ለማሻሻል ከመሯሯጥ ይልቅ ኢህአዴግን መኮነን
መርጠዋል። የአውራ ፓርቲ ስርዓትን ከአንድ ፓርቲ ስርዓት ጋር ለማመሳሰልና መሰረተ ቢስ በሆነ ክስ ህዝቡን ለማደናገርም
ሞክረዋል፡፡
የአውራ ፓርቲ ስርዓት
በተለያዩ የዓለማችን አካባቢዎች ተግባራዊ የሆነና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አካል ሆኖ ሳለም ኢህአዴግ ያመጣው እስከማስመሰል ተጣድፈዋል።
በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት በተሻለ ሁኔታ ተራምደዋል የሚባሉ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ሳይቀር የአውራ ፓርቲ ስርዓት እውን
ሆኖባቸዋል። የሲዊድን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ የሜክሲኮው ሪቮልሽናል ኢንስቲትሹናል ፓርቲ እንዲሁም የጃፓኑ ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከ40 እስከ 60 ዓመታት በስልጣን የቆዩበት እውነታ እናገኛለን።
በአህጉራችንም የአውራ ፓርቲ ስርዓት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየና አሁንም ያለ የመድብለ
ፓርቲ ስርዓት አንድ አካል ነው፡፡ ለአብነት የታንዛኒያው ቻማ ቻማ፤ የአንጎላው ዘ ፖፑላር ፍሮንት ፎር ሊብሬሽን ኦፍ አንጎላ፤
የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ኮንግረስ ፓርቲ ለበርካታ ጊዜያቶች በተደጋጋሚ በማሸነፍ አገሮቻቸውን እየመሩ ቆይተዋል፡፡ በአውራ ፓርቲ
ስርዓት ረጅም ታሪክ ያላት ሌላኛዋ አፍሪካዊት አገር ቦትስዋና ስትሆን የቦትስዋና ዴሞክራቲክ ፓርቲ ከ1965 ጀምሮ በበርካታ ምርጫዎች
በማሸነፍ እስካሁን በስልጣን ላይ ይገኛል፡፡
በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ወሳኙ ጉዳይም የትኛው ፓርቲ ስንት ጊዜ በስልጣን ላይ ቆየ ሳይሆን ህዝቡ በእውን ድምፁን
በነፃነት ይሁንታውን ሰጥተዋል ወይ የሚለው ይሆናል። እናም ህዝቡ በነፃነት ወጥቶ ያለምንም ጫናና ተፅዕኖ ድምፁን እስከሰጠና የመንግስታዊ
ስልጣን ብቸኛው ምንጭ ህዝቡ እስከሆነ ድረስ የህዝቡ ይሁንታ ያገኘ አካል በተደጋጋሚ መመረጡ ስርዓቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አይደለም
ተብሎ ከተቃዋሚዎች የሚነሳው ሐሳብ ውሃ የሚቋጥር አይደለም።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
በዴሞክራሲያቸው አደጉ
የሚባሉት ሀገራት አሁን ካሉበት የዴሞክራሲ ደረጃ ለመድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ የእኛ ዴሞክራሲ ግን በዕድሜው
ለጋ የሚባል ዴሞክራሲ ቢሆንም በእስካሁን ሂደቱ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል። በመድብለ ፓርቲ ስርዓትም ቢሆን በሀገራችን
በርካታ ፓርቲዎች በነፃነት የሚሳተፉበትና የህዝቡን የስልጣን ምንጭነትና ተቆጣጣሪነት በተግባር ማረጋገጥ ችለናል። የዴሞክራሲ ባህል
የመገንባት ጉዳይ ቀጣይነት ያለው ትግል የሚጠይቅ ሂደት ቢሆንም በእስካሁን ጉዟችን ውጤታማ ስኬቶች አስመዘግብናል። በቀጣይም የዴሞክራሲ
ስርዓታችን ይበልጥ መዳበር እንዳለበትና የህዝቦች የዴሞክራሲ ተሳትፎም እየጎለበት መሄድ እንዳለበት ይገነዘባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ
ኢህአዴግ ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ መጎልበት አሁንም ሃላፊነቱን በቁርጠኘነት መወጣቱን እንደሚቀጥል ለመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዳግም
ያረጋግጣል፡፡
ኢህአዴግን መምረጥ፤ ህዝቦች ለዘመናት ተነፍገው የቆዩትንና በኋላም በመራራ ትግላቸው የተጎናጸፉትን የዴሞክራሲ ስርዓት ማጠናከርና ማስቀጠል ነው፡፡
ኢህአዴግ የሚያስተላልፋቸውን
የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶች ከቴሌቪዥን፤ ሬዲዮና ጋዜጣ በተጨማሪ
በድረ ገፃችን www.eprdf.org.et
እንዲሁም በፌስቡክ ገፃችን EPRDF official ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
No comments:
Post a Comment