EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday, 16 March 2015

ለፈጣን ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና ለዴሞክራሲ ኢህአዴግን ይምረጡ!!



ለነጻና ፍትኃዊ ምርጫ  ተዘጋጅተናል!
ኢህአዴግ መላ ህዝቡን አስተባብሮ በመራው ህዝባዊ ትግል በአገራችን ስልጣን በጠመንጃ አፈ ሙዝ የሚያዝበት ምዕራፍ ተዘግቷል። በምትኩም ህዝቦች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት የሆኑበትና ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው አዲስ ዴሞክራሲያዊ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡
የዚህ አዲስ ስርዓት መስራችና ባለቤት የሆኑት መላው የአገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት 23 ዓመታት አራት ስኬታማ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን በማካሄድ የአዲሱን ምዕራፍ ትሩፋቶች ማጣጣም ጀምረዋል።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች
ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የሚከበሩበት፣ የዴሞክራሲ ባህልና ተቋማት የሚያብቡበት፣ ህዝቡ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ የነቃ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎውን የሚያረጋግጥበትን አቅጣጫ ገና ከጠዋቱ በፕሮግራሙ ቀርፆ ተግባራዊ አድርጓል፤ በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነትን በማጎልበት የዳበረ የመድብለ ፓርቲ ስርአት መፍጠርንም በፕሮግራሙ አስፍሮ ለተግባራዊነቱ በፅናት በመታገል ላይ ይገኛል።  
 እነሆ ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫም የህዝባችን ህገመንግስታዊ የስልጣን ባለቤትነት መብት ተረጋግጦ በልማትና እድገት እየገሰገሰች ያለችው ሀገራችን  የህዝቦቿ የዕድገትና የብልፅግና ራዕይ ይሳካ ዘንድ ኢህአዴግ ስኬቱን ወደ ላቀ ምዕራፍ በማሸጋገር ከህዝቡ ጋር የጀመረውን አገራዊ የህዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ በመረባረብ ላይ ነው።
 ምርጫው ከሂደቱ እስከ ፍፃሜው ድረስ  ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና በህዝባችን ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኢህአዴግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ተዘጋጅቷል። ለዚህም የምርጫ ስትራቴጂ በማዘጋጀት፣ ለአመራሮቹና ለአባላቱ በስትራቴጂውና በፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ላይ በቂ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ ገብቷል። ስልጠናው አመራሮቹና አባላቱ የምርጫ ስነ ምግባር ደንቡን በተሟላ ሁኔታ ተገንዝበው እንዲንቀሳቀሱ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።
ኢህአዴግ የሚወክሉትን እጩዎች በተገቢ መስፈርቶች የመለመለ ሲሆን እጩዎቹን አቅርቦ በአባላቱ እንዲተቹ ማድረጉም ይታወቃል፡፡ የኢህአዴግ እጩዎች የድርጅቱን ህዝባዊ ወገንተኝነት በፅኑ በመረዳት  ህዝብ የሚሰጣቸውን አደራ አክብረው በከፍተኛ ቁርጠኝነት ይንቀሳቀሳሉ፤ ለአገራቸው እድገትና ለህዝባቸው ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ቀና አመለካከት ያላቸው በመሆናቸው በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ አመኔታ የሚጣልባቸው ናቸው።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!  
ከዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች አኳያ የህዝቦች የስልጣን ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ ፓርቲዎች በህጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለህዝቡ አማራጭ ፖሊሲዎችን እንዲያቀርቡ ማስቻል ነው። ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት በህዝብ ይሁንታ በተሰጠው የመንግስትነት ስልጣንም ሆነ በፕሮግራሙ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ፣ ህጉን ተከትለው ህዝቡን እንዲያደራጁ፣ ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲገልጹና በፖለቲካ ጉዳዮች በነጻ እንዲሳተፉ ሳያሰልስ ሰርቷል።
ሕግና ስርዓት ባለው ሁኔታ በነጻ የመወዳደርና የመከራከር ባህል በሀገሪቱ እንዲዳብር ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ያለው ኢህአዴግ ይህን መብት ለማፈን የሚደረግ የትኛውንም ዓይነት አስተሳሰብና ተግባር በጥብቅ ሲታገል ቆይቷል። በቀጣይም ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲዳብርና ህዝቡ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦች የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲፈጠር ይተጋል።
አንድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነው ወይም አይደለም ተብሎ የሚለካው በሂደቱ እንጂ በውጤቱ እንዳልሆነ በፅኑ የሚያምነው ኢህአዴግ፣ የህዝባችንን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት ከማረጋገጥ አኳያ ባለፉት 23 ዓመታት ዜጎች በነፃነትና በራሳቸው ይሁንታ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያካሂዱ ሰርቷል። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን የሀገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመመረጥ የሚያበቃ አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂ ማቅረብ ተስኗቸው በህዝብ ድምፅ በተሸነፉ ቁጥር የተለያዩ ምክንያቶችን እየፈጠሩ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ አይደለም ብለው መተቸታቸው የተለመደ ሆኗል።
ተቃዋሚዎች በአገራችን በተካሄዱ ሁሉም ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ ነው የሚሉትን የምርጫ ሂደት ውጤቱ ሲገለፅና የህዝቡን ይሁንታ አለማግኘታቸው ሲነገራቸው ይህንኑ ተቀብለው ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ምርጫውን ጥላሸት ይታያሉ። ይህን መሰሉ በውጤት ማጣት ላይ የተመሰረተ ትችት ሀገራችን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመራት ከጀመረች ወዲህ በተካሄዱ አራት አጠቃላይ ምርጫዎች የሽንፈት ማጀቢያና ማድመቂያ ሆኖ ተስተውሏል።
ህዝቡ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ኢህአዴግን በመምረጥ ተቃዋሚዎችን ወንበር ባሳጣበት ምርጫ 2002 አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የርዕዩተ ዓለም ጣጣ ይዟቸው ፍላጎታቸውን በህዝባችን ላይ ለመጫን የቋመጡ ኒዮ ሊበራሎች የምርጫውን ውጤት ለማጉደፍ ያደረገትን ሙከራ ህዝቡ “ድምፃችን ይከበር” በሚል ሰፊ ንቅናቄ በሉዓላዊነቱ ጉዳይ ፈፅሞ እንደማይደራደር በአደባባይ በማውገዝ ህዝቡ ለኢህአዴግ የሰጠው ድምፅ ትክክል መሆኑን አረጋግጧል።
በዚሁ ወቅትም ታላቁ መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ በህዝባዊ ሰልፉ ላይ በመገኘትና ህዝቡ ለኢህአዴግ ለሰጠው ድጋፍ እጅ በመንሳት ኢህአዴግ ለህዝቡ የላቀ ተጠቃሚነት እና ለሀገራችን ህዳሴ እውን መሆን የተለጠጡ ግቦችን ቀርፆ በተሻለ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ መሰረትም ኢህአዴግ ለህዝቡ በገባው ቃል መሰረት ወገብ የሚያጎብጡ ሰፋፊ እቅዶችን አዘጋጅቶ ህዝቡን በማሳተፍ ባከናወነው ተግባር በርካታ ስኬታማ ወጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ኢህአዴግ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ  ህዝቡ በመምረጥና መመረጥ ዴሞክራሲያዊ መብቱ በንቃት እየተሳተፈ፣ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነቱን እንዲያረጋግጥ ኃላፊነቱን በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛል። ነገር ግን የሀገራችን ተቃዋሚዎች ለስልጣን ካላቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ሁሉንም ጠቅልሎ በመያዝ አሊያም ሁሉንም በማጣት የዜሮ ድምር ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ መዋኘታቸውን ቀጥለዋል። ለዚህም በምርጫ 97 ህዝብን ባለማክበር፣ የሰጣቸውንም የመራጭነት ድምፅ ሜዳ ላይ በመበተን ያሳዩት ያልተገባ ተግባር አስረጂ ነው።
ተቃዋሚዎች ህዝብ የሰጣቸውን ድምፅ አክብረው በቀጣይ የተሻለ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ከመሞከር ይልቅ በነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ አገራዊ ምርጫዎችን በውጤታቸው ይኮንናሉ። ኢህአዴግ የበርካታ የሀገራችን ተቃዋሚዎች አሰተሳሰብ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ቅኝት ነው የሚለው ለዚህ ነው።
አሁንም አንዳንድ የሀገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተለመደው የተሳሳተ አስተሳሰብ በመውጣት ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱና ለህዝቦች ሉዓላዊነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ኢህአዴግ ጥሪውን ያቀርባል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በተመዝጋቢም ሆነ በተሳትፎ የተሻለ እንደሚሆን ህዝባችን የመራጭነት ካርድ ለማውጣት ካደረገው ከፍተኛ ተሳትፎ መረዳት ችለናል። ህዝቡ ልማትና ዴሞክራሲን በማስቀጠል በዕለት ተዕለት ህይወቱ ላይ የተሻለ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መንግስት ለማቋቋም የምርጫን አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ መገንዘቡንም በአድናቆት ታዝበናል፤ ለዚህም ኢህአዴግ ከፍተኛ ክብርና ምስጋና ያቀርባል።
ከዚህ አኳያ የምርጫው ዋነኛ ባለቤት ራሱ ህዝቡ በመሆኑ ኢህአዴግ ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ትልቁ ድርሻ የመራጩ ህዝብ ነው ብሎ ያምናል። ይህም ሲባል በምርጫ ሂደቱ በንቃት በመሳተፍ፣ ድምፁ እንዲከበር በማድረግ፣ ሰላሙን በማስጠበቅና ምርጫውን ለመበጥበጥ የሚሹ ሀይሎች ካሉም መብቱ እንዳይጣስ በመከላከል ከመንግስት ጋር እንደሚሰራም እምነቱ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ህዝቡ በምርጫው ይበጀኛል ብሎ እምነት የጣለበትን የፖለቲካ ፓርቲ በነፃነት መምረጥ እንዲችል ኢህአዴግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ያረጋግጣል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች
ለዘንድሮው  አጠቃላይ  ምርጫ ሰኬታማነት ካርድ ከማውጣት ጀምሮ ላሳያችሁት ከፍተኛ ተሳትፎ ኢህአዴግ አድናቆትና ክብር አለው። በዚህ አጋጣሚም ህዝባችን እያደረገ ላለው ተሳትፎና ቁርጠኝነት ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል።
የዘንድሮው ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሚናችሁን በአግባቡ እንደምትወጡም ኢህአዴግ ሙሉ እምነት አለው።
የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት በማደናቀፍ የተያያዝነውን የህዳሴ ጉዞ ለማጓተት የሚታሰቡና የሚተገበሩ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በንቃት በመከታተልና በመመከት ለነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውንነት ሁላችንም በጋራ እንድንሰራ ኢህአዴግ ጥሪውን ያቀርባል።
ኢህአዴግ እስካሁን ባከናወናቸው ስኬታማ ስራዎች ሳይኩራራ የሀገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ የበለጠ ለመስራት፣ ህዝብ የሚሰጠውን ተጨማሪ እድል በአግባቡ ለመጠቀምና የላቁ ድሎችን ለማስመዝገብ ቁርጠኛ እንደሆነ ዋነኛው ምስክራችን ህዝባችን በመሆኑ ለበለጠ ለውጥና እድገት የሚተጋውን ኢህአዴግን ይምረጡ!
ኢሕአዴግ ምርጫውን አስመልክቶ የሚያስተላልፋቸውን ተከታታይ መልዕክቶች በድረ ገፃችን
http://www.eprdf.org.et 
በፌስቡክ ገፃችን 
EPRDF official 
እንዲሁም በቲዊተር 
@EPRDFEthiopia ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ኢህአዴግን መምረጥ ህዳሴን ማስቀጠል ነው!
ኢህአዴግን ይምረጡ!!

No comments:

Post a Comment