EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Tuesday 3 March 2015

በዓላማ ፅናትና ህዝባዊ ወገንተኝነት የዘለቀ ድርጅት - ኢህአዴግ!

የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን በህዝቦች ተሳትፎ በስኬት ተጠናክሮ ቀጥሏል!
ኢህአዴግ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ሰላም የማይነጣጠሉና አንዱ ያለሌላው መቆም እንደማይችል ይገነዘባል፡፡ ይህን ጉዳይ በፕሮግራሙም ላይ ቀርጾ ለተግባራዊነቱ በመንቀሳቀሱ ዛሬ የበርካታ ስኬቶች ባለቤት ሆነናል፡፡ ዴሞክራሲ በአገራችን የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን በጽናት በማመን ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል፡፡
ለዴሞክራሲ እውንነት የታገለ ድርጅት - ኢህአዴግ!
ባለፉት ስርዓቶች ያልተመለሱ የሰላምና ዴሞክራሲ እጦት እንዲሁም የድህነትና የኋላቀርነት ምንጭ የሆኑ በርካታ የህዝብ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ በተለይ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብት ጥሰቶች በርካታ ስቃይ አሳልፈዋል፡፡ የመሬት ባለቤትነት መብታቸውን ለረጅም ዘመናት ከመነፈጋቸውም በላይ ለስም የመሬት ባለቤት ሆነዋል በተባሉበት ጊዜ እንኳ በመሬታቸው ያመረቱትን ምርት እንዳይጠቀሙና የበይ ተመልካች እንዲሆኑ በአምባገነኖች ጫና ሲደርስባቸው ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች በማንነታቸው እንዳይኮሩ ከመደረጉም በላይ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸውን ለዘመናት ተነጥቀው ኖረዋል፡፡ በአገራችን ህዝቦች የተባበረ ትግልና መስዋእትነት የአምባገነናዊ ስርአት ግብአተ መሬት ከመፈፀሙ በፊት የዴሞክራሲ መብቶች መታፈን ከሚዘገንን ድህነት ጋር ተዳምሮ የብሄር ቅራኔ እጅግ በጣም ወደተካረረበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። አገሪቱ ከዳር ዳር በቅራኔውና ቅራኔው በፈጠረው ጦርነት የምትታመስበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር።
ሆኖም የተሸከሙትን የጭቆና ቀንበር ለማራገፍ እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረጉት ህዝቦች መብቶቻቸው እንዲመለሱ በፅናት ታግለዋል፡፡ ኢህአዴግም ባለፉት ስርዓቶች ያልተመለሱ የሰላምና ዴሞክራሲ እጦት ምንጭ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ ትግሉን በስኬታማነት መርቷል። በዚህም አማካይነት የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በርካታ ድሎችን ተጎናፅፈዋል። በውጤቱም በሀይል አንድነት ጥላ ስር እንዲሆኑ ተገድደው ሲደርስባቸው የነበረው ጭቆናና ሰቆቃ ተወግዷል፡፡ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አዲስ ዴሞክራሲያዊ አንድነትም እውን ሆኗል።
ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በቋንቋቸው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋቸውን የማሳደግ እና ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት፣ ታሪካቸውን የመንከባከብ መብት ከመጎናፀፋቸውም በላይ ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር በቅተዋል።
ዛሬ አገራችን የነበረባትን የጦርነትና የሰላም እጦት አስወግዳ ከእራሷ አልፋ የጎረቤቶቿ ሰላም እንዲከበር በማድረግ የሰላም ተምሳሌት ሆናለች፡፡  በዓለም ደረጃ በረሃብ ስትታወቅ የነበረችው አገር ተከታታይ፣ ፈጣንና ዘላቂ ልማት ከሚያስመዝግቡ ጥቂት የዓለም አገሮች አንዷ ለመሆንም በቅታለች፡፡
አገራችንን ከመበታተን አደጋ ያዳነ ድርጅት - ኢህአዴግ!
በአገራችን እየተመዘገቡ ያሉ ወርቃማ ስኬቶች የትግላችሁና የመስዋእትነታቸሁ ውጤቶች መሆናቸውን ኢህአዴግ በጽናት ያምናል፡፡ እነዚህ ስኬቶች አልጋ በአልጋ የተገኙ ሳይሆን ይልቁንም እልህ አስጨራሽና አስቸጋሪ ሂደቶቹን በማለፍ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
የዘመናት ጥያቄ የነበሩ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለዋል። ኢህአዴግ የትጥቅ ትግሉን በከፍተኛ ቁርጠኝነትና መስዋእትነት መርቶ ህዝቦች ተፈቃቅደውና ተከባብረው የሚኖሩባት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት አዲስ ምእራፍ በመክፈት የሚያኮራ ታሪክ ያስመዘገበ የእናንተው ድርጅት ነው።
በደርግ መንግስት ውድቀት ማግስት አገራችን ትበታተናለች የሚለውን ስጋት ከዴሞክራሲያዊ ባህሪው በመነጨ በሳል አመራር መቀልበስ የቻለው ኢህአዴግ የአገራችን ህዝቦች ለዘመናት ሲመኙት የነበረውን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲጓዝ ታሪካዊ ሃላፊነቱን ተወጥቷል፡፡ ኢህአዴግ በህዝብ ሳይመረጥ በብቸኝነት ስልጣን ይዞ ለመቀጠል እንደማይፈልግ፤ ይልቁንም ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት እንደሚፈልግ ገና የትጥቅ ትግሉ ሳይጠናቀቅ ለመላ የአገራችን ህዝቦች ይፋ ያደረገው አቋሙ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ከአምባገነናዊው ስርዓት መወገድ ማግስት የሽግግር መንግስት እንዲመሰረትና የህዝብ ሉአላዊነት እንዲከበር የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ቁርጠኛነቱን አረጋገጧል፡፡ የሽግግር ሂደቱ እንዳይሳካ ሳንካ የነበረውን የትምክህትና የጠባብ ሃይልንም በጽናት ታግሏል፡፡  
ህዝባዊው ድርጅት ኢህአዴግ በሽግግር መንግስቱ ቻርተሩ መሰረት የተሰጠውን ህገ መንግስት የማርቀቅና በህዝብ ነፃ ምርጫ በተቋቋመ የሕገ መንግስት ምክር ቤት ኃላፊነቱን በአግባቡ  የተወጣ ሲሆን የተለያዩ አማራጮችን ጎን ለጎን ይዞ የቀረበ ረቂቅ ህገ መንግስት ተዘጋጅቶ ለህዝቡ ውይይት እንዲቀርብ የጎላ ሚና ነበረው፡፡ በወቅቱ እስከ አስራ ስምንት ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች በየአካባቢው በተፈጠሩ መድረኮች   በረቂቅ የህገ መንግስት ድንጋጌዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ  ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ተደርጓል፡፡ በተለያየ ደረጃ በተካሄዱ ውይይቶች የዳበረው ረቂቅ ህገ መንግስት የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች በተገኙበት  ህዳር 29 ቀን 1987 . ፀድቋል፡፡ይህ ሂደት የአገራችንን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የዘመናት ጥያቄ ከመመለሱም በላይ አስተማማኝ ዋስትና እንዲያገኙና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲመሰርቱ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡
ብዝሃነትን ያስተናገደ ድርጅት - ኢህአዴግ!
ለዘመናት ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ተስኗት የቆየችው አገራችን ብዝሃነትን በአግባቡ ወደሚያስተናግድ አዲስ ህገ መንግስታዊ የእኩልነትና የፌዴራላዊ አስተዳደር ስርዓት የተሸጋገረችው በዚሁ ህገ መንግስት አማካይነት ነው፡፡
የኢፌዲሪ ህገ መንግስት መጽደቅን ተከትሎ የአገራችን ህዝቦች  ግንቦት 1987 ዓ.ም በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄዱት ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚበጃቸውን መንግስት በመምረጥ ለዘመናት የታገሉለትን የሉአላዊ ስልጣን ባለቤትነት መብታቸው አረጋግጠዋል፡፡ እስካሁን ድረስም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በየአምስት አመቱ ጊዜያቸውን የጠበቁ አራት የተሳኩ አገራዊ አጠቃላይ ምርጫዎችን በማካሄድ ህገ መንግስታቸው ያጎናጸፋቸውን መብት በተግባር አጣጥመዋል፡፡ ዘንድሮም  በግንቦት ወር ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ በነቂስ ወጥተው የተመዘገቡ ሲሆን  በፍቃዳቸው መንግስት ለመመስረት የሚያበቃቸውን መብታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህም የዴሞክራሲዊ ስርአት ግንባታችን በህዝቦች ባለቤትነትና የነቃ ተሳትፎ በስኬት ታጅቦ እየቀጠለ በመሆኑ ኢህአዴግ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን ከፍተኛ ስኬት አድርጎ ይመለከተዋል ፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች!
ዴሞክራሲያዊ አንድነታችን እንዲጠናከር ያደረገ ድርጅት- ኢህአዴግ!
የአዲሱን ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት እውን መሆን ተከትሎ በሀገራችን የተዘረጋው የፌዴራሊዝም ስርዓት አገር ይበታትናል በማለት ተቃዋሚው ሃይል ቢዘበትበትም ስርዓቱ ለአገራችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ አገራችን በፌዴራል መንግስትና በክልል መንግስታት ተዋቅራ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤቶች እንዲሆኑም አስችሏል፡፡ የፌዴራል ስርዓታችን ባለፉት ስርዓቶች ለዘመናት ተዘንግቶ የኖረውን የብዝሃነት ጥያቄዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ምላሽ ሰጥቷል። የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሁሉም መስክ እኩል የመሳተፍ፤ የመልማትና የመጠቀም የመብት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙም አድርጓል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረና እያደገ የመጣው የህዝባችን ተሳትፎ በተለያየ መልኩ የሚገለፅ ነው። ዛሬ አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሕዝቦች ቀጥተኛ የዴሞክራሲ ተሳትፎ የተረጋገጠባት፣ ሕዝቡ ከዝቅተኛ የአስተዳደር እርከኖች ጀምሮ በእቅድ አወጣጥ እና አፈፃፀም ላይ የሚሳተፍበት እንዲሁም በአካባቢው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች ተመቻችተው ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው፡፡ አገራችን አሁን ከአራት ሚሊዮን በላይ አባሎች ያሏቸው በየደረጃው የተቋቋሙ የህዝብ ምክር ቤቶች ያሏት ሲሆን ሕዝቡ በየአካባቢው ባሉ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይወሰን በአገራዊ ጉዳዮች ጭምር በመወያየት እቅዶችና ፖሊሲዎች ሲዘጋጁ ግብዓት የሚሰጥበት፣ በመንግስት እቅድ አፈፃፀም ላይም ገንቢ አስተያየትና ሂስ የሚሰጥበት ስርዓት እውን እንዲሆን ኢህአዴግ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት አድርጓል።
ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እነሱን በሚመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው የህገ መንግስታችን  ትሩፋት ነው።
ከላይ እንደተገለፀው እነዚህ ሁሉ ስኬቶች በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኙ ናቸው፡፡ኢህአዴግም ህዝቦች በነፃነት የሚሳተፉበት ስርዓት እውን እንዲሆን በከፈለው መስዋዕትነት ይኮራል። በቀጣይም የህዝባችንን ቀጥተኛ ተሳታፊነት በላቀ ሁኔታ ለማረጋገጥ  በላቀ ሁኔታ እና በቁርጠኝነት እንሚረባረብ ቃል ይገባል። 
አሳፋሪ ገፅታችንን የቀየረ የህዝብ ድርጅት- ኢህአዴግ!
የህዝባችን የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመመለሳቸው ለዘመናት ከምንታወቅበት የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የረሃብና ጉስቁልና ታሪክ ወጥተን ለጋራ ልማት በጋራ መረባረብ ጀምረናል፡፡ የእነዚህ መብቶች ህገ መንግስታዊ ዋስትና ማግኘትና ያለፉት አመታት ስኬታማ አተገባበር አገራችን ከመበታተን አደጋ ወጥታ በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲኖራት አስችሏል፡፡
የፌዴራል ስርዓታችን በቀድሞ ስርዓት ወቅት ከነበረው የሃይል አንድነት እሳቤ ተላቀን በመተማመን ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንድናዳብር አስችሎናል። እየገነባን ያለነው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዘላቂ ሰላም በማስፈን የውስጣችንን የትርምስ ታሪክ ከመዝጋት አልፎ በምንገኝበት የትርምስ ቀጠና የሰላም ተምሳሌት ለመሆን አብቅቶናል። የአገራችን ግፉአን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበት እድል በማግኘታቸው ቀጣይነት ያለው እድገት ለማምጣትና ለመጠቀም በቅተዋል። ዛሬ በአገራችን እውን የሆነው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የአገራችንን ታሪክ ከመሰረቱ ለመቀየር ያስቻለ መሰረተ ሰፊ፣ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ባለ ሁለት አሃዝ እድገት እንድናስመዘግብ ያስቻለን ነው።
በዓላማ ፅናትና ህዝባዊ ወገንተኝነት የዘለቀ ድርጅት - ኢህአዴግ!
ዛሬ ሁሉም እንደሚገነዘበው ሌት ከቀን በሚተጉ ህዝቦቿ አገራችን ተስፋ የሰነቀች፣ ሩቅ አዳሪ ራዕይ ያላትና ይህንኑ ራዕይ እውን ለማድረግ እየተጋች ትገኛለች። ይሁን እንጂ የአገራችን ተቃዋሚዎችና በውጭ የሚገኙ ፅንፈኛና አክራሪ የኒዮ ሊበራል አቀንቃኞች ዛሬም እንደ ጥንቱ የአገራችንን ትርምስና መበታተን  ሲያሟርቱ ማየት የተለመደ ነው። የአገራችን ተቃዋሚዎችና የጥፋት ተላላኪዎች የአገራችንን የህዳሴ መሰረት ለመሸርሸር ሲዋትቱ ማየትም አዲስ አይደለም።
ተቃዋሚዎቻችን በትብብር ላይ የተመሰረተውን ዴሞክራሲያዊ የፌዴራሊያዊ ስርአታችንን ለማጥላላትና ፋይዳውን ለማንኳሰስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።  የትምክህት ሀይሉ በአንድ በኩል በመልክአ ምድር አወቃቀር ላይ የተመሰረተ የፌዴራሊዝም ስርአት ለአገራችን የሚበጀው አማራጭ ነው በማለት የወደቀውን የአፄና የደርግ አሃዳዊ የጠቅላይ ግዛት አሰራር ዳግም በህዝቦች ላይ በሃይል ለመጫን ሲውተረተር ይታያል። በሌላ በኩል ደግሞ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተውን የፌዴራል ስርአታችንን አገር እንደሚበታትንና እንደሚያፈርስ ሲወተውት ይደመጣል።
ጠባቡ ሃይል በበኩሉ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ለጥጦ በመተርጎም ማሳካት ለሚፈልገው ለኪራይ ሰብሳቢነት አላማው ስኬት በህጋዊ ሽፋን ጭምር ሲንቀሳቀስ ይስተዋላል። ከዚህ አኳያ የወደቁ ስርአቶችን መልሶ በህዝቦች ላይ ለመጫን የሚንቀሳቀሰውም ሆነ ለግል ጠባብ ዓላማው የሚተጋው ሃይል ለዘመናት የአገራችን ህዝቦች ብሄራዊ ጭቆናን አሽቀንጥረው ለመጣል ያደረጉትን እልህ አስጨራሽ ትግልና የተገኘውን ውጤት እውቅና የሚነፍግ ከመሆኑም በላይ አንዳችም ህዝባዊ ውግንና የሌላቸው ኪራይ ሰብሳቢዎች መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ሃቅ ነው።
ኢህአዴግ የአገራችን ኪራይ ሰብሳቢዎች በመገንባት ላይ ባለው ብዝሃነትን የተቀበለ ዴሞክራሲያዊ ስርአታችን ላይ ከሚያራምዱት ፖለቲካዊ አቋም በመሰረቱ የተለየና ለብሄራዊ ጭቆና ምንጭ የሆነውን አሃዳዊ አወቃቀር በመሰረቱ በመለወጥ በብዝሃነት ላይ የተመሰረተችውን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ላይ እየገነባ ነው። 
ለጀመርነው የህዳሴ ጉዞ መረጋገጥ - ኢህአዴግ!
በኢህአዴግ መሪነት በአገራችን እውን እየሆነ ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚሰብከውና የቆመውሰላም፤ ለዘላቂ ልማት፤ ለእኩልነትና በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ መደጋገፍ ነው። ስርዓታችን አብሮ መኖርንና ማንነትን ያልጨፈለቀ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያበረታታ ነው። ድርጅታችን ዴሞክራሲ የህልም እንጀራ ሳይሆን ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ እኩል የሚሳሳለት፣ እኩል የሚቋደሰውና እኩል የሚንከባከበው እንደሆነ ያምናል። ስለሆነም በመገንባት ላይ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት ሁላችንም እንድንጠብቀው ኢህአዴግ ጥሪውን ያቀርባል።   
የአገራችን ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ በዘላቂነት የሚረጋገጠው በኢህአዴግ መሪነት ስለሆነ   የህዝባዊ ወገንተኝነት ትክክለኛ ማሳያ የሆነውን ኢህአዴግን በመምረጥ የህዳሴ ጉዟችንን እናስቀጥል!!  
ኢሕአዴግ ምርጫውን አስመልክቶ የሚያስተላልፋቸውን ተከታታይ መልዕክቶች በድረ ገፃችን www.eprdf.org.et በፌስቡክ ገፃችን EPRDF official ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ኢህአዴግን መምረጥ ህዳሴን ማስቀጠል ነው!!

5 comments:

  1. The camel do not stop walking whatever the dog is barking.

    ReplyDelete
  2. uncompromising regarding their interest of people.

    ReplyDelete
  3. ኢህአዴግን መምረጥ የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል ነው!!

    ReplyDelete
  4. yes we can not need to continue as we have we need change. but the change is only with EPRDF in order to fulfil our benefits but not benefit of EPRDF we are under the umbrella of EPRDF,,,,we can not give a chance for those needs to break this umbrella.

    ReplyDelete