EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday 6 March 2015

በኢህአዴግ አመራር የማሽቆልቆል ጉዞዋ ተገትቶ ወደ ቀድሞ ስልጣኔዋ እየተመለሰች ያለች ሀገር!


እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድ ወቅት የሚያኮራ ታሪክ ባለቤት የሆነውን ያህልያለ ፉት ስርዓቶች በተከተሉት የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት በዓለም ላይ አንገታችንን ያስደፋ የኋላቀርነትና የተመፅዋችነት፣ የጦርነትና የብጥብጥ፣ የጭቆናና የፀረ ዴሞክራሲ ምድር ተብለን እስከመታወቅ ደርሰን ነበር። ሀገራችን በርካታ ልዩነቶች ባላቸው ብዙ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተዋቀረች ሕብረ ብሔራዊ ሀገር ብትሆንም በየወቅቱ የነበሩት ስርዓቶች ይህንኑ እውነታ በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችል አቅጣጫ ባለመከተላቸው በዓለም ከምትታወቅበት የስልጣኔና የእድገት  ማማ ወርዳ ወደ ማያቋርጥ የማሽቆልቆል ጉዞ በመግባቷ በዓለም ላይ የረሃብና ኋላቀርነት ምሳሌ ለመሆን መብቃታችን ሲያሳፍረን፣ ሲያስቆጨንና ሲያንገበግበን ቆይቷል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ሀገራችን ዓለም ካደነቀው ከፍተኛ የስልጣኔ ማማ ተነስታ የዓለም ህዝቦች ጭራ ያደረገን ታሪክ እንዲቀየር ሰላማዊ የመፍትሄ አማራጭ ያቀረቡ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስርዓቶች በግፍ ተገድለዋል፡፡ እኩልነትና ዴሞክራሲ ይስፈን ብለው የታገሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለዋል። በየወቅቱ የነበሩ ገዥዎችም በየጊዜው ይነሱባቸው የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎች ለማፈን ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም የትኛው የህዝብ ጥያቄዎችንና ትግሎችን ለአፍታም ቢሆን ማስቆም አልቻሉም ነበር። በአምባገነኖች ይፈፀሙባቸው የነበሩ ግፍና መከራዎችን አሜን ብለው ሳይቀበሉ ለመብታቸው፣ ለእኩልነታቸውና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው የተፋለሙ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአምባገነኖችን ግፍና በደል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሽቀንጥረው ጥለው አዲስ ምዕራፍ እውን አድርገዋል። የዛሬ 23 ዓመት በኢህአዴግ ግንባር ቀደም መሪነት የተጀመረው ስኬታማ ጉዞ የኢትዮጵያ አሳፋሪ የታሪክ ምዕራፍ እንዲቀየር፣ የህዳሴ ጉዞአችንም እንዲጀመር አድርጓል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
ከውጭ ወራሪ ነፃነቷ ተጠብቆ የኖረችው ሀገር ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገራዊ ነፃነቱን የማንነቱ አንዱና ዋነኛ መለያው አድርጎ ይመለከታል። የሀገራችን ህዝብ አፍሪካውያን ጥቁር ህዝቦች ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ የሚወጡበትን መንገድና ወኔ ያመላከተ የነፃነት ተምሳሌትም ነው። አሁን ያለው ትውልድም ይህን የፅናት ፈለግ በማስቀጠል ዳግም የስልጣኔ ማማ ላይ የደረሰች ሀገርመፍጠር ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ውሎ አድሯል። የተጀመረው የህዳሴ ጉዞም እውን መሆን የሚችለው ከዚህ በፊት ለውድቀት የዳረጉንን ችግሮች ምንጭ አውቆ ስህተቱን አርሞ በተገቢው ሁኔታ መጓዝ ሲችል ብቻ እንደሆነ ኢህአዴግ በጥብቅ ያምናል። ይህን እምነቱንም ከሚመራበት ፕሮግራም ጋር አዋህዶ፣ ህዝቡን አሳምኖና አሳትፎ ወደ ተግባር በመቀየሩ ስኬታማ ውጤቶች ማስመዝገብ ችሏል።
ኢህአዴግ እንደ ሀገር ከስልጣኔ ማማ የመውደቃችን፣ የቁልቁለቱ ጉዞ ውስጥ የመዘፈቃችንና ወደ መበታተን አፋፍ ደርሰን የነበረ የመሆናችን ዋነኛ መንስኤ ብዝሃነትን ያከበረ ስርዓት በኢትዮጵያ ያልነበረ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ያምናል። ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች፣ብዙ ቋንቋዎች ሀገር መሆኗ እውነት ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያዊነት ሽፋን ማንነትን ያላከበረ የኃይል አገዛዝ በሀገሪቱ ለረጅም ዘመናት በመስፈኑ ህዝባችን በርካታ ዓመታትን ለፈጀ ተከታታይ ጦርነት፣  ረሃብ እንዲሁም  ስር ለሰደደ ድህነት ተጋልጦ ቆይቷል።
በሀገራችን የቀደመ ታሪክ የገዥ መደቦች እነሱ ከሚናገሩት ቋንቋና ከሚከተሉት ኃይማኖት ውጭ ሌላ ቋንቋና እምነት እንደሌለ በመቁጠር በዜጎች ላይ ሲፈጥሩ የነበረው ጭቆናና መገለል ሌላው የቅሬታ ምንጭ ነው። በራስ ቋንቋ መማርም ሆነ መስራት ፍፁም በማይታሰብባት የድሮዋ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መብትን መጠየቅ ለሞትና ስደት የሚዳርግ ነበር። ሆኖም መላው የሀገራችን ህዝቦች ከልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተገለውና ተነጥለው የኖሩበት የግፍ አመታት በከፈሉት አኩሪ ተጋድሎ ተዘግቶ ዛሬ አዲስ የህዳሴ ምዕራፍ ተከፍቷል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
የኢትዮጵያ የህዳሴ ዘመን ላይቀለበስ ተጀምሯል፡፡ በህዝባችን ሙሉ ተሳትፎና ሀገራዊ ርብርብ የቀጠለውን የህዳሴ ጉዞ ኢትዮጵያውያን እንደ ጥንቱ ዘመን የስልጣኔ ጀግኖቻችን የማይቻሉ የሚመስሉ ፕሮጀክቶችን በመተግበርና ድህነትን አሸንፎ ለመውጣት በመስራት እያረጋገጥን መጥተናል። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመቻላችን አንዱ ማሳያና የህዳሴያችን አይቀሬነት ማረጋገጫ ነው። በስልጣኔ ዘመናችን ሌሎች ያልቻሏቸውን ተግባሮች መፈፀም የቻልን ህዝቦች በዚህ ዘመንም ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ጋር መጓዝ መቻላችንን የሚያረጋግጡልን በአካባቢያችንና በአህጉራችን ቀዳሚ የሚያደርጉን ግዙፍ ፕሮጀክት ነድፈን በስኬት እየፈፀምን እንገኛለን፡፡ የጀመርናቸው ታላላቅ ስራዎች በመሰረተ ልማት አቅርቦት የተሳሰሩ ህዝቦች ብሎም የአካባቢው አገሮች  የጋራ ህዳሴ ተቋዳሽ የሚሆኑበትና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩባቸው ናቸው። ዛሬ የሀገራችን የህዳሴ ጉዞ መሰረት ተጥሏል። በሀገራችን ለዘመናት ስር ሰዶ የኖረው የሰላም እጦት ታሪክ ሆኗል።እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት መብት ተረጋገጧል፡፡ በሀገራችን የብሔሮች፣ ሀይማኖቶች እና እምነቶች  ብዝሃነት በተጨባጭ ብዝሃነት እያለ  እኩል እውቅናና እኩል የመከበር መብት ተነፍጓቸው የኖሩበት የስቃይ ምዕራፍ ተዘግቷል። ዛሬ ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመብት ጥሰቱ ላይደገም መቋጨቱን በጋራ ይሁንታቸው እውን ባደረጉት ህገ መንግስት ረጋገጡ በኋላ የጋራ ጠላታቸውን የሆነውን ድህነት ወደ መፋለም ፊታቸውን አዙረዋል።
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
የሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር፣ የመስራትና የመዳኘት፣ የፈለጉትን እምነት የመከተል፣ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ መከበራቸው ኢትዮጵያውያን ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ እና የጀመርነው የህዳሴ ጉዞ በተሳካ ሁኔታ እንዲቀጥል ያደረጉ ናቸው። ኢህአዴግ ከሁሉም ነገር በፊት ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የዴሞክራሲ መብቶች መከበር በፅናት የሚቆመው እነዚህ መብቶች ለማንም ሰብዓዊ ፍጡር ሊሟሉለት ከሚገቡ መብቶች ውስጥ ስለሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በሀገራችን ሰላምና ብሄራዊ መግባባት እንዲሰፍን፣ በዚህም ምክንያት መላው ህዝብ ድህነትን በመታገል እንዲረባረብና በተደራጀ ልማት ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ ማድረግ የሚቻለው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ ነው የሚል መሰረታዊ አቋም ስላለው ነው፡፡ ይህም ህዝባዊ ወገንተኝነቱን ያረጋግጣል።
ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ህዳሴ ብዝሃነትን ባከበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የሚገነባና እየተገነባ ያለ እንደሆነ ያምናል። የህዳሴያችን ባለቤትና ፈፃሚ ህዝቡ በመሆኑ በሀገራችን ለዘመናት ሲፈፀሙበት የነበሩትን በደሎችምንጫቸው በመለየት እንዲታረሙ አድርጓል፡፡ እንዳይደገሙም ሁሉን አቀፍ የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጦ በመንቀሳቀስ ባለፉት 23 ዓመታት ህዝቡ የሰላም፣ የልማትና ዴሞክራሲ ስኬት እንዲጎናፀፍ አድርጓል። ስለሆነም የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ የትላንቷን ኢትዮጵያ መነሻ የሚያደርግ፣ የዛሬውን ትክክለኛ ጉዞ አስቀምጦ የሚጓዝና የነገውን መዳረሻችንን የሚያመላክት ነው።
ኢህአዴግ ይህን መነሻ በማድረግ ላለፉት 23 ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት የሀገራችንን የተመፅዋችነት ታሪክ ቀይሯል፤ ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር በእርዳታ ላይ ከተመሰረተ ግንኙነት ተላቅቃ ትብብር ላይ ወደ ተመሰረተ የኢኮኖሚ አጋርነት መሸጋገር ችላለች። ትላንት በድህነቷና ኋላቀርነቷ በመዘባበት የረሃብ ተምሳሌት ያደርጓት የነበሩ መንግስታትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በልማቷ ባስገኘችው ስኬት ተስፋ ያላትና በእድገት እየገሰገሰች ያለች ሀገር መሆኗን መመስከር ጀምረዋል። አሁን ሀገራችን ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት የዓለም ሀገራት አንዷ መሆኗን፤ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም መዳረሻነት ከተመረጡ የዓለም ሀገራት አንዷ ስለመሆኗ እየዘገቡ ያሉት የእነዚሁ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ናቸው፡፡ ይህም ኢህአዴግ በቀየሰው ትክክለኛ ፖሊሲና በህዝባችን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ የተገኘ ሰኬት እንደሆነ ህዝባችን የሚገነዘበው እውነታ ነው።
ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ለራሳቸውና ለሀገራቸው ክብር በእልህና ቁጭት ከመስራት አልፈው ለጎረቤት ሀገሮች ህዝቦች የጋራ ጥቅም በሰላምና ልማት የሚሰለፉ መሆናቸውን ማስመስከር ችለዋል። ይህም ኢትዮጵያን እንደ ስጋት ያዩዋት የነበሩ ጎረቤት ሀገሮች አቋማቸውን ቀይረው ኢትዮጵያ የሰላምና አብሮ የመልማት ራዕይ ያላት ሀገር መሆኗን ተቀብለው በመሰረተ ልማት ተሳስረዋል፡፡ በኢህአዴግ አመራር እየተተገበረ ያለው የልማትና ዴሞክራሲ ክንውን በሀገራችን ባለፉት 23 ዓመታት ውጤት የማስመዝገቡ አንዱ መገለጫ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ገቢ እንዲጨምር ማስቻሉ ነው። የዜጎቻችን ዓመታዊ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ በ1983 ከነበረበት 70 የአሜሪካን ዶላር ተነስቶ አሁን ወደ 632 ዶላር ከፍ ብሏል፡፡ በሀገራችን ሁሉም አካባቢዎች   እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ከህዝቡ የዕለት ተዕለት ተጠቃሚነት ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ በመሆናቸው በዜጎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ አወንታዊ ለውጥ እንዲኖር ያደረጉ ናቸው።  ከምግብ እህል ተመፅዋችነት ተላቀን በአመት በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ ከ250 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እህል በማምረት በምግብ እህል አቅርቦት በሀገር ደረጃ ራሳችንን ችለናል፡፡ ልትበታተን ከነበረች ሀገር በመነሳትና ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ በማስቀመጥ በመስራታችን አስተማማኝ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በማካሄዳችን ለሀገራችን ህዳሴ የተሳካ ጉዞ መሰረት ጥለናል።
ጅምሩ የህዳሴ ጉዟችን በአንፀባራቂ ውጤት እንደቀጠለው ሁሉ ለፈጣኑ ልማታችን ሌት ተቀን እየተጋን በመሆናችን የድህነት አዙሪቱን መውጣት ጀምረናል፡፡ ይህ የህዳሴ ጉዟችን ዘመን በስኬት መጀመሩ ህዝቡ በታላቅ ፅናትና ቁርጠኝነት ከኢሕአዴግ ጎን በመሰለፉ መሆኑን  ድርጅታችን ይገነዘባል፡፡
በአንፃሩ ገና ከጅምሩ ህዳሴ ብሎ ነገር ቀልድ ነው በማለት ልማቱን ከዳር ሆነው በመተቸት የመበታተናችንን መርዶ ለመስማት የቋመጡ ሀይሎች ነበሩ። አንዳንድ የዋህ ተጠራጣሪዎች ደግሞ የህዳሴ ጉዟችን መጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝቡ በጠንካራ ተሳትፎ በጀመረ ጊዜ በአንድ የተቃውሞ ግንባር ተሰልፈው አንዳንዶቹ  ግድቡ አሁን መጀመሩ ወቅታዊ አይደለም፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ታስቦ ነው ሲሉ ሌሎቹ  ደግሞ ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ለማጋጨት ታስቦ ነው በሚል ሲያጥላሉት ተደምጠዋል፡፡
ይህ የሚያስገነዝበው የሀገራችን ተቃዋሚዎች ይህንን ታላቅ ህዝባዊ አደራና ኃላፊነት የመቀበልና የመተግበር ዝግጁነት የሌላቸው፣ ወገብ የሚያጎብጥ እቅድ፣ ሀገርና ህዝብን የሚለውጥ የልማት አጀንዳ በተግባር ለመሞከር ቀርቶ ለማሰብም የሚከብዳቸው መሆኑን ነው። የሀገራችን ተቃዋሚዎች በልማት ጉዳይ ላይ ከሕዝቡ ፍላጎት በተፃራሪ የተሰለፉና ኢሕአዴግና መላው ሕዝባችን በጋራ ሆነው ላሳኳቸው የልማት ውጤቶች ተገቢ እውቅና ለመስጠት የሚቸገሩ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ታዝበናል
የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች!
አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለማንኛውም አይነት የፀረ እኩልነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት አስተሳሰብና ተግባር ቦታ የምትሰጥ አይደለችም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን በገነቡበት የቃል ኪዳናቸው ሰነድ  በሆነው ህገ መንግስት በሁሉም መስክ ያሉ የእኩልነት መብታቸው ዋስትና አግኝቷልና። ይህ ህገ መንግስት ሲቀረፅ ጀምሮ የመሪነት ሚናውን በአግባቡ የተወጣው ድርጅታችን ኢሕአዴግም ብዝሃነትን በአግባቡ በማስተናገድ የበለፀገች ዴሞክሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ባደረገው ተጋድሎ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ አንድነቷ የተጠናከረ ሀገር ለመገንባት በቅተናል፡፡

ይህ የሕዝባችን፤ የመንግስትና የድርጅታችን ስኬት የማይዋጥላቸው ኃይሎች ዛሬም በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን ስርዓታችንን ለመሸርሸርና ለመናድ መጣራቸውን ቀጥለውበታል፡፡ ራሳቸውን የአንድ ብሔር ወይም ሀይማኖት ተቆርቋሪ አድርገው በመቅረብ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከታቸውን ሊጭኑብን የሞት ሽረት ትግል ሲያደርጉ ማስተዋል ችለናል። በሀገራችን ያሉት አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም የዚህ አመለካከትና ተግባር ተሸካሚ ናቸው፡፡

የህዳሴ ጉዟችን ዋነኛ አቅጣጫ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚን በመናድ በምትኩ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚን በተሟላ ሁኔታ መገንባት ነው፡፡ ይህ እውን እስኪሆን ድረስም ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋሻ ሆነው የሚያገለግሉትን ትምክህት፣ ጠባብነትና አክራሪነትን እንደዚሁም የእነዚህን አመለካከትና ተግባሮች መሸሸያ የሆኑትን ፅንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመላ የሀገራችን ህዝቦች ጋር ሆነን እንታገላቸዋለን፡፡
የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ ተጠናክሮ የቀጠለው በእናንተ ተሳትፎና ርብርብ መሆኑን ኢህአዴግ በጥብቅ ያምናል። ለዚህም ከፍ ያለ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ ህዳሴው ያለ እናንተ ተሳትፎም ሊሳካ እንደማይችል ይገነዘባል። ኢህአዴግ በእያንዳንዱ የልማትና ዴሞክራሲ ጉዳይ ህዝብ እንዲሳተፍ በማድረግ በሁሉም ከተሞችና ገጠሮች ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው ባሉ አደረጃጀቶች የህዝቡን ፍላጎትና አስተያየት ባካተተ ሁኔታ በመንቀሳቀሱ ለውጤት በቅቷል። የህዝብ ተሳትፎና ርብርብ ክንድና አቅም ሆኖት እንደ መንግስት በሀገሩም በአካባቢው ሀገራትም ጠንክሮ የወጣው ኢህአዴግ፣ በሀገራችንም ሆነ በአካባቢው አገራት ሰላማዊ ግንኙነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።
እናም በዚህ የዴሞክራሲ ስርዓታችን ዋነኛ መገለጫ በሆነው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ድምፃችሁን ለኢትዮጵያ ህዳሴ እውንነት ለሚተጋው ህዝባዊ ድርጅት እንድትሰጡ ኢህአዴግ  ጥሪውን ያቀርብላችኋል። ኢሕአዴግን መምረጥ የኢትዮጵያን ሕዳሴ ማስቀጠል ነው!!

ኢሕአዴግ ምርጫውን አስመልክቶ የሚያስተላልፋቸውን ተከታታይ መልዕክቶች በድረ ገፃችን www.eprdf.org.et በፌስቡክ ገፃችን EPRDF official ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ 
ኢህአዴግን መምረጥ ህዳሴን ማስቀጠል ነው!!

No comments:

Post a Comment