EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Friday, 27 February 2015

ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው!




የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች

ኢህአዴግ በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፤ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና እንዲያገኝ በጽናት የታገለ፣ ያታገለና ውጤት ያስመዘገበ ህዝባዊ ድርጅት ነው።

መላ የሀገራችን ህዝቦችም የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች የተከበሩባት፤ መልካም አስተዳደር የነገሰባት የበለፀገች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት ታግለዋል፤ ብዙዎችም ለዚህ ታላቅ አላማ ህይወታቸውንና አካላቸውን ሰውተዋል፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት ስርዓቶች ያልተመለሱ የሰላምና ዴሞክራሲ እጦት ምንጭ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ ትግሉን በስኬታማነት መርቷል። በጋራ ጥረታችን በምንገነባው የዴሞክራሲ ስርዓት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል መብት ያለ ገደብ እንዲከበር በህገመንግስቱ መደንገጉን ተከትሎ መብቱ እንዲከበር ፕሮግራም ነድፎ በፅናት ታግሏል። ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በግዳጅ አንድነት ጥላ ስር ሆነው ሲደርስባቸው የነበረን ጭቆና ንዶ በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እውን እንዲሆንም አስችሏል። ዛሬ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  በቋንቋቸው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋቸውን የማሳደግ እና ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበርና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪካቸውን የመንከባከብ መብታቸው ያለገደብ ተከብሯል። ሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደርም ችለዋል።


ኢህአዴግ የሚከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ከሌሎች የልማታዊ መንግስታት የሚለየው  ልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርአት ግንባታን በማስተሳሰሩ ብቻ ሳይሆን ለብሔር ጥያቄ ከሌሎች በተለየ መልኩ የተሟላ ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ መስጠት በመቻሉ ነው፡፡ ይህ ልዩነት የመነጨው ደግሞ ከዓላማና ፕሮግራሙ ነው፡፡ ኢህአዴግ ዴሞክራሲን ማስፈን አለብኝ ብሎ በቁርጠኝነት ሲንቀሳቀስ ዴሞክራሲ በራሱ ለሰው ልጆች አስፈላጊ ስለሆነ ብቻ አይደለም፡፡ ገና በትጥቅ ትግሉ ፀረ ዴሞክራሲያዊውን የደርግ አገዛዝ ለመጣል ሲነሳ ለሀገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄ የህልውና ጥያቄ እንደሆነ አምኖበት ስለተነሳ ነው፡፡ ለእኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ማለት ልማትን ማረጋገጥና ዘላቂ ሰላም ማስፈን ብሎም እንደ ሀገር አብሮ ለመዝለቅ የነበሩትን ችግሮች በማስወገድ ለጠንካራ  ዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ አንድነት መሰረት በመሆኑ ጭምር ነው።

በእኛ ሁኔታ ዴሞክራሲ የእልቂት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምንጮችን በማድረቅ ለዘላቂ ሰላምና ብልፅግና የተመቻቸ ሁኔታን በመፍጠር ለሀገራችን ህዝቦች ህልውና መረጋገጥ የሚጫወተው ሚና በሌላ ምንም ሁኔታ የሚተካ አይደለም፡፡  ሀገራችን ለረጅም ጊዜ ከኖረችበት ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ተላቃ ወደ አዲስ ስርዓት የተሸጋገረችበት ወቅት የሚያሳየን ነገር ቢኖር የሰላም፤ የልማትና የዴሞክራሲ እጦት ተመጋግበው ሊበታትኑን ከቋፍ አድርሰውን እንደነበር ነው፡፡ ስለሆነም በወቅቱ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ካልቻልን፣  ፈጣን እድገት ካላመጣንና ህዝባችን በቀጥታና በተወካዮቹ አማካኝነት የሚሳተበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካልመሰረትን ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ እንደማንሰጥ ግልፅ ነበር፡፡ ስለሆነም የዴሞክራሲና የልማት ቅድመ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመመለስ የረዥሙን ጉዞ በመጀመራችን ባለፉት 23 አመታት በሁሉም መስክ አመርቂ ድሎችን ማስመዝገብ ችለናል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከመተላለቅና ከመበታተን አፋፍ ተመልሰን ዴሞክራሲያዊ አንድነቷ የተጠበቀ በፈጣን የልማት ጎዳና የምትገሰግስ አገር ገንብተናል፡፡
ለዘመናት በህዝባችን ጫንቃ ላይ ተጭኖ የኖረው ድህነትና ኋላቀርነት ኢህአዴግ በቀረፃቸው ሀገር በቀል የልማትና የዴሞክራሲ መርሃ ግብሮችና በታታሪው ህዝባችን ሁለገብ ተሳትፎ እየተረታ በመሆኑ የተዋረደው ክብራችን እና የጎደፈው ስማችን መታደስ ጀምሯል፡፡ ስሟ በድርቅና በረሃብ ብሎም በእርስ በርስ ጦርነት የምትታወቀው ሀገራችን ዛሬ  ፈጣንና ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ከሚጠቀሱት ጥቂት ሀገሮች መካከል አንዷ መሆን ችላለች። ባለፉት ስርዓቶች በነበረው የተዛባ አስተሳሰብና ተግባር አማካኝነት በህዝቦች ላይ ተጭኖ የኖረው አሃዳዊ አመለካከትና ህዝቦችን በአስተዳደራዊ መንገድና በሃይል ለማዋሃድ የተፈፀሙት አፈናዎች በህዝቦች መራራ ትግል ተወግደው ዛሬ የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሁሉን አቀፍ እኩልነት የተረጋገጠበት የፌደራል ስርዓት ባለቤት ሆነናል።  

የፌዴራል ስርዓታችን በቀድሞ ገዢዎች አማካኝነት በህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የተዛባ ግንኙነት በማረም የሀገራችን ህዝቦች በመተማመን ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲያዳብሩ አስችሎናል። እየገነባን ባለው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የውስጣችንን የትርምስ ታሪክ ከመዝጋት አልፈን በምንገኝበት የትርምስ ቀጠናም የሰላም ተምሳሌት ለመሆን በቅተናል።  ዛሬ በሀገራችን እውን የሆነው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሀገራችንን ታሪክ ከመሰረቱ ለመቀየር ያስቻለ  መሰረተ ሰፊ፣ ፈጣንና ተከታታይነት ያለው ባለ ሁለት አሃዝ እድገት እንድናስመዘግብ ያደረገን ነው።

ሀገራችን የራሳቸውን ሀይማኖት ህገ-መንግስታዊ ሽፋን ሰጥተው ይፋ የአገሪቱ የመንግስት ሀይማኖት አድርገው በሌላው ላይ ተጽእኖ  ሲያደርጉ የቆዩ ስርአቶችን አስተናግዳለች። ይባስ ብሎም  ቀጥሎ ወደ ስልጣን የመጣው የደርግ ስርዓት ሁሉንም አይነት እምነትና ሀይማኖት ለማጥፋት አቋም ወስዶ ሲንቀሳቀስ የነበረ መሆኑ ይታወሳል። ሆኖም ይህንን ግፍና በደል መቋቋም ያቃታቸው ውድ የህዝብ ልጆች አምባገነኑን የደርግ ስርአት  በእልህ አስጨራሽ ትግል አስወግደዋል። 

ዛሬ የሀይማኖት ብዝሃነትን ማስተናገድ ከተሳነው ስርዓት ተላቀን ሁሉንም ሃይማኖቶች እና እምነቶች እኩል የሚመለከትና ሃይማኖትንና የመንግስት አስተዳደርን ነጣጥሎ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚስተናገዱበት ስርዓት ተፈጥሯል፡፡ ሁሉም ዜጎች የመረጡትን እምነትና ሀይማኖት የመከተልና የማምለክ ህገ-መንግስታዊ ዋስትና አግኝተዋል።  የሀይማኖትን እኩልነት ለመደፍጠጥ መሳርያ የነበሩትን እንደ ትምህርትና የመገናኛ ብዙኃን የመሳሰሉት ወሳኝ ተቋማት ከሀይማኖት እንዲለዩ  እርምጃ ተወስዷል። ለዘመናት ስር ሰደው የቆዩ መሰረታዊ የፍትህ መጓደሎችም ተወግደዋል። ኢህአዴግ ባለፉት ስርዓቶች ህጋዊ እውቅና ተነፍጎት የሀገር አደጋ እንደሆነ ሲቆጠር የነበረውን ብዝሀነት በአግባቡ በመገንዘብ የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከመገለል ስሜት ተላቀው የሀገር ፍቅራቸውና ቀናኢነታቸውን እንዲያሳድጉ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። አዲሱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት በማስተናገድ እኩል የህግ መብትና ፍትሀዊ የሀብት ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ያደረገ ነው። ለዚህም ነው ከብጥብጥና አለመረጋጋት ወጥተን በታሪካችን ረጅሙን የሰላም ጊዜ ማሳለፍ የቻልነው፡፡

ባለፉት ስርዓቶች በህግ ሳይቀር የእኩልነት መብታቸውና ነፃነታቸው ተነፍጎ የሰቆቃ ህይወት እንዲገፉ ተደርገው የነበሩት የሀገራችን ሴቶች   የሕግ ማዕቀፎች በማሻሻልና በማረም ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው ማደግ እንዳለበት በማመን አፋኝ የነበሩ ሕጋዊ ድንጋጌዎችን በሌላ ዴሞክራሲያዊ የሕግ ማዕቀፎች እንዲተኩ ተደርጓል።

በኢህአዴግ እምነት የሴቶች እኩል ተሳትፎና እኩል ተጠቃሚነት የችሮታ ጉዳይ አይደለም። ሴቶች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከወንዶች ጋር በእኩልነት መሳተፍና መጠቀም አለባቸው ሲባል ከሕብረተሰባችን ግማሽ የሚሆነውን እውቀትና ጉልበት ያመከነ የልማት ጉዞ ዘላቂና አስተማማኝ ለውጥ የማምጣት ዕድሉ እጅግ ጠባብ በመሆኑም ጭምር ነው። ኢህአዴግ የህግ ማዕቀፎችን በመቅረፅ ብቻ ሳይወሰን የሴቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅ አዘጋጅቶ የገጠርና የከተማ ሴቶች በልማት ስራዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሳተፉና በተሳትፎአቸው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሌት ተቀን እየተረባረበ ይገኛል። ለዚህም ነው ሴቶችን የማሳተፍና ያለማሳተፍ ጉዳይ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን የመመለስ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ የህልውና ጉዳይ ነው ብሎ በጽናት የሚታገልለትና ድህነትን የማስወገድ ጉዟችንም ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው የሚለው። በተመሳሳይ መልኩ ባለፉት ስርዓቶች ለጦርነት ብቻ ሲፈለጉ የነበሩት የሀገራችን ወጣቶች ዛሬ በትምህርትና ስልጠና ራሳቸውን እንዲያበለፅጉና በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሳተፉ በመደረጋቸው በሀገር ግንባታ ሂደቱ ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነዋል።   
                    
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች
በሀገራችን መንግስትን የሚቃወሙ መልእክቶችን መናገርና መፃፍ ቀርቶ ማሰብ እንኳን ከማይቻልበት እና ዜጎች አስበህ ይሆናል እየተባሉ ከሚታሰሩበት፣ ከሚገረፉበትና ህይወታቸውን ከሚያጡበት አስከፊ አገዛዝ ወጥተን የአመለካከትና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በህገ መንግስት ጭምር የተረጋገጠው በኢህአዴግ አመራር ነው፡፡ ለዘመናት በገራችን ስር ሰዶ የቆየው ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትና የሚዲያ ነጻነትን ቀፍድዶ ይዞ የነበረው የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) አሰራር ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳውና ማንኛውም ዜጋ  በነፃነት መንግስትን መተቸት የተቻለው በኢህአዴግ ግንባር ቀደም ተጋድሎ ነው። ለዚህ መብት ጥበቃ ከማድረግ ጎን ለጎን የመገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ በወቅቱ እንዲሰጡ የሚያስችል ግልፅ አሰራር የተዘረጋውም በኢህአዴግ መሪነት እውን በሆነው ስርዓት ነው። 

ማንኛውም ያደገ ዴሞክራሲ ሊኖረው የሚገቡ የዴሞክራሲ ተቋሞች እንዲኖሩን የተጋነው ገና የዴሞክራሲ ስርዓትን አንድ ብለን ከጀመርንባቸው ዓመታት ጀምሮ ነው። ይህም ለዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን ከፍተኛ ሚና ያላቸው ነፃና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ በየደረጃው ያሉ የህዝብ ምክር ቤቶች፣ የህዝብ እንባ ጠባቂና የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ተቋማት ለመቋቋምና ወደ ስራ ለመግባት በቅተዋል፡፡ በሀገራችን የፍትህ ስርዓት እንዲዳብር እና የህግ የበላይነት እንዲጠናከር ኢህአዴግ የመሪነት  ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ ያለ ህዝባዊ ድርጅት ነው፡፡ ሀገራችን ከሁለት አስርት ዓመታት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ  ተአምራዊ ሊባል የሚችል ለውጥ ልታመጣ የቻለችው ኢህአዴግ የጠራ ህዝባዊ የትግል መስመር ቀርፆ በመንቀሳቀሱና ግልጽ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በመቀየስና የመላውን ህዝብ ተሳትፎ በማረጋገጥ በቁርጠኛነት በመንቀሳቀሱ ነው፡፡ 

በሌላ በኩል የሀገራችን ተቃዋሚዎች የህዝብን ጥቅም የሚያረጋግጥ ግልጽ የሆነ የፖሊሲና የስትራቴጂ አማራጭ ሳይዙ በሀገራችን እየተመዘገቡ ያሉና ከውስጥም ሆነ ከውጭ ምስክርነት የተቸራቸውን ለውጦች  ጥላሸት በመቀባት ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ በተለይ ህግንና ህገ-ወጥነትን እያጣቀሱ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ኃይሎች  “ከየትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው” እንዲሉ አገር ተሸጦም ቢሆን ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ ሲባዝኑ ይታያሉ፡፡ ይኸው ተቃዋሚ ሃይል በራሱ በውስጡ ዴሞክራሲያዊ አሰራር የሌለውና እርስ በእርሱ በጸረ ዴሞክራሲ ሲተራመስ እየዋለ በሀገራችን እተገነባ ያለውን ዴሞክራሲያዊ ስርአት በማጥላላትና ጥላሸት በመቀባት ለዴሞክራሲ ጥብቅና እቆማለሁ ቢል ከባህሪው የማይመነጭ ውግንና እንደሆነ ህዝባችን እንደሚገነዘበው ኢህአዴግ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ የለውም፡፡

ኢህአዴግ ጠንካራ የሆነ የውስጠ ዴሞክራሲ ባህልና አሰራር የገነባና የራሱን ችግሮች በትግል እያረመ አሁን ከደረሰበት ደረጃ የደረሰ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ነው፡፡ የኢህአዴግ ህዝባዊነት የህዝብን አደራና ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት የሚገለፅ ነው። እስከ አሁንም ድረስ  ከህዝባችን የተሰጠንን ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት በታማኝነትና በዓላማ ጽናት እየተወጣን ቆይተናል።  የበለፀገች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያስመዘገብናቸውን ሁሉን አቀፍ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስኬቶቻችንን ወደ ላቀ ደረጃ ልናደርስ የተለመደውን ቁርጠኛ አቋማችንን ስናረጋግጥ ዛሬም እንደትናንቱ በፀረ ድህነት ላይ የጀመርነውን ተጋድሎ ከህዝባችን ጋር በመሆን ከዳር እንደምናደርስ በመተማመን ነው፡፡

ኢህአዴግ ከመላው ህዝባችን ጋር በመሆን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞአችንን በማፋጠን የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ ዛሬም እንደትናንቱ ቁርጠኛ፣ ብቁና ዝግጁ ነው፡፡ በዚህ የምርጫ ዋዜማ ላይ ሆኖም የመላ ኢትዮጵያውያንን ዙሪያ መለስ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የገባውን ቃል እያደሰ ሀገራችንን ቀድሞ ወደነበረችበት የስልጣኔ ማማ ለሚያደርሱ ተጨማሪ ድሎች በትጋት የሚረባረብ መሆኑን ኢሕአዴግ ለመላ ህዝባችን ቃል ይገባል፣ ለተግባራዊነቱም በቁርጠኝነት ይረባረባል፡፡

ኢህአዴግን መምረጥ የተጀመረውን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በላቀ ፍጥነት ማስቀጠል ማለት ነው፡፡

ኢህአዴግን መምረጥ ህዳሴን ማስቀጠል ነው!
ኢህአዴግ ምርጫውን አስመልክቶ የሚያስተላልፋቸውን ተከታታይ መልዕክቶች 
በድረ ገፃችን www.eprdf.org.et 
በፌስቡክ ገፃችን EPRDF official እና 
በትዊተር ገፃችን @EPRDFEthiopia  ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

1 comment:

  1. yes in deed what a nice article keep working on this ways i am happy to see such ....articles

    ReplyDelete