EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Monday 23 February 2015

ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አርባ የድል ዓመታት


ህወሓትና የትግራይ ህዝብ በአርባ የትግል፣ የመስዋዕትና የድል ዓመታት

I.          መግቢያ፣
ስለ ህወሓት አርባኛ የትግል ዓመት ስናነሳ ስለ ሁለተኛው የወያነ ንቅናቄ ማንሳታችን ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ስለ ትግራይ ህዝብ ትግል የቀረበ መረጃ የሌላቸው ሁሉ ከዚህኛው የአርባ ዓመታት ትግል በፊት ሌላ የወያነ ንቅናቄ ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የሚታወቀው ወያኔነት ምንጩ ሁለተኛው የወያነ ንቅናቄ ሳይሆን የመጀመሪያው የወያነ ንቅናቄ ነውና ስለ ህወሓት አርባ የትግል ዓመታት ከማንሳታችን በፊት የመጀመሪያውን የወያነ ንቅናቄ ማስታወስ ነገሮችን አስተሳስሮ ለመገንዘብ ዕድል ይሰጣል፡፡ በመሆኑም ህወሓት ከተመሰረተበት ከ1967 ዓ.ም ሳይሆን የመጀመሪያው የወያነ ንቅናቄ ከተለኮሰበት ከ1935 ዓ.ም በመጀመር ታሪኩን መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡

II.        ቀዳማዊ ወያነና የትግራይ ህዝብ ትግል፣
አገራችን ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ስልጣኔ የነበራትና ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረች አገር ነች፡፡ በዚህ ላይ የበርካታ ብሔር፤ ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች አገርም ነች፡፡ በየዘመኑ ገናና ደረጃ ላይ ደርሰው የነበሩት ስልጣኔዎቿ ደረጃ በደረጃ እያሽቆለቆሉ በመሄድ በተለይ ከዘመነ መሳፍንት በኋላ በማያቋርጥ የማሽቆልቆል ሂደት ውስጥ ልታልፍ ተገዳ ነበር፡፡ የማሽቆልቆሉ ሂደት ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እየተባባሰ በመሄዱ በተከታታይ ለሚከሰቱ የረሃብ መቅሰፍቶች ህዝቧን እስከ ማጋለጥ የደረሰም ነበር፡፡ በአፄ ምኒልክ አገዛዝ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ከተከሰተውና “ክፉ ቀን” በመባል ከሚታወቀው ረሃብ ጀምሮ በ1966 እና በ1977 እስከ ተከሰቱት አውዳሚ የረሃብ መቅሰፍቶች ድረስ እያሰለሰ በሚከሰት ችግር ዜጎቻችን በሚሊዮኖች ሰለባ እስከ መሆን ደርሰው ነበር፡፡ ይህ ያነሰ ይመስል በተማከለ አስተዳደር ውስጥ የገቡት ብሔር ብሔረሰቦች የእኩልነት መብታቸው ተረግጦ ለአስከፊ ብሄራዊ ጭቆና የተጋለጡበትና መፈናፈኛ ያጡበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በአገራችን የተማከለ አህዳዊ አስተዳደር ሲመሰረት ብሄረሰቦቻችን አንድም የነበራቸውን የራስ በራስ አስተዳደር ተነጥቀው አሊያም አስተዳዳሪዎቻቸው የነበራቸውን አንፃራዊ ነፃነት ተገፈው በማዕከላዊ መንግስት ሥር ሊወድቁ ተገደው ነበር፡፡ በአገራችን በብሔር ብሄረሰቦች መካከል የነበረው ያልፀና ግንኙነት ቀጣይነት ባለው የተማከለ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን በብሔሮች መካከል በጭቆና ላይ በተመሠረተ ቋሚ አስተዳደር እንዲተካ የተደረገውም ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነው፡፡  ይህ ሂደት የደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅና ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦችን ከመሬት ባለቤትነት በመንቀል ከፍ ሲል በተገለፀው ዓይነት በጭቆና ላይ የተመሰረተ አሃዳዊ አስተዳደር ውስጥ በማስገባት የተሟላ መልክ ያለው ብሔራዊ ጭቆና እንዲደርስባቸው ያደረገ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ይኸው የተማከለ አሃዳዊ ስርአት የመመስረት ሂደት ከ1880ዎቹ በኋላ በትግራይና በሰሜን ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ላይ አርሶ አደሩን ከመሬቱ ላይ ከማፈናቀል በመለስ ከሞላ ጎደል በትግራይ፣ አገው፣ አፋርና መሰል ህዝቦች ላይ ተመሳሳይ ብሔራዊ ጭቆና ያሰፈነ ሥርዓት ነበር፡፡

ይህ ሥርዓት ምንም እንኳ ለጊዜው የኃይል ሚዛን ብልጫ በነበረው የወቅቱ ገዥ መደብ ዘመቻ ድል ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ገና ከጅምሩ አንስቶም ሆነ በሂደት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ተቃውሞ ያልተለየው ሥርዓት ነበር፡፡ የአፄ ምኒሊክን ዘመቻ ባለመቀበል በርካታ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ተካሂደዋል፡፡ የኦሮሚያ፣ የትግራይ፣ የወላይታ፣ የከፋ፣ የጉራጌ፣ የሲዳማ፣ የሐረሪ ወዘተ…… ህዝቦች የአፄ ምኒልክን የመስፋፋት ዘመቻ አሻፈረኝ በማለት የገጠሙት በብሔራዊ ጭቆና ላይ የተመሠረተው አሃዳዊ ሥርዓት ገና ከጥዋቱ ለህዝቦች መልካም ነገር ይዞ ስላልመጣ ነበር፡፡ በሂደት ደግሞ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግስት አገሪቱን ባስተዳደረበት ጊዜ የአገራችን ብሄር ብሔረሰቦችና ለብሔራዊ ጭቆና ሳይጋለጥ የቆየው የአማራ ህዝብ ጭምር በየራሳቸው አንገብጋቢ አጀንዳዎች ዙሪያ እየተነሳሱ ትግላቸውን ቀጥለዋል፡፡

የኦሮሚያ፣ የኢትዮጵያ ሱማሌዎች፣ የትግራይ፣ የጎጃም ገበሬዎች አመፆች ሁሉ ፍፁም ዘውዳዊ የነበረው የኃይለሥላሴ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይ ደግሞ በአስከፊ ብሔራዊ ጭቆና ይማቅቁ ከነበሩት ብሔር ብሄረሰቦች ከባድ ተቃውሞ እንደገጠመው የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ ንጉስ ኃይለሥላሴ ከጣልያን ሽንፈት በኋላ ከምዕራባውያን አገሮች ባገኙት ዙሪያ መለስ ድጋፍ ተጠናክረው ብሔራዊ ጭቆናውን በባሰ ደረጃ  ለማስቀጠል በተንቀሳቀሱ ጊዜ ከሞላ ጎደል ከመላው የአገራችን ህዝቦች ተከታታይ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ ንጉሱ እስከ 1967 ዓ.ም መጀመሪያ በስልጣን ላይ ሊቀጥሉ የቻሉት በአንድ በኩል ከገጠማቸው ተቃውሞ በላይ የጠነከረ ኃይል ስለነበራቸው በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው በአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መነሳሳት መልክ ይገለፁ የነበሩት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የተበተኑ፣ ብቃት ያለው አመራር ያልነበራቸውና ግብታዊ መነሳሳቶች ስለነበሩ ነው፡፡

ከእነዚህ ግብታዊ መነሳሳቶች አንዱ ጣልያን በህዝባችን ተጋድሎ ተሸንፎ በተባረረ ማግስት የትግራይ ህዝብ በአፄ ኃይለሥላሴ መንግስት ላይ ያካሄደው አመፅ ነበር፡፡ ቀዳማይ ወይም የመጀመሪያው ወያነ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ይኸው የትግራይ ህዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በ1935 ዓ.ም ሲቀጣጠል መነሻ ምክንያቱ አስተዳደሩ በአርሶ አደሩ ላይ የጣለው ከፍተኛና ከአቅም በላይ የሆነ ግብር ነበር፡፡ አርሶ አደሩ በድህነቱ ምክንያት ግብር ለመክፈል እንደማይችል በተደጋጋሚ ቢማፀንም ሰሚ ከማጣቱ በላይ የመንግስት አስተዳዳሪዎች በተደጋጋሚ ወታደር እየላኩና እያስገደዱ ለማስከፈል ከመሞከር ወደ ኋላ አላሉም ነበር፡፡ በዚህ ሂደት እንቢተኛነቱን ያጠነከረው የትግራይ አርሶ አደር ለተደጋጋሚ ቅጣቶች ተዳረገ፡፡ ቅጣቱ ሲበዛበትም በትግሪኛ አባባል “ወይ ኣነ” በሚል ቃል ዙሪያ ተሰባስቦ መፋለሙን ቀጠለ፡፡ በግብታዊ መነሳሳቱም መቀሌን ጨምሮ በርካታ ትንንሽ ከተሞችን እስከ መቆጣጠር ደረሰ፡፡ በዚህ ግብታዊ የትግራይ አርሶ አደሮች መነሳሳት የተደናገጠው ንጉሳዊ አስተዳደር በራስ አበበ አረጋይ የተመራ ሠራዊት አዘመተ፡፡ በተጨማሪም ለንጉሳዊው ስርዓት ከፍተኛ ድጋፍ በነበረው የእንግሊዝ መንግስት ተባባሪነት ከየመን የተነሱና በአለም አቀፍ ህግ ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከለከለ የጦር መሳሪያ ጭምር የተጠቀሙ የጦር አውሮፕላኖች በመታገዝ ከባድ የአየር ድብደባ በማካሄድ የመጀመሪያውን የወያነ ንቅናቄ ሙሉ በሙሉ አከሸፈው፡፡ የቀዳማይ ወያነ ንቅናቄ  ሽንፈትን ተከትሎ ከሞት የተረፉት የንቅናቄው መሪዎች እየታደኑ ለእስርና ግዞት ተዳረጉ፡፡ በትግራይ ህዝብ ላይ ደግሞ ከበፊቱ የባሰ የግብር ዕዳ ጫናና መቀጮ ተጣለበት፡፡ ይህም ግፍና በደል ንጉሣዊው ሥርዓት እስከ ተገረሰሰበት ወቅት ድረስ ቀጠለ፡፡

III.       የህወሓት ምስረታና ታሪካዊ አስተዋፅኦው፣
የትግራይ ህዝብ ለመብቱ መከበር ያደረገው ከባድ ትግል ከአቅሙ በላይ በሆነ ወታደራዊ ዘመቻ ከከሸፈ ከ32 ዓመታት በኋላ ግን በጥቂት የትግራይ ተራማጆች አዲሱና ሁለተኛው የወያነ እንቅስቃሴ ተለኮሰ፡፡ እንቅስቃሴው ለተወሰኑ ጊዜያቶች ማህበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ /ማገብት/ ወይም የትግራይ ተራማጆች ማህበር በሚል ስም ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ ከቆየ በኋላ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም በምዕራብ ትግራይ ውስጥ ደደቢት በተባለ ቦታ ላይ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ /ተኀህት/ በሚል ይፋዊ ስም  የትጥቅ ትግል አወጀ፡፡  ከ1969 በኋላ ደግሞ ድርጅቱ በአንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤው መጠሪያውን ወደ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ / ህወሓት/ በመቀየር ትግሉን አጠናክሮ ላለፉት 40 ዓመታት በከባድ ፍልሚያ ውስጥ እያለፈ ለአዲሲቱ  ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መመስረትና መጎልበት ታሪካዊ ሚናውን ሲጫወት ቆየ፡፡ ህወሓት በእነዚህ 40 የትግል ዓመታት ያለፈባቸው ጠመዝማዛ ሂደቶችና የተጫወተው ሚና ወይም ታሪካዊ አስተዋፅኦው በወፍ በረር አተያይ ቀጥሎ የተዘረዘረውን ይመስላል፡፡
     
1.          ህወሓትና ያለፈበት ጠመዝማዛ የትግል ጉዞ፣
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ የትጥቅ ትግሉን ሲጀምር የነበረው የአገራችን ሁኔታ የየካቲት 66 ዓ.ም ህዝባዊ መነሳሳት ንጉሣዊውን አገዛዝ የገረሰሰበት ነገር ግን ለተሟላ ድል ያልበቃበትና ትግሉ በወታደራዊ አምባገነን መንግስት ተጠልፎ ወደፊት መራመድ ያልቻለበት ወቅት ነው፡፡ መላ የአገራችን ህዝቦች ለዘመናት በላያቸው ላይ ተጭኖ ያሰቃያቸውን ዘውዳዊ አገዛዝ በተናጠል ሲፋለሙ ከቆዩ በኋላ በየካቲት 1966 ዓ.ም በአንዴ ከዳር እስከ ዳር ተንቀሳቀሱ፡፡  አርሶ አደሮች፣ አርብቶአደሮች፣ ላብአደሮች፣ ሴቶችና ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በየራሳቸው አንገብጋቢ ጥያቄዎች ዙሪያ ተሰባስበው ዘውዳዊውን አገዛዝ ገጠሙ፡፡ በኢኮኖሚና ማህበራዊ እንዲሁም በብሔር፣ በሃይማኖትና በፆታ እኩልነት ጥያቄዎች ዙሪያ ተነሳስተው የታገሉት መላ የአገራችን ህዝቦች በመስከረም ወር 1967 ዓ.ም የአፄ ኃይለሥላሴን መንግስት ለመገርሰስ በቁ፡፡ ይህም በአገራችን ከሺ ላላነሰ ዓመት ተንሰራፍቶ የቆየውን ፊውዳላዊ ሥርዓት ግብዓተ መሬት ያረጋገጠ ድል  ሆነ፡፡

ይህም ሆኖ ህዝቡ ከግብታዊ መነሳሳት አልፎ በተደራጀ አኳኋን የሚመራው ኃይል አላገኘም ነበር፡፡ ህወሓትና ኢህአፓን የመሳሰሉ በወቅቱ የህዝቡን ትግል የመምራት ሃሳብ ይዘው የተነሱ ድርጅቶችም ገና ራሳቸውን በአግባቡ ያልፈጠሩበትና ያላስተዋወቁበት ጊዜ የነበረ መሆኑ የየካቲት አብዮት ምን ያህል የተደራጀ አመራር ዕጥረት የነበረበት እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህን የመሰለ የመሪ ድርጅት ዕጦት የነበረበት የየካቲት ህዝባዊ መነሳሳት በዚህ ድክመቱ የተነሳ  አሮጌውን መንግስት ከማፍረስ አልፎ መንግስታዊ ሥልጣንን ወደ ህዝቡ ለማሸጋገር ሳይችል ቀረ፡፡ በምትኩ ደግሞ በወቅቱ የተደራጀ ከነበረው ወታደራዊ ኃይል ውስጥ በተፈጠረው ክፍተት በመጠቀም ሥልጣን ለመያዝ የተነሳው የከፍተኛ መኮንኖች ኃይል ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በሚል መጠሪያ መስከረም  2 ቀን 1967 ዓ.ም መንግስታዊ ሥልጣኑን ተቆጣጠረ፡፡

በዚህም ስልጣን በመጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ የማሰብ ነፃነትን ጨምሮ ሁሉንም መሠረታዊ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችን በአዋጅ ከለከለ፡፡ ከዚህም ጊዜ ጀምሮ በአገራችን ለ17 ዓመታት ያህል የቆየ  ፍፁም አምባገነናዊ መንግስታዊ ሥርዓት ተመሰረተ፡፡ ህወሓት ለትጥቅ ትግል በተነሳበት ወቅት የየካቲት ህዝባዊ መነሳሳት ህዝብን ለስልጣን እንዳላበቃና በአንፃሩ ደግሞ ፍፁም አምባገነናዊ አዝማሚያ ያለው መንግስት የተመሰረተበት ስለዚህም ደግሞ ትግሉን በወሳኝነት በከባዱና አስቸጋሪው የገጠር ትጥቅ ትግል አማካይነት የማራመድ አማራጭ ብቸኛው የድል መንገድ ሆኖ የወጣበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በከተሞች የሚካሄደው ትግል የደርግን አምባገነናዊ አዝማሚያዎች ለማጋለጥ የሚያስችል አስተዋፅዖ የነበረው ቢሆንም ደርግን የማስወገድ ተልዕኮ የሚሳካው በተራዘመ የህዝባዊ ትጥቅ ትግል አማካይነት መሆኑን በትክክል የመለየትና ይህም የሚጠይቀውን መስዋዕት ለመክፈል የመዘጋጀት ጉዳይ በወቅቱ  መሪ ድርጅት ነን ብለው የቀረቡትን ሁሉ በጥብቅ የሚፈትሽ የሆነበት ወቅትም ነበር፡፡ ህወሓት ከዚህ አኳያ ሲታይ የወቅቱን የትግል ስልት በትክክል ለይቶ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የቻለ ድርጅት ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር እኩል የተመሠረቱና የትጥቅ ትግል እናካሄዳለን ብለው ያወጁ እንደ ኢህአፓ የመሳሰሉ ድርጅቶች ከገጠር ትጥቅ ትግል ይልቅ ለከተማ ጀብደኛ ትግል ቅድሚያ ሰጥተው በሚረባረቡበት ወቅት ህወሓት በዚህ ትክክለኛ አቅጣጫ እየተመራ ሊጓዝ በመቻሉ ከ17 የትጥቅ ትግል ዓመታት በኋላ የደርግን ግዙፍ ወታደራዊ አቅም ገርስሶ በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ዕውን እንዲሆን አስችሏል፡፡

በእነዚህ 17 ዓመታት ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ለተደጋጋሚ ወረራዎች ተጋልጠዋል፡፡ ደርግ ህወሓትን ገና ትንሽ ድርጅት እያለ ጀምሮ ለማጥፋት ተከታታይ ዘመቻዎችን አካሂዶበታል፡፡ 1967 .  ጀምሮ እስከ 1983. ድረስ ባሉት 17 የትጥቅ ትግል ዓመታት በርካታ መጠነ ሰፊ ተከታታይ ዘመቻዎች ተካሂደውበታል፡፡ ዘመቻዎቹ በተለይ ትግሉ ወደወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገር በጀመረበት ወቅት በአንድ ጊዜ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ወታደራዊ ኃይል የተሳተፈባቸው፣ በከባድ መሣሪያዎች፣ ታንኮችና  እንደ ስታሊን ኦርጋን ዓይነት  በአንዴ በርካታ ሮኬት አስወንጫፊ መሣሪያዎችና የሄሊኮፕተርና የጦር አውሮፕላን ድብደባዎች የተሸኙ ነበሩ፡፡ አንዱ ዘመቻ በከባድ ትግል ሲከሽፍ ቀጣዩ ዘመቻ ያለፋታ እየቀጠለ  በትግሉ ላይ ከባድ ፈተናን የደቀነ ነበር፡፡ አምባገነኑ የደርግ መንግስት በእነዚህ ዘመቻዎች የታጠቀውን የህወሓት ወታደራዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን ያልታጠቀውን ሰፊውን የትግራይ ህዝብ ጭምር ዋነኛ ዒላማው በማድረግ  ከባድ ጭፍጨፋ አካሂዶበታል፡፡ በ1981 ዓ.ም ለገበያ በተሰባሰቡ ንፁሃን የትግራይ አርሶ አደሮች ላይ በአንድ ቀን ብቻ በሃውዜ ገበያ ላይ በተካሄደ ተደጋጋሚ የአውሮፕላን ድብደባ ሶስት ሺህ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ይህን በመሰለው የደርግ መንግስት ተከታታይ ጥቃት ውስጥ ለመኖር፣ ለማደግና የማታ ማታ ደግሞ ለማሸነፍ የቻሉ ፅኑ የዴሞክራሲ ኃይሎች ናቸው፡፡

ከደርግ ጋር ለአስራ ሰባት ዓመታት በተካሄደው ትግል ህወሓት የገጠመው ከአገራችን ወታደራዊ መንግስት ጋር ብቻ አልነበረም፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ዘመን በዓለማችን ለበላይነት ይፋለሙ የነበሩት የምስራቅና የምዕራብ አገሮች ባልበለፀጉ አገሮች ላይ የተፅዕኖ ቀጠናቸውን አስፋፍተው በእጅ አዙር የሚቀጣቀጡበት ዘመን ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በአሜሪካን የሚመራው የምዕራቡ ዓለም የራሱን ደጋፊ አገሮች እየመለመለና እያስታጠቀ ከሩስያ ተከታይ አገሮች ጋር የሚፋለምበት፣ ሩስያም በተመሳሳይ ደጋፊዎቿን እያስታጠቀች ጦርነቱ በተዘዋዋሪ የተፋፋመበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከንጉሣዊው ሥርዓት መውደቅ በኋላ ስልጣን ላይ የወጣው የደርግ መንግስት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የአሜሪካንን አመራርና ድጋፍ በመሻት እርዳታ እንዲደረግለት ጠይቆ የነበረ ሲሆን አሜሪካኖች በንጉሱና መኳንንቶቹ መታሰር አኩርፈው ላለመርዳት በመወሰናቸው የደርግ መንግስት መጀመሪያ ፊቱን ወደ ቻይና ቀጥሎ ደግሞ ወደ ሩስያ በማዞር በሶቭየት ህብረት ጥላ ስር እስከ መግባት ደረሰ፡፡ በወቅቱ የዚያድ ባሬን መንግስት ሲደግፉ የነበሩት ሩስያውያን በራሳቸው ምክንያት ከሶማሊያ መንግስት ጋር በመጣላታቸው የደርግ መንግስት ያቀረበላቸውን ጥሪ ሲቀበሉ አፍታም አልወሰደባቸውም፡፡ አሜሪካኖችም በእነርሱ እግር ተተክተው የሶማሊያን መንግስት በእጃቸው ሲያስገቡ ብዙም አልቆዩም፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ኢትዮጵያና ሶማሊያ የምዕራቡና የምስራቁ ዓለማት የእጅ አዙር ፍልሚያ የሚካሄድባቸው የጦር አውድማዎች ሊሆኑ ተገደዱ፡፡ 

አሜሪካኖች የሶማሊያውን የዚያድ ባሬ መንግስት በሙሉ አቅማቸው ሲደግፉ የሶቭየት ህብረትና አጋሮቿ  ደግሞ ደርግን ለማጠናከር ያልሰጡት እርዳታ አልነበረም፡፡ ይህ እርዳታ ከሶቭየት ህብረት መንግስት ብቻ የሚቸር አልነበረም፡፡ ከምስራቅ ጀርመን እስከ ሩማንያ፣ ከኪዩባ እስከ ሰሜን ኮሪያ ድረስ በነበሩ መንግስታት ጭምር የሚሰጥ ግዙፍ ሰብዓዊና ቁሳዊ ድጋፍ ነበር፡፡ በደርግና በኢትዮጵያ አቅም ብቻ በቀጣይነት ሊሸመቱ የማይችሉ ነገር ግን የኃይል ሚዛኑ በተለይ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ወደ ደርግ መንግስት እንዲያጋድል ለማድረግ ያስቻሉ እርዳታዎች የጎረፉበት፣ ደርግም በዚህ አቅም በመተማመን በተለይ ከ1969 ዓ.ም የምስራቅ ዘመቻ ድሉ በኋላ መላ አቅሙን በአንዴ በሰሜን ኢትዮጵያ ታጋዮችና በኤርትራ የነፃነት ንቅናቄዎች ላይ ለማሰማራት የቻለበት ሁኔታ የተፈጠረበት ነበር፡፡ ደርግ በዚህ መጠነ ሰፊ ርዳታ ተጠናክሮ የዚያድ ባሬ መንግስት የኢትዮጵያን ሶማሌ ክልል በኃይል በመንጠቅ ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት የነበረውን ህልም ካካሸፈ በኋላ “የምስራቁ ድል በሰሜኑም ይደገማል” በሚል መፈክር ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ፊቱን ወደሰሜን ኢትዮጵያ አዞረ፡፡ በዚህ መጠነ ሰፊና  ተደጋጋሚ ዘመቻ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበሩ ትግሎችን ከባድ ፈተና የደቀነባቸው ነበር፡፡  በዚህ ዘመቻ የኤርትራ ንቅናቄዎች አፈግፍገው  በኤርትራ ሰሜናዊ ጫፍ በሳህል ተራራማ ቦታዎች ሊመሽጉ ሲገደዱ ህወሓት ደግሞ በከፍተኛ ተነቃናቂነት በልዩ ልዩ የትግራይ አካባቢዎች እየተወናጨፈ ተከታታይ ዘመቻዎችን ለማክሸፍ ተገደደ፡፡ የደርግ መንግስት በሰብዓዊ ኃይል ብዛት ብቻ ሳይሆን በታጠቀው ዘመናዊ የምድርና የአየር ትጥቅ ተመክቶ በሶቭየትና የምስራቅ ጀርመን ወታደራዊ ጠበብቶች እየታገዘ ያካሄደውን ዘመቻ በተራዘመ ህዝባዊ ጦርነት መመከት ቀጠለ፡፡ ይህ ምከታ እስከ 1970ዎቹ መጨረሻ ከተካሄደ በኋላ ህወሓት ደርግ የነበረውን የበላይነት ሰብሮ የአቻነት ሁኔታ እስከ መፍጠር ደረሰ፡፡ ከሞላ ጎደል ከ1976 – 1979 ዓ.ም አካባቢ በቆየው በዚህ የአቻነት ሁኔታ ደርግ ሙሉ በሙሉ የበላይነቱን ያጣበት ሁኔታ ቢፈጠርም በህወሓት የሚመራውም ትግል የበላይነቱን መቀዳጀት ያልጀመረበት ነገር ግን በኋላ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ለተካሄዱትና ስትራቴጂያዊ የኃይል ሚዛን ብልጫ ማስያዝ ለጀመሩት ትግሎች ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ቻለ፡፡ የማታ ማታ ደግሞ የትግሉ ኃይል ይበልጥ ሊጠነክር በመቻሉ ህዝባዊ ንቅናቄው ከ1980 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በከፍተኛ ፍጥነት ተቀጣጠለ፡፡ ይህ ለውጥ በወሳኝነት ሊመዘገብ የቻለው በ1970ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ በተለይ ደግሞ ከ1977 ዓ.ም በኋላ በትግሉ አመራር ላይ ከፍተኛ ዕድገት ሊመዘገብ በመቻሉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የታየውን የለውጥ ሂደት ወረድ ብለን የምንመለስበት ይሆናል፡፡

በህወሓት የተመራው የትግራይ ሰፊ ህዝብ ትግል ይህን ከመሰለው የደርግ መንግስት ጥቃት ጎን ለጎን በተለይ በ1968 – 1969 ዓ.ም ድረስ ጉልህ ጥንካሬ ማሳየት ችሎ በነበረው የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ ኃይል ጭምር ከባድ ፈተና ተጋርጦበት ነበር፡፡ በወቅቱ በየካቲቱ ህዝባዊ መነሳሳት ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም ይሞክር የነበረው ዘውዳዊ  ኃይል የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት /ኢዴህ/ በመባል ይታወቅ የነበረ ሲሆን ይህ ኃይል በወሳኝነት በአማራና በትግራይ ክልል በነበሩ ፊውዳሎች የተደራጀና የሚመራ በዋነኛነት ደግሞ በየአካባቢው በነበሩ ሽፍቶች የጦር መሪነት እንዲሁም በገጠር ሥራ አጥ ወጣቶችና በመሳሰሉት የተዋቀረ ነበር፡፡ የኢዴህ የአማራው ክንፍ በምዕራብ አማራና በምዕራብ ወሎ አካባቢዎች፣ የትግራዩ ክንፍ ደግሞ በራስ መንገሻ ስዩም በመመራት በወሳኝነት ህወሓት ትጥቅ ትግል በጀመረበት በምዕራብ ትግራይ መንቀሳቀስ የጀመረ ኃይል ነበር፡፡  ኢዴህ በወቅቱ ከዘውዳዊው መንግስት ጋር ከፍተኛ ሽርክና ከነበራቸው እንደ እንግሊዝና አሜሪካ ከመሳሰሉ ምዕራባውያን አገሮች ከፍተኛ የገንዘብ፣ የትጥቅና የሞራል ድጋፍ ሊያገኝ በመቻሉ በአጭር ጊዜ ግዙፍ ኃይል ለመሆን ችሎ ነበር፡፡

ኢዴህ በህወሓት ህልውና ላይ ከባድ ፈተና የደቀነው በአጭር ጊዜ ግዙፍ ኃይል በመሆኑ ብቻ አልነበረም፡፡  ይልቁንም በራስ መንገሻ ስዩም የሚመራው ይህ ኋላ ቀር ድርጅት ልክ እንደ ህወሓት ሁሉ ትግርኛ ተናጋሪና የትግራይን ህዝብ በሚገባው ቋንቋ  እያናገረ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ ይደርስ የነበረውን ብሔራዊ ጭቆና የሚያወግዝ መስሎ በመቅረብ ሊያደናግር ችሎታ የነበረው በመሆኑም ጭምር ነበር፡፡ ህወሓት ይህን ትግርኛ ተናጋሪ የፊውዳል ኃይል በቋንቋ አንድነት ሳይሸፈን በዓላማ ልዩነት ላይ በተመሰረተ ትግል እያጋለጠና ከባድ መስዋዕት በከፈለበት ትግል ድል እየነሳ የማታ ማታ ኢዴህን ከትግራይ ብቻ ሳይሆን ከመላው ኢትዮጵያ ጭምር የተነቀለበትን ወሳኝ ድል ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ ህወሓት በትግራይ ውስጥ የብሔር ጥያቄን ለኋላ ቀር ፊውዳላዊ ዓላማ ሊጠቀምበት የሞከረውን የራስ መንገሻ ድርጅት የወንዜ ልጅ ሳይል ታግሎ ያሸነፈው ድርጅቱ የብሔር ጥያቄን በዴሞክራሲያዊ ብሄረተኝነት አቅጣጫ ለመፍታት በመቻሉ ነው፡፡

በትግራይ ውስጥ በህወሓት መሪነት ትግሉ በተጀመረበት ጊዜ በራስ መንገሻ ስዩም የተመራው ፊውዳላዊ የጦር ኃይል በብሔር ሽፋን ተጠልሎ የትግሉን መሪነት ለመጨበጥና የትግራይን ህዝብ በተሳሳተ አቅጣጫ ለመምራት ያደረገውን አደገኛ ሙከራ ለማክሸፍ በቁጥሩ አነስተኛ የነበረው የህወሓት ሠራዊት በከባድ የዓላማ ፅናት መፋለም ነበረበት፡፡ አንድ ቋንቋ እየተናገረ በብሔር ጥያቄ ስም ለማደናገር ከፍተኛ ዕድል ብቻ ሳይሆን የተጠናከረ የምዕራባውያን ድጋፍ የነበረውን ኢዴህ በጥቂት ኃይል ገጥሞ ማሸነፍ ከባድ መስዋዕት ያስከፈለ ትግል ነበር፡፡ በዚህ በአጭር ጊዜ ነገር ግን ከባድ ደም መፋሰስ ባጋጠመበት ህዝባዊ ትግል ህወሓት ምርጥ ወንድና ሴት ታጋዮችን ገብሯል፡፡ ብዙ ታጋዮችም ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርገዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ የህዝብ ልጆች በከፈሉት መስዋዕት ፊውዳሊዝምን በትግራይ ብቻ ሳይሆን በመላ አገራችን ዳግም ለማንገስ የተደረገው ሙከራ በአስተማማኝ ደረጃ ሊከሽፍ ችሏል፡፡ ህወሓት በለጋ ዕድሜው ከኢህአፓ ጋር ባደረገው ፍልሚያም ሌላ ከባድ ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡ ከኢዴህ ጋር የሚካሄደው ፍልሚያ ገና ሙሉ በሙሉ ባልተጠናቀቀበት በምስራቅ ትግራይ የተቀሰቀሰው ግጭት እንደገና ሌላ ውጥረት የፈጠረ ሲሆን በዚህም ጦርነት ብዙ የህዝብ ልጆች መስዋዕት ሆነዋል፡፡ የማታ ማታ ደግሞ ጦርነቱ በህወሓት አሸናፊነት ተጠናቆ ህወሓት ቀሪውን ጊዜ በወሳኝነት በፀረ-ደርግ ትግሉ ላይ በማትኮር ሊታገልና ለተሟላ አገራዊ ድል ለመብቃት ችለናል፡፡

ህወሓት በትግሉ ሂደት በተቃራኒ ካምፕ ከተሰለፉ የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች ከተደቀነበት ፈተና ባልተናነሰ በውስጡም በተለያዩ ኋላ ቀር አስተሳሰቦች ምክንያት ከባድ ፈተና የገጠመው ድርጅት ነበር፡፡ በ1969ና 1970 ዓ.ም ላይ ልዩ ልዩ የጎጠኝነትና የበታኝነት አስተሳሰብ የነበራቸው አባላት በፈጠሩት ቀውስ የድርጅቱ ህልውና ለከፋ አደጋ ተጋልጦ ነበር፡፡ ወቅቱ ህወሓት ከውጭ ሊያጠፉት ከተሰለፉ ኃይሎች በኩል ከባድ ጫና ይደርስበት የነበረበት ወቅት በመሆኑ ይህ ከውስጥ የተቀሰቀሰ የብተና አደጋ እዚያው ሳለም የድርጅቱን ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያባብስ ነበር፡፡ ይሁንና ህወሓት ይህን የብተና አደጋ በዴሞክራሲያዊና ፅኑ ህዝባዊ ትግል ተቋቁሞ ለማለፍ ችሏል፡፡ ከዚህ በመቀጠል በ1970ዎቹ መጨረሻ ላይ በከፍተኛ አመራሩ መካከል የተቀሰቀሰው ፖለቲካዊ ልዩነት እንደዚሁ ህወሓትን የገጠመው ሌላ ከባድ ፈተና ነበር፡፡ ምንም እንኳ ይህ ልዩነት በተቀሰቀሰበት ጊዜ በድርጅቱ ውስጥ የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለማዊ ትግል የማካሄድ ብቃትና ባህል በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ አሳይቶ ድርጅቱ ማንኛውንም ዓይነት ማዕበል የመቋቋም ብቃቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ በመሆኑ ችግሩን ያለብዙ ምስቅልቅል ሊፈታው የቻለ ቢሆንም ኋላ ቀር አስተሳሰብን በመወከል ከሚከራከሩት መካከል ድርጅቱን የመሰረቱና ገና ከጥዋቱም ይመሩት የነበሩ ግለሰቦች መሆናቸው ፈተናውን ከባድ እንዲሆን አድርጎት ነበር፡፡ ነገር ግን ህወሓት ይህን በአመራር ደረጃ የተከሰተ ቀውስ በመርህ ላይ በተመሰረተ ትግል ብቻ ሳይሆን ሰፊ ዴሞክራሲያዊ የውስጠ ድርጅት ፖለቲካዊ ህይወትን በማጠናከርና መድረኮችን በማስፋት ሊፈታው ችሏል፡፡ በህወሓት አመራር ኃላፊነት ላይ ከነበሩት ከእነአረጋዊ በረሄና ግደይ ዘርዓ ፅዮን ጋር የተካሄደው የውስጠ ድርጅት ትግልም የህወሓትን ዴሞክራሲያዊ የውስጠ ድርጅት የትግል ባህል ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያሸጋገረ ነበር፡፡

ህወሓት ይህን የመሰለው ውስጣዊ ፈተና ያጋጠመው በትጥቅ ትግሉ ወቅት ብቻ አልነበረም፡፡ ትጥቅ ትግሉ ከተጠናቀቀ በኋላ በተለይ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ የአመራር አባላት ማዳበር በጀመሩት የጥገኛ ዝቅጠት አስተሳሰብና ከትምከህት ኃይሎች ጋር የመደራደር ዝንባሌ ምክንያት የተፈጠረው አደጋም ድርጅቱን ከሁለት ሊሰነጥቀው ተቃርቦ ነበር፡፡ በዚህ የአንጃ ስያሜ በተሰጠው ንቅናቄ ውስጥ የነበሩት የአመራር አባላት ደረጃ በደረጃ እያዳበሩት በመጡት አደገኛ የፖለቲካ ዝንባሌ ህወሓትን ብቻ ሳይሆን መላውን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ለብተና አደጋ ሊያጋልጡት ተዘጋጅተው ነበር፡፡ ይህ ችግር ላይ ላዩን ሲታይ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዙሪያ ይነሱ በነበሩ ሃሳቦች መካከል የሚንፀባረቅ ቢመስልም በመሰረታዊ ይዘቱ ግን በወሳኝነት የሥርዓታችንን ፈተናዎች በመለየትና ለዚህም ተስማሚ መፍትሔ በማመላከት ጥያቄ ዙሪያ የተቀሰቀሰ ልዩነት ነበር፡፡ አንጃው የሁሉም ነገር ማጠንጠኛ የሥርዓቱ ውስጣዊ ፈተና መሆኑን በመካድ የኤርትራ መንግስትን በጠላትነት እያመላከተ ከሥርዓቱ ውስጣዊ ችግሮች ለመሸሽ፣ ከዚህም አልፎ ሥርዓታችን በሌላ ውጫዊ ኃይል የማይሳበብ የራሱ ችግሮች ያሉበት መሆኑ በተነሳ ቁጥር ይህን የሚሉትን የአመራር አባላት ሁሉ በከሃዲነት እየወነጀለ ዝም ለማሰኘት ያላደረገው ጥረት አልነበረም፡፡ የማታ ማታ ደግሞ የራሱን ጥገኛ መረብ ፈጥሮ ከህጋዊው ድርጅታዊ ሥርዓት ውጭ በመንቀሳቀስ የበላይነቱን ለመጨበጥ ተረባርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን የመሰለው የጥፋት እንቅስቃሴ በወቅቱ በተካሄደውና የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባችንን የበላይነት ባረጋገጠው ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ ትግል ሊመከት ችሏል፡፡ የጥገኛ ዝቅጠት የተደራጀ ወኪል የነበረው ኃይልም ዴሞክራሲያዊ መድረኮችን የመቋቋም ብቃት አጥቶ ከድርጅት የውይይት መድረኮች እያፈነገጠ ተጉዟል፡፡ የዚህ አደገኛ ኃይል አንዳንድ አባላትም ለይቶላቸው ከትምከህት ኃይሎች ጋር የተሰለፉ ሲሆን በእጅ አዙርም ከኤርትራ መንግስት ጋር እስከ መተባበር እንደደረሱ ያለፉት አስር ዓመታት ያረጋገጠውም ነው፡፡

በትጥቅ ትግሉም ሆነ በኋለኛው ዘመን ህወሓትን ከውስጥም ከውጭም የገጠሙት ፈተናዎች የተለያዩና ከባድ የነበሩ ቢሆንም ህወሓት እነዚህን ፈተናዎች በህዝባዊ ፅናትና ብስለት መክቷቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ያለው የድርጅቱ ባህል በዝርዝር ሲፈተሽ የምናገኘው እውነታ ፈተናዎች በሚያጋጥሙበትም ሆነ በሚከብዱበት ጊዜ ሸብረክ የማለት ሳይሆን ፈተናዎችን ፊት ለፊት ገጥሞ በፅናትና በብስለት የመወጣት ባህል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ፈተናዎቹ ከጊዜና ቦታ ጋር ያለማቋረጥ እየተቀያየሩ በተከሰቱበት ጊዜ ሁሉ ህወሓት ፈተናዎቹን በድፍረትና ህዝባዊ ወገንተኝነት መንፈስ እየለየ በፅናት ከመፋለም ውጭ ግንባሩን ያጠፈበት ጊዜ እንዳልነበር ከህወሓት የአርባ ዓመታት ፈተና የበዛበት የትግል ጉዞ ለመገንዝብ ይቻላል፡፡ በትግሉ ወቅት በትግርኛ “ዘይንድይቦ ጎቦ፣ ዘይንሰግሮ ሩባ የለን” / የማንወጣው ጋራም ሆነ የማንሻገረው ወንዝ የለም/ በማለት እየዘመረ  የተጓዘው ህወሓት በእርግጥም በዚህ ጠመዝማዛ የትግል ጉዞ ያልተሻገረው ወንዝም ሆነ ያልወጣው ጋራ እንዳልነበር ለማረጋገጥ አይከብድም፡፡  ህወሓት ይህን በመሰለው ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ በአገራችን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ካበረከተው ዙሪያ መለስ አስተዋፅዖ መካከል ጉልህ የሆኑትን ስናነሳ የሚከተለውን ስዕል እናገኛለን፡፡

2.         የህወሓት የትግል አስተዋፅዖ፣
ይህን በመሰለ መፅሔት የህወሓትን የትግል አስተዋፅዖ በሁሉም መስክ ለመዘርዘር ቢፈለግ በእርግጠኛነት ከፍተኛ የአምድ ጥበት እንደሚኖር ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በመሆኑም በዛሬው ዕትማችን ስለ ህወሓት የትግል አስተዋፅዖ ስናነሳ መሠረታዊ በሆኑትና አንባብያን ሊገነዘቡዋቸው ይገባል ብለን በመረጥናቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለመወሰን እንገደዳለን፡፡ ስለዚህም በቅድሚያ በሁሉም ጉዳዮች ላይ የተሟላ መረጃ እንድናቀርብላቸው ለሚጠብቁ የመፅሔታችን ደንበኞች ያቀረብነው ወሳኝ የሆኑ የትግል አስተዋፅዖዎች በምንላቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሃሳቦችን ብቻ እንደሆነ አስቀድመን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

2.1        ግፈኛውን አገዛዝ በትግል የማስወገድ ቁልፍ ሚና የተጫወተ ድርጅት፣
የደርግ መንግስት ከፍ ሲል የተገለፀውን ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ይዞ በነበረበት ዘመን እንዲህ በቀላሉ ይወገዳል ተብሎ የማይገመት ነበር፡፡ ይልቁንም ብዙዎች ያነገቡትን የትግል መስመር እየተዉ አንድም ወደ ስደት አሊያም ከደርግ ጋር ተስማምቶ ማደር በመረጡበት፣ ሌሎቹ ደግሞ በተሳሳተ የትግል አቅጣጫ ተጉዘው ህዝባዊ ትግሉን ባዳከሙበት በዚህ ሂደት ህወሓት ገና ከጥዋቱ ትክክለኛ የትግል አቅጣጫ ተከትሎ በመጓዙ የደርግን መንግስት ለማስወገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡ ህወሓት በትግሉ የመጀመሪያ ዓመታት በአጭር ጊዜ ግዙፍ አቅም የገነባውን የወታደራዊ መንግስት ጥቃት ተቋቁሞ ለመዝለቅ ከመቻሉም በላይ የማታ ማታ ደግሞ ከሌሎች ዴሞክራቲክ አጋሮቹ ጋር በመሆን የደርግ መንግስት እንዲገረሰስ አስችሏል፡፡

በአገራችን ለአስራ ሰባት ዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየው ወታደራዊ አገዛዝ በትጥቅ ትግል መገርሰሱ ዛሬ በአገራችን ለተፈጠረው መሠረታዊ ለውጥ ልዩ ትርጉም የነበረውና ያለው ነው፡፡ ከሁሉ በፊት የደርግ መንግስትና ግዙፍ የአፋና መዋቅሩ በአገራችን ላይ እስከ ነበሩ ድረስ ዴሞክራሲን ዕውን ማድረግ አይቻልም ነበር፡፡ የዴሞክራሲ መብት በሥራ ላይ ሊውል የሚችለው በስልጣን ላይ ያሉ መንግስታት በህዝብ ላይ ቅጣት የሚያወርዱባቸው የአፈና ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ ግዙፍ ሠራዊትና ከሠራዊቱ ያልተናነሰ የታጠቀ የፖሊስና የሚሊሻ ኃይል ባለበት እንዲሁም ረጅም መዳረሻ ያለው የስለላ አውታር በተዘረጋበት አገር ሁሉ ዜጎች በነፃነት ፍላጎታቸውን መግለፅም ሆነ የዴሞክራሲን ትሩፋት መቋደስ አይችሉም፡፡ በጠየቁ ቁጥር ሥርዓቱን ለአደጋ አጋልጠሃል ተብለው ይታሰራሉ፣ ፍላጎታቸውን በገለፁ በተለይ ደግሞ የዜግነትና የእኩልነት ጥያቄዎችን ባነሱ ቁጥርም ለእስር፣ ለግርፋትና ግድያ ይዳረጋሉ፡፡ ስለዚህም ዜጎችና ህዝቦች የዴሞክራሲ መብታቸውን ይጠቀሙበት ዘንድ አፋኙ ሥርዓት ከነአፈና መዋቅሮቹ መገርሰስ ይገባዋል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ያደረጉትም ይህንኑ ነው፡፡ ትግሉ ከፍተኛ መስዋዕት የጠየቀ ቢሆንም  ይህን ከባድ ክፍያ ያላንዳች ማቅማማት በመክፈል የደርግን የአፈና ተቋማት ለመደምሰስ መቻሉ በርግጥም በአገራችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበሕት ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት ወሳኝ ነበር፡፡ 

በአገራችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊከበሩ፣ ዜጎች በግለሰብ ደረጃና ልዩ ልዩ ማህበረሰቦች ደግሞ እንደ ቡድን መብታቸውን ሊያስከብሩ የቻሉት ከደርግ ውድቀት በኋላ መሆኑ ይህንኑ እውነታ በግልፅ የሚያመላክት ነው፡፡ በብሔሮች እኩልነትና ባልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት መርሆ የሚመራ ፌደራላዊ ሥርዓት መገንባቱ፣ የሴቶችን እኩልነት በማክበር ላይና በሃይማኖት እኩልነት ላይ የተመሰረተ ሴኩላራዊ መንግስት  ሥርዓት መዋቀሩ፣ የፖለቲካ ብዝሃነትን በማወቅና በማክበር ላይ የተመሰረተ የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካዊ ሥርዓትና  የመንግስት ስልጣን በህዝብ ነፃ ምርጫ የሚዋቀርበት የፖለቲካ ሥርዓት መገንባቱ፣ በመንግስት አካላት መካከል በህግ የተወሰነ የስልጣን ክፍፍል የሚደረግበት ሥርዓት መበጀቱ ወዘተ……. ሁሉ ይህንኑ የሚያረጋግጡ  ናቸው፡፡ ግፈኛውን የአገዛዝ ሥርዓት ከመላ የአፈና ተቋማቱ ጋር በከባድ ትግልና መስዕዋት ማስወገድ ባይቻል ኖሮ ኢትዮጵያው ውስጥ ዴሞክራሲን በዚህ ስፋት ፍጥነትና ጥልቀት ማስፈን ባልተቻለ ነበር፡፡  

2.2       ያልተመጣጠነው ነባራዊ እውነታ የጫነበትን ከባድ ሸክም ያለማንገራገር የተሸከመ ድርጅት፣
በትጥቅ ትግሉ ዘመን የነበረው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ በተጨባጭ እንደሚያመላክተው ትግሉ በተለያዩ የአገሪቱ ማዕዘናት ተመሳሳይ የጥንካሬ ደረጃ አልነበረውም፡፡ አንዳንድ አካባቢ ትግሉ ቀደም ብሎ የተጀመረበት ሆኖ እያለ በመሪ ድርጅቶቹ ድክመት ብዙም መነቃነቅ ሳይቻለው የቆየ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ተጠቃሽ የሆነው በኦነግ የሚመራው ንቅናቄ ሲሆን ይህ ድርጅት ከፍተኛ የህዝብ የትግል መንፈስ በነበረበት በኦሮሚያ ክልል የተመሰረተ ቢሆንም ድርጅቱ በነበረው ጠባብ ብሔረተኛና ራስ ወዳድ አመራር ትግሉ ወደፊት መራመድ ተስኖት የቆየ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የደርግ መንግስት የሚቋቋመው አጥቶ የአካባቢውን ወጣቶች እያፈሰ ወደ ጦርነት እንዲማግድ ሁኔታው ተመቻችቶለት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በመሃል አገር በተለይ በብዙ የአገራችን ከተሞች የተቀሰቀሰውና በኢህአፓ የተመራው ትግል ድርጅቱ በፈፀመው ከባድ ስህተት ተመትቶ የተዳከመበት ወቅት ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ በከተሞች ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥና አንገት መድፋት ተከስቶ ነበር፡፡ ኢህአፓ በሰሜን አማራ የጀመረው የትጥቅ ትግልም በድርጅቱ የአመራር ድክመት ምክንያት ከመበታተኑ በተጨማሪ ከዚህ ብተና የተረፈውን ኃይል ይዞ የተደራጀው የኢህዴን/ብአዴን ኃይል ደግሞ ገና በለጋነት ደረጃ የሚታይ ብቻ ነበር፡፡

እነዚህ ሁሉ ተዳምረው ደርግ በመሃል አገርና በስተደቡብ ከሚገኙ የአገራችን አካባቢዎች በኃይል እያስገደደ በሚያሰልፋቸው ወጣቶች የገዘፈውን ሠራዊቱን በሰሜን ኢትዮጵያና በኤርትራ የነፃነት ንቅናቄዎች ላይ ሊያረባርብ የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለት ነበር፡፡ ህወሓት ገና ከለጋ ዕድሜው ጀምሮ በዚህ ሁኔታ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እየተገደደ የተረባረበበትን ግዙፍ ሠራዊት ለመመከት፣ ስለዚህም ደግሞ ባልተመጣጠነው የትግል ሁኔታ ምክንያት የተጫነበትን ተጨማሪ ሸክም ያለማቅማማት ለመሸከም የሚገደድ ድርጅት ነበር፡፡ ሌሎች ድርጅቶችና ትግሎች ደርሰው ሸክሙን ቢያግዙትም ባያግዙትም ህወሓት  ነባራዊ ሁኔታው የጫነበትን ይህን ሸክም ያለማቅማማት የተሸከመ ሊሆን ችሏል፡፡ አንድ በተነፃፃሪ ትንሽ አካባቢና ጥቂት ህዝብ ከተገቢ ድርሻው በላይ መስዋዕት እየከፈለ የተጓዘውም ህወሓት ያልተመጣጣነው ነባራዊ የትግል እውነታ የጫነበትን ሀገራዊ ግዴታ ያለማቅማማት ለመወጣት የቆረጠ ድርጅት ስለነበር ነው፡፡ ህወሓት ብቻ ሳይሆን በእርሱም የተመራው ሰፊው የትግራይ ህዝብ ልጆቹን እየመረቀ በመሸኘት የተፋለመውና ከባድ መስዋዕት የከፈለው ይህንኑ እውነታ በመቀበልና አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ሁሉ በልጆቹ ህይወት የከፈለውን መስዋዕት መጠን በተመለከተ ከማንም ጋር ሂሳብ ሳያወራርድ ሸክሙን በፀጋ ስለተቀበለ ነው፡፡

ህወሓት ይህን ሸክም ያለማቅማማት የተሸከመው በትጥቅ ትግሉ የመጀመሪያ ዓመታት ብቻ አልነበረም፡፡ በትጥቅ ትግሉ ማብቅያም ጭምር እንጂ፡፡ በአገራችን የደርግን መንግስት ለመገርሰስ ያስቻለው ከባዱ ወታደራዊ የማጥቃት እርምጃ የተሳካው የኃይል ሚዛኑ ከሞላ ጎደል ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይላችን ማጋደል መጀመሩን ተከትሎ የማታ ማታ ደግሞ በ1983 ዓ.ም ወደ ተሟላ ስትራቴጂያዊ ማጥቃት ከተሸጋገረ በኋላ ነው፡፡ ይህ ወቅት የ604ኛ፣ የ603ኛ እንዲሁም የ605ኛ ወታደራዊ ዕዞች የተደመሰሱበት፣ ትግሉ ከሰሜን ኢትዮጵያ ወጥቶ ወደ መሐል አገር የተስፋፋበትና በኋላ ደግሞ በዘመቻ ዋለልኝ፣ በዘመቻ ቴዎድሮስና በዘመቻ ቢልሱማ ወልቂጡማ አማካይነት የደርግን መንግስት ለመጨረሻ ግብዓተ መሬት ያበቃንበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ኦህዴድ የተመሰረተና የራሱን ጀማሪ ወታደራዊ አህዶች ያቋቋመ ቢሆንም፣ ኢህዴንም በተለያዩ ክፍለ ጦሮች ተደራጅቶ በጦርነቱ የበኩሉን አስተዋፅዖ  ያበረከተበት ወቅት ቢሆንም ወሳኙ የስትራቴጂያዊ ማጥቃት ኃይላችን የህወሓት ወታደራዊ አቅም ነበር፡፡ ይህ አቅም የደርግን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዎች በብቃት ለመመከት በመቻሉ በጉና፣ በሐይቅ፣ በሰሜን ሸዋና በአምቦ አካባቢዎች ደርግ ያካሄዳቸውን ከባድ ጥቃቶች በወሳኝነት ለመቋቋም ተችሏል፡፡ በዝያው ልክ ደግሞ  በትግሉ የተከፈለውን ከባድ የመስዋዕት ሸክም ህወሓት ያለማቅማማት ተሸክሟል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ህወሓት ለመስዋዕት የተዘጋጀ ድርጅት እንደሆነ ለማረጋገጥ አይከብድም፡፡ ምርጥ የህዝብ ልጆችን ያለ ስስት ለመስዋዕትና ለአካል ጉዳተኝነት አሳልፎ እየሰጠ ከማንም ጋር ሂሳብ ሳያወራርድ የተጓዘ በእርግጥም ራሱን የማያስቀድም ድርጅት እንደሆነ ያስመሰከረ ነው፡፡ ይህ በህወሓት ታጋዮች መስዋዕት በድምቀት የተፃፈው ታሪክ ነው፡፡

2.3       አዳዲስ ሃሳቦች ለማመንጨት ቀዳሚነትን የሚወስድ ድርጅት፣
ህወሓት ከፍ ሲል ከተገለፁት ጥንካሬዎቹ በማይተናነስ ደረጃ አስተዋፅዖ ያበረከተበት ሌላው ጉዳይ ድርጅቱ አዳዲስ ሃሳቦች በማመንጨትና እነዚህን ተግባራዊ በማድረግ ለውጥ ለማምጣት ቀዳሚነቱን የሚወስድ ድርጅት በመሆኑም ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ህወሓት ሁሌም ቢሆን ለታዳጊ ሃሳቦች ብቻ ሳይሆን የህብረተሰብን ችግር በመሰረቱ የመቅረፍ ብቃት ያላቸው ሃሳቦችን የማመንጨት ብቃት የነበረው ድርጅት ነው፡፡ ይህ እውነታ በትጥቅ ትግሉ ብቻ ሳይሆን በኋለኛውም ዘመን በግልፅ የታየ ነው፡፡ ህወሓት እንደ መለስ ዜናዊ ዓይነት ምጡቅ ስብዕና የነበራቸውን ሰዎች የፈጠረ ድርጅት በመሆኑ የሃሳብ ድህነት መሠረታዊና ዘላቂ ችግሩ ሆኖ የማያውቅ ድርጅት ነው፡፡ ለአጭር ጊዜ የቆዩ የግልፅነት መጓደል የታየባቸው መድረኮች አላጋጠሙትም ባይባልም መሠረታዊ ባህሪው በአዳዲስ መድረኮች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ሃሳቦችን በተደጋጋሚ የማመንጨትና በፅኑ ዲስፕሊን ተግባራዊ የማድረግ  ችሎታ የነበረው ድርጅት እንደሆነ የታየበት መሆኑ ነው፡፡ የዚህን ባህሪ ፋይዳ በትክክል ለመገንዘብ በለውጥ ሂደት ውስጥ ጥራት ያለው የትግል ሃሳብ የመጨበጥና ያለመጨበጥ ጉዳይ የሚጫወተውን ሚና ዘርዘር አድርጎ መመልከት ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀው ማንኛውም የለውጥ ሂደት ለስኬት ሊበቃ የሚችለው ከምንም ነገር በፊት ጥራት ባለው አስተሳሰብ ሊመራ ሲችል ነው፡፡ ጥራት ያለው አስተሳሰብ የሚባለው ደግሞ ከሁሉ በፊት መሠረታዊ የህብረተሰብ ችግሮችን በትክክል ለመለየትና ተስማሚና አስተማማኝ የመፍትሔ ሃሳብ በማመንጨት ችግሮቹን ለመፍታት የሚያስችል ብቃት ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህን የመሰለው አስተሳሰብ የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ችግሮችን በትክክል ለመለየት ያስችላል፡፡ ህብረተሰብ ምንም ጊዜ ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ባህሪ ያላቸው ችግሮች የማይታጡበት በመሆኑ ህዝብን መርቶ ለስኬት ለማብቃት የሚሻ ማንኛውም መሪ ድርጅት በየወቅቱ የመቀያየር ገፅታ ያላቸውን እነዚህን ችግሮች በትክክል መለየት ይጠበቅበታል፡፡

አመራር ከምንም ነገር በላይ የሚፈለገው ችግሮችን ለመፍታት በመሆኑ በጠራ አስተሳሰብ የመመራት ችሎታ አንዱና ዋነኛው መለያው የመድረኩን ችግሮች የመለየት ብቃት ነው፡፡ ከዚህ በማይነጠል መልኩ ደግሞ በትክክል ለተለዩት ችግሮች ትክክለኛና ዘላቂ መፍትሔ መቀመር የአስተሳሰብ ጥራት ሌላው ማሳያ ነው፡፡  እነዚህ ብቃቶች ተሟልተው ሲገኙ ትግሉ ከአንድ መድረክ ወደ ሌላ መድረክ በድል አድራጊነት ሊሸጋገር ይችላል፡፡ በአንፃሩ የዚህ ዓይነት ብቃት በሌለበት ወይም እየተጓደለ በሄደበት ደግሞ ትግሉም አብሮ ተንገራግጮ ይቆማል፣ ወይም ደግሞ በማያቋርጥ የማሽቆልቆል ጉዞ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ በብዙ አገሮች ህዝባዊ ትግሎች ላይ ያጋጠመ ክስተት ነው፡፡

የሃሳብ ድህነት የተጠናወታቸው ህዝባዊ ትግሎች ከሁሉ በፊት መሠረታዊ የሚባሉትን የህብረተሰብ ችግሮች በትክክል የመመልከትም ሆነ የመለየት ብቃት ይሳናቸዋል፡፡ መሪዎቹ በራሳቸው ጠባብ ፍላጎት ታጥረው የህዝቡን መሠረታዊ ችግሮች መመልከትም ሆነ መቀበል ያቅታቸዋል፡፡ ይህን መሠረታዊ ችግር የተሸከሙት መሪዎች የፈለገውን ዓይነት መልክ ሊኖራቸው ቢችልም ለህብረተሰቡ ችግሮች ተስማሚና ዘላቂ መፍትሔ ማዘጋጀትም ይቸግራቸዋል፡፡ ይህም ሲሆን ህዝባዊ ትግሉ የሃሳብ ድህነት የሰፈነበት ወይም በአስተሳሰብ ድርቅ የተመታ መሆን ይጀምራል፡፡ ይህን የመሰለው ትግል በአጋጣሚ ለስልጣን ቢበቃ እንኳን ዞሮ ዞሮ የጥቂቶችን ጥቅም ያስከብር እንደሆነ እንጂ ለህዝቡ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሔ ማምጣት የማይችል መሆኑ እሩቅ ሳንሄድ ዓመታት በወሰደ የትጥቅ ትግል ለስልጣን የበቁ የአህጉራችንን ንቅናቄዎች በመመልከት ሊረጋገጥ የሚችል ነው፡፡

የአስተሳሰብ ጥራትን የመላበስ ጉዳይ ምን ጊዜም ቢሆን ሃሳብን ከመድፈር በተለይ ደግሞ አዳዲስ ሃሳብን ለመስማት ከመሻት የሚጀምር ብቃት ነው፡፡ ይህ ብቃት ይኖር ዘንድ ከድርጅቱ መሪዎች ጀምሮ ራሳቸውን ለአዳዲስ ሃሳቦች ክፍት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንድ አዲስ ሃሳብ ብቅ ሲል የያዙትን ነባር ሃሳብ የሙጥኝ ብለው ሌላውን ላለመስማት ከመፈለግ ተቆጥበው የአዲሱ ሃሳብ ተፅዕኖ ምንም ይሁን ምን ሊሰሙትና ጥቅምና ጉዳቱን በፅሞና ለመመዘን መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ የበፊቱ ሃሳብ ጠቃሚና ተገቢ የነበረ መሆኑ በማያከራክርበትም ጊዜ ቢሆን አዲሱ ሃሳብ እንዲደመጥ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ አዲሱ ሃሳብ በእርግጥም ተገቢና ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ያለማቅማማት ተቀብለው ሊመሩበት ይገባል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ የድርጅቱ መሪዎች ሁሌም ቢሆን የመማር ብቃት ሊኖራቸው ይገባል፡፡  ከራሳቸው የስኬትና የውድቀት ልምዶች ይማሩ ዘንድ የማያቋርጥ የሁኔታዎች ግምገማ ብቻ ሳይሆን ነገሮችን አስቀድሞ ከተያዘ የመውደድ ወይም የመጥላት አባዜ ተላቀው በደቃቁና በጥልቀት ለመፈተሽ የሚያስችል ግምገማ የማካሄድ ባህል ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሌሎች ስኬታማና የከሸፉ ልምዶች ለመማር ይችሉም ዘንድ ጠንካራ የንባብ ባህል ማዳበር ይገባቸዋል፡፡ ሃሳብን በተለይ ደግሞ አዳዲስ ሃሳቦችን ከመፍራት፣ ግምገማዎችን ከመጥላት፣ የነበረውን ከማሞካሸት ወይም ከማብጠልጠል አካሄድ ተላቀው ነገሮችንና አዳዲስ ሃሳቦችን በይዘታቸውና በነባራዊነታቸው የማየት ድፍረት ሊኖራቸው ይገባል፡፡

 ህወሓት እነዚህ መሠረታዊ ባህሪያት የነበሩት ድርጅት እንደሆነ ባለፉት 40 የትግል ዓመታት ያረጋገጠ ድርጅት ነው፡፡ ከሁሉ በፊት ድርጅቱ ታግሎ የሚያታግለውን ማህበረሰብ መሠረታዊ ችግሮች በትክክል ለመለየት የቻለ ድርጅት ነው፡፡ ገና ከለጋ ዕድሜው ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ዘንድ መሠረታዊ ለውጥ ያመጡ ሃሳቦችን የማቀንቀን ብቃት የተጎናፀፈውና በሂደትም ይህን እያዳበረ የተጓዘው የህብረተሰቡን ችግሮች በትክክል ለመለየትና መፍትሔ ሃሳብ ለማመንጨት በመቻሉ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የመጀመሪያው የህወሓት ትክክለኛ ሃሳብ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችልና የሚገባው በኢትዮጵያ የሚታዩ ልዩ ልዩ ቅራኔዎችን በትክክል የፈረጀበት ሂደት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በ1960ዎቹ አጋማሽ በአገራችን በነበሩት ተራማጅ ድርጅቶች መካከል ከታዩት ልዩነቶች አንዱ በኢትዮጵያ የብሔርና የመደብ ቅራኔ በነበራቸው ተዛምዶና የቀዳሚና ተከታይነት ሚና ጋር የተያያዘው ልዩነት አንዱ ነበር፡፡ ህወሓት በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የብሔር ቅራኔው ቀዳሚውና ዋነኛው በመሆኑ ይህን አስቀድሞ መፍታት ለሌላው ትግል መቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል በሚል እሳቤ በመመራት በእርግጥም ይህን ቅራኔ በመፍታት ዙሪያ ተረባርቧል፡፡ ህወሓት ይህን እሳቤ ሲያራምድ መጀመሪያ ላይ ከአብዛኞቹ የኢትዮጵያ የወቅቱ ተራማጅ ኃይሎች የተለየ ቢሆንም በአቋሙ ፀንቶ በመታገሉ የብሔርን ጥያቄ በዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ ለመፍታት ያስቻለ ሊሆን በቅቷል፡፡

ህወሓት በ1970ዎቹ አጋማሽ ላይ አጋጥሞት የነበረውን ወደ ፊት ለመራመድ ያለመቻል ፈተናም ያለፈው ተጨባጭ ሁኔታውን በፅሞና በመገምገምና ትግሉ ወደ ፊት መራመድ ተስኖት በመቆም ሂደት ውስጥ የገባ መሆኑን አስተውሎ ከዚህ ለመውጣት የሚያስችል አዲስ ሃሳብ ለማመንጨት በመቻሉ ነበር፡፡ ይህ ወቅት ራሱ ህወሓት በትግርኛ “ደውታ” ወይም “ባለህበት መርገጥ” በሚል መልክ የሰየመው ወቅት ነበር፡፡ ትግሉ ገና ሲጀምር ሁሌም በዕድገት ጎዳና እንዲረማመድ በመፈለግ የተቀሰቀሰና እስከ ተወሰነ ጊዜም ወደ ፊት እየተራመደ የተጓዘ ሲሆን በዚህ ወቅት ግን ወደፊት መራመድ ተስኖት ባለበት መርገጥ ጀመረ፡፡ ይህ በወሳኝነት ሠራዊቱንና በደጀንነት የተሰለፈውን ህዝብ ጥርት ባለ የፖለቲካና ወታደራዊ አቅጣጫ ለማንቀሳቀስና የደርግን ጥቃት ከመቋቋም አልፎ ደርግን ለማሽመድመድ የሚያስችል አቅጣጫ የማጣት ችግር ነበር፡፡

በዚህም አጋጣሚ የደርግ መንግስት በብቃት የሚመክተው ባለማግኘቱ ነፃ የወጡ የትግራይ አካባቢዎችን ለማተራመስ ዕድል እስከማግኘት ደረሰ፡፡ ነገር ግን በህዝባዊ ትግሉ ፊት የተደቀኑ ችግሮችን ለመፈተሽና በትክክል ለመፍታት የማይቦዝነው ህወሓት የሚገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በፅሞና መርምሮ ትግሉ ባለበት የመቆም ችግር እንደገጠመውና ይህም በወሳኝነት ለወቅቱ ችግሮች መፍትሔ የሚሆን ሃሳብ ከማጣቱ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋገጠ፡፡ ከማረጋገጥም አልፎ ተመሳሳይ ችግሮች ካጋጠማቸው ትግሎች ልምድ በመማርና የራሱን የፈጠራ ብቃት በመጠቀም ትግሉ በአጭር ጊዜ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚችልበትን ምጥቀት ያለው አስተሳሰብ ማመንጨት ጀመረ፡፡ በተለይ ከ1977 ዓ.ም እስከ 1980 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት ደግሞ የአስተሳሰብ ምጥቀቱ ወደ አዲስ ከፍታ እንዲወጣ አደረገ፡፡ በዚህ ወቅት ህወሓት የፖለቲካና ወታደራዊ እንዲሁም የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ትግል መስመሮቹን ከመቼውም በላይ አጥርቶ አዘጋጀ፡፡ ይህ ሂደት ህወሓት በውስጡ ሰፊ ዴሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል የተካሄደበትና ድርጅቱ ከክርክሮች እውነታን ፈልቅቆ የማውጣት ችሎታ አንደነበረውና እንዳለው ያስመሰከረበትም ሆነ፡፡ ከዚህም አልፎ ከፍ ሲል የተጠቀሰውን አገራዊ ስትራቴጂያዊ ማጥቃት በአነስተኛ ጊዜና ውጤታማነት ለማረጋገጥ ያስቻለም ነበር፡፡

ህወሓት በዚህ መድረክ ራሱን ለአዳዲስ እሳቤዎች ክፍት ባያደርግ ኖሮ የያዙትን ያረጀ ያፈጀ ሃሳብ የሙጥኝ እንዳሉ ከመሸባቸው እንደ ኢህአፓ ከመሳሰሉ ድርጅቶች የተለየ ባልሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠመንጃ የማያስፈራው ህወሓት የተለየ ሃሳብ የሚያስፈራው አልነበረምና ለአዳዲስና የትግል እመርታን ላመጡ ሃሳቦች ሰፊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ የነበረው ህወሓት በእርግጥም በኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ሂደት የአዳዲስ አስተሳሰቦች ምንጭ የሆነ ድርጅት ነበር፡፡ በህወሓት የአርባ ዓመት ተጋድሎ አንዱ የድርጅቱ ልዩ አስተዋፅዖ ፈር ቀዳጅ ሃሳቦች የሚመነጩበት ድርጅት ሆኖ መቆዩቱ ነው የሚባለው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡

ይህ ሂደት ከትጥቅ ትግሉ በፊት የታየና በዚያ ደረጃ ብቻ የታጠረም አልነበረም፡፡ ከትጥቅ ትግሉ መጠናቀቅ በኋላም የተከሰተ ጭምር ነበር፡፡ ዛሬ በአገራችን ከፍተኛ እምርታ በማስመዝገብ ላይ ያለው የተሃድሶ መስመር ይነደፍ ዘንድ ህወሓት ሚናውን ተጫውቷል፡፡ እንደሚታወቀው ተሃድሷችን ከመቀስቀሱ በፊት በአገራችን አስፈሪ የጥገኛ ዝቅጠት አዝማሚያ መንሰራፋት ጀምሮ ነበር፡፡ ይህ የዝቅጠት አደጋ ከማንም በፊት የተጠናወተው ደግሞ ከፍተኛውን የድርጅት አመራር ነበር፡፡ አደጋው ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት ጀምሮ የተከሰተ ቢሆንም ጦርነቱ በፈጠረለት ምቹ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገነገነ ሊሄድ ችሎም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ትግሉ ሌላ የመቆምና ከዚያም አልፎ የመቀልበስ አደጋ አንዣብቦበት ነበር፡፡ ብዙዎቹ የድርጅታችን የአመራር አባላት በዚህ ወቅት የተከሰተውን ችግር ባህሪ በትክክል ለማስቀመጥ የተቸገሩ ቢሆንም በወቅቱ በተካሄደው ዴሞክራሲያዊ ትግልና በተለይ ደግሞ ጓድ መለስ በተጫወተው የመድረኩን ተግዳሮቶች በትክክል ለይቶ ይህንን ለመፍታት የሚያስችል ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የማመንጨት ሚና የተሃድሶ መስመራችን ሊነደፍ በቅቷል፡፡ የተሃድሶ መስመራችን ነባር ድርጅታዊ ጥንካሬያችንን በማስጠበቅ ሳይወሰን በአዳዲስ መሪ ሃሳቦች አበልፅጎ ለላቀ ውጤት ያበቃን የትግል መስመር ነው፡፡ ምንም እንኳ ይህ መስመር በተነደፈበት ጊዜ በወሳኝነት በህወሓት ቁልፍ የአመራር ኃላፊነት ከነበሩ ግለሰቦች ጠንካራ ተቃውሞ የገጠመው ቢሆንም በህወሓትና በሌሎች እህት ድርጅቶች ውስጥ በተካሄደ ዴሞክራሲያዊ ትግል አዲሱ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር በአሸናፊነት ሊወጣ ችሏል፡፡

ህወሓት የአዳዲስ ሃሳቦች ምንጭ በመሆን ሚናውን የተጫወተበት ሂደት ሲታይ መላው የአመራር ኃይሉ ያላንዳች ልዩነት ሃሳብ የማመንጨት ብቃትና ዝግጁነት ነበረው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም አንዳንዱ የአመራር አባል አዳዲስ ሃሳቦችን ለማመንጨት የሚያስችለውን ሂደት በፀጋ ለመቀበል ይችገር እንደነበር ከድርጅቱ የውስጥ የትግል ታሪክ በግልፅ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ በድርጅቱ  ዘንድ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሃሳብ እጥረት ያገጠመበት ከዛም አልፎ ኋላ ቀር ባህሪ ያላቸው አስተሳሰቦች በቅድመ ተሃድሶ ወቅት እንደታየው ለአጭር ጊዜ ቢሆንም የበላይነት የያዙበት አጋጣሚ አልተከሰተም ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ በአንድ በኩል ኋላ ቀር አስተሳሰቦችን የመታገልና የማሸነፍ ልምድና ባህል ያለው በመሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሃሳቦች መካከል ትግል ሊካሄድበት የሚችል ሰፊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ የመክፈት ባህል የነበረው ድርጅት በመሆኑ ኋላቀር ይዘትና ባህሪ የነበራቸው አስተሳሰቦች ከጊዜያዊ ሞቅ ሞቅ ያለፈ ዘላቂ ተቀባይነት ወይም የበላይነት አግኝተው አያውቁም፡፡ በአንፃሩ በተሟላ ህዝባዊ ወገንተኝነትና ተራማጅ አቋም ላይ በመመስረት የተጠበቁት ነባር አቋሞችና እነዚህን በማዳበር የተጨመሩት አዳዳስ እሳቤዎች ሁሌም ተቀባይነትና የበላይነት ሲያገኙ ቆይተዋል፡፡ ህወሓትን ዘመን ተሻጋሪ ድርጅት እንዲሆን ያስቻለው አዳዲስ ሃሳቦች የማመንጨት ችሎታ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚታይ ብቻ ነው፡፡ ትግሉ እስካለና እስከቀጠለ ድረስ ህወሓት ኢህአዴግ በማያቋርጥ የለውጥ አራማጅነት አገራዊ እመርታ የሚያመጡ አስተሳሰቦችን እያመነጩ እንደሚሄዱ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ 

2.4      ተራማጅ ሃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ቀዳሚነት ያልተለየው ድርጅት፣
ህወሓት አዳዲስ ሃሳቦችን ለማመንጨት ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጥ የመቆየቱን ያህል የመነጩትን ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ቀዳሚነቱን የሚወስድ ድርጅትም ነበር፡፡ ሃሳቦች ማመንጨት የሚያስፈልግበት ዓይነተኛ ምክንያት እነዚህን መልካምና የለውጥ መሣሪያ የሆኑ ሃሳቦች በተግባር ላይ በማዋል ነባራዊን ሁኔታ ለመቀየር ነው፡፡ የለውጥ ሃሳብ የመጨበጥና ይህንኑ በፅኑ ዲስፕሊን በተግባር ላይ የማዋል ጥረት ብቻ ለውጥን እውን ያደርጋል፡፡ ጥራት ያላቸው ሃሳቦች ዞሮ ዞሮ በተግባር ላይ ካልዋሉ ደግሞ ነባራዊ ሁኔታ እንዳለ ይቀጥላል እንጂ አይቀየርም፡፡ ስለሆነም ለውጥ የሁለት መሠረታዊ አቅሞች ድምር ውጤት ተደርጎ ይወሳዳል፡፡

አገራችን የምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ በብዙ መልኩ ከፍተኛ መሻሻልና ለውጥ ሊመጣበት የሚገባ ሲሆን ይህም በተግባር የሚካሄድ ለውጥ ሊሆን ይገባዋል፡፡  ከዚህ አኳያ ሲታይ በአጠቃላይ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በተለይ ደግሞ ህወሓት የለውጥ ሃሳቦችን ለማመንጨት የሰጡትን ያህል ትኩረት እነዚህን በተግባር ላይ አውሎ መሠረታዊ ለውጡን በቀጣይነት ለማረጋገጥ እንደተረባረቡ ከታሪካቸው ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ በአጭሩ ህወሓትና ኢህአዴግ ለውጥን ያለሙ ብቻ ሳይሆኑ የተገበሩ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ለውጥን በፅኑ ዲሲፕሊን ተግባራዊ የማድረግ ጠንካራ አቋምና ባህል መሠረቱ ደግሞ ህወሓት ነበር፡፡ ቀጥለን በአጭሩ የምንጠቅሳቸው ጉዳዮች ሁሉ የለውጥ ሃሳብና ትግበራ ከህወሓት/ኢህአዴግ አኳያ ምን እንደሚመስል ጠቋሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ትግሉ ሲጀምር የመነሻ ነጥቡ ተደራጅቶ የመታገል አስፈላጊነት ወይም ሃሳብ ነበር፡፡ ይህ ሃሳብ ህወሓት/ኢህአዴግን በማደራጀት ዕውን ሆነ፡፡ ትግሉ በከባዱ የትጥቅ ትግል አማካይነት ደርግን አሸንፎ ህዝባዊ መንግስት በመመስረት እሳቤ የተመራ ነበር፡፡ በተጨባጭም ከባዱ የትጥቅ ትግል ለአስራ ሰባት ዓመታት በተግባር ተካሄደ፡፡ የፈተናው ብዛት፣ የመስዋዕቱ ገደብ የለሽ መሆን የሃሳቡን ተግባራዊነት አልገታውም፡፡ ይልቁንም የትግሉ ክብደትና ውስብስብነት የአስተሳሰብ ብስለትና ጥልቀትን እየጨመረ በዚያው ልክ ደግሞ በሰብ ሰሃራ አፍሪካ ግዙፍ የነበረውን የአፈና ተቋም በተግባር እስከ መደምሰስ ተደረሰ፡፡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ህዝብን በነቃ፣ በተደራጀና በታጠቀ አኳኋን የማሳተፍ እሳቤ ነበረ፡፡ በተግባርም ላይ ዋለ፡፡በትጥቅ ትግሉ ወቅት መሬት ለድሃና መካከለኛ አርሶ አደሮች የማከፋፍል ሃሳብ ነበር፡፡ ይህ ሃሳብ በተወሰነ ደረጃ ከደርግ ውድቀት በኋላም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች አስፈላጊ ሆኖ ታይቶ ነበር፡፡ ህዝቡን ባሳተፈ አኳኋን በተግባር ላይ እንዲውል ተደርጎም ለልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ተጣለ፡፡  ሴቶችን በተደራጀ መንገድ በማሳተፍ ትግሉ የተሟላ ድል ባለቤት እንዲሆን የማድረግ እሳቤም በተግባር ላይ ተተርጉሞ እነሆ በአገራችን የሴቶች እኩልነት የተከበረበት ሥርዓት ሊተከል በቃ፡፡ የሃይማኖትና የብሔር እኩልነትም የትግል መመሪያ የሆኑ አስተሳሰቦች ብቻ ሳይሆኑ በተግባር ላይ ውለው በአገራችን የፌደራላዊ ሥርዓት ባለቤት ልንሆን ችለናል፡፡

ህወሓት ጉልህ ሚና የተጫወተበት የድህረ ግንቦት 20 አገራዊ ትግላችንም ሆነ ህወሓት ወሳኝ ሚና የተጫወተበት የድህረ 1983 ዓ.ም የትግራይ የለውጥ ጉዞ በቅርበት ሲመረመሩ የምናገኘው እውነታ ተመሳሳይ የለውጥ ሃሳቦች በፅኑ ዲሲፕሊን ተግባራዊ የተደረጉበት ነው፡፡ በግንቦት 1983 ዓ.ም ደርግ በወደቀ ማግስት ለአንድ ወር ብቻ የሚቆይ የኢህአዴግ ጊዜያዊ መንግስት የማቋቋም ሃሳብ፣ ከአንድ ወር በኋላ ሁሉንም በሠላም ለመታገል የቆረጡ ነባርና አዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ኮንፈረንስ በማካሄድ የሽግግር ሂደት እንዲኖርና  ሂደቱም ከፓርቲዎች በተውጣጣ መንግስት እንዲመራ የማድረግ እሳቤ ገና ከጥዋቱ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ የሽግግሩ መንግስት ህዝብን ባሳተፈ አኳኋን ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት እንዲዘጋጅና በህዝብ በተመረጡ ተወካዮች እንዲፀድቅ ለማድረግ፣ ህገ-መንግስቱ ከፀደቀ በኋላ በህዝብ ነፃ ምርጫ መንግስት ማቋቋምን ጨምሮ ሁሉም ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ላለፉት 24 ዓመታት ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በልማቱ መስክ በየመድረኩ የተወጠኑ የልማት እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተካሂዷል፡፡ በመጀመሪያው መርሃ-ግብር በወቅቱ ዘላቂነት ያለው የገጠርና የግብርና ልማት በተለይ አነስተኛ ግድቦችን በማስፋፋት ለማምጣት የተደረገው ጥረት በኋላ ደግሞ በገጠርና በከተማ የተሃድሶውን ልማታዊ መስመር ተግባራዊ በማድረግ የህዝብን ተጠቃሚነት የማጎልበት ሥራዎች ሁሉ ህወሓት ምን ያህል የለውጥ ሃሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል የሚተጋ ድርጅት እንደሆነ በተጨባጭ የሚያሳዩ የሥራ ምስክሮች ናቸው፡፡ በትግራይ ከፍተኛ ለውጥ ካመጣው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና እንክብካቤ ጀምሮ እስከ ማህበራዊ ልማቶች ድረስ የዘለቀው የለውጥ ሃሳቦች ትግበራ ድርጅቱ የማሰብ ብቻ ሳይሆን የመተግበር ችሎታ ያለው እንደሆነ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ስለሆነም ህወሓት በትግራይም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጣው ለውጥ በሃሳብ አመንጪነት ብቻ የማይወሰን ይልቁንም የለውጥ ሃሳቦችን በፅኑ ዲሲፕሊን ተግባራዊ የማድረግ ብቃት ያዳበረ ድርጅት እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡

ለ40 ዓመታት ያህል ከድል ወደ ድል እየተረማመደ የተጓዘው ህወሓት በአገራችን ለሚካሄደው ህዝባዊ ትግል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተ ድርጅት እንደሆነ ከፍ ብሎ ከተጠቀሰው መለስተኛ ማስረጃ በመነሳት ብቻ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ይህ እውነታውን በትክክል ለማየትና ለመቀበል ፍቃደኛ በሆኑት ወገኖች ሁሉ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ በአንፃሩ ይህን እውነታ ለማየት ዝግጁነቱና ፍቃደኝነቱ በጎደላቸው ወገኖች ዘንድ ደግሞ በተደጋጋሚ ሲካድ የምናስተውለው ነው፡፡ ከአገራችን ህዝቦች መካከል እጅግ በጣም ብዙሃኑ ከለውጥ ሃሳቦቻችንና ከእነዚሁ ትግበራ ተጠቃሚዎች በመሆናቸው ይህን የህወሓት አስተዋፅዖ በቅን ልቦና ይመለከቱታል፡፡ ይቀበሉታልም፡፡ በአንፃሩ በለውጡ ብዙሃኑ እየተጠቀሙ መጓዝ መጀመራቸው ያልተዋጠላቸው ክፍሎች ደግሞ ይህንን አስተዋፅዖ በመጥላት ብቻ ሳይወሰኑ የማጥላላትና ጥላሸት የመቀባት ስራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ህወሓት የእነዚህ ክፍሎች የጥቃት ሰለባ ሆኗል፡፡ ይህን የመሰለው ጥቃት ዛሬም ድረስ ያላባራ ቢሆንም የመጀመሪያ ጥቃት ነው ሊባል ግን አይችልም፡፡ ህወሓትን ገና ከለጋነቱ ጀምሮ ለማጥፋት የተካሄደው ቀጣይ ዘመቻ አካል ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ዘመቻዎች ህወሓትን በአካል ጭምር የማጥፋት ምኞት የነበራቸው ከዛም አልፎ በግዙፍ መንግስታዊ የፕሮፖጋንዳና ወታደራዊ አቅም ተሸኝተው የተካሄዱ ጥቃቶች ነበሩ፡፡ ምንም ነገር አይሳነኝም ብሎ ያምን በነበረው የደርግ መንግስት የተመሩና የተቀነባበሩ ዘመቻዎችም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ውለው አድረው ከመክሸፍ ያልተረፉ ዘመቻዎችና ጥቃቶች ነበሩ፡፡ እናም የትላንት ታሪክ ስለ ወደፊቱ ጠቋሚ ምልክት የመስጠት ችሎታ ካለው የዛሬዎቹ ዘመቻዎች ዕጣ ፋንታም ተመሳሳይ እንደሚሆን ለመገንዘብ አያስቸግርም፡፡ ይህ ሲባል ግን እነዚህ ሌት ተቀን የሚካሄዱና የአገር ውስጥና የውጭ ኋላ ቀር ኃይሎች በቅንጅት የሚያካሂዱዋቸው ጥቃቶችና ዘመቻዎች በብቃት ይመከቱ ዘንድ ህወሓት ራሱን ሁሌም ለመድረኩ ተልዕኮዎች ማዘጋጀት አይገባውም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ወረድ ብለን የምንዘረዝራቸውን ሁኔታዎች ታሳቢ በማድረግ ህወሓት ለቀጣይ የየመድረኩ ተልዕኮዎች ራሱን በይበልጥ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ 

3.        ህወሓትና ቀጣይ የመድረክ ተልዕኮዎቹ፣
ከፍ ሲል ከዘረዘርነው የህወሓት የ40 ዓመታት የትግል ጉዞ ለመገንዘብ እንደሚቻለው የትግል ድርጅቶች የሚገጥማቸው ፈተና በአንድ መድረክ ተጀምሮ በዚያው መድረክ ብቻ የሚጠቃለል አይደለም፡፡ ይልቁንም ትግሉ በሚያልፍባቸው ጠመዝማዛ መንገዶችና አዳዲስ መድረኮች ሁሉ ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ አንዳንዱ ፈተና የቆየና የተለመደ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የቆየም ሆኖ በዓይነቱና በመጠኑ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው ፈተና ደግሞ ከአዲሱ የትግል መድረክ ጋር ተያይዞ የሚገጥም የተለየ ባህሪ ያለው አዲስ ፈተና ሊሆን ይችላል፡፡ ትግሉ ወደፊት ሲያስገመግም ይዞት የሚመጣው አዲስ ፈተና ይኖራል፡፡ ትግሉ በልዩ ልዩ ምክንያቶች መደነቃቀፍ ሲገጥመውም ሌላ ፈተና መከሰቱ አይቀርም፡፡ ለ40 ዓመታት የተካሄደው ህዝባዊ ትግል ቀጥ ባለ መስመር ያልተጓዘው ይልቁንም ሂደቱ ዚግዛግ ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ መመለስና ወደ ፊት መራመድ ያልተለየው ሊሆን የቻለውም እያንዳንዱ መድረክ የራሱን ፈተናዎች የሚደቅን ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ህወሓትና መሰል የትግል ድርጅቶች ከፊታቸው የሚደቀኑ ፈተናዎችን በጊዜ እየለዩ በተለመደው ህዝባዊ ፅናት፣ የአስተሳሰብ ብስለትና ብቃት መፍታት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ ወደ ፊት ስለሚሆነውና ስለሚከሰቱ ፈተናዎች ማንም በእርግጠኝነት ለመናገር የሚያስችል ነቢይነት ባይኖረውም ሊገመቱ የሚችሉ ፈተናዎችን ከወዲሁ መለየትና ለመፍታት መዘጋጀት ተገቢ ይሆናል፡፡ ፈተናዎችን ሲያጋጥሙ እየተንደፋደፉ ከመፍታት ይልቅ አስቀድሞ ገምቶ ለመፍታት የመዘጋጀት ባህል ካዳበረው ህወሓት የ40 ዓመት የትግል ጉዞ የምንማረውም ይህንኑ ነው፡፡ ቀጥለው የተጠቋቆሙት ጉዳዮችም በዚህ ቅኝት የቀረቡ ናቸው፡፡

3.1.      የመንግስት ስልጣን ባለቤት ከመሆን ጋር ተያይዘው የሚመጡ ፈተናዎችን ማሸነፍ፣
ይህ ፈተና መላውን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይላችንን የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ዛሬ እንደ አዲስ የምንፈለስፈው ፈተና አይደለም፡፡ በዚህ ልዩ ዕትም በጉዳዩ ላይ ለመፃፍ ስንሞክርም ችግሩ የአንዱ ወይም የሌላው ብቸኛ ችግር እንደሆነ በማሰብ አይደለም፡፡ ይልቁንም እኛን ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮች ሁሉ ስልጣን ላይ ያሉ መሰል ንቅናቄዎችን ሁሉ የሚሞግት ፈተና እንደሆነ በማሰብም ጭምር ነው፡፡ ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው የተሃድሶ መስመራችን በተነደፈበት ጊዜ በግልፅ የተቀመጠው የሥርዓታችን ፈተና አንድ ዋነኛ ምንጭ የመንግስት ስልጣን  ነው፡፡ በአገራችንም ሆነ በመሰል ሌሎች አገሮች የመንግስት ስልጣን አንድም ሃብት ለመፍጠር አሊያም የተፈጠረ ሃብትን ለመቀራመት ዕድል የሚሰጥ ግዙፍና አይነተኛ ተቋም ነው፡፡ የፖለቲካ ኢኮኖሚው ለጥገኝነት የተመቸ በሆነበት አገር ሁሉ የመንግስት ስልጣን አዲስ ሃብት ከመፍጠር ይልቅ ያለውን ለመቀራመት ዓላማ ማስፈፀሚያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህ ሲሆን በስልጣን ላይ ያሉ ኃይሎች ከሁሉ በፊት ስልጣናቸውን በመጠቀም ለራሳቸው ከልክ በላይ ጥቅም ማግበስበስ ይጀምራሉ፡፡ በመቀጠል ደግሞ ከባለስልጣናት ጋር ተሻርከው ለሚከብሩ ጥገኞች በጣም የተመቸ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡ የመንግስት ስልጣን የሚያጎናፅፋቸውን ሃብት የማደላደል ዕድል በመጠቀም ራሳቸውና በጥቅም የተሳሰሯቸው ለህብረተሰብ ዕድገት ካበረከቱት አስተዋፅዖ በላይ እንዲጠቀሙ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ሲሆን በህብረተሰብ ውስጥ አዲስ ሃብት የመፍጠርም ሆነ እሴት የመጨመር ዕድል እየመከነ አስቀድሞ የተፈጠረውን ሃብት መቀራመት እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ድህነት እየጨመረ ወይም ህብረተሰቡ ከድህነት የመላቀቅ ዕድሉ እየተመናመነ ይቀጥላል፡፡

ከራሳችን ልምድ እንደምንመለከተው የመንግስት ስልጣን ሃብት የመቀራመቻ ሳይሆን አዲስ ሃብት የመፍጠሪያና ብዙሃኑን ህዝብ ከድህነት ማላቀቂያ መሣሪያ ከሆነ ደግሞ የሚገኘው ውጤት በመሰረቱ ዕድገትን የሚያፋጥንና የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያሰፋ ይሆናል፡፡ የመንግስት አቅም ልማትን ለማፋጠን ዓላማ ይውላል፡፡ በመንግስት እጅ ያሉ ልዩ ልዩ ፀጋዎች በሙሉ ልማትን በሚያጎለበት መልኩ እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡ መሬት፣ ፋይናንስ፣ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት እንዲሁም አስተዳደራዊና የፍትህና ፀጥታ የማስከበር አቅሞች ሁሉ ተዳምረው የህብረተሰብን የማምረት አቅም ለመገንባት እንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡ ይህም ሲሆን ብቻ ፈጣንና ህዝብ የሚጠቅምበት ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ልማትና አስተማማኝ ዴሞክራሲ ይሰፍናል፡፡

መንግስት ልማታዊ ባህሪ ሲይዝና የኪራይ ሰብሳቢነት ባህሪ ሲጠናወተው የሚጫወተው ሚና ይህን ያክል መሠረታዊ ልዩነት ያለው መሆኑ እንደተጠበቀና በእኛ ዓይነት ማህበረሰቦች አንድም ለይቶለት ጥገኛ ወይም የለየለት ልማታዊ መንግስት የመሆን እድሉ እንዳለ ሆኖ በሽግግር መድረኮች በሚያልፍ ህብረተሰብ ደግሞ ሁለቱም ባህሪያቶች ተዳብለው የሚገኙበት ጊዜ ያጋጥማል፡፡ በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለተካ ኢኮኖሚ ካለበት ማህበረሰብ በመውጣት ወደ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ግንባታ ሽግግር በሚያደርግ ህብረተሰብ የሚቋቋሙ ልማታዊ መንግስታትን የኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያ ያለማቋረጥ የሚፈታተናቸው መሆኑ አይቀርም፡፡ ልማታዊነት ጎልብቶና አሸንፎ የሚወጣው ይህ ፈተና ረዘም ላሉ ዓመታት የሂደቱ የማይነጠል ገፅታ እንደሚሆን ለአፍታም ቸል ሳይሉ በመገንዘብና በመታገል ብቻ ነው፡፡

በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሳይሰሩ የመክበር አዝማሚያ የሥርዓታችን ዓይነተኛ ፈተና ሆኖ የቆየና ዛሬም በተጨባጭ የሚገኝ ፈተና ነው፡፡ ይህ ነባራዊ ፈተና ከመሆኑ በተጨማሪ ድርጅታችን ለረጅም ዓመታት ስልጣን ላይ የቆየ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ካልተጠነቀቅን በስተቀር በየቀኑ እየጠነከረ ሊሄድ የሚችል ፈተናም ነው፡፡ የአባላትን በተለይ ደግሞ የከፍተኛ አመራሩን አስተሳሰብና ሥነ-ምግባር በአስተማማኝ ደረጃ በመገንባት ጤናማ መሆኑን ማረጋገጥ ካልተቻለ በስልጣን ላይ ረጅም ከመቆየት ጋር ተያይዞ እየከፋ ሊሄድ የሚችል አደጋ ነው፡፡ ይህን አደጋ በንቃትና በብቃት ታግሎ ማስተካከል ካልተቻለ የተከፈለውን መስዋዕትና በዚህም የተመዘገበውን ድል መና ሊያስቀር የሚችል አደጋ ነው፡፡ ይህ አደጋ መላውን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይላችንን ያለማቋረጥ የሚፈታተን አደጋ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ ባይሆንም ሁሌም እንደምናደርገው መልሰን መላልሰን ማንሳትና ራሳችንን ያለማቋረጥ በመፈተሽ ዝንባሌውን መቅጨት ይገባናል፡፡ የህዝባችንን መብትና ጥቅሞች ያለማቋረጥ ለማስፋት የሚቻለው የመንግስት ስልጣን ያለውን የማበላሸት ችሎታ ተቋቁሞና አልፎ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪያትን በማስጠበቅ ብቻ ነውና፡፡  

3.2.     የአሰላለፍ ጥራትን ከሚያዘበራርቁ ችግሮች ራስን መጠበቅ፣
የመንግስት ስልጣን ባለቤት ከመሆን ጋር ተያይዞ በተለይ ደግሞ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪያትን ለማስጠበቅ በመቻልና ባለመቻል ጥያቄ ዙሪያ የሚከሰት ሌላም ፈተና ይገጥመናል፡፡ ይህ ፈተና በወሳኝነት የህዝብ ወገናዊነትን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ከመቻልና ካለመቻል ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ጉዳይ ነው፡፡ የመንግስት ስልጣን የያዘ ፓርቲ እንደመሆናችን መጠን ትግልና ለውጥ ፈልጎ የሚጠጋንን ብቻ ሳይሆን የመንግስት ስልጣንን ተጠግቶ መዝረፍ የሚፈለገውን ጭምር የመሳብ ዕድል አለን፡፡ ፈለግነውም አልፈለግነውም ከመንግስት ስልጣን ጋር ተጠጋግቶ ለመክበር የሚሻ ሁሉ ወደ እኛ ለመጠጋት ዕድሉን መሞከሩ አይቀርም፡፡ የምልመላ መስፈርታችን ጥብቅና በተጨባጭ ችግር ያለባቸውን የሚለይ እንዲሆን በማድረግና በማያቋርጥ ትግል ጥራታችንን እያስጠበቅን መሄድ ካልቻልን በስተቀር ከእነዚህ ወገኖች የሚመጣብን ፈተና በቀላሉ የማይታይ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ደጋግመን እንደምናነሳው ለአብዛኛው ህዝብ ያለንን ወገናዊነት የሚያላሉ ይልቁንም ደግሞ ግንኙነታችን ከጥቂት እላፊ ጥቅም ከሚሹ ወገኖች ጋር እንዲሆን የሚፈልጉ ኃይሎች ባጋጠሙንና በተሳካላቸው ቁጥር አንድም ከትምክህት አሊያም ከጠባብነት ኃይሎች ጋር የሚያሰልፈን የጎራ መደበላለቅ ችግር ይከሰታል፡፡ ይህ ችግር በሚከሰትበት ጊዜ ይዘነው የተነሳነውን የተቀደሰ ዓላማ ለድርድር እስከ ማቅረብ ሊያስገድደን ይችላል፡፡ የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ወይም ደግሞ አላግባብ የሆነ ጥቅም ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ሰልፋችንን በሚሞሉት ጊዜ የህዝብን መብትና ጥቅም የማስከበር ችሎታችን እየቀነሰ የእነዚህን የተሳሳተና አደገኛ ጥቅም ለማሳካት የሚንቀሳቀስ ወደ መሆን መሸጋገር አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ትላንት የነበረና ዛሬም ያለ ፈተና ነው፡፡ ይህ ትላንትም ሆነ ዛሬ ታግለን ስናሸንፈው የቆየን ፈተና ነው፡፡ ነገር ግን ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ የምንተውን ታጋዮች ከመሆናችን ጋር ተያይዞ ዛሬም ሆነ ነገ በተነፃፃሪ ረዘም ላለ ጊዜ የማይለየን ፈተና ነው፡፡

ይህን ፈተና ለመቋቋም የሚቻለው ያስቀመጥነውን መፍትሔ በፅናትና በማይበርድ ህዝባዊ ትግል ጠንክረን ተግባራዊ ስናደርግ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የጀመርነውን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ግንባታ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ የፖለቲካ ኢኮኖሚው ለኪራይ ሰብሳቢነት ያለውን አመቺነት ተገንዝበን ይህንኑ በማያቋርጥ ትግል መቀየር ይገባናል፡፡ የጀመርነውን የህዝቡን የማምረት አቅም የመገንባት ሥራ በፍጥነትና በጥራት ማጎልበት ይገባናል፡፡ ትምህርትና ስልጠናን የማስፋፋት ስራችን፣ የመሠረተ ልማት አውታር ግንባታችን ፣ ለአልሚዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የመስጠት ጅምራችን በተቀመጠለት ቅደም ተከተልና የጥራት ደረጃ እንዲከናወን ማድረግ ይገባናል፡፡ ከዚህ በማይተናነስ ደረጃ ለኪራይ ሰብሳቢነት አመቺ የሆኑትን መስኮች በልማታዊ ቅኝት እየታገልን ማዳከም ይገባናል፡፡ የመሬት አስተዳደርና ዕደላ ሥርዓታችንን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ባህሪ የማጠናከር፣ የግብር መደበቅ ዝንባሌን በተለይ ደግሞ ልማታዊ አስተዋፅዖ ሳይኖራቸው በግብር ማጭበርበር ከፍተኛ ጥቅም የሚያገበሰብሱ ወገኖችን በጥብቅ ተከታትሎ ግብር በማስከፍል፣ የንግድ ሥርዓታችንን ለውድድር በማጋለጥና የመንግስትን ግዥ ሥርዓት ጤናማ በማድረግ የኪራይ ሰብሳቢነትን አረንቋ ማድረቅ ይገባናል፡፡ እነዚህን በማከናወንና ከእነዚህ ተግባራት ጎን ለጎን የደርጅታችንና የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችንን የአሰላለፍ ጥራት ማጎልበት ይገባናል፡፡ በዚህ ረገድ ሊታዩ የሚችሉ መዛነፎችን ያለማቋረጥ እየተከታተልን በተለመደው ህዝባዊ ጽናታችን መታገልና ማስተካክል ይገባናል፡፡ ይህን ስናደርግ እስካሁን ያስመዘገብናቸው ድሎች በሌሎች አዳዲስና መሠረታዊ ድሎች ይጎለብታሉ፡፡ ስኬታማ ጅምሮቻችን ተጠናክረው የህዝባችን ተጠቃሚነት እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ህወሓት እንደተለመደው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ህዝባዊ ድሎችን እያስመዘገበ ይቀጥላል፡፡ 
    
3.3.     የኒዮ-ሊበራሊዝምን ተፅዕኖ መመከት፣
የምንገኝበት ዓለም ኒዮሊበራሊዝም ግዙፍና በከባድ አቅም በመታገዝ የዓለም ህዝቦችን መብትና ጥቅሞች የሚጋፋ ሥርዓት የሆነበት ነው፡፡ ይህ ሥርዓት መነሻና መድረሻው የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን ልዕልናና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም በሌሎች በርካታ አገሮች እንዳደረገው በአገራችን በኢትዮጵያም የበላይነቱን ለማረጋገጥ ይንቀሳቀሳል፡፡ ለዚህም ያግዘው ዘንድ ከርዕዮተ ዓለማዊ ዘመቻ ጀምሮ እስከ ቀለም አብዮት ድረስ ያሉ ስልቶችን በመጠቀም ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግ ይሞክራል፡፡ ኒዮ ሊበራላዊው ኃይል ተራ ግምት የማይሰጠውና የራሱን ጥቅሞች በውል የተገነዘበ ነው፡፡ በመሆኑም የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግ የሚሞክር ኃይል ነው፡፡ ምንም እንኳ ባለፉት 35 ዓመታት ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች አገሮችን ከቀውስ ወደ ቀውስ የመሩ ብቻ እንደሆኑ በይፋ የተረጋገጠ ቢሆንም ዛሬም ባለ በሌለ አቅሙ ተረባርቦ ፍላጎቱን ለማሳካት የሚሞክር ነው፡፡ ስለዚህም ባለፉት ዓመታት የደረሰበትን መጋለጥ በመመልከት ብቻ ተዝናንተው ሊገጥሙት የማይችሉና የማይገባ የጥፋት ኃይል ነው፡፡

አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ኃይላችን ይህንን እውነታ በመገንዘብ ርዕዮተ ዓለማዊና ፖለቲካዊ ብቃቱን እያጎለበተ፣ በተግባር ደግሞ ፖለሲና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ እያደረገ ለመጓዝ በመቻሉ ከኒዮሊበራሊዝም የፖሊሲ አቅጣጫዎች ውጭ በመጓዝ ፈጣን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ለውጥን በማሳካት ላይ ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ልምድ በመማርና ምንግዜም ቢሆን ከዓለም አቀፉ የገበያ አክራሪ ኃይል በኩል የሚሰነዘር ጥቃት እንደማይቀርለት በመገንዘብ ዘላቂ ድሉን ለማረጋገጥ የሚያስችል ብቃት እየገነባ መጓዝ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ ለመዘናጋት ዕድል የሚሰጥ ነገር እንደሌለ በመገንዘብ ሁሌም በተጠንቀቅ መቆምና ትግሉን ማጠናከር ይገባዋል፡፡ የኒዮ ሊበራሊዝምን አደጋዎች ተገንዝቦ ይህን የሚተካውን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አማራጭ አጥብቆ ይዞ በመታገል ያስመዘገበውን ስኬት ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ ይህ ሲሆን ያለፉት 40 ዓመታት ትግላችን ያጎናፀፈንን ድሎች በአዳዲስ ህዝባዊ ድሎች እያጎለበትን ለመሄድ እንችላለን፡፡

4.        ማጠቃለያ
ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ላለፉት 40 ዓመታት በዴሞክራሲያዊ የለውጥ ሃሳቦች ዙሪያ ተደራጅተው ያካሄዱት ትግልና የከፈሉት አኩሪ መስዋዕት በመላ አገራችን በመካሄድ ላይ ላለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ቁልፍ አስተዋፅዖ ያበረከተ ነው፡፡ ትግሉ ከጀመረበት ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ ያለው ሂደት በማያወላዳ አኳኋን የትግል መስመሩን ጥራት፣ የአደረጃጀቱን ትክክለኛነትና የተግባሩን ፍትሃዊነት ያረጋገጠ ነው፡፡ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የከፈሉት መስዋዕት ጤናማ ፍሬ ያፈራ እንጂ የመከነ እንዳልሆነ ያረጋገጠም ነው፡፡ አንድ ህዝባዊ ትግል በጠራ መስመርና አደረጃጀቶች ሲመራ የሚገኘው ውጤት በእርግጥም የብዙሃኑን ህዝብ ፍላጎት የሚያረካ እንጂ ሌላ ሊሆን እንደማይችል ያመላከተም ነው፡፡ የትላንት ታሪክ የነገን መጪ ሂደት አመላካች ከሆነም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ 40ኛ የትግል የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ ለሌሎች አዳዲስ ድሎች መታጨታቸውን ለመመስከር አያስቸግርም፡፡ ነገር ግን ፈረንጆች “ስለ መፃዒ ዕድልህ በእርገጠኛነት ልትናገር የምትችለው እራስህ ስትገነባው ነው” እንደሚሉት ነገ ሌላ ቀን ብቻ ሳይሆን ሌላ የትግል ቀን ነው፡፡ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ መቼም ተዘናግተው እንደማያውቁት በ40ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው ለሌላ አዲስ ትግልና አዲስ ድል እንደሚዘጋጁ እምነታችን የፀና ነው፡፡ 

ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት

No comments:

Post a Comment