EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 12 March 2015

በትክክለኛ መስመር ሀገራችን በለውጥ ጎዳና እንድትገሰግስ ያስቻለ ድርጅት - ኢህአዴግ



የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ኢህአዴግ የሚከተለው የርዕዮተ ዓለም አማራጭ መነሻውም መድረሻውም የሁሉንም ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ የህዝቦችን መብቶችና ጥቅሞች ማስከበር ዋነኛ አላማው ያደረገው ደርጅታችን ሀገራችን የምትመራበትን ትክክለኛ የርእዮተ ዓለም አማራጭ አስቀምጦ በመንቀሳቀሱ ለዘመናት ስር ሰደው የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ በሁሉም መስኮች ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡

ኢህአዴግ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ መነሻ ያደረገ ቁልፍ ችግሮቻችን ሊፈታ የሚችል አማራጭ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምርም ሆነ በሂደቱ የገበያ አክራሪው የኒዮ ሊበራል ሃይልና የአገር ውስጥ ተላላኪዎቹ መስመሩን ለማስቀየር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ በተለይ የደርግ ስርአት በወደቀበት ማግስት የሀገራችን ኢኮኖሚ ደቆ ባዶ ካዝና በተረከብንበት ወቅት የዓለም የገንዘብ ተቋማት ብድርና እርዳታቸውን ለማግኘት የእነሱን አማራጭ እንድንከተል በተለያየ መልኩ ጫና ቢያሳድሩብንም አርቆ የሚያልመው ኢህአዴግ ለጊዚያዊ ችግሮች ሳይንበረከክ ችግሮችን ከሀገራችን ህዝቦች ጋር በጽናት ታግሎ ማለፍ በመቻላችን የተከተለው ትክክለኛ አማራጭ ለዛሬ ስኬቶቻችን ምንጭ ሆኗል፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ኢህአዴግ ከጅምሩ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዓላማን አንግቦ የተነሳ አብዮታዊና ህዝባዊ ድርጅት ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዋነኛ ዓላማም በሀገራችን ስር ሰዶ የነበረውን ጸረ ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ አገዛዝ በህዝቡ የተደራጀና የታጠቀ አብዮታዊ ኃይል አስወግዶ በምትኩ አስተማማኝ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት ነበር፡፡ ይህ ኃያል የኢህአዴግ ህዝባዊ ዓላማ በወቅቱ ደርግን መጣል ተራራን በገመድ የመጎተት ያክል የማይቻል መስሎ የሚታይበትን ሁኔታ በመቀየር የሀገራችንን ህዝቦች ከጎኑ አሰልፎ አምባገነኑን ስርአት ሙሉ በሙሉ ለመጣል በቅቷል፡፡

ኢህአዴግ በደርግ መቃብር ላይ የተሟላ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት ባነገበው ዓላማ መሰረት ከሽግግር መንግስት ምስረታው ጀምሮ በስኬት ላይ ስኬት እያስመዘገበ ሀገራችንን ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ ወጥታ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ ስርአት በመገንባት ላይ የምትገኝ ሀገር አድርጓታል፡፡ ከሁሉም በላይ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታችን ዋስትና የሆነ በሀገራችን ህዝቦች ተሳትፎና ባለቤትነት የጸደቀው ዴሞክራሲያዊ ህገ መንግስት ነው፡፡ በህገ መንግስቱ እየተመራን ባለፉት አመታት በዴሞክራሲ፣ በልማትና በሰላም ስኬቶች እያስመዘግብን በህዳሴ ጉዞ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ስኬት የእናንተ የሀገራችን ህዝቦች የመስዋእትነታችሁ ውጤት በመሆኑ ኢህአዴግ ይኮራበታል፡፡ ኢህአዴግ እናንተው የሰጣችሁትን ኃላፊነት በታላቅ ህዝባዊ መስመርና በትክክለኛ ፖሊሲዎች እየተመራ በብቃት እየተወጣ የሚገኝ ሲሆን ለወደፊትም ይበልጥ ሊያገለግላችሁ የተዘጋጀ መሆኑን ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች፤

ማንኛውም የፖለቲካ አማራጭ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ቁልፍ የሀገርና የህዝብ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ሲሆን ብቻ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ኢህአዴግ የተከተለው አማራጭ ዋነኛ ማጠንጠኛም የሀገራችንን ቁልፍ ችግሮችን መፍታት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በደርግ ውድቀት ማግስት ያለፉት ስርአቶች ለዘመናት አከማችተዋቸው የቆዩ የሀገራችንና የህዝቦቿን ህልውና አደጋ ውስጥ ያስገቡ ችግሮች ነበሩ፡፡ የዴሞክራሲ እጦት ሀገራችንን ጦርነት ውስጥ ከቷት ጦርነቱ ደግሞ ድህነትን አባብሶ ከመበታተን አፋፍ ላይ ደርሳ ነበር። የሀገራችን ኢኮኖሚ ደቅቆ ዜጎች በከፋ ድህነት የሚማቅቁበትና በህዝቦች መካከል ጥላቻና መጠራጠር የነገሰበት፣ በብሄር ጥያቄ የተደራጁ 17 የሚደርሱ የታጠቁ ድርጅቶች በመኖራቸው ሀገራችን ልትበታተን ጫፍ የደረሰችበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም ጥያቄዎች በወቅቱ መፍትሄ የሚሹ የህልውና ጉዳይ ነበሩ፡፡  

በሌላ በኩል ወቅቱ በአለም ደረጃ የእዝ ኢኮኖሚ እንዳልሰራ የተረጋገጠበትና ብቸኛው አማራጭ የገበያ ኢኮኖሚ የሆነበት ከፓርቲ ስርዓት አንፃርም የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ አስፈላጊነት ግልጽ የሆነበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚና የመድበለ ፓርቲ መፍትሄዎች አጠቃላይ ተቀባይነት የማግኘታቸውን ያህል በዚሁ ማእቀፍ መሰረታዊ ልዩነቶች ጎልተው የወጡበት ሁኔታም ነበር፡፡ በወቅቱ በአንድ በኩል ገኖ የወጣው የኒዮ ሊበራል አማራጭ በሌላ በኩል ይህንን አማራጭ የማይቀበሉ በነጻ ገበያ ኢኮኖሚና የመድበለ ፓርቲ ማእቀፍ ውስጥ ሆነው የተለያዩ አማራጮችን የሚከተሉ ኃይሎች የርእዮተ አለም ፍልሚያ ያደርጉ ነበር፡፡

ኢህአዴግ ይህን በመሰለ ሀገራዊና አለማዊ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለሀገራችን የህልውና ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ትክክለኛ አማራጭ መከተል የግድ ይለው ነበር፡፡ እናም በነጻ ገበያ ኢኮኖሚና በመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ማእቀፍ የሚመራ ነገር ግን የሀገራችን ቁልፍ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል አማራጭ መከተል እንደሚገባው አቋም ወሰደ፡፡ የሀገራችን ቁልፍ ችግሮች ሁሉን ነገር ለገበያ ክፍት በማድረግ ሊፈቱ እንደማይችሉ በማመን በነጻ ገበያ ማእቀፍ መንግስት በተመረጠና በተቀናጀ መልኩ ጣልቃ በመግባት ቁልፍ የልማትና ዴሞክራሲ ሚናውን መወጣት የሚችልበት አቅጣጫ ተከተለ፡፡ ይሄው አማራጭ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብቶችን ያከበረ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት የግድ አስፈላጊ መሆኑንና ዴሞክራሲ በሀገራችን የህልውና ጉዳይ መሆኑን የተቀበለ አማራጭ ነው፡፡

ድርጅታችን በዚህ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር እየተመራ በተጓዘባቸው አመታት ሀገራችንን ከመበታተን ጫፍ ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለስ ፊቷን ወደ ልማትና ዘላቂ እድገት እንድታዞር አድርጓል፡፡ ይሁንና እየተመዘገበ የነበረው ውጤት ከገባንበት የድህነትና የኋላቀርነት አዙሪት በምንፈልገው ፍጥነት የሚያወጣን አልነበረም፡፡ እናም ሁልጊዜም እራሱን እየፈተሸ ከልምዶቹ እየተማረ የሚሄድ ተራማጅ ድርጅት በመሆኑ በውስጡ የነበሩ ችግሮችን በጥልቀት ገምግሞ በ1993 ተሃድሶ በማድረግ ልማታዊና ዴሞክራሲ መስመሩን አጠራ፡፡ በተሃድሷችን የስርዓቱ አደጋ የሆነው የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ እየተናደ በምትኩ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ እየተጠናከር መሄድ እንደሚገባውም ግልጽ አቋም በመያዝ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመሩን መሰረት ያደረጉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተቀርፀው መተግበር ጀመሩ፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

የኢህአዴግ መስመር ከኒዮ ሊበራል አስተሳሰብ የሚለይበት አንዱ ጉዳይ የቡድንና የግል መብቶች ሳይነጣጠሉ ሁለቱም መከበር አለባቸው በሚለው አቋሙ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ የሆነውን እውነታ በመካድ አንድ ህዝብ፣ አንድ ሃይማኖት፤ ወዘተ... በማለት የብዝሃነትን መብት በሃይል ለማፈን መሞከር ውጤቱ ምን እንደሆነ ከተሞክሯችን ተምረናል፡፡  የሀገራችን ህዝቦች በከፈሉት ከፍተኛ መስዋእትነት አሁን በርካታ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት የሚኖሩባት እና የተለየያየዩ እምነቶችና ሃይማኖቶች የሚገኙባት በብዝሃነት የደመቀች አዲሲቷን ኢትዮጵያ ገንብተዋል፡፡ የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት በህገ መንግስታችን መከበሩ በተጨባጭ የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ አንድነት እየተጠናከረ የአስተማማኝ ሰላም ባለቤት እንድንሆንና መላ አቅማችንን ለልማት እንድናውል አስችሎናል፡፡ ኢህአዴግ ብዝሃነትን በመቀበል ማስተናገድ ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መጠናከር ወሳኝ ሚና እንደሚጫዎት በጽናት ያምናል፡፡ ለዚህም ነው የግለሰብ መብትን ብቻ በማክበር የቡድን መብት ሊከበር ይችላል የሚለውን የኒዮ ሊበራል አቋም የማይቀበለው፡፡ ይልቁንም የግለሰብም ሆነ የቡድን መብቶች በተሟላ ሁኔታ ሊከበሩ የሚችሉት ሁለቱም እውቅና ሲያገኙና መከበር ሲችሉ መሆኑን ያለፉት 23 አመታት ጉዟችን አረጋግጧል፡፡

ሀገራችን ያለችበትን ሁኔታ መመልከትና ከተሞክሮ መማር የማይችሉት የሀገራችን ተቃዋሚዎች ግን በአንድ በኩል የብሔሮችና ብሔረሰቦች መብት መከበሩ ይበታትነናል እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ በህገ መንግስቱ የተቀመጡ የቡድን መብቶች በአግባቡ ስራ ላይ አልዋሉም የሚል መሰረተ ቢስ ክስ በማንሳት የኪራይ ሰብሳቢነት ፍላጎታቸው ጥቅም ላይ ለማዋል ሲጣጣሩ ይታያሉ፡፡ 

የድርጅታችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አማራጭ ከኒዮ ሊበራል አማራጭ የሚለየው ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ መንግስት በልማት ላይ ያለን ሚና በተመለከተ ነው፡፡ የኒዮ ሊበራል አቋም የገበያ ክፍተት መሞላት ያለበት በገበያው እንደሆነና  የመንግስት ሚና ህግና ጸጥታ በማስከበር ላይ መታጠር አለበት የሚል ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደ ሀገራችን ባሉ ጠንካራ የግል ባለሃብት ባልተፈጠረበትና ከፍተኛ የልማት ክፍተት ባለባቸው ሀገሮች በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ መንግስት በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ መግባት እንዳለበት ያምናል፡፡ በተለይ በግል ባለሃብቱ በማይሸፈኑና  በመንግስት ቢያዙ ልማቱን በማፋጠን ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል በሚባሉ ዘርፎች መንግስት መሳተፍ ካልቻለ ልማት እንደማይረጋገጥ ይገነዘባል፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የሚያሳየውም በልማታዊ መንግስት አማራጭ በመመራት ልማትን የሞት ሽረት አድርገው የያዙ የእስያ ሀገሮች ፈጣንና ተከታታይ እድገት ሲያስመዘግቡ ሁሉንም ክፍተት ለገበያውና የግል ባለሀብቱ የለቀቁ የኒዮሊበራል አስተሳሰብ ተከታይ የአፍሪካና የሌሎች አህጉራት ሀገሮች ልማት ማረጋገጥ እንዳልቻሉ ነው፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ኢህአዴግ የልማታዊና ዴሞክራሲዊ መስመርን ተመራጭ ያደረገው እንደ ፖለቲካ ድርጅት የመቆም መነሻውም መድረሻውም የህዝብን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለሆነ ነው፡፡ የኢህአዴግ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ለ12 አመታት ፈጣንና ተከታታይ ልማት እንድናስመዘገብ፣ አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግ ተጨባጭ ስኬቶች ተመዝግበውበታል፡፡ በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ልማት ያለ ዴሞክራሲ እንዲሁም ዴሞክራሲ ያለ ልማት መረጋገጥ እንደማይችል በማመን ልማትና ዴሞክራሲን አጣምረን መተግበራችን ህዝባችንን በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ አብቅቶናል፡፡

ህዝቡ በጥረቱ ልክ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ በቀጣይ ለውጥና ዕድገት ምህዋር ውስጥ እንዲገባ የሚያስችል መስመር የቀረፀውም መስመሩ ህዝባችንን በልማቱም ሆነ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር በተደራጀ መልኩ ዋና ተዋናይ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ስለሆነ ነው፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ኢህአዴግ የቀረጸው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ዛሬ ባስመዘግብናቸው ስኬቶቻችን ረክተን እጃችን አጣጥፈን እንድንቀመጥ የሚያደርግ ሳይሆን ይልቁንም ሀገራችንን ከበለጸጉት ሀገራት ለማሰለፍ የሚያስችል የሀገራችን ህዳሴ የማረጋገጥ ግብ ያለው ለቀጣይ ስኬቶችና ድሎች እንድንተጋ የሚያደርግ ኃያል መስመር ነው፡፡ በመስመራችን አማካኝነት በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገባችን እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ልንፈታቸውና ልናርማቸው የሚገቡ እጥረቶች እንዳሉም ኢህአዴግ ይገነዘባል፡፡ የጀመርንው ድህነትን ድል የመንሳት ትግል፣ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የመገንባት ትግል፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በመናድ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲተካ የማድረግ ትግል አሁንም በሀገራችን ህዝቦች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትቨኢህአዴግ በጽናት ያምናል፡፡

በአንጻሩ ሁልጊዜም የኢህአዴግን የልማታዊና ዴሞክራሲዊ አማራጭ የማብጠልጠልና ስኬቶችን ጥላሸት መቀባት ላይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱት የሀገራችን ተቃዋሚዎች አሁንም በሀገራችን እየተመዘገበ ያለው እድገትና ለውጥ ማየት ተስኗቸው ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡ ይህ ነው የሚባል ለሀገርና ለህዝብ የሚበጅ አማራጭ ማቅረብ ያልቻሉት ተቃዋሚዎች አሁንም የሀገራችን ቁልፍ ችግሮች በመፍታት ላይ የሚገኘውን የኢህአዴግ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ይዘቱን እንኳ በአግባቡ ሳይረዱት የተለያዬ ስያሜ በመለጠፍ በምርጫ ቅስቃሳቸውና በአገኙት አጋጣሚ ለማደናገር ይሞክራሉ፡፡ ስኬቶቹ ደምቀው የሚታዩትን የልማታዊና ዴሞክራሲያው መስመራችንን በማውገዝ በዓለም ደረጃ የፋይናስ ችግር እያስከተለ የሚገኘውን የኒዮ ሊበራል አማራጭ ለሀገራችን መፍትሄ እንደሆነ ሊነግሩን ይሞክራሉ፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግ የሀገራቸን ተቃዋሚዎች የተጀመረውን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስቀጠል ብቃት የላቸውም የሚለው፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

የምንከተለው አማራጭ ተጨባጭ ስኬቶችን በማስመዝገብ የሀገራችን ህዳሴ በማይቀለበስ መልኩ መጀመሩን ያበሰረ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ነው፡፡ ድርጅታችን ኢህአዴግም በዚህ የጠራ የልማትና ዴሞክራሲያዊ መስመር እየተመራ የሰጣችሁትን ኃላፊነት በብቃት እየተወጣ ያለ ስኬታማ ድርጅት ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግን መምረጥ የተጀመረውን ፈጣን ልማት፣ አስተማማኝ ሰላምና ዴሞክራሲ ማስቀጠል ነው የምንለው፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግን መምረጥ ህዳሴን ማስቀጠል ነው የምንለው፡፡

የሀገራችን ህዳሴ ጉዞ ያስጀመረ የጠራ የልማትና ዴሞክራሲያዊ መስመር ባለቤት የሆነውን ኢህአዴግን ይምረጡ!!   

ኢሕአዴግ የሚያስተላልፋቸውን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶች ከጋዜጣ፤ ከቴሌቪዥንና ሬዲዮ በተጨማሪ በድረ ገፃችን  www.eprdf.org.et እንዲሁም በፌስቡክ ገፃችን EPRDF official ማግኘት ይችላሉ፡፡

ከኢህአዴግ ጋር አሁንም መጭው ጊዜ ብሩህ ነው!!

No comments:

Post a Comment