EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Sunday, 18 January 2015

የህዝብ ወሳኝነት ለህዳሴያችን

(በፈድሉ ጀማል)
ድርጅታችን ኢህአዴግ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ከህዝብ ኃያልነት ወይም ወሳኝነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ለመሆኑ አያሌ አብነቶችን በመጥቀስ ማሳየት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ አምባገነኑን ስርዓት ለማስወገድ የትጥቅ ትግል የጀመረው በህዝብ ጥያቄ መነሻነት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የትግሉ ሂደትም ህዝቡን በሚገባ ያሳተፈ ስለነበር “በአፍሪካ ወደር የማይገኝለት” የተባለውን ሰራዊት የገነባውን የደርግ ስርዓት ማስወገድ ችሏል፡፡
ከትጥቅ ትግሉ በኋላም ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓት እንዲቋቋም የሚያስችል ህገ መንግስት ለማፅደቅ በተደረገው ሰፊ ትግል አማራጭ አለን የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ አማራጫቸውን ለህዝብ እንዲያቀርቡ ጥሪ በማድረግ እና በረቂቅ ህገ መንግስቱ ላይ በየደረጃው በተደረጉ ውይይቶች ህዝቡን በሰፊው በማሳተፍ የማሻሻያ ሃሳብ እንዲያቀርብ ማስቻሉም ኢሕአዴግ ለህዝብ ወሳኝነት ያለው ፅኑ እምነት መገለጫ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ በፀደቀበት ወቅትም የሀገራችንን ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት በሀገራቸው እጣ ፈንታ ላይ ወሳኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገው እስካሁን በተካሄዱ አራት ሀገራዊና ሌሎች በርካታ ምርጫዎች ህዝቡ በንቃት በመሳተፍ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ይበጀኛል ያለውን አካል መምረጥ መቻሉም ድርጅታችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የሕዝቡን ሉዓላዊነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲፈፀም ካለው ቁርጠኝነትና ከሰጠው ብቃት ያለው አመራር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ባለፉት ሀገራዊ ምርጫዎች የምርጫ ካርድ በመውሰድና በመምረጥ ረገድ የህዝቡ ተሳትፎ መጨመሩ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሃቅ ነው፡፡
በሀገሪቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይም እንዲሁ ከእቅድ ማውጣት እስከ ትግበራ ባሉት ሂደቶች የህዝቡ ተሳትፎ ተኪ አልነበረውም፡፡ ኢሕአዴግና በሱ የሚመራው መንግስት ማንኛውንም እቅድ ከመተግበራቸው በፊት ከየአካባቢው ህዝብ ጋር የሚመክሩትም ምንም ያህል ጠቃሚ እንኳን ቢሆን ህዝብ ያላመነበትና ተሳትፎ ያላደረገበት ሀገራዊ ፕሮጀክት እውን እንደማይሆን በተግባር ስለሚያዉቁት ነው፡፡ ሕዝቡ አምኖ በወሰነባቸው የልማት እንቅስቃሴዎች በሚሊዮኖች ተምሞ በመውጣት ለሌሎች ተዓምር የሚመስሉ ስራዎችን የፈፀመውም በዚሁ የህዝብ ሃያልነትና ወሳኝነት ላይ ባለን ፅኑ እምነት ተገዝተን በመንቀሳቀሳችን ነው፡፡
ኢህአዴግ ህዝቡን በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሳተፍ እያደረገ የሚገኘው ለይስሙላ ሳይሆን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አንዱ መገለጫ የህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በመሆኑ ነው፡፡ በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ ከዚህም በተጨማሪ ዋንኛው አቅማችን የህዝባችን ጉልበትና እውቀት ስለሆነ ነው፡፡ ባለፉት ስርዓቶች ሳይደፈር የኖረውን የአባይ ወንዝ ለማልማት ወስነን በአፍሪካ ትልቁን የሃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባን ያለንው በዚሁ የህዝባችን አቅም ላይ ስለተማመንን ነው፡፡
ህዝቡ በተለያዩ መስኮች እያደረገው ያለው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሄዱ ለሀገራችን የህዳሴ ጉዞ ዋስትና የሚሰጥ ነው፡፡ የህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እየተጠናከር በሄደ መጠን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመራችን በማይናወጥ መሰረት ላይ ይገነባል፡፡ በድምር ሲታይ ሀገራችን ባለፉት 23 ዓመታት የተጓችበት የለውጥ ሂደት ይህን የህዝብን ወሳኝነትና ሃያልነት ያረጋገጠ እና ለህዳሴ ጉዟችን ስኬት ምቹ መደላድል የፈጠረ ነው፡፡
በዚህ አመት የሚካሄደው አምስተኛው አጠቃላይ ምርጫ በህዝቡ የነቃ ተሳትፎ ታጅቦ መዝለቁ ከላይ ለገለፅነው ሀሳብ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የመራጮች ምዝገባ ከተጀመረ ገና በሳምንቱ የተመዘገበው ህዝብ ይመዘገባል ተብሎ ከሚጠበቀው 35 ሚሊዮን ህዝብ ከግማሽ በላይ መድረስ ችሏል፡፡ ይህ የሚያሳየው ህዝቡ በልማቱ እንዳደረገው ሁሉ ሀገራችን በምትገነባው የዴሞክራሲ ስርዓትም ባለቤት ሆኖ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ነው፡፡
ስለሆነም የምርጫው ባለቤቶችና ባለድርሻ አካል የሆንን በሙሉ በምናደርገው የምርጫ ተሳትፎ ይህን የህዝቡን የባለቤትነትና ወሳኝነት መንፈስ አክብረን ልንንቀሳቀስ ይገባናል፡፡

No comments:

Post a Comment