EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Wednesday, 7 January 2015

በአንፀባራቂ ድሎች የታጀበው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን


በፈድሉ ጀማል

ከድርጅታዊ ተሃድሷችን በኋላ በጠራ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ላይ የገነባንው የውጪ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂያችን ከማንኛውም ሀገር ወይም ሀገራት ስብስብ ጋር የሚኖረን ግንኙነት መሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችንና ደህንነታችንን የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበት አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ግንኙነቱ የልማትና ዴሞክራሲ አላማና ግቦችለማሳካት በሚያስችል መልኩ መፈፀም እንዳለበት ግልፅ ነው፡፡ ከሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ስናነሳ በቅድሚያ ጎረቤታችን ከሆኑት ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ጋር ያለን ግንኙነት የሚታይ ይሆናል፡፡

በፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ እንደተገለፀው ሀገራቱ በጥቅሉ ሲታዩ ከረጅም ጊዜ አኳያ አካባቢው ሲለማ ሰፊ የንግድ እድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ቢሆንም ከአጭርና መካከለኛ ጊዜ አኳያ በልማታችን ላይ ያላቸው በጎም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ውስንና በዋናነት ከወደብ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በተመሳሳይ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ የሚያበረክቱት በጎ አስተዋፅኦ ውስን ቢሆንም ከሀገራቱ ጋር የሚኖረን አሉታዊ ግንኙነት ግን የሃይማኖት አክራሪነትንና ጠባብ ብሔርተኝነትን በመጠቀም ሰላማችንንና የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችንን በማወክ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡

ስለሆነም የልማትና የዴሞክራሲ አጀንዳችን መሳካት ሀገራችን በአካባቢው ካላት ቦታ አኳያ ሲታይ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጎረቤቶቻችን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን እነርሱም ተገንዝበው የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት በሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲያተኩሩ የማድረግ ተልዕኮን መወጣት ይኖርብናል፡፡ ሀገራችን ለረጅም ጊዜ ሰላም በራቀው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን አለመረጋጋት ለማስወገድ በኢጋድ ማዕቀፍና ከሀገራቱ ጋር ባለን የሁለትዮሽ ግንኙነት አማካኝነት ባደረገችው እንቅስቃሴ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የመሪነት ሚና እየተጫወተች ያለችውም ለዚሁ ነው፡፡

በሶማሊያ ውስጥ የተፈጠረውን መንግስት አልባነት ተጠቅመው አሸባሪዎች በሀገራችን ላይ የፈጠሩትን ስጋት ለማስወገድ ካደረግነው ስኬታማ እንቅስቃሴ ጎን ለጎንና ባሻገር በሶማሊያ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ መንግስት እንዲመሰረት ለዚህም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገቢ ትኩረት እንዲሰጥ ሀገራችን በኢጋድና በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ጭምር ሰፊ ጥረት አድርጋለች፡፡

በውጤቱም ሀገራችን የምታካሄደውን የዴሞክራሲና የልማት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍና የቀጠናውን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሰውን አለም አቀፍ አሸባሪ እንቅስቃሴ ለመግታት የቻልን ሲሆን በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ደረጃ በደረጃ ሰፍኖ አለም አቀፍ እውቅና ያለው መንግስት ለመቋቋም በቅቷል፡፡ ይህ የሀገራችን ጥረትና ስኬታ በሶማሊያ ህዝብ በበጎ የሚታይ ነው፡፡ በአለም አቀፉ ማህበረሰብም እውቅና ተሰጥቷታል፡፡

ሱዳንን በተመለከተ በአባይ ጉዳይ ላይ ሀገራችን ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት የቆመች መሆኗን በተደጋጋሚ በማሳየቷ ሱዳንም በዚህ መርህ ተጠቃሚ መሆኗን በመረዳት መሰረታዊ መተማመን ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ሱዳን ሌላኛወዋ የታችኛው ተፋሰስ ሀገር ግብፅ ተመሳሳይ አቋም እንድትወስድ ጠንከር ያለ መልዕክት ከማስተላለፍ አልፋ የግንባታ ማሽነሪ ድጋፍ አበርክታለች፡፡ በቅርቡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የግድቡን ግንባታ በአካል ተገኝተው መጎብኘታቸውም በድል መስመር ላይ እየተጓዘ ላለው ዲፕሎማሲያችን ሌላኛው የላቀ ስኬት ነው፡፡ ከሱዳን ጋር ያለን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተሻለ ሁኔታ የተጠናከረ ሲሆን በመሰረተ ልማት ግንባታ በተለይ በመንገድና በኤሌክትሪክ ኃይል ከሀገራችን ጋር የማስተሳሰር ስራ እንዲሁም የንግድና የቱሪዝም እንቅስቃሴ በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ 

በሁለቱ ሱዳኖች መካከል 20 ዓመታት የተካሄደው ጦርነት ጦሱ ለሀገራችንም ስለሚተርፍ ለሀገራቱ ሰላም አበክረን የምንሰራበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙና ጦርነቱ እንዲቆም እንዲሁም የደቡብ ሱዳን ህዝብ ህዝበ ውሳኔ አካሄዶ የራሱን መንግስት እንዲመሰርት ሀገራችን የበኩሏን ጥረት አድርጋለች፡፡ በመካከላቸው ያለው ግጭት እንዲቆምና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሀገራችን ፍላጎት መሆኑን የተገነዘቡት ሁለቱም መንግስታት በእኛ ላይ እምነት በማሳደራቸው በአደራዳሪነትም በሰላም አስከባሪነትም ከአለም ማህበረሰብ ጋር በመሆን እንድንሰራ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን እራሷን ችላ እንደሀገር ከተቋቋመች በኋላም ከሀገሪቱ ጋር መልካም የሚባል ሁሉን አቀፍ ግንኙነት መፍጠር የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰውን የእርስ በርስ ግጭት በዘላቂነት እንዲፈታ ሀገራችን በግንባር ቀደምትነት እየሰራች ትገኛለች፡፡  

ከጅቡቲ ጋር በተያያዘ የሀገራችንና የጅቡቲ ግንኙነት በጉርብትና ብቻ ሳይወሰን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በጋራ ደህንነት መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመሄድ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ሁለቱ ሀገራት በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር ችለዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል በኤሌክትሪክ፣ በፋይበር ኦፕቲክስ፣ በባቡር መስመርና በወደብ ግንባታ ያለውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ ከጅቡቲ ጋር በፈጠርንው የሁለትዮሽ ግንኙነት በአካባቢ ጉዳዮች ላይ በተለይም በሶማሊያና በኤርትራ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት መቻላችን በመካከላችን ያለው መተማመን መጎልበቱን የሚያሳይ ነው፡፡

በተመሳሳይ ሀገራችን ከኬንያ ጋር ያላት ግንኙነት በጥንካሬ የሚወሰድ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና በአካባቢያዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የጋራ ጠቀሜታ ባላቸው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችን ላይ ተግባራዊ በሚደረጉ የልማት ስራዎች ዙሪያ ተግባብቶ የመሄድ ልምድን መፍጠር ችለዋል፡፡

ሀገራችን ባልተረጋጋው የአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ መሆኗ በራሱ ለውስጣዊ ሰላማችንና ለምናካሄደው የልማትና የዴሞክራሲ እቅስቃሴ አሉታዊ ሚናው እንደተጠበቀ ሆኖ አካባቢውን ለማመስ በዋናነት እየጣረ ከሚገኘው የሻዕቢያ መንግስት ጋር በጉርብትና መገኘታችን ተፅዕኖው የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ለሀገራችንና ለአካባቢው ሰላም ጠንቅ የሆነው የኤርትራ መንግስት ከአካባቢው ሀገሮችና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲነጠልና የትንኮሳ አቅሙ እንዲዳከም ማድረጋችን ጦርነትን በርቀት የመግታት አላማ ያለው የውጭ ግንኙነትና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን ሌላው ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የኤርትራ መንግስት ከአፍራሽ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ለማድረግ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ለጣለው ማዕቀብ መነሻ የሆነ ውሳኔ በኢጋድ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኝ እንዲሁም ውሳኔው በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እንዲፀድቅ ለማድረግ ሀገራችን ውጤታማ የሆነ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ችላለች፡፡ በሌላ በኩል አሁንም ከኤርትራ መንግስትም ጋርም ቢሆን የሰላም ሃሳባችንን አጥብቀን ይዘን ችግሩን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፍታት እንደሚቻል የኤርትራ መንግስት እንዲቀበል ተፅዕኖ ማድረጋችንን ቀጥለንበታል፡፡

የገዥው ሃይል ፀረ ህዝብ ተግባሮች እንዳሉ ሆነው ከኤርትራ ህዝብ ጋር ያለን ግንኙነት እንዳይሻክር ያከናወንናቸው ተግባሮች ከኢሕአዴግ ህዝባዊነት የሚመነጩ ናቸው፡፡ እየተከተልን በምንገኘው ትክክለኛ ፖሊሲያችን ሳቢያ የኤርትራ ህዝብ የነበረውን ጥርጣሬ በመቅረፍ ከኤርትራ መንግስት እየሸሸ ወደ ሀገራችን ለመጠለል በሺዎች የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ችለናል፡፡ ከሀገራቸው ተሰደው ለመጡ ኤርትራዊያን የትምህርት እድል ከመስጠት ጀምሮ ሀገራችን እያደረገች ያለው መልካም አቀባበል የዚሁ ማሳያ ነው፡፡

ምንም እንኳን በድንበር የምትጎራበተን ባትሆንም በአባይ ወንዝ የተነሳ ከምትተሳሰረን ግብፅ ጋር ለሚኖረን ግንኙነትም ልዩ ትኩረት የሰጠ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ያለን ነን፡፡ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ሀገሪቱ በነበራት -ፍትሃዊ አቋም ሳቢያ የነበረን ታሪካዊ ግንኙነት ውጥረት የበዛበት እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ ሀገራችን በአባይ ወንዝ ላይ የራሷንና የሌሎችን የተፋሰሱን ሀገራት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለረጅም ጊዜ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ ኢህአዴግ ተግባራዊ ባደረገው የተሃድሶ መስመር በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በአባይ ጉዳይ የላይኛውን የተፋሰስ ሀገሮች በአንድ አቋም ስር ለማሰባሰብ ችለናል፡፡ ይህ ሊሳካ የቻለው አባይን በጋራ በማልማት በጋራ የመጠቀም ፍትሃዊ እሳቤን በግንባር ቀደምነት በማራመድ ሌሎቹም እንዲከተሉት ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ በማከናወናችን ነው፡፡

በዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በአባይ ወንዝ ላይ ያለውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ዘመቻ ጎን ለጎን ሀገራችን ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ በመቻሏ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአባይ ላይ በራሳችን አቅም ታላቁን የህዳሴ ግድብ በመገንባት ላይ እንገኛለን፡፡ በግብፅ በኩልም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሀገራችን ጋር በአባይ ጉዳይ የተሻለ መቀራረብ እየታየ ሲሆን የተለያዩ ውይይቶችን ማድረግ ተጀምሯል፡፡ ሀገራችን የምትገነባውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ በተመለከተ ሁለቱም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የተካተቱበት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ በመግባቱ ሀገራችን አባይን በተመለከተ ያላትን ግልፅ አቋም ግብፅ በመጠኑም ቢሆን መረዳት ችላለች፡፡

ይህንን እንደመነሻ በመጠቀም በቅርቡ በግብፅ ጉብኝት ያደረገው የሀገራችን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን አንድ እርምጃ የሚያራምድ ተልዕኮውን ፈፅሞ ተመልሷል፡፡ በዚህም ምክንያት ግንኙነቱ ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከአባይ ውጪ ሁለታችንም  በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በአቅም ግንባታ ረገድ ተባብረን ለመስራት ተስማምተን እንቅስቃሴዎች መጀመራችን የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን አመላካች ነው፡፡

በጠራ መስመር ላይ ከተገነባው ፖሊሲያችን የሚመነጩት ተግባሮች ያስገኙልን ስኬት በሀገር ውስጥ ለምናደርገው የልማት፤ የዴሞክራሲና ሰላም ስርዓት ግንባታ አስተማማኝ የድጋፍ ሃይል ሆነውናል፡፡ ከራሳችን አልፈን የጎረቤቶቻችንን ሰላም የምንጠብቅ፤ ከራሳችን አልፈን ከጎረቤቶቻችን ጋር በመሰረተ ልማት የምንተሳሰር ለመሆን የበቃነው ከተሃድሷችን ማግስት ለቀረፅነው ሀገራዊ ፖሊሲ ታማኝ ሆነን በመዝለቃችን ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ በአንፀባራቂ ድሎች የታጀበው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ጎረቤቶቻችንን በጥርጣሬ ከማየትና የእነሱን እድገት በስጋት ከመመልከት ተላቀን በጋራ እንድንለማ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment