(በአሜሳይ ከነዓን)
እለቱ
እሮብ ጥር 13 ቀን 2007 ነው፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበር በሸራተን አዲስ
አንድ ትልቅ አገራዊ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ ኢህአዴግና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንቦት ወር የሚካሄደው ምርጫ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና
ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መጫወት ስለሚገባቸው ሚና ለመወያየት ተገኝተዋል፡፡
የመላው
ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን /ኢዴፓ/ በመወከል ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ መድረክን በመወከል አቶ ጥላሁን እንዳሻው፣ ኢህአዴግን በመወከል
ጓድ ደስታ ተስፋው እንዲሁም ከምርጫ ቦርድ አቶ ነጋ ዱፊሳ የውይይት መነሻ ነጥቦች እንዲያቀርቡ መድረክ ላይ ተሰይመዋል። ከፋና
ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አቶ ብሩክ ከበደ ውይይቱን ይመራሉ።
የኢትዮዽያ
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ፀሃፊ እና የቦርዱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ የመምረጥና የመመረጥ መብት በኢትዮጵያ ብሄሮች፤
ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይሁንታና ባለቤትነት ስር ከመሆኑ በፊት በየአካባቢው በባህላዊ መንገድ ምርጫዎች ይካሄዱ እንደነበር አስታውሰው
በአገራችን የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ ዴሞክራሲያዊ መብት ህገ መንግስታዊ ዋስትና አግኝቶ መተግበር ከጀመረ ወዲህ የህዝቡ ተሳትፎ
በቀጣይነት እያደገ መምጣቱን በማስረጃ አስደግፈው አብራርተዋል፡፡
በምርጫ
ቦርድ ህጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ከ70 በላይ እንደሆኑ ይታወቃል። አቶ ነጋ በገለፃቸው ታዲያ በአንዳንድ የተቃዋሚ
ፖለቲካ ፓርቲዎች ለራሳቸው የውስጥ አሰራርና ደንብ ተገዥ ያለመሆን የተነሳ በቦርዱ ስራ ላይ አሉታዊ ጫና እንደተፈጠረ አመላክተዋል፡፡
ኃላፊው ተግዳሮት ብለው ካቀረቧቸው ማሳያዎች መካከል ፓርቲዎች ደንቦችን ሲያሻሽሉ ለቦርዱ አለማሳወቅ፣ ህገ ወጥ ማህተም በማስቀረፅ
ያለቦርዱ እውቅና መጠቀም፣ ቦርዱ በሚጠራቸው ስብሰባዎች ላይ አላግባብ በሆነ መልኩ እና ስብሰባውን በሚያውክ ሁኔታ መድረክ ረግጦ
በመውጣት ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንገድን መከተልና የቦርዱን ስም በሐሰት ማጥፋትና በጥቅሉ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደቱ
እንቅፋት የሚፈጥሩ ፓርቲዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በምርጫ
ቦርድ በኩል የቀረበውን የውይይት ሰነድ ተከትሎ ኢዴፓ የራሱን የውይይት መነሻ ሐሳቦች በፓርቲው ፕሬዝዳንት በዶ/ር ጫኔ ከበደ አማካኝነት
አቅርቧል፡፡ አራቱን ምርጫዎችና የፓርቲዎችን ተሳትፎ በተመለከተው ፅሁፉቸው ኢህአዴግ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ምርጫዎች ራሱ ተወዳድሮ
ራሱ ያሸነፈ ፓርቲ ነው ሲሉ ገልፀዋል የፓርቲው ፕሬዝዳንት፡፡ እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ መረጃዎች የሚያመለክቱት ከ1987 ጀምሮ
በተካሄዱት አራቱም ምርጫዎች በሁሉም ክልሎች ለህዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት መቀመጫ የግል ተወዳዳሪን ጨምሮ የተፎካከሩ ፓርቲዎች
እንዳሉ ነው፡፡
በ1987ዓ.ም
ምርጫ 57 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወዳደሩ ሲሆን 43 ፓርቲዎች የፓርላማ መቀመጫ አግኝተው ነበር። በተመሳሳይ በ1992ዓ.ም ምርጫም
ከተወዳደሩት 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 42 የሚሆኑት የፓርላማ መቀመጫ ያገኙበት ሁኔታ ነበር። ዶ/ር ጫኔ በ1997 ምርጫ
በርካታ ተቃዋሚዎች በምርጫ መሳተፋቸውንና አሸናፊ እንደነበሩም አብራርተዋል። እዚህ ላይ በዚህ ምርጫ ከተወዳደሩ 35 ፓርቲዎች
29ኙ የፓርላማ መቀመጫ አግኝተው እንደነበርም ማስታወስ ተገቢ ይሆናል። በመሆኑም የፓርቲው ፕሬዝዳንት ድምዳሜ ከመረጃ የራቀ እንደሆነ
ማየት ይቻላል፡፡
እንደ
ዶ/ር ጫኔ አባባል በ2002 ምርጫ ኢህአዴግ ሁሉንም መቀመጫዎች በመያዙ የምርጫው የዴሞክራሲ ጉዞ ወደ ኋላ ተመልሷል፡፡ በአገራችን
ህዝቡ በነቂስ እየወጣ የመሰለውንና ይመራኛል ብሎ ያሰበውን ፓርቲ በሚዛናዊነት የመረጠበትን የምርጫ ሂደትና ውጤት ያለመቀበል በሚመስል
ሁኔታ ‹‹ምርጫው በቅርፅ እንጂ በይዘት ዴሞክራሲያዊ አልነበረም›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ የህዝቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ
የመጣበትን እውነታ እንኳን ደፍረው ሊቀበሉት አልፈለጉም።
ኢዴፓ
የዘንድሮው 5ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መሰራት ያለበት በሚል ሃሳቦችንም አቅርቧል፡፡ በተለይ የምርጫ
ስነ ምግባር ደንቡ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከማድረግ ባሻገር ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የጎላ ጥቅም እንዳለው ኢዴፓ
እንደሚያምን ዶ/ር ጫኔ አስቀምጠዋል፡፡ የስነ ምግባር ደንቡ አስፈላጊነት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም በማለትም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከመራጩ
ህዝብ፣ ከመንግስትና ከተወዳዳሪ ፓርቲዎች እንዲሁም እንደ ሲቪክ ማህበራትና መገናኛ ብዙሃን ካሉ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቀውን ሚና
በዝርዝር በማስቀመጥ ሁሉም በእኩልነትና በሚዛናዊነት መርህ መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ
በአገራችን ህዝቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንጂ በዲያስፖራ የሚመራ ከሆነ ጤናማ ሊሆን እንደማይችልም አብራርተዋል፡፡
በቀጣይነት
የውይይት ፅሁፉን መድረክ ያቀረበ ሲሆን በአገራችን የነበረውን ያለፉት ዘመናት የምርጫ ሁኔታ በመነሻነት አቅርቧል፡፡ በመድረክ በኩል
ፅሁፉን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጥላሁን እንዳሻው ያቀረቡ ሲሆን የዴሞክሲያዊ ምርጫ መገለጫ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን
ንድፈ ሃሳቦች በማንሳት የአገራችንን የምርጫ ሁኔታ በንፅፅር አቅርበዋል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባህሪያትን ከዘረዘሩ በኋላ በአብዮታዊ
ዴሞክራሲም ሆኖ በሶሻሊዝም ማዕቀፍ የሚካሄድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ አይደለም የሚል ድምዳሜያቸውን አሰምተዋል፡፡
ለዘንድሮው
ምርጫ ካርድ ማውጣት ላይ ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ቢሳተፍም እንኳን አማራጭ በሌለበት የሚካሄድ በመሆኑ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም
በማለትም ዴሞክራሲና የህዝብ ፍላጎት እንደማይገናኙ ተንትነዋል። በመሆኑም ህዝቡ የመራጭነት ካርድ ለማውጣት እያደረገ ያለውን የነቃ
ተሳትፎ አጣጥለውታል። ይህ ንግግራቸው ፓርቲያቸው አማራጭ ሆኖ መቅረብ እንዳልቻለ የሚገልፅ መሆኑን ልብ አላሉትም፡፡ በርግጥ መድረክ
የተለያዩ የፖለቲካ ፍልስፍናዎችንና ርዕዮተ አለሞችን የሚከተሉ አባል ፓርቲዎች ስብስብ መሆኑና የፓርቲው አመራሮች በተለያዩ ጊዜያት
በሰጡት መግለጫ ከምርጫው በኋላ ወጥ መስመር እንደሚከተሉ ከገለፁት ጋር ሲዳመር ፓርቲው አማራጭ መስመር እንደሌለው አመልካች ነው፡፡
መድረክ
ከዚህ በፊት በተለያዩ የህትመት ሚዲያዎች ሲያንፀባርቀው እንደነበረው በዚህ የውይይት መድረክ ላይም ሚዲያውና ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ
ባልሆኑበት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ አይሆንም ሲል ጨለምተኛ አስተያየት ሰንዝሯል፡፡ አቶ ጥላሁን ‹‹የፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብ
አለም አቀፍ ተቀባይነት ካለው የምርጫ ደንብ ቃል በቃል የተተረጎመ ነው የሚባለውም ሃሰት ነው›› ካሉ በኋላ ደንቡ የውጭ ታዛቢዎችን
ሁኔታና የምርጫ አስተዳደር ጉዳዮችን የሚመለከተው ክፍል ሳያካትት መውጣቱን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡
አቶ ጥላሁን
እንደሻው ከኢሕአዴግ ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር የሚቻልበት መድረክ እንደሌለም አንስተዋል፡፡ የስነ ምግባር ደንቡ እንዳይፀድቅ
መድረክ ሶስት ጊዜ መድረክ ረግጦ መውጣቱንና በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገብቶ በውይይቶቹ ለመሳተፍ አሻፈረኝ ማለቱን ግን
ሊጠቅሱ አልፈለጉም፡፡ መድረክ የጋራ ምክር ቤት አባል መሆን ያልፈለገው እንደ ፓርቲና በአባላት ደረጃ በስነ ምግባር ለመገዛት ስለማይፈለግ
መሆኑን ህዝቡ የሚገነዘበው እውነታ ነው።
በአራተኛ
ደረጃ የውይይት ፅሁፍ ያቀረበው ኢህአዴግ ሲሆን ፅሁፉ በኢህአዴግ የህዝብና ውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ጓድ ደስታ ተስፋው ቀርቧል፡፡
ጓድ ደስታ የመንግስት ስልጣን በህዝብ ውሳኔ ብቻ የሚያዝበትና መድብለ ፓርቲ እውን የሆነበት ስርዓት መኖር የዴሞክራሲያዊ ስርዓት
ዋና መገለጫዎች መሆናቸውን አብራርተዋል። ከፓርቲዎች አንፃርም ፓርቲዎች የውስጥ ዴሞክራሲ ባህልና የተዘረዘረ አማራጭ ፖሊሲ ሊኖራቸው
ይገባል ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው የሚል እምነት እንዳለው በመግለፅ ፓርቲዎችም ለህዝቡ ውሳኔ ተገዥ ሊሆኑ
እንደሚገባ አስገንዝበዋል ጓድ ደስታ ተስፋው፡፡
የዴሞክራሲ
ባህል ያለመዳበር፣ ህገ መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልግ ኃይል መኖር፣ ለህዝብ ውሳኔ ያለመገዛት፤ የራስን የውስጥ
ችግር በሚገባ አይቶ ውስጣዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ውጫዊ ሽፋን መስጠትና ህጋዊና ህገ ወጥነትን እያጣቀሱ የሚሄዱ ፓርቲዎች መኖር
ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ተግዳሮት እንደሆኑም አስቀምጠዋል፡፡
የመድረኩ
መሪ የስነ ምግባር ደንቡን አስመልክቶ ያንፀባረቁት ሃሳብም ተገቢ እንዳልሆነ አብራርተዋል፡፡ የስነ ምግባር ህጉ በተጨባጭም አለም
አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነ ተናግረው የመድረክ ተወካይ ያነሷቸው ጉዳዮችም ቢሆኑ በሀገራችን ተቀባይነት ያገኙ መሆናቸውን ለተሳታፊዎች
አሳይተዋል፡፡ የእኛ ትኩረት መሆን የሚገባው ምርጫው በሀገራችን ህዝቦች ዘንድ ተዓማኒ እንዲሆን ማድረግ ነው ያሉት ጓድ ደስታ ያም
ሆኖ የታዛቢዎች አሰራር ራሱን ችሎ መመሪያ የተቀረፀበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የምርጫ አስተዳደር ጉዳም ቢሆን በምርጫ ቦርድ በኩል
መመሪያ ተቀርፆበት እየተሰራበት ነው ብለዋል፡፡ ለጋራ ምክር ቤቱ የሚያስፈልገው ፓርቲዎች የሚተደደሩበት የስነ ምግባር ደንብ በመሆኑ
እሱ በፓርቲዎች ተመክሮበት ተግባር ላይ መዋሉን አስረድተዋል፡፡
ከህዝብ
ተወካዮች ምክር ቤት የተወከሉት የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴም የምርጫ ስነ ምግባር ደንቡ ተቆርጦ የቀረበ ነው በሚል ከመድረክ
የቀረበው ሃሳብ ተገቢነት የሌለውና 65 ፓርቲዎች በተፈራረሙበት መሰረትና ፓርቲዎቹ ባቀረቡት መሰረት መፅደቁን አብራርተዋል። ፓርቲዎቹ
ከተስማሙበት ውጭ ቃል እንኳን እንዳልተጨመረና እንዳልተቀነሰም እንዲሁ።
በምርጫ
ቦርድ ላይ የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተም አስተያየት የሰጡት የተከበሩ አቶ አስመላሽ የቦርዱን አባላት የጠቆሙት የተለያዩ የፖለቲካ
ፓርቲዎች ሆነው እያለ አሁን ላይ ሆነው በቦርዱ አባላት ላይ የተለያዩ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄዱ ተገቢ አይደለም ብለዋል። የቦርድ
አባላቱ ሲመረጡ አንድም ተቃውሞ ያቀረበ ፓርቲ አለመኖሩንና በፓርላማ መቀመጫ ያልነበራቸው ፓርቲዎች ጭምር የተሳተፉበት እንደነበረም
አብራርተዋል።
የምርጫ
ሜዳው እንዲሰፋ መንግስት ለፓርቲዎች የሚሰጠውን የፋይናንስ ድጋፍ ጨምሮ ፓርቲዎች ሳይሸማቀቁ በነፃነት ቅስቀሳ እንዲያደርጉ እጅ
ከፍንጅ ወንጀል ካልፈፀሙ በስተቀር በሕግ እንዳይጠየቁ የተደረገ በመሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ እንጂ እየጠበበ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
አንዳንድ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ላይ እያቀረቡ ያሉት ውንጀላ በሕግ የሚያስጠይቅና ሆን ተብሎ የተለያዩ ስሞችን በመስጠት ለማሸማቀቅ
ያለመ በመሆኑ ሊታረሙ እንደሚገባ አቶ አስመላሽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ
ተሳታፊ የነበሩ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰላቸውን ሃሳብ የሰጡ ሲሆን በአብዛኞቹ መድረኩ ተገቢና ወቅታዊ እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
መድረክ ፓርቲ በአገሪቱ የጨለመ ነገር እንዳለ አስመስሎ እያቀረበ ያለውን አስተያየትም ተሳታፊዎቹ ተችተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment