EPRDF is a ruling party committed to realize Ethiopia's Renaissance.

Thursday 11 December 2014

የከተሞች ልማት ለዘላቂ የግብርና ምርታማነት




በፈድሉ ጀማል

ድርጅታችን ኢሕአዴግ ከተሃድሶው በኋላ በተከተለው የጠራ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መስመር ከቀረፃቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አንዱ የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው፡፡ ሁሉን አቀፍ የከተማ ልማት ስትራቴጂ ነድፎ ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የከተማው ህዝብ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን የሚችልባቸው ዘርፎች ተፈጥረዋል፡፡  ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን መጥቀም የቻሉባቸው ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የዚህ መገለጫ ናቸው፡፡

በተለይ ከዚህ በፊት ዜጎች ዝንባሌው ስላላቸው ብቻ ወደ ዘርፉ በመግባት ተግባራዊ ሲያደርጓቸው የነበሩ የስራ አይነቶችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት አማካኝነት ለየስራ መስኮቹ የሚያስፈልገውን መሰረታዊ የቴክኒክ ክህሎትና የስራ ስነ ምግባር ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ የሰለጠኑትንም በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቶ ወደ ስራ ማስገባት በመቻሉ ውጤታማነታቸው ሊያድግ ችሏል፡፡ የዚህ ስልጠና አጠቃላይ ውጤትም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞቹን ወደ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዝ በማሸጋገርና ከውጭ ሀገር የምናስገባቸውን ማሽነሪዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ በማስቻል ጭምር የሚገለፅ ሆኗል፡፡

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች በትንሽ ካፒታልና ጉልበታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ እያደረገ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የከተሜውን የመግዛት አቅም በማሳደግ ለግብርና ምርቶች ሰፊ ገበያ ፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል የሚበዙት በርካታ ኢንተርፕራይዞች የግብርና ምርትን እንደ ግብዓት የሚጠቀሙ በመሆናቸው ተጨማሪ ገበያ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ በመሆኑም በከተሞች እየመጣ ያለው ልማት ከተሞችን ተጠቃሚ ከማድረግ አልፎ ለአርሶ አደሩ ምርት አስተማማኝ ገበያ በመሆን ምርትና ምርታማነቱ እንዲያድግ አጋዥ ሚና አለው፡፡ 

በሀገር ውስጥ የሚመረቱት የዘርፉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ከሚያስገኙት ጠቀሜታ በተጨማሪ ታዲያ የማምረቻ ወጪያቸውን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ በመቻሉ አርሶ አደሩን ጨምሮ አጠቃላይ ህብረተሰቡ በቀላሉ ገዝቶ እንዲጠቀምባቸው አስችለዋል፡፡

የግብርና ቴክኖሎጂ በቀጣይነት እያደገ እንዲሄድ ከተሞችና ኢንዱስትሪ በመጠንና በዓይነት እየጨመረ የሚሄድ የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ማሟላት አለባቸው፡፡ አለበለዚያ የቴክኖሎጂ እድገቱ ተሰናክሎ የግብርናው እድገትም አብሮ ሊሰናከል ይችላል፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በመተሳሰር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ የሚያደርጉት እንቅስቃሴም የከተማና የገጠር ልማቱ ትስስር የሚገለፅበት ነው፡፡ ዘርፉ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ከሚሰራባቸው መስኮች አንዱ ግብርና በመሆኑ ከውጪ ከሚገቡት ባነሰ ዋጋ የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦቱን በዓይነትና በጥራት አስተማማኝ በማድረግ አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን በማገዝ ላይ ይገኛል፡፡ አርሶ አደሩ በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ በሆነ መጠን ግብርናችን በአሰራሩ እየዘመነ ተጨማሪ ምርት እንዲገኝ ያደርጋል፡፡

አርሶ አደሩ ምርታማነቱ አድጎ ገቢው ጨምሮ ሳለ ገንዘቡን ትራሱ ስር የሚያስቀምጠው ከሆነ ቀጣይነት ያለው ልማት ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ ይህንኑ አደጋ ለማስወገድ የሚቻለው ከተማና ኢንዱስትሪ ለአርሶ አደሩ መጠኑና ዓይነቱ እያደገ የሚሄድ የግብዓት፣ የፍጆታ እቃና የአገልግሎት አቅርቦት ሲያሟሉና አርሶ አደሩ በግብርና መስክ ብቻ ሳይሆን ከግብርናም ውጭ ኢንቨስት የሚያደርግበት ወይም የአርሶ አደሩ ገንዘብ በባንክ ተቀምጦ ሌላው ዜጋ ተበድሮ ሊሰራበት የሚችልበትን ሁኔታ ሲፈጥሩ ነው፡፡

ፈጣን የከተማና የኢንዱስትሪ ልማት ከሌለ የግብርና ምርቶች እያደገ የሚሄድ ገበያ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ የአርሶ አደሩን ትርፍ ምርት ተቀብሎ በፋብሪካ በማደራጀት የሚሸጥ ኢንዱስትሪ ከሌለ፤ የመግዛት አቅሙ ያለውና የግብርና ምርትን በሰፊው የሚጠቀም የከተማ ህዝብ በብዛት ከሌለ የግብርና እድገት ሄዶ ሄዶ በገበያ እጦት መታነቁ የማይቀር ነው፡፡ በመሆኑም የኢንዱስትሪና የከተማ ልማት ስትራተጂያችን በግብርና ልማታችን የሚፈጠርለትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለአጠቃላዩ የሀገራችን የኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ በሌላ በኩል ፈጣን የኢንዱስትሪና የከተማ ልማት ማረጋገጥ በራሱ የግብርና ልማቱ ቀጣይነት እንዲኖረውና የላቀ ፍጥነትም እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስችል መሰረታዊ መሳሪያ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ በሀገራችን ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የከተሞች ልማትና የስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም ከተሞችን በማሳደግና በከተሞች የሚኖሩ ዜጎችን በተለይ በዝቅተኛና በመካከለኛ ገቢ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ከሚያበረክተው ቀጥተኛ ፋይዳው በተጨማሪ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል በግብርና ስራ ለሚተዳደረው የህብረተሰብ ክፍል የገበያ አቅም በመሆን፣ ዘመናዊና የተሻሻሉ የግብርና ግብዓቶችን በመጠንና በጥራት በማቅረብ ግብርናችንን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አሰራር እንዲታገዝ በማድረግ እና ከፍተኛ የምርት ጭማሪ እድገት እንዲመዘገብ በማድረግ ድርሻው የጎላ ነው፡፡ የግብርናው እድገት የሚፈጥረው ተጨማሪ የገንዘብ አቅም በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲንቀሳቀስም እድል ይሰጣል፡፡

በመሆኑም በከተሞች ልማት እየመጣ ያለው እድገት ፋይዳው በከተሞች ብቻ ታጥሮ የሚቀር ሳይሆን ለገጠር ልማቱም ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ኢኮኖሚው በዘላቂነት በፍጥነት እያደገ እንዲጓዝ በማገዝ ህዳሴያችን እውን የሚያደርግ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment